መነሻውን ዕውቀትና ልምድ ያደረገው አሚጎስ

ብርቱዎች የዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ብሎም ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ላይ በብዙ ይጥራሉ፤ ይውተረተራሉ፡፡ ለጥረታቸው ስኬትም የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህ አማራጮች መካከል የገንዘብ ቁጠባና ብድር የፋይናንስ ተቋማት ይገኙበታል። የቁጠባና ብድር ተቋም ሰዎች የቆጠቡትን ገንዘብ እስከተወሰነ እጥፍ ድረስ መበደር የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዚህም በርካታ ሰዎች ጓዳ ጎድጓዳቸውን ሲያሟሉ፣ ጥሪት ሲያፈሩ፣ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ሲጀምሩና ሲያስፋፉ ይስተዋላል፡፡

ሀገራት የሚሰሩበትና ኢትዮጵያ ውስጥም እየተስፋፋ የመጣው የቁጠባና ብድር አገልግሎት ተቋም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጉልህ ነው፡፡ ሰዎች ሀብትና ንብረት በማፍራት ነገን የተሻለ ለማድረግ ሲያስቡ ገንዘብ በብድር ማግኘትን ተቀዳሚ ጉዳያቸው ያደርጋሉ። ለዚህ ጥያቄም ለአባላት በቅርበት የሚገኙት የቁጠባና ብድር ተቋማት ምላሽ አላቸው፡፡

በኢትዮጵያም በርካታ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የተቋማቱ አባላት የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ችግሮቻቸውን መፍታት፣ ጥሪት ማፍራት፣ ሀብት ማግኘት የቻሉባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ የቁጠባ ማህበራቱም ከአባላት መዋጮ ተነስተው ብዙ ቢሊየን ብር እስከማንቀሳቀስ የደረሱበት ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፣ ወደ ባንክ ያደጉም እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የቁጠባና ብድር ተቋማት መካከል አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አንዱና ቀዳሚ ተጠቃሹ ነው፡፡ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ በሥራና በትምህርት የሚተዋወቁ ጓደኛሞች ተሰባስበው ያቋቋሙት አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር፤ ማህበረሰቡ የቁጠባ ባህሉን ማሳደግ እንዲችልና ኑሮውን በማሻሻል ነገን ተስፋ እንዲያደርግ ላለፉት አስር ዓመታት ሲተጋ ቆይቷል፡፡

በአስር ዓመት የሥራ እንቅስቃሴውም የአባላቱን ቁጥር አስፍቷል፤ ገቢውንም ከዓመት ዓመት እያሳደገ ውጤታማ ሥራ መሥራት ችሏል፡፡ በ20 አባላት በዘጠኝ ሺ ብር ካፒታል የተጀመረው አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር በአሁኑ ወቅት / ስድስት ሺ / 6000 አባላትን ማፍራት ችሏል፤ ካፒታሉንም ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ነው፡፡

የዕለቱ የስኬት እንግዳችን የአሚጎስ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም አብርሃ ነው፡፡ አቶ ፍጹም በትግራይ ክልል ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ከ8ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ትምህርቱን በአዲስ አበባ ተከታትሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ኢኮኖሚክስ ላይ ትኩረት አድርጎ መከታተል መቻሉ ደግሞ ለዛሬ ማንነቱ እንደጠቀመው ይናገራል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ባጠናቀቀ ማግስት በአንድ የፋይናንስ ኩባንያ ውስጥ ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ በማማከር አገልግሎት ተቀጥሮ ለአምስት ዓመታት አገልግሏል፡፡

የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን በሥራ ላይ ባዋለበት ጊዜ የቁጠባን ጥቅም በሚገባ መረዳት መቻሉን የሚናገረው አቶ ፍጹም፣ በተለይም ህብረት ሥራ ማህበር፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ባንኪንግ ወዘተ… ምን ማለት እንደሆነና ጠቀሜታውን ጭምር መረዳት መቻሉን ይናገራል፡፡ በትምህርት ያገኘውን ዕውቀት እንዲሁም በሥራ ዓለም ያካበተውን ልምድ ቀምሮ የቁጠባና ብድር አገልግሎት ህብረት ሥራ ማህበር ለማቋቋም ከልቡ ተማክሯል፡፡ ምክሩን ወደ ተግባር ለመቀየር ጊዜ ሳይወስድ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ማህበሩን የማቋቋም ሥራ እንደጀመረ ይናገራል፡፡

ሰዎች ቁጠባን ባህል ቢያደርጉ ነገን የተሻለ ማድረግ እንደሚችሉ በልኩ የተረዳው አቶ ፍጹም፤ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በወር ሃምሳ ብር በመቆጠብ ቁጠባው ‹‹ሀ›› ብሎ እንደተጀመረ ያስታውሳል። በወቅቱ አንደኛው አባል ሃምሳ ብር መቆጠብ ባለመቻሉ አርባ ብር ቆጥቦ በወር 140 ብር ሲቆጥቡ ቆይተዋል፡፡ ከስምንት ወራት ቁጠባ በኋላ ግን በማህበር በመደራጀትና አባላቱን በማብዛት የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል በማመን ጓደኞቹን አሳምኖ ተጨማሪ አባላትን በማምጣት ወደ ማህበር ምስረታው ተገባ ፡፡

የፋይናንስ ህብረት ሥራ ማህበር ብዙ ካፒታል የማይፈልግና በቀላሉ የሚጀመር መሆኑ የገባው አቶ ፍጹም፣ በፍጥነት ወደ ማህበር ምስረታው ገባ፤ ሰዎች ቆጥበው እንዲበደሩ በማድረግ ወለድ እንደሚያገኙና ገቢ እንደሚኖራቸው ከጓደኞቹ ጋር በመመካከር አባላቱን ማብዛትና የአባላቱ ቁጥር ሲጨምርም የገቢ መጠናቸው እንደሚያድግ በመረዳት በዘጠኝ ሺ ብር ካፒታልና በ20 አባላት አሚጎስ የቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማህበርን ከጓደኞቹ ጋር መሰረተ፡፡

በቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አማካኝነት ብዙ ሀገራት ማደግ እንደቻሉ የጠቀሰው አቶ ፍጹም፤ ብዙም ገቢ የሌላቸውና በገጠር የሚኖሩ ዜጎች ቁጠባን ባህል አድርገው ተጠቃሚ ሲሆኑ በሥራ አጋጣሚ መመልከት መቻሉን ይገልጻል፡፡ ለዚህም ነው በሥራ ያካበተውን ልምድ ካለው የኢኮኖሚክስ ዕውቀት ጋር ደምሮ ሥራውን ወደ ከተማ በማምጣት ከጓደኞቹ ጋር ቢሠራ ውጤታማ ሆኖ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ያመነው፡፡

ከሁለት ጓደኞቹ ጋር የተጀመረው ቁጠባም ሃያ አባላትን በማሰባሰብ በዘጠኝ ሺ ብር ካፒታል በወርሃ ጥር 2005 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ህብረት ሥራ ማህበር ጽ/ቤት አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር በሚል ስያሜ ተደራጀ፡፡ በሥራና በትምህርት የሚተዋወቁ ጓደኛሞች ተሰባስበው የመሰረቱት ይህ ማህበርም በአሁኑ ወቅት አስር ዓመቱን አጠናቅቆ ለ11ኛ ዓመት የሥራ ውጤት እየተጋ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከአባላቱ ጋርም እንዲሁ በቆጠቡት ገንዘብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በማድረግ ጥብቅ የሆነ ግንኙነትን መፍጠር መቻሉን አጫውቶናል፤ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በጓደኛሞቹ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር መቻሉን ይገልጻል፡፡

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር እስካሁን ባለው የሥራ እንቅስቃሴ ከሶስት ሺ ለሚልቁ አባላቶች ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መስጠት እንደቻለ የጠቀሰው አቶ ፍጹም፤ የብድር ዓይነቶቹም በትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎችም ለተሰማሩ ማቅረብ እንደተቻለ አስረድቷል፡፡ ለአብነትም ቀደም ሲል በትራንስፖርት ዘርፍ ለ2 ሺህ 100 የራይድ አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖችን ገዝቶ ለአባላቱ አስረክቧል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም እንዲሁ ሚስማር የሚያመርቱ፣ በምግብ ዘርፍ የተሰማሩና የጽዳት ዕቃዎችን ፈሳሽ ሳሙና እና ሌሎችንም የሚያመርቱ አባላት የብድሩ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቤት ውስጥ ቁሳቁስ በተለይም ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን በመግዛት በርካታ አባላት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ንግድ ለመጀመር ላሰቡና የጀመሩትን ለማስፋፋት ጭምር ብድር ያገኙ አባላት ስለመኖራቸው የገለጸው አቶ ፍጹም፤ ሰዎች መቆጠብ በመቻላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ያስረዳል፡፡ በተለይም የቁጠባና ብድር ተቋማት በተስፋፉበት በዚህ ወቅት በሚቆጥቡት ገንዘብ ጊዜያዊ ችግሮቻቸውን ከመሻገር ባለፈ ቋሚ ንብረት በማፍራት የገቢ ምንጭ መፍጠርና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጎልበት የቻሉ ሰዎች በርካቶች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በዚህም አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ቁጠባና አክሲዮን በመሰብሰብ የተሻለ የብድር አገልግሎት በማቅረብ የተሳለጡ የማህበራዊ ግንኙነቶችን እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በአባላትና በማህበሩ ዘንድ መፍጠር መቻሉን ነው የገለጸው፡፡

በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ከተማ ውስጥ ያሉትን አሮጌ ላዳ ታክሲዎችን ለመቀየር እያደረገ ባለው ጥረት አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ለባለታክሲዎቹ ብድር እያቀረበ መሆኑን የተናገረው አቶ ፍጹም፤ የአሚጎስ አባል የሆኑ ባለ ላዳ ታክሲዎችን የአዳዲስ መኪኖች ባለቤት ለማድረግ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር በሀገር ውስጥ ከሚገኙና መኪና ገጣጥመው ከሚሸጡ ድርጅቶች ጋር በመዋዋል አዳዲስ መኪኖችን እንዲያቀርቡ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ላይ 200 ታክሲዎችን በአዳዲስ መኪኖች ለመተካት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቅሶ፣ አባላቱ ከ20 እስከ 35 በመቶ ቆጥበው አዳዲስ መኪኖችን ከኩባንያው ማግኘት የሚችሉበትን ውል ፈጽመዋል ብሏል፡፡

ማንም ሰው የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አባል መሆን እንደሚችል አቶ ፍጹም ጠቁሟል፤ ማህበሩ ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖትና ከብሔር ነጻ መሆኑን ጠቅሶ፣ ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ሰው አባል መሆን እንደሚችል ነው ያስረዳው፡፡

ማህበሩ በአስር ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶም ሲያብራራም፤ አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት ማህበሩ በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑን ገልጿል፡፡ ማህበሩ የብድር አገልግሎቱን ባቀደው ልክ እንዳይሰጥና አባላቱም ብድሩን ባገኙ ጊዜ ገበያው ላይ ወጥተው የፈለጉትን መግዛት እያስቻላቸው አለመሆኑን የገለጸው አቶ ፍጹም፤ በየጊዜው የሚጨምረው የዋጋ ንረት የሰዎችን የመግዛት አቅም እያዳከመና የማህበሩን የማበደር አቅምም ውስን አድርጎታል ነው ያለው፡፡

ሌላው የሁሉም ነገር መሠረት የሆነው ሰላም በራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ፤ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳደር ጠቅሶ፣ ለዚህም በትግራይ ክልል ጦርነት በነበረ ወቅት የባንኮች መዘጋት ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ፣ የሰላም እጦት ቢዝነሱን እንደሚጎዳ አመልክቷል፡፡

ባንኮች ከአብዛኛው ማህበረሰብ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለጥቂቶች ወይም ትልቅ ሀብት ላላቸው የሚያበድሩ መሆናቸው የጠቀሰው አቶ ፍጹም፣ እንደ አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ያሉ ተቋማት ገንዘቡን ለቆጠበው አባል ሁሉ የሚያበድሩ በመሆናቸው ከባንኮች በእጀጉ ይለያሉ ይላል፡፡ ዓላማቸውም ሰዎች ገንዘባቸውን ቆጥበው መበደር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነ አስረድቶ፣ በዚህም አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ እንደሚያደርጉ ተናግሯል፡፡

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ለሌሎች አርዓያ መሆን እንዲችል በተለያየ ጊዜ ስልጠና እንደሚሰጥ የጠቀሰው አቶ ፍጹም፤ በተለይም በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ለሚፈልጉ የተለያዩ አካላት በዘርፉ ስልጠና ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጿል። ይህም ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ መካከል ተጠቃሹ እንደሆነ አመላክቶ፣ ከዚህ በተጨማሪም በክፍለ ከተማው የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አቅመ ደካሞች በማገዝ እንደሚሰራም ተናግሯል፡፡ ለተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን ያደርጋል ብሏል። ሀገራዊ በሆኑ ጥሪዎችም እንዲሁ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ሥራ አስኪያጁ እንደሚለው፤ የቁጠባና ብድር ተቋሙ 70 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ በትርፍ ጊዜ የሚሠሩ አስር የሚደርሱ ሠራተኞች/ አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው/ አሉት፡፡ በቀጣይም ማህበሩ የአባላቱን ቁጥር በማስፋትና የብድር መጠኑን በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተጋ መሆኑን መሆኑን አመላክቷል፡፡ በተለይም የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል የአባላቱን ቁጥር እስከ አስር ሺ ለማድረስና አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማፍራት ዕቅድ እንዳለው አቶ ፍጹም ተናግሯል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You