ከኑሮ ውድነት ጫና ለመላቀቅ ወደራስ መመልከት!!

በአሁኑ ግዜ ኑሮ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ጫና ይህ ነው ተብሎ ሊገለፅ አይችልም። የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል፡፡ በኑሮ ውድነት ያልተፈተነና ያልተማረረ የኅብረተሰብ ክፍል የለም። ዋጋ ያልጨመረ የምግብና የሸቀጣቀጥ እቃ የለም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ኅብረተሰቡ ከነገ ዛሬ የኑሮ ውድነቱ ይቀነሳል ብሎ ተስፋ ቢያሳድርም እስካሁን ድረስ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በመንግሥም በኩል የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ቢኖሩም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

በርግጥ አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የነዳጅና ሌሎች ሸቀጣሸቀጦች መናር ነፀብራቅ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ሀገራት በዚሁ የኑሮ ውድነት ጦስ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ዜጎቻቸውም ኑሮን መቋቋም ተስኗቸው በከፋ ችግር ውስጥ ቀናትን አሸንፎ ለመውጣት በብርቱ እየታገሉ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት አሁንም አስደንጋጭ የሚባል ደረጃ ላይ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ የባሱ በርካታ ሀገራት አሉ፡፡ ለምሳሌ በቱርክ የዋጋ ንረቱ 70 ከመቶ ደርሷል። በአርጀንቲና 51 በመቶ ተጠግቷል፡፡ በሲሪላንካ ደግሞ 30 ከመቶ ሆኗል፡፡

እንደውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል የሆነው የዓለም ሠራተኞች ድርጅት/ ILO/ እንደሚለው ከሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ጨምሯል። ባለፈው መጋቢት ወር የዋጋ ንረቱ 3 ነጥብ 7 ከመቶ ብቻ እንደነበር፣ በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር ወደ 9 ነጥብ 2 ከመቶ ማሻቀቡን ተናግሯል፡፡ ይህም ማለት የማንኛውም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች እንዲሁም የአገልግሎቶች ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሻቀቡን ይጠቁማል፡፡

ዓለም ከሚገመተው በላይ በንግድ ሰንሰለት የተሳሰረ ነው፡፡ ለምሳሌ የኮቪድ ወረርሽኝንና ምጣኔ ሀብትን ምን ሊያገናኛቸው ይችላል? ተብሎ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ መልሱ በሚገባ ይገናኛሉ ነው። ምክንያቱም በንግድ ዓለም ሁሉ ነገር የተሳሰረ በመሆኑ ነው፡፡ እንዴት ከተባለ ደግሞ ለምሳሌ ኮቪድ በግዜው የእንቅስቃሴ ገደብ አስከትሏል፡፡ ላብ አደር ፋብሪካ አልሔደም፡፡ ምርት አልተመረተም፡፡ በዚህም ፋብሪካዎች ምርት ቀንሰዋል፡፡ ሠራተኛው ሥራውን አጥቷል፡፡ ሸማችም ምርት አልደርስ ብሎታል፡፡

በኮቪድ ምክንያት እዳቸውን በቱሪዝም ገቢ የሚከፍሉ ሀገራት ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ አምራች ሀገራት በበቂ ሁኔታ ማምረት አቁመዋል፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን አስከትሏል፤ ይህንኑ ተከትሎ የኑሮ ውድነት ተከስቷል፡፡ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ በፊት የተፈጠረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትም ሁለቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ስንዴ አምራቾች ምርት መላክ በማቆማቸው ዓለም አቀፍ የስንዴ ምርት እጥረት ተከስቷል፡፡ በዚህም በስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ታይቷል፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ደግሞ በኑሮ ውድነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

በየዘመኑ የኑሮ ውድነት ይከሰታል፡፡ የዘንድሮውስ የከፋ ነው ሲባል ሌላ የከፋ ይመጣል፡፡ ነገሩ ከሚገመተው በላይ ውስብስብ በመሆኑ ሀገራትም ይህንን የሚቋቋሙበት ሁነኛ መላ የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ቀጥተኛ መልስ መስጠት የሚከብዳቸው፡፡ ሆኖም ግን ከችግሩ መውጣት የሚያስችለው አንዱ መንገድ ምርትን መጨመር ነው፡፡ እርግጥ ነው ደሃ ሀገራት መርፌም ጭምር ከውጪ ሀገራት ስለሚያስገቡ ከዚህ የኑሮ ውድነት ለመውጣት ፍዳቸውን ማየታቸው አይቀሬ ነው፡፡

አንዳንድ ሀገራት አሁን እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ የየራሳቸውን ስትራቴጂ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የሀገር ውስጥ ምርታቸውን በስፋት በማሳደግና ከውጭ ሀገር የሚያስገቧቸውን ምርቶች በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን ጫና በመጠኑም ቢሆን መቀነስ ችለዋል። ሌሎቹ ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርታቸውን በማሳደግ ያጋጠማቸውን የኑሮ ውድነት ጫናን ከመቋቋም አልፈው ለሌላም ሀገር ተርፈዋል፡፡ ያ ማለት ምርቶቻውን ወደውጪ ሀገራት በመላክ የውጪ ምንዛሪ ጭምር እስከማግኘት ደርሰዋል፡፡

ኢትዮጵያም ብትሆን የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እያደረገቻቸው ካሉ ጥረቶች ውስጥ አንዱ ይሄው የሀገር ውስጥ ምርት መጠንን ማሳደግና ለዜጎቿ በስፋት ማቅረብ ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያው በተለይ ስንዴን በስፋት በማምረት ለዜጎች ማቅረብና አለፍ ሲል ደግሞ ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪ ማግኘት ነው፡፡ ይህ ስንዴን በስፋት የማምረት ሥራ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በስፋት ተሠርቶበት ከፍተኛ ምርት ማግኘት ተችሏል። እንደውም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ኬንያ ልካ የውጪ ምንዛሪ እስከማግኘት ደርሳለች፡፡ አሁን ደግሞ ለዜጎቿ ስንዴን የማዳረስ ሥራ በስፋት ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች፡፡

ይህ በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የስንዴ ምርት በማሳደግ የዜጎችን የኑሮ ጫና የመቀነስና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ስልት እጅግ የሚያበረታታ ነው። እንደውም ከበቂ በላይ ስንዴ በማምረትና ወደውጪ ሀገራትም ጭምር በመላክ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘትና አሁን የሚታየውን የውጪ ምንዛሪ ክፍተት ለመሙላት በእጅጉ ያግዛል፡፡ ከዛ ባለፈም የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ለሌሎች አንገብጋቢና ለኑሮ ውድነት ጫና ማርከሻ ለማዋል ያግዛል፡፡

በሀገር ውስጥ ስንዴን አምርቶ አሁን የሚታየውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት ታዲያ ሌሎች ምርቶችንም በማምረት ሊደገም ይገባል፡፡ በተለይ ወሳኝ የሆኑ እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ዱቄትና ሌሎችንም አላቂ የምግብ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ሊለመድ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት በስንዴ ልማት ላይ የጀመረውን እንቅስቃሴ በነዚህ ሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ላይ ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡

ምንም እንኳን የኑሮ ወድነቱ ከአቅም በላይ ቢሆንም አንዳንድ ግዜ ወደራስ ተመልክቶ ለችግሩ መፍትሔ ማበጀት አንድ ነገር ነው፡፡ ኑሮ እያደረሰ ያለውን ጫና አምኖና ተቀብሎ መደቆስ ሕልውናን ማሳጠር ነው፡፡ እናም ለኑሮ ውድነት እጅ ሳይሰጡ ለመኖር በዜጎችም በኩል ትግል ማድረግ ይገባል፡፡

ስለዚህ በፍላጎት መናር የሚከሰተው የዋጋ ንረት የምርት እጥረትን ይፈጥራልና ነጋዴዎች የፍላጎትን መጨመር በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ ሲሳናቸው ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት በዚህ በኩል ለኑሮ ውድነት አስተዋፅዖ የሚያደርጉና በአንዳንድ ሕገወጥ ነጋዴዎች የሚደረጉ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን በመከታተል እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡

የነዳጅ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን በማስከተል ረገድ ከሚጠቀሱ ዋንኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው። ነጋዴዎች ዋጋ ቢጨምሩም ተገልጋይ ወይም ሸማች በቀላሉ ስለማይሸሽ አያሳስባቸውም፡፡ በተደጋጋሚ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ይህን ችግር በተወሰነ መልኩ ለመቋቋም ሸማቹ የነዳጅ ዋጋን ታከው ከሚጨምሩ ምርቶች ለመራቅ የራሱን አማራጭ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ትራንስፖርት ዋጋ ከጨመረ የሕዝብ ትራንስፖርቶችን መጠቀም አልያም ደግሞ ግማሹን መንገድ በእግር በመሄድ ጤንነቱን ጠብቆ ገንዘቡን ማዳን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለኑሮ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ብቻ በመሸመት ከዚህ የኑሮ ውድነት ማምለጥ ይቻላል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You