‹‹የኮሚሽኑ ዋና ተግባር በየአካባቢው ለግጭት የዳረጉንን ጉዳዮች ወደ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳነት ማምጣት ነው››ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

 ሀገራዊ ምክክር ስር የሰደዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን፣ ግጭቶችን ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውል አንድ አይነት የግጭት መፍቻ ዘዴ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር (negotiation) የተለያየ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክሉ አካላት በሰጥቶ መቀበል መርሕ ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱበት ዘዴ ነው፡፡ ሌላው እርቅ (reconciliation) ሲሆን የደረሰ በደል ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረግና በመተማመን ይቅር በመባባል ስምምነትን ማስፈኛ ዘዴ ነው። የማስማማት (mediation) የግጭት መፍቻ ዘዴ በሦስተኛ ወገን አማካኝነት ልዩነትን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡

ከግጭት መፍቻ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር (national dialogue) ለማድረግ እንዲቻል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋያ አዋጅ አፅድቆ ወደ ሥራ ከገባ አስራ ሰባት ያህል ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ተግባራዊ ያደረገው ዘዴ አካታች ሀገራዊ ምክክርን ሲሆን ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተመራጭ ግጭት መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር አንድ ወጥ ሀሳብ እና አንድ ወገን ብቻውን የሚመክርበት ሳይሆን በየአጀንዳው የተለያዩ ሀሳቦች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መብቶች የሚወከሉበትና ምክክር የሚደረግበት፣ እነዚህን ሀሳቦች የሚያንጸባርቁ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበት ብዝኃነት ያለው መድረክ ስለመሆኑም ተደጋግሞ ይነሳል ፡፡

በዚህም በሀገራችን የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችን እና ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት፣ የተለያዩ ጥቅሞችና የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚሳተፉበት ምክክር የጋራ መፍትሔ ለማምጣት የተመረጠና ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ ሆኖ እየተተገበረ ነው፡፡

የሀገራዊ ምክክር ጥቅም በዋናነት ግጭትን ለማስወገድ፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚጠቅም ነው። በተለይም ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማስተዳደር እና ለመፍታት አይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መነሻ ምክንያቶች ሀገራዊ ምክክሮችን አካሂደዋል። የተወሰኑት የተሳካላቸው ሲሆን በተወሰኑት የሚፈለገውን ግብ ሳያሳካ ቀርቷል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ዓላማዎች መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ መግባባትን ለመፍጠር፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከልና ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመንን ለማጎልበት፣ የመነጋገር የፖለቲካ ባሕልን ለማስፈን፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት በጋራ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ሽግግር ለማስቻል፣ ልማትን ለማፋጠን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር ዓላማ መሠረታዊ አለመግባባቶች፣ ልዩነቶችና ግጭቶች ምን እንደሆኑና መሠረታዊ ምክንያታቸውን መለየት እና በእነዚህ ላይ ልዩነቶችን በምክንያታዊ፣ በሠለጠነ፣ በመቻቻል መንገድ የጋራ መግባባቶች ላይ ለመድረስ እና የግጭቶቹ መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን ለማጥበብ ካልሆነም በልዩነቶች ላይ በመስማማት በሀሳብ ለመለያየት ብሎም ይህን የሀሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን ዘዴ በጋራ በመቀየስ ተግባራዊ ለማድረግ ለመግባባት የጋራ ጥረት የሚደረግበት መድረክ ነው፡፡

ሀገራዊ ምክክር ዓላማን ለማሳካት ምክክሩ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሆች እንዳሉት በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በዚህም መሠረት አካታችነት፣ ግልጽነት፣ ተአማኒነት፣ መቻቻልና እና መከባበር፣ ምክንያታዊነት፣ የምክረ ሀሳቦች ተግባራዊነት እና ዓውድ ተኮርነት፣ ገለልተኛ አመቻች፣ የአጀንዳ ጥልቀትና አግባብነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕግ የበላይነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች በቅን ልቦና እንዲሳተፉ እና ፍትሐዊነት መርሆችን ሊያካትት ይችላል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምን ዓይነት ተግባራትን አከናውኗል? በውጤት ደረጃስ ያለበትና አሁን እየሠራ ያለውን ሥራ በተመለከተ ከኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጋር ቆይታን አድርገናል።

አዲስ ዘመን፦ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እስከ አሁን የተከናወኑ ተግባራት ምን መልክ አላቸው?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ 17 ወራት አካባቢ እያለፉት ነው። በእነዚህ ጊዜያት ደግሞ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፤ በተለይም ሀገር ካለችበት ሁኔታ አንጻር ምን ዓይነት ተግባር ማከናወን ነው የሚጠበቅበት? የሚለውን በጥልቀት በማየትና በመገምገም ብዙ ርቀቶችን ለመጓዝ ሙከራን አድርጓል።

አሁን ላይ የቅድመ ዝግጅት ጊዜውን አጠናቆ የዝግጅት ምዕራፉንም በማገባደድ ላይ ይገኛል። ይህም ሲባል በመላው ሀገራችን ምን መሠራት አለበት? እነማን ናቸው ተሳታፊ ሊሆኑ የሚገባቸው? የሚለውን የማየትና የመወሰን ሥራንም አብሮ እየሠራም ነው።

አዲስ ዘመን፦ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ የዝግጅት ምዕራፉን በማገባደድ ላይ ከሆነ በተለይም በዝግጅት ሥራው ላይ ምን እያከናወነ ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ አዎ በመላው ሀገሪቱ ለምክክር ኮሚሽኑ ግብዓት ይሆናሉ ያስፈልጋሉ ሥራውንም ውጤታማ ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉ ሥራዎችን በሙሉ እየሠራን ነው። በተለይም በሀገሪቱ ካሉ 1ሺ 4 መቶ ወረዳዎች ዘጠኝ ዘጠኝ ባለድርሻ አካላትን የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ውስጥ ደግሞ አስር አስር ሰው ማለትም ከዘጠና እስከ መቶ ሰው ድረስ እየተመረጠ ነው። እዚህ ላይ ከዘጠና እስከ መቶ ሰው ሲባል ምን ለማለት ነው ብትይ ከባለድርሻ አካላት ዘጠና ተወካዮች ይመረጡና የቀሩት አስሩ ደግሞ በወረዳው ላይ ተፈናቃዮች ካሉ ለእነሱ የሚሰጥ እድል ይሆናል ማለት ነው። ከእነዚህ ሰዎች ደግሞ እንደገና ሁለት ሁለት ሰዎች እንዲመረጡ ይሆናል፤ እነዚህ ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ ክልል በመምጣት የወረዳቸውን አጀንዳ የሚያንጸባርቁ ይሆናል።

 በነገራችን ላይ በክልል ደረጃ 16 ገደማ ባለድርሻ አካላት የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን እነዚህ ተቋማት የክልል መስተዳድር ምክር ቤትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎችንም ያቀፈ ነው።

በመሆኑም ከወረዳ የሚነሱት ከክልል ጋር ከሚገኙት ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሰብሰብ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ያላቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች የሚያስረክቡበት ሂደት ይኖራል።

አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ሥራዎች ከተሠሩ የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቋል ማለት እንችላለን?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቀቀ የሚባለው አጀንዳዎች ከተሰባሰቡ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ ክልል የደረሱ ተሳታፊዎች በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን መርጠው ሲያጠናቅቁ ነው።

ይህም ሲባል የወረዳ ተሳታፊዎች ክልል ላይ መጥተው አጀንዳዎቻቸውን ከክልል ጋር አብረው ሰጥተው በተመሳሳይ በፌደራል ደረጃ የተለዩ ተሳታፊዎችም አጀንዳቸውን ሰጥተው ካጠናቀቁ በኋላ በክልልና በፌደራል ደረጃ ለዋናው ሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ይመረጣሉ።

አዲስ ዘመን ፦ ይህ እንግዲህ በሀገር ውስጥ የሚከናወነው ተግባር ነው፤ ነገር ግን የምክክር ኮሚሽኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም ለማሳተፍ እቅድ ይዞ ነበርና እዚህስ ላይ የተሠራው ሥራ ምን መልክ ይኖረው ይሆን ?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ ከላይ ያነሳነው ወረዳ ክልልና ፌደራል የሚባለውን ሂደት አንዱ ነው፤ በስተመጨረሻም ግን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የሚደረግበት አካሄድም ይኖራል። በጠቅላላው በእስከ አሁኑ ሂደት ተሳታፊዎችን በወረዳ የመለየት በእነዚህ መካከል ደግሞ ሁለት ሁለት ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ ማድረግ ተሠርቷል።

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ሥራው በሁሉም ክልሎች ተዳርሷል ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ አሁን በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ መስተዳደሮች ላይ ሥራው ተገባዷል። ከእነዚህ ክልሎች መካከልም ሲዳማ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚገኙበት ሲሆን፡፡ በቀጣይ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግራይና አዲሶቹ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ ለማድረግ ታቅዷል፤ ሶማሌ ክልል በአሁኑ ጊዜ ሥልጠናዎች ተጀምረዋል፤ በቅርቡ በክልሉ በወረዳ ደረጃ የተሳታፊዎች ልየታ ይደረጋል። ቀሪ ክልሎች ደግሞ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን። በዚህ ሰሞን አፋር ላይ ሥራዎች እየተሠሩ ነው በሚቀጥሉት ቀናቶች ደግሞ ሶማሌ ክልል እንሄዳለን።

አዲስ ዘመን ፦ በሥራው ላይ የክልሎችን እንዲሁም የሌሎችን አካላት ተሳትፎና ትብብር እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ ተባባሪዎች ሲባል እንግዲህ እስከ አሁን ድረስ በየወረዳው አምስት ተባባሪ አካላትን መርጠናል፤ በዚህም መምህራን። የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች እድሮች የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ይካተታሉ። በእስከ አሁኑ የሥራ ሂደትም ከእነዚህ ተቋማት ጋር የስምምነት ማዕቀፍ የተፈራረምን በመሆኑ የእኛ ተባባሪ ሆነው በየወረዳው ተወካዮቻችንን የሚያስመርጡልንና ወደፊት እንዲመጡ የሚያደርጉልን ናቸው።

ሥራዎቻችንን የምንሠራው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመጣመር ነው። ለምሳሌ ወደየወረዳው በምንወርድበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲ አጋሮቻችን ብዙ ድጋፎችን ያደርጉልናል። በዚህም የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን በመመልመልና ስለ ምክክሩ ጽንሰ ሃሳብና ሂደት በማሰልጠን ሲሆን እነዚህ መምህራን ደግሞ የአካባቢውን ቋንቋ በመጠቀም ለአካባቢያቸው ሰዎች ሥልጠናውን ይሰጡልናል።

ይህ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የኮሚሽኑ ሥራ ወደአንድ ጎን ያጋደለ እንዳይሆን ለማድረግ ሲሆን በፓርቲዎች ደረጃ እንኳን ተቃዋሚዎችንም በሙሉ ፍቃደኝነት ያሳተፈ በመሆኑ ሥራዎች በትክክል እንዲሠሩና ተመራጮችም በፍጹም ነፃነት ወደፊት መጥተው ቀጣዩን ሥራ ለመሥራት መደላድሎችን ይፈጥራል። ይህ በራሱ አላስፈላጊ የሆኑ ሐሜቶችን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ የኮሚሽኑንም ገለልተኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ በአሁኑ ወቅት ወደሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች እየተንቀሳቀሳችሁ እንደሆነ ገልጸዋል፤ ችግሮች ሲስተዋሉባቸው የቆዩት ትግራይና አማራ ክልል ላይስ ምን ታስቧል፤ ሂደቱ ምን መልክ አለው?

ፕሮፌሰር መሰፍን፦ አዎ ወደሁለቱ ክልሎች ሄደናል፤ አሁን ላይ በሶማሌ ክልል ሥልጠናዎችን ሰጥተን ወደማጠናቀቁ ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ኦሮሚያም እንደዚሁ ነው። ትግራይ እስከ አሁን ድረስ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ሳንሄድ ቆይተናል። ነገር ግን ከቀናት በፊት እኔም ባለሁበት ወደክልሉ ተጉዘን ነበር። በዛም የጊዜያዊ መንግሥቱን ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም ረዳቶቻቸውን አግኝተን ብዙ ነገሮችን ተነጋግረናል፤ በቀጣይም ካቢኔያቸውንና በየደረጃው ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በየክልሉ እንዳደረግነው የማኅበረሰቡን አመራሮች በማነጋገር በዞኖቹና በወረዳዎቹ የሚደረጉትን የሥራ ሂደቶች በሚገባ ለመወያየት አቅደናል።

በነገራችን ላይ ከትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ባደረግነው ውይይት ከፍ ያለ ይሁንታን አግኝተናል፤ የበለጠ ይሁንታን ማግኘት የምንችለው ግን ከካቢኔያቸውና ከሌሎች አመራሮች ጋር በሚኖረን ውይይት መሆኑን እሳቸውም ገልጸውልናል።

እንግዲህ ሀገራችን ላይ ብዙ ችግሮች አሉ በተለይም ጋምቤላ አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ምክትል ኮሚሽነሩ ቡድናቸውን ይዘው ተንቀሳቅሰው አብዛኛውን ችግር ፈተው ተመልሰዋል። በቀጣይም ይህንን ሁኔታ በተጀመረው መልኩ የማጠናቀቅ ሥራም ይሠራል። እዚህ ላይ ግን ኮሚሽኑ ሰላም በደፈረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ሰላምን ለማምጣት ያላሰለሰ ሥራን እየሠራ ቢሆንም መንግሥት በግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች በተቻለ መጠን ወደግጭት ያስገቧቸው አጀንዳዎች በመያዝ ወደ ድርድርና ምክክር መጥተው ነገሮች በሰላም እንዲቋጩ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው። ይህንንም ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ነው ያለን።

አዲስ ዘመን ፦ እንደ ኮሚሽን አብረዋችሁ የሚሠሩ ብዙ ባለድርሻ አካላት እንዳሉ ሲገልጹ ከዚህ በኋላ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፦ ኮሚሽኑ ያለፉትን 17 ወራት ሥራዎቹን ሲያከናውን የቆየው በሙሉ ነፃነት ነው። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አልነበረም፤ እኛም የውጭም ሆነ የውስጥ ጣልቃገብነት እንዲኖር አንፈቅድም፤ በመሆኑም በተለይም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ይህ የምክክር መድረክ በትክክል እንዲሄድና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከፍ ያለ እገዛቸውን ማድረግ አለባቸው።

በመሆኑም ሚዲያ የእኛን መልዕክት ለሕዝቡ ከማድረስ ጎን ለጎን የአስተማሪነት ሚናውንም መወጣት ይጠበቅበታል። በመሆኑም ለየክልሉ ሕዝብ በራሱ በሚገባውና በሚያግባባው ቋንቋ የምክክርን ፅንሰ ሀሳብና ዓውድ ማስረዳት ትልቁ ሥራ ሊሆን ይገባል። የተለመደ ትብብርን ከማድረግ ባሻገር ሰፊ ሚናንም መወጣት የምንጠብቀው ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ?

ፕሮፌሰር መሰፍን፦ የምክክር ኮሚሽኑ የጥቂት አካባቢዎች ሥራ ብቻ አይደለም እየሠራ ያለው። ሁሉንም የሀገራችንን ክልሎችና ሕዝቦች ማካተት መቻል ያለበት በመሆኑ በዚህ ልክ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደዚህ ሥራ መምጣት ይጠበቅባቸዋል።

ኮሚሽኑ ሥራ ሲጀምር አብረውን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሦስት የነበሩ ሲሆን ባከናወናቸው ተከታታይ ሥራዎች ግን በአሁኑ ወቅት የፓርቲዎቹ ቁጥር 47 ደርሷል፡፡ ሥራ ስንጀምር ከእኛ ጋር አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑት ፓርቲዎች ከሦስት ባለመብለጣቸው በወቅቱ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ገብተን ነበር፤ ኮሚሽኑ ደረጃ በደረጃ ባከናወናቸው ሥራዎችና በፈጠረው ቅርርብ በአሁኑ ጊዜ በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ 47ቱ ከእኛ ጋር አብረው ለመሥራት የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራርመዋል። በተከታታይ ሥራዎቻችን የተነሳ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብረውን ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል፤ አሁንም ጥቂት ፓርቲዎች ገና አልመጡም፤ እነዚህ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን እኛም በቀሪዎቹ ጊዜያቶች መሥራት ያለብንን ነገር እንሠራለን።

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኢትዮጵያውያን መሳተፍና መካተት አለባቸው፤ የቀሩትን ትተን ምክክር ማድረግ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ኢትዮጵያውያንና ፖለቲካ ፓርቲዎች ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን እኛ የምንሠራውን ሥራ መከታተል ብቻ ሳይሆን በቀናነት ከኮሚሽኑ ጋር ተገናኝቶ አብሮ መሥራትና መደገፍ ያስፈልጋል። እኛ ሥራችንን እየሠራን ያለነው በሙሉ ነፃነት ነው። እስካሁን የመንግሥት ይሁን የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር አልፈቀድንም፤ መቼም ቢሆን አንፈቅድም።

የኮሚሽኑ ዋና ተግባር በየአካባቢው ለግጭት የዳረጉን ጉዳዮችን እጅግ መሠረታዊ የሚባሉትን ወደ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳነት ማምጣት ነው። ኮሚሽኑ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን እየሠራ ቢሆንም መንግሥትም ሆነ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች በተቻለ መጠን ወደ ድርድርና መነጋገር መጥተው ወደ ግጭት ያስገቧቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ምክክር በማድረግ ችግሮቻቸውን ሊፈቱ ይገባል ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር መስፍን ፦ እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You