ዘራፊው ተሳፋሪ

በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው። የጨረቃ ብርሃን አይታይም፤ ድቅድቅ ጨለማ ነበር። ጨለማውን ለማሸነፍ ትንቅንቅ ከገጠሙት የመንገድ መብራቶች ስር አንዲት ቪትዝ መኪና ቆማ ትታያለች።

የቪትዟ መኪና ሾፌር በመጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ15 አካባቢ ጀሞ መንገድ ዳር ቆሞ ተሳፋሪዎችን በመጠባበቅ ነበር። በወቅቱ አንድ ተሳፋሪ ወደ አየር ጤና መሄድ እንደሚፈልግ ተናገሮ የመኪናዋን የኋላ በር ከፍቶ ገባ።

የእለት ሥራውን ለማጠናቀቅ አንድ ተሳፋሪ ብቻ የሚጠብቀው ወጣት ወደ መኖሪያ ሰፈሩ አቅጣጫ ተሳፋሪው መሄዱ አስደስቶት መኪናውን አስነሰቶ ጉዞ ጀመረ። ከጀሞ የተነሳው መኪና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ልዩ ስሙ ቆሼ ታፍ ነዳጅ ማደያ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርስ፤ ተሳፋሪው መውረድ እንደሚፈልግ ተናግሮ መኪናውን አስቆመው።

መኪናው ይቁምልኝ ብሎ የጠየቀበት ቦታ የመንገድ መብራት ባለመኖሩ የተነሳ ጨለማው ከበድ ያለ ነበር። የመኪናው መብራትም ጨለማውን አቋርጦ ረዥም ርቀት መብራት ተስኖታል። ሹፌሩ ልክ መኪናውን እንዳቆመ ተሳፋሪው የተገለገለበትን ገንዘብ እንዲሰጠው ዞር ሲል ባላሰበው ሁኔታ ከኋላ ሽጉጥ ተደቅኖበት ይመለከታል።

ለቀን ገቢው ማሟያ ያሰበው ሥራ የቀን ሕይወቱን ሊያጨልም መሆኑን ሲመለከት በድንጋጤ የሚያደርገው የጠፋው ወጣት የዘራፊውን ትእዛዝ መቀበል ጀመረ።

ባለ ራይዱ

ወጣት ያሬድ መንግሥቱ በጠዋቱ የወጣትነት ዘመን እንደ ረፋድ ፀሐይ ሳያቃጥል ሳይቀዘቅዝ ሞቅ ባለ ልስላሴ የሚጓዝ ዓይነት ወጣት ነው። በሕይወት ዘመኑ ልክነትን የሕይወት መርሁ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። የሰው ሀቅ የማይፈልግ የራሱንም ያለአግባብ የማያስነካ ነው። የላቡን ፍሬ ይበላ ዘንድ ማልዶ ተነስቶ እስከ ምሽት ደፋ ቀና የሚል፤ ደከመኝ ሰለቸኝን የማያውቅ ወጣት ነው።

በትጋቱ የገዛትን መኪና ማልዶ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥበት ቆይቶ በሥራ መግቢያ ሰዓቱ ወደ ሥራው ይገባል። ከሥራም ሲወጣ እስከ ምሽት ገንዘብ ሰብስቦ ወደቤቱ ይገባ ነበር። ኑሮን በሥራ መለወጥ የሚያቅደው ወጣት ወደ ትዳር ሕይወት ከመግባቱ በፊት ጥሪት መያዝን አላማው አድርጎ ደፋ ቀና ይል ነበር።

ለእናቱ ብቸኛ ልጅ የሆነው ወጣት፤ እንደተለመደው በእለቱም ማልዶ እናቱን ተሰናብቶ ከቤት ወጣ። የጠዋት ሥራውን ጨርሶ በመደበኛ ሥራው ላይ ከዋለ በኋላ ልክ ከመሥሪያ ቤቱ ሲወጣ ያገኘው የስልክ ጥሪ ወደ ጀሞ የሚያደርስ ነበርና ይዞት የሄደውን ተሳፋሪ አድርሶ ባዶውን እንዳይመለስ በጀሞ የጋራ መኖሪያ መንደር አካባቢ ቆመ።

በጠዋት ስለወጣ ድካም ተሰምቶት ነበር። ስለዚህ ያገኘውን ሰው ጭኖ ለመመለስ በሚል ከራይድ ሳይደወልለት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ የጠየቀውን ሰው ጭኖ አድርሰኝ የተባለበት ቦታ ለመድረስ ጉዞ ጀመረ።

የጉዞውን የመንገድ ግማሽ እንዳጋመሰ ‹‹ወራጅ አለ›› የሚል ድምፅ ሰማ። እሱም አየር ጤና አድርሰኝ ያለው ሰው ድንገት አቁመልኝ ማለቱ አስገርሞት የመንገዱን ዳር ይዞ ቆመ። ለመንገዱ የሚጠይቀውን ክፍያ ለመቀበል ዞር ሲል፤ ይሆናል ብሎ ያልገመተው ነገር አጋጠመው።

ቅድሚያን መተዳደሪያው ያደረገው ሌባ

እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ያደገው ሮጦና ቦርቆ ነው። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ተገቢውን ትምህርት ተምሮ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል። በምንም ምክንያት ተቀጥሮ መሥራት የሚሉትን ሃሳብ ወደ አእምሮው ጓዳ አስገብቶ አያውቅም ነበር። ሁልጊዜ በአቋራጭ መክበርን ህልሙ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። ወጣት ማርቆስ ጡምደደ ጊባንቾ ይባላል። እድሜው 24 ነው።

በዚህ እድሜው ሳይሰራ የመክበር ፍላጎት የተጠናወተው ወጣት፤ ይህን ፍላጎቱን ለመሳካት ዝርፊያን ተቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ወደ ሥራው ገባ። ዝርፊያን ሥራዬ ብሎ የያዘው ወጣት አንድ ሁለት እያለ ፍርሃቱ ጠፍቶ ቋሚ ሌባ እስኪሆን ድረስ ንጥቂያን ተለማመደ።

ይህንን ልምዱን ደግሞ አቅዶና ተዘጋጅቶ ሰዓት እየጠበቀ በንጥቂያ ያለመው የሀብት ማማ ላይ ለመቆናጠጥ ይታተር ጀመር። ከተራ ሌብነት ወጥቶ መኪና ለመቀማት ያቀደው ቀማኛ አድብቶ ሲጠብቅ ከነበረበት አካባቢ ለህልሙ መሳካት የምትሆን የትራንስፖርት አገልግሎት የምትሰጥ መኪና ቆሞ ተመለከተ።

ምንም ሳያመነታ ወደ መኪናው ገብቶ ጉዞ ጀመረ። ቀደሞም ለዘረፋ ተዘጋጅቶ የገባው ይህ ሰው ለእኩይ ተግባሩ ምቹ ቦታ ሲያገኝ መውረድ እንደሚፈልግ ተናገሮ መኪናውን ካሰቆመ በኋላ አላማው ዝርፊያ ብቻ በመሆኑ ̋እገልህ ነበር ግን አሳዘንከኝ በማለት ̋ መኪናውንና ሌሎች የተበዳዩን ንብረቶች በሽጉጥ አስፈራርቶ ዘርፎ ተሰወረ።

ጥቆማ የደረስው ፖሊስ

የግል ተበዳይ አቶ ያሬድ መንግሥቱ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 – በ.38528 አ.አ የሆነ የሻንሲ ቁጥሩ ኤስ ሲ ፒ 10 0325833 የሞተር ቁጥሩ 1 ኤስ ዜደ -0812672 የሆነ እና የዋጋ ግምቱ ብር 830ሺህ ብር የሆነ ቪትዝ መኪና ይዞ የራይድ አገልግሎት ለመስጠት በቆመበት መዘረፉን ለፖሊስ ካመለከተ በኋላ ፖሊስ ጉዳዩን ይዞ መከታተል ጀመረ።

ዝርፊያው ሲካሄድ በዳይ መኪናውን እንዲያቆም ካደረገ በኋላ ሽጉጥ በመደቀን ‹‹እገልህ ነበር፤ አሳዝነከኝ ነው፤ አሁን ከመኪናህ ውረድ›› በማለት አስፈራርቶ ከመኪናው እንዲወርድ አድርጎ ተሽከርካሪው ውስጥ ያገኘውን የግል ተበዳይን መንጃ ፍቃድና የቀበሌ መታወቂያ እንዲሁም የአዋሽ ባንክ ኤ ቲ ኤም ካርድ ከነሚስጥር ቁጥሩ እንደያዘ የተሰወረውን ቀመኛ ለማገኘት ፖሊስ ብዙ ጥረት ካደረገ በኋላ አንድ ቀን በለስ ቀናው።

ፖሊስ ስለመኪናዋ ያለውን መረጃ በሙሉ ለሁሉም የፖሊስ ክፍል አባላት በማድረሱ በመጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ መኪናውን ሰሌዳ ቁጥር 2-11562 ኦሮ የሚል ለጥፎበት ያየ አንድ ባልደረባ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል።

ፖሊስ ሊይዘው በሚሞክርበት ጊዜም ሊያመልጥ ያደረገው ሙከራ በአካባቢው ሰዎች በተደረገ ርብርብ ሲደረስበት መኪናውን ጥሎ ያመለጠ ቢሆንም በኋላ ግን በብዙ ትግል ተይዞ፤ በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሷል።

የፌደራል አቃቤ ሕግ ክስ

ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ሕግ ተከሳሽ ማርቆስ ጡምደደ ጊባንቾ እድሜው 24 ሲሆን፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 671(1) (ለ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ክስ ቀርቦበታል።

የወንጀሉ ዝርዝርም ተከሳሽ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማስብ በመጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ15 ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ልዩ ስሙ ቆሼ ታፍ ነዳጅ ማደያ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይ አቶ ያሬድ መንግሥቱ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-በ.38528 አ.አ የሆነ የሻንሲ ቁጥሩ ኤስ ሲ ፒ 10 0325833 የሞተር ቁጥሩ 1 ኤስ ዜደ -0812672 የሆነ እና የዋጋ ግምቱ ብር 830ሺህ ብር የሆነ ቪትዝ መኪና ይዞ የራይድ አገልግሎት ለመስጠት እየተጠባበቀ እያለ ተከሳሽ ጀሞ አካባቢ መንገድ ላይ ቆሞ በመጠበቅ የግል ተበዳይን በማስቆም አየር ጤና እንዲወስደው ጠይቆ በተሽከርካሪው ከኋላ በኩል ከገባ በኋላ፤ ከላይ የተገለፀው አካባቢ ሲደርሱ ደርሻለሁ አቁምልኝ በማለት የግል ተበዳይ መኪናውን እንዲያቆም አድርጓል፡፡

ከኋላ በኩል ሽጉጥ በመደቀን እገልህ ነበር አሳዝነህኝ ነው አሁን ከመኪናህ ውረድ በማለት አስፈራርቶ ከመኪናው እንዲወርድ አድርጎ ተሽከርካሪው ውስጥ የግል ተበዳይን መንጃ ፍቃድ የቀበሌ መታወቂያ የአዋሽ ባንክ ኤቲ ኤም ካርድ ከነሚስጥር ቁጥሩ እንደያዘ ከተሰወረ በኋላ በ29/07/2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 12ሰዓት ከ30 ላይ መኪናውን ሰሌዳ ቁጥር 2-11562 ኦሮ የሚል ለጥፎበት ሲገኝ ሊያመልጥ ሲል በአካባቢው ሰዎች በተደረገ ርብርብ ሲደረግበት መኪናውን ጠሎ ያመለጠ መሆኑን በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሷል።

ሁለተኛ ክስ ወንጀሉ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 አንቀፅ 35/4/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ሲሆን፤ የወንጀሉ ዝርዝር ተከሳሽ የክፍያ ሰነዱን የተሰረቀ መሆኑን እያወቀ በ1ኛ ክስ በተገለፀው ጊዜ እና ቦታ በወሰደው ተሽከርካሪ ውስጥ ያገኘውን የግል ተበዳይ አቶ ያሬድ መንግሥቱ የአዋሽ ባንክ የኤቲ ኤም ካርድ ከነሚስጥር ቁጥሩ በተለያዩ ጊዜያት በመጠቀም ከግል ተበዳይ ሂሳበ ቁጥር ላይ ሃምሳ ሺ ብር የወሰደ መሆኑን የተሰረቀ የክፍያ ሰነድ በመጠቀም ክስ ወንጀል ተከሷል።

ሶስተኛ ክስ ተሽከርካሪ መለያና መመርመሪያ መመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 618/2002 አንቀፅ 48/2/ለ/ ስር የተመዘገበውን በመተላለፍ ሲሆን፤ የወንጀሉ ዝርዝርም ተከሳሽ በአንደኛ ክሰ በተገለፀው አግባብ የወሰደውን ንብረትነቱ የግል ተበዳይ አቶ ያሬድ መንግሥቱ የሆነ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- በ.38528አ.አ የሻንሲ ቁጥሩን ኤስሲፒ 10-0325833 የሞተር ቁጥሩ 1 ኤስ ዜደ -0812672 የሆነውን ተሽከርካሪ የራሱ ያልሆነውን እና ከአቶ ኤሊያስ አዳነ ከተባለ ሰው በተሰጠ ውከልና መሠረት የሚያስተዳድረው በመምሰል እና የሰሌዳ ቁጥር 2-11562 ኦሮ በመለጠፍ ተሽከርካሪውን የተጠቀመበት በመሆኑ በፈፀመው አንድን ተሽከርካሪ የራሱ ያልሆነውን የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ለጥፎ በመገኘት ወንጀል ተከሷል።

 ውሳኔ

 ተከሳሽ ማርቆስ ጡምደደ ጊባንቾ በተከሰሱበት የውንብድና ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ አንደኛ ምድብ በሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓመተ ምህረት በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እና በአስር ሺ ብር ቅጣት እንዲቀጣ ወስኗል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You