ጥቅምት 24፤መቼም የትም አይደገምም!

 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሀገሩ ክብር የሚከፍለው መስዋዕትነት በተግባር ከታየባቸው ቀናት መካከል ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም አንዱ ነው። በዕለቱ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ጥቃት በሀገራችን ታሪክ ጥቁር ጠባሳ አሳርፎ ያለፈ ክስተት ነው። ይህ በሠራዊቱ አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት መቼም ቢሆን፣ በየትኛውም ቦታ ሊደገም የማይገባውና ታሪክ የማይረሳው አስከፊ ድርጊት ነው።

በሠራዊታችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሀገራችንን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ፣ ወደ አውዳሚ ጦርነት ጎትቶ ያስገባንና ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰ በመሆኑ ሊረሳ የማይችልና ሊደገም የማይገባው አሳፋሪና አሳዛኝ የታሪክ አንጓ ነው። ምንም እንኳን ጥቃቱን ተከትሎ የተገባበትን ጦርነት በሠላም ስምምነት መቋጨት ቢቻልም ቀኑ በታሪካችን እንደ ነውር መቆጠር ያለበት ተግባር የተፈፀመበት ቀንና ትምህርት የሚወሰድበት ክስተት በመሆኑ ዕለቱ ሁሌም ሊዘከር ይገባል።

ይሄንን ቀን የምናስበው ለቂምና ለበቀል አይደለም። ያ ስህተት እንዳይደገም ነው። እናቶች የሚያለቅሱበት፤ ወጣቶች የሚማገዱበት፣ የሕዝቦች ትሥሥር የሚላላበት፤ ቤተሰብ የሚበተንበት፣ የሀገር ሀብት የሚወድምበት የጦርነት መንገድ ይብቃ ለማለት ነው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመውን ጥቃት በመቀልበስ በኢትዮጵያ ላይ ተከፍቶ የነበረውን ጦርነት በጋራ ርብርብ መክተን የሀገራችንን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት አስጠብቀናል። ይህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ሊሳካ እንደማይችል ፅኑ ማሳያ ነው:: በመሣሪያ ኃይል ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት በኢትዮጵያ ምድር ሊሳካ እንደማይችል አረጋግጧል።

መንግሥት ለዘላቂ ሀገራዊ ሠላምና ለሀገር አንድነት ሲል ችግሩን በሠላማዊ መንገድ ለመቋጨት የወሰነው፤ ተመሳሳይ ስህተቶች በየትኛውም አካባቢና ጊዜ እንዳይደገሙ ትምህርት እንዲወሰድበት ለማስቻል ነው። መከላከያ ሠራዊትን ማጥቃት መደገም የሌለበት ትልቅ ስህተት መሆኑን በዚህ ወቅት በየጥሻው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ሊገነዘቡት ይገባል።

መከላከያ ሠራዊታችንን ማጥቃት የሀገራችን የኅልውናዋ የመጨረሻ ምሽግን መንካት እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል። በየመንደሩ እየዞሩ የሕዝብን ሠላም የሚነሱ፣ ዝርፊያ የሚፈጽሙና ሀብት የሚያወድሙ አካላትም እየሄዱበት ያለው መንገድ የስህተት መሆኑን ተገንዝበው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ የሚፈፅሙትን ትንኮሳ ሊያቆሙ ይገባል። ወንዝ የማያሻግር የፅንፈኝነት ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ የመንደር ታጣቂዎች፤ ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ሰንቆ የተሰለፈውን መከላከያ ሠራዊታችንን በማጥቃት ምንም ዓይነት ድል እንደማያገኙ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ የቆመው ሠራዊታችን ዛሬም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

መከላከያ ሠራዊታችን በጥቅምት 24 የደረሰበትን ጥቃት አልፎ፣ ሀገራችን ላይ የተከፈተውን ጦርነት መክቶና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በመሥዋዕትነቱ አስከብሮ ኢትዮጵያን ከታላቅ አደጋ ታድጓል። በዚህ ወቅት መከላከያ ሠራዊቱ ለሀገራችን እየከፈለ ያለውን ክቡር መሥዋዕትነት በማቃለል የሐሰት ቅስቀሳ የሚያሰራጩ አካላትም ከባለፈው ስህተት ተምረው ከእኩይ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል።

ጥቅምት 24 ጥቃት የተፈጸመበት ጀግናው ሠራዊታችን አሁን ላይ የበለጠ ዐቅሙን በሰው ኃይል፣ በሥነምግባር፣ በመሣሪያ፣ በቴክኖሎጂና በወታደራዊ ሳይንስ ገንብቶ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ጥቃት ጠብቆ ኢትዮጵያን ወደላቀ ከፍታ ለማሸጋገር በሚችልበት አስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ምንጊዜም ፍላጎታቸው ሠላም፣ ልማትና አብሮነት ብቻ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንም እነዚህን የሕዝብና የመንግሥት ፍላጎቶች እውን ለማድረግ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው፤ እየከፈለም ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ቅጥረኞች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሐሰት ዘመቻዎችን ከፍተው የሠራዊቱን ክቡር ስም ለማጠልሸት ሲሞክሩ ታይቷል። ሆኖም ሠራዊታችን እንኳን ከሃሰተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመበት ጥፋት እንኳ የማይንበረከክ ፅኑ መሠረትና ኢትዮጵያዊ ጀግንነት የተላበሰ መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በተለመደው ደጀንነቱ ሠራዊቱን ለላቀ ድልና ክብር እያበረታታ ይገኛል። ይህንን ተግባሩንም አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል። መከላከያ ሠራዊትን የማጥቃት የባንዳነት ተግባር በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው። ለዚያም ነው ዘንድሮ የጥቅምት 24ን ለሦስተኛ ዓመት ስናስብ ይህ ዓይነት የሀገር ክህደት እንዳይረሳም እንዳይደገምም የምንዘክረው።

ክብር ለሀገር ሉዓላዊነት ለተሠዉ ጀግኖች!!

ይቅር እንላለን ግን አንረሳም።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You