በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነው እግር ኳስ በዘመናችን ከስፖርትም የዘለለ ትርጉም አለው። በተለይም ከስፖርታዊ ውድድርና ከመዝናኛነት ባሻገር ምጣኔ ሀብታዊ እንድምታው እየጎላ መምጣቱ ለማንም ግልፅ ነው። ለዚህ አባባል በዓለም በዓመት በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ ኢንዱስትሪ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።
ስፖርቱን በአግባቡ መጠቀም ለቻሉበት እንደ እንግሊዝ ዓይነት ሀገራት በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማመንጨት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢን ከሚሸፍኑ ኢንዱስትሪዎች አራተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ሆኗል።
በስፖርቱ ቀጥተኛ ተዋናይ የሆኑትን ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ሳይጨምር በዓለም ደረጃ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረም ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን እግር ኳስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንጀራ ከመሆን አልፎ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ መሆኑ አያሻማም።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች ሀገር ናት፣ ከዚያም ባሻገር የአህጉሪቱን ትልቅ ውድድር ሦስት ጊዜ በማዘጋጀት አንድ ጊዜ ዋንጫ አንስታለች። ይድነቃቸው ተሰማን ዓይነት የተከበሩ የአፍሪካ እግር ኳስ ቁንጮ መሪዎችን ማፍራት የቻለች ሀገርም ናት።
ያም ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለበት ደረጃ ራሱን የቻለ የሕዝብ ጥያቄ ቢሆንም ትልቅ የእግር ኳስ ፍላጎት ባለባት ሀገር የካፍና የፊፋን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ አንድ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የሚያስተናግድ ሜዳ ማጣቷ እንቆቅልሽ ሆኖ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቀው፤ በዓመቱ ለብሔራዊ ቡድን ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ እያወጣ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩም የወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሌሎች ሀገራት ሜዳ ላይ እንዲጫወት ተገድዷል።
በዚህም ሀገሪቱ በዓመት ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጋለች። ፌዴሬሽኑም ብሔራዊ ቡድኑ በሀገሩ ባለመጫወቱ በአራት ዓመት 56 ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ሽፕ ገቢ አጥቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ከማላዊ አቻው ጋር ያደርግ የነበረውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በሜዳ ችግር ምክንያት በሞዛምቢክ ማፑቶ እንዲያካሂድ በመወሰኑ፤ የሆቴል፣ የቡድን አባላቱ፣ የዳኞች የአውሮፕላን ወጪና አበልን ሳይጨምር፤ ለሜዳው ኪራይ ብቻ 8 ሺ ዶላር ለማውጣት ተገድዷል። ለአባላቱ የአውሮፕላን ጉዞም 1.9 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
አሁን ላይ የስታዲየሞችን ጉዳይ ከእግር ኳሳዊ ምክንያቶች ባለፈ ማየት የሚገባን ወቅት እንደሆነ ይታመናል። ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎችን በሜዳው ማድረግ ቢችል የተለያዩ ወጪዎቹን በብር ከመሸፈን ባለፈ፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር ለውድድሮች ማስፈጸሚያ ወጪ የምናደርገውን የውጭ ምንዛሬ መታደግ ይቻላል። ሀገር ውስጥ ለሚካሄዱ ጨዋታዎች ከውጭ ሀገር የሚመጡ ቡድኖችና ደጋፊዎች ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ መሆንም ቀላል ነገር አይደለም።
ከዚህም በላይ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳውና በደጋፊው የመጫወቱ ጉዳይ ቅንጦት ሳይሆን የክብር፣ የታሪክና የበርካታ ሕዝብ ፍላጎት ነው። ለቡድኑ ውጤታማነት ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ አስተዋጽኦም፤ ለስፖርቱ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእግር ኳስ ስፖርት ካለው ፍቅር፤ በስፖርቱ በአህጉር ደረጃ ካለው ትልቅ ታሪክ አንጻር እንደ ሀገር አንድ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለቤት አለመሆናችን ሁሉንም ሊያስቆጭ የሚችል፤ ሀገራዊ ክብርን የሚያደበዝዝ፤ በስፖርቱ ላይ ጥላን የሚያጠላ ክስተት ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ በሀገሩ መጫወት የሰፊው ሕዝብ ፍላጎት፣ የታሪክ፣ የሞራልና የገፅታ ግንባታ አንድ አካል ነው። ቢያንስ አንድ ዓለም አቀፍ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም በተቻለ ፍጥነት ማዘጋጀት ለነገ የሚባል ሀገራዊ የቤት ሥራ ሊሆን አይገባም። በተለያዩ ክልሎች ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ ስታዲየሞችን አቅም ታሳቢ ባደረገ መንገድ ማጠናቀቅ የሚቻልበትን አግባብ መፍጠርም ተገቢ ነው።
ለዚህ ደግሞ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ስታዲየሞቹ የሚገኙባቸው ክልሎች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ባለሀብቶች በአጠቃላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደ ተቋም እና ዜጋ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከፍባለ ቁጭት እና ቁርጠኝነት እየተናበቡ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም