ስደትና ፍልሰት “የታሪካችን ሾተላይ”

 “እግር ከቤት ልብ ከደጅ”

“በዜጎች ጎርፍ የሚጥለቀለቀው ኢሚግሬሽን” በሚል መሪ ርዕስ በዚህ ዓምድ የጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም በተስተናገደው ጽሑፍ ስለተጠቀሰው መንግሥታዊ ተቋም መረርና ኮስተር ያለ ትዝብት ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ባለጉዳዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ለቀረበበት ስሞታ “ንስሐ ገብቶ” የዐይኑን ጉድፍ ይጥረግ አይጥረግ ወደፊት የምናየው ስለሆነ ለጊዜ ጊዜ ሰጥተን ወደ ዛሬው ተያያዥ ጉዳያችን ማዝገሙን መርጠናል፡፡

ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጽሑፉ ውስጥ “የቀደምት ዜጎቻችን የስደት ታሪክ እንዴት፣ ወዴትና ምን ይመስል እንደነበር በሚቀጥለው ሳምንት የአንድ የደቡብ አሜሪካ ሀገርን ታሪክ በመንደርደሪያነት ተጠቅመን የዳሰሳ ያህል ለማሳየት ስለምንሞክር ለጊዜው ርዕሰ ጉዳዩን በይደር አቆይተናል” የሚል የቤት ሥራ ተቀብለን ማለፋችን ይታወሳል፡፡ በቃላችን መሠረትም የዛሬው ጽሑፋችን ዋና ትኩረት ልንፈወስበትና ልንፈውሰው ባልቻልነውና በሾተላይ በመሰልነው የዜጎቻችን የስደት ጉዳይ ላይ ጥቂት ቁዘማ እናደርጋለን፡፡

“ሾተላይ” የሚለውን ቃል በሙያው ባለሙያዎች የተዘጋጁ ሰነዶች ሳይሆኑ የዘወትር መጠቀሚያችን የሆኑት መዛግብተ ቃላት የሚበይኑት እንዲህ በቀላሉ እንዲገባን አድርገው ነው፡- “ሾተላይ የወንድና የሴት የደም ዓይነት ቅንጅት ተስማሚ ባለመሆኑ ሽሉ እንደ ተፀነሰ ወይም እንደተወለደ እንዲሞት ያደርጋል ተብሎ የሚታመንበት ከወሊድ ጋር የተያያዘ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡”

የሀገራችንና የታሪካችን መስተጋብር ከሾተላይ ጋር ተነጻጽሮ መቅረቡ በየሥርዓተ መንግሥታቱ ያለፍንበትና ዛሬም እያለፍንበት ያለው ኑሯችን በአብዛኛው ትውልዱን ለስደትና ለፍልሰት እየዳረገ ሲያመክን የኖረ ክፉና ፈውስ ያልተገኘለት በሽታ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ የሀገር ማህፀን ያፈራቸው በርካታ ዜጎች በባሕር፣ በየብስና በአየር እየወጡ የፈለሱባቸው ታሪኮች ዓይታቸውም ሆነ ዝርዝራቸውም የትየለሌ የሚሰኝ ነው፡፡

“አይሄ! ያስለቅሳል፣ ያስተክዛል፣

ያሳለፍነው መች ይረሳል፣

የእኛ ነገር መች ይረሳል፡፡”

በሰቲት ሑመራ በገዳሪፍ ካርቱም፣

ጅቡቲ ኬኒያ በእግሬ ሳዘግም በረሃ ሳቋርጥ፣

እግሬ አውጭኝ እያልኩኝ ድንበር ኬላ ስሰብር”

በማለት ድምፃዊ ነዋይ ደበበ በአራራይ እንጉርጉሮ በተቃኘ ዜማው ያስደመጠን ሀገሪቱን የወላድ መካን አድርጎ “ሾተላይ” የሆነባት የትናንትና ብቻ ሳይሆን ዛሬም ያልተፈወሰችበት ተግዳሮቷ ግድ ብሎት ይመስላል፡፡ ሌላዋ ድምፃዊትም እንዲሁ “ስደት ይጠራኛል አቤት አልለውም፤ ቃሉ ያስፈራኛል” በማለት ያዜመችው ይህንኑ እንደ መዥገር ተጣብቆ አልፈወስ ያለውን የሀገር ማህፀን አምካኝ “በላ” ለማስታወስ ሳይሆን አይቀርም፡፡

የታሪክ ማስታወሻ፤

በሕዝቦች የስደት ዜና መዋዕል ተደጋግመው ከሚጠቀሱት መካከል በኩባ የተደረገው የዜጎች ፍልሰት ብዙ የሚነገርለት ታሪክ አለው፡፡ እ.ኤ.አ በ1959 በፊደል ካስትሮ የሚመራው የተዋጊ ቡድን በለስ ቀንቶት የአምባገነኑን የባቲስታ መንግሥት አንበርክኮ ካስወገደ በኋላ 1.4 ሚሊዮን ዜጎች ሀገራቸውን ትተው ወደ አሜሪካ የተሰደዱት በማግሥቱ ነበር፡፡ በማስከተልም 300,000 የሚሆኑ ተጨማሪ ዜጎች ውለው ሳያድሩ ወደ ተጎራባች ሀገራት እና ወደ አውሮፓ በመትመም ዓለም አጋጥሟት በማያውቅ ፍልሰት እንድትጥለቀለቅ ምክንያት ሆነዋል፡፡

እነዚህ ስደተኞች ዝርያቸው የሚመዘዘው በአብዛኛው ከ1492-1898 በምድሪቱ ላይ በባርነት ተግዘው ከተወሰዱ የመከረኛዋ አፍሪካ ልጆች ነበር። ከፊደል ካስትሮ መራሹ የኩባ አብዮት ማግሥት በጀልባ ባሕር እያቋረጡ ወደ አሜሪካ የገቡትን ዜጎች በተመለከተ ሀገሪቱ የዜጎቿን የፍልሰት ታሪክ ለልጆቿ የምታስተምረው በአምስት አንጓ በመከፋፈል ነው፡፡

የመጀመሪያውን የፍልሰት ማዕበል (ከ1959-1962) የሰየመችው “ታሪካዊ ፍልሰት” (Historical exile) በማለት ነው፡፡ በዚህ የመጀመሪያው የስደት ጎርፍ ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ የበቁት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ዜጎቿ ብዙዎቹ በከፍተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በዝባዥ የሚል ቅጽል የተሰጣቸውና ለነፍሳቸው ሰግተው የኮበለሉ ነበሩ፡፡

ከ1965-1973 የተከናወነው ሁለተኛው የፍልሰታቸው ስያሜ “የነፃነት ፍለጋ ሽሽት” (Free­dom flights) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቅንብሩ ደግሞ በአሜሪካ እውቅና የተቸረውና ፍልሰተኞቹን ዜጎች የምትቀበለው ሀገር ራሷ የአውሮፕላን ቲኬት እየገዛችላቸው “ኑልኝ!” በማለት በይፋ በመጋበዝ ነበር፡፡ የታሪክ ልሒቃን ይህንን መሰሉን የኩባ ስደት የሚገልጹት “የክብር ባርነት፣ የፖለቲካ አስቀያሚ መገለጫ መልክ ወዘተ.) በማለት ነው፡፡

ከኤፕሪል እስከ ሴፕቴምበር 1980 ለስድስት ወራት ያህል በተከናወነውና ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ ኩባውያን የተሰደዱበት ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ የማሪዬል ዘፀአት (Mariel exodus) በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ የስደት ማዕበል የተገፉት አብዛኞቹ ዜጎች ከእስር ቤት ምሕረት አግኝተው የተለቀቁና የትኛውንም የጉልበት ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑ ምስኪኖች እየተመረጡ የተሰደዱበት የፍልሰት ዓይነት ነበር፡፡

የባልሴሮ ቀውስ (Balsero crises) በሚል ስያሜ የሚታወቀውና ለሁለት ወራት ብቻ በፈጣን ሁኔታ የተከናወነው አራተኛው የዜጎች ፍልሰት በአሳዳጇ ሀገር በኩባና በስደተኞች ተቀባይዋ አሜሪካ መካከል በተደረገ የጋራ ስምምነት ውል የተደረገ ፖለቲካዊ ወዘና የነበረው ክስተት ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ከ1995-2017 ለረዥም ዓመታት የዜጎች ኩብለላ የተስተዋለበትና በአምስተኛነት የሚጠቀሰው (Post-Soviet migration) የኩባውያን ስደት ግን የተለየ ስያሜና ታሪክ ያለው ነው፡፡ በተጠቀሱት ዓመታት 650,000 ያህል ስደተኞች “ሁሉ በሁሉ ነኝ” ባዩዋ አሜሪካ የገቡት ስደተኞች ይለዩ የነበረው “ኮቴ ደረቅ” (dry-foot) ወይንም ኮቴ ርጥብ (wet-foot) በሚሉ ስያሜዎች ነበር፡፡ “ኮቴ ርጥብ” የሚባሉት በጀልባና በባሕር ወደ አሜሪካ ለመግባት ሞክረው የተሳካላቸው ወይንም ሙከራው ከሽፎባቸው ተጠርዘው ወደ ሀገራቸው የተመለሱትን ሲመለከት፤ “ኮቴ ደረቆቹ” ደግሞ በሕጋዊ መጓጓዧ በየብስ ወይንም በአየር የገቡትን ለማመላከት ነው፡፡ ዝርዝር ታሪኩ ሰፋ ስለሚል ለማሳያነት ይሄው ይበቃ ይመስለናል፡፡

የእኛ ዜጎች የስደትና የፍልሰት ታሪክ ምን ስያሜ ሊሰጠው ይችላል?

መቼም ተወዳጁን እንጂ ጥዩፉን ታሪካችንን በይፋ ለመግለጽ ለማንደፋፈረው ለእኛ ቢወራና ቢተረክ ከልብ የምንወደውና ሌሎችም እንዲወዱልን “ታሪካችን” ብለን ሳንሰለች የምንተርከው “ኢትዮጵያችን የስደተኞች ተቀባይ ሀገር እንደሆነች” እንጂ “የከፋ የዜጎች ፍልሰት ባለታሪክ” እንደሆነች አፍ ሞልተን ለመናገር አፋችንን ይይዘናል፡፡

በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ምክንያት የተሰደዱ የብዙ ሀገራት ዜጎችን መቀበላችንን የምንሰብከውን ያህል እኛ እርስ በእርስ መሳደዳችን በፍጹም እንዲነሳብን አንፈልግም፡፡ ከቅርቡ ዘመናት እንጀምር እንኳን ብንል ሀገሬን “ሾተላይ” ሆኖ ማህፀኗን ለእርግማን የዳረገው የዜጎቿ የስደትና የፍልሰት ታሪክ በእጅጉ አንገት አስደፍቶ የሚያስለቅስ እንጂ ለመስማት የሚያጓጓ አይደለም፡፡

በተለዋጭ ትርጉም ግልጋሎት ላይ የሚውሉትን “ስደት” እና “ፍልሰት” የሚሉ ሁለቱ አሻሚ ቃላት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አገልግሎት ላይ የዋሉት “ስደት” በአንድ ጉዞ ለሚደረግ ውሱን የዜጎች ኩብለላ፣ “ፍልሰት” ደግሞ በርከት ላሉና በቡድንና በጅምላ የሚፈጸም ሽሽትን ለመወከል ነው፡፡

በነጠላም ሆነ በቡድን፣ በጥቂትም ሆነ በእልፍ ቁጥር ሲፈጸሙ የኖሩት የሀገሬ ዜጎች የፍልሰት ታሪኮች የሚነገሩት “ትናንት” በሚል የኃላፊ ጊዜ ብቻ ሳይሆን “ዛሬም” እየተባለ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለምን ስደት የኑሯችን ዘይቤ ሊሆን ቻለ? እያንዳንዱ ዜጋ ከሀገሩ ለመሸሽ ልቡ ሊሸፍት የቻለውስ ለምንድን ነው? ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለማኖር አቅም ስለሌላት ወይንስ “አቅመ ስንኩል ያደረጋትን” ወደረኛ መከራዋን መቋቋም ስለተሳናት? ምላሹ ድፍረት፣ መልሱም ጎምዛዛ ስለሆነ “በሆድ ይፍጀው” እህህታ ማለፉ ይመረጣል፡፡

በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ዜጎች ሀገር ጥለው ለመኮብለል እጅግም አይደፋፈሩም ነበር፡፡ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ተስፋፊዋ እብሪተኛ ሀገር ዜጎቻችንን እያፈሰች ከሀገር ውጭ ታፈልስ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ከወረራው በኋላ መንግሥት በእግሩ ከቆመም በኋላ ሥርዓቱን ይቃወሙ የነበሩ የነውጠኞቹ የኮሌጅ ተማሪዎች ሙከራ “አውሮፕላን እስከ መጥለፍ” በደረሰ ድፍረት በየብስም ሆነ በአየር “የትግል ስልት” በሚል ስያሜ ሀገር ጥሎ መኮብለልና መሰደድ የዘመኑ ፋሽን ከመሆን የዘለለ እጅግም የሚነገርለት ዝርዝር ታሪክ የለውም፡፡

የዜጎች ፍልሰት ሊባል የሚቻለው በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ይፈጸም የነበረ እንጂ ድንበር የሚሻገሩት ስደት እጅግም ነበር፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን የ1966 ዓ.ም ክፉ የድርቅና የረሃብ ታሪካችን እጅግ ዘግናኝ የሀገር ውስጥ የፍልሰት ታሪክ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ንጉሡን ከመንበራቸው ያስወገደ ክስተት ጭምር መሆኑ በሚገባ ይታወቃል፡፡

የደርግ ዘመን የዜጎች ፍልሰት ግን በታሪካችን ውስጥ ጥቁር አሻራው የደመቀና መከራና ስቃዩም የከፋ እንደነበር ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው፡፡ በቀይና ነጭ ቀለማት የሚታወቀው ሽብር ብዙ ዜጎቻችንን ለከፋ ስደትና ፍልሰት መዳረጉን የምናስበው በጨፈገገ ስሜት ነው፡፡ የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዓመታት ያጋዘቻቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንም የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ በርዕዮተ ዓለማቸው ልዩነት፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት የተሰደዱትን ሁለቱን ብቻ ተገቢ ትኩረት ሰጥተን በየፈርጁ እንዘርዝር ብንል የጋዜጣው ውሱን ዓምድ ስለሚገድበን እንዲሁ ብቻ አስታውሶ ማለፉ ይበጅ ይመስለናል፡፡

በዘመናት ውስጥ በአይሁድ እምነታቸው ምክንያት የመከራ ወስከንባይ ተደፍቶባቸው አሳር እያዩ የኖሩትና የተገፉት የእምዬ ልጆች “ቤተ እሥራኤላውያን” ሀገር ጥለው ስለምን የኢያሱን፣ የሙሴንና የሰሎሞንን ስያሜ በያዙ የፍልሰት ኦፕሬሽኖች ወደ ተስፋ ሀገራቸው እንደገቡ በዝርዝር ለመተረክ ርዕሰ ጉዳዩ ይገድበናል፡፡

የዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ግን በታሪካችን ውስጥ እጅግ የከፋና የከረፋ ታሪክ የተሸከመ ስለሆነ ክርፋቱን ለመዘርዘር ይፈታተናል፡፡ የሀገር ሠራዊት በትኖ በመቶ ሺህዎችን ያሳደደና ለፍልሰት የዳረገ ሌላ ሀገር ስለመኖሩ በታሪክ ላይ የተመሠረተ ጥናት ተደርጎ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ እንዲሁ እንዳንገሸገሸን ብናልፈው ይቀላል፡፡ የኬኒያና የጎረቤት ሀገራት የስደተኛ ጣቢያዎች ይመስክሩ ብሎ በደምሳሳው ማለፉ ይቀላል፡፡ አሜሪካ በዕጣ ያንበሸበሸቻቸው ዜጎች ፍለሰት ግን አከራካሪ ስለሆነ የምናልፈው በጥቅሻ ይሆናል፡፡

በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በቀያቸው ጭምር ዜጎቿ ተረጋግተው እንዳይኖሩ “የመከራዋ ሾተላይ” የጸናባት ሀገሬ ዛሬም ልጆቿን በብብቷ አቅፋ ለማኖር ስለተቸገረች ቀለቧ እንባዋ ከሆነ ውሎ አድሯል። ብዙው ዜጋ ልቡና መንፈሱ ለስደት አኮብኩቦ መቀመጡን በድፍረት ባንናገር ከሕሊናችን ጋር እንጣላለን፡፡ ግን ስለምንና በማን ምክንያት? መልሱን እናውቀዋለን፤ ብንናገር ዝርዝሩ ስለሚሰፋ ግን እናልፈዋለን፡፡

ዳሩ በታመመ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንዴት መረጋጋት ይቻላል? እንደምንስ ጦርና የጦር ወሬ የዕለት ስንቅ ሆኖ እስኪቆጠር ድረስ “የሰላም ርግብ በቆሰለችበት” ሀገር ዜጎች ተረጋግተው እንዲቀመጡ ይበረታታሉ? ከቶ እንደምን በተሳከረ የኑሮ ምሕዋር ውስጥ ሚዛንን ጠብቆ ቀን መግፋት ይቻላል? ዜጎች በቋንቋቸው፣ በባሕላቸው፣ በብሔራቸውና የራሳቸው መለያ በሆኑ በሚያከብሯቸው ማንነታቸው ተከብረውና ተከባብረው እንዲኖሩ ምድሪቱ እስካልፈቀደች ድረስ እንደምን ስደትና ፍልሰትን ምርጫ አይሆኑም?

ሀገሬ ሆይ! ዜጎችሽ በቅርብም ሆነ በርቀት ሆነው ለሚሞግቱሽ ጥያቄ ምን መልሱ እንደማይጠፋሽ እናምናለን፡፡ ግን በርግጡ ልጆችሽን ለማኖር አቅም የለሽም? “በስደትና ፍልሰት ሾተላይ” የወላድ መካን መባሉስ ተስማምቶሻል? በመደማመጥና በመነጋገር ለማያምኑ ልጆችሽ በእምባሽም ይሁን በምክርሽ ምን ትያቸዋለሽ? ስለ አንቺ እንጃልሽ! ስለ እኛ ግን ባለቅኔው “እስኪ ተጠየቁ” ያለውን ጥያቄ ተውሰን እንጠያየቃለን!

ቸገረኝ ጨነቀኝ ብጠይቅ አጥብቄ፣

ምላሽ አጥቼለት ለልቤ ጥያቄ፣

ያንጀት ልቅሶ ሆኖ የዘመኑ ሳቄ፡፡

እንዲህ ተወስኖ ኑሮው ምጥ ነው እንጂ፣

ሳይገላገለው ታሥሮ እጅ ከፍንጅ፤

እንዳማጡ መኖር የኑሮ አተላ፣

መፍትሔ የሌለው በድፍን ነው ሾላ፡፡

ይሄው ነው፡፡ ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You