ችግሮችን በውይይትና በድርድር መፍታት በብዙ መልክ አትራፊ መሆን የሚያስችል ሰብዓዊ እሴት ነው። በተለይም በግጭት አዙሪት ውስጥ እየኖሩ ላሉ፣ በዚህም በየዘመኑ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ለሚገደዱ የኛ ብጤ ሕዝቦች ችግሮችን በውይይትና በድርድር መፍታት እንደ ሀገር ያላቸውን ሕልውና አስጠብቆ የመሄድ ያህል ትርጉም ያለው እውነታ ነው።
በርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የልዩነት ምንጭ የሚሆኑ አስተሳሰቦች መፈጠራቸው ተፈጥሯዊ ነው። እነዚህ የሀሳብ ልዩነቶች አንድን ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ /የአስተሳሰብ ዓውድ/ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ማሻገር የሚያስችሉ ማኅበረሰባዊ አቅሞች ናቸው። እነዚህ አቅሞች ደግሞ የማኅበረሰቡ ፀጋዎች ተደርገውም ይወሰዳሉ።
እነዚህን ልዩነቶች አቻችሎ ማስተናገድ የሚያስችል የአስተሳሰብ ማዕቀፍ በተዘረጋበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ እነዚህ ልዩነቶች ማኅበረሰቡን ከትናንት በመውጣት ዛሬን በራሱ መዋጀት የሚያስችል አቅም በመፍጠር፣ ነገን የበለጠ ብሩህና በተስፋ የደመቀ በማድረግ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ጉልበት በመሆን ያገለግላሉ። የለውጥ እና የመለወጥ አስተሳሰብ መሠረትም ይሆናሉ ።
እነዚህን የአስተሳሰብ ልዩነቶች በኃይል/በጉልበት ለመደፍጠጥ እና ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶች፤ ማኅበረሰብ ከትናንቶቹ ጋር አብሮ እንዲኖር የመፍረድ ያህል ነው። ውጤቱም ማኅበረሰብ ከትናንት ችግሮቹ፣ ችግሮቹ ከሚወልዱት ሁለንተናዊ መጎዳቶች ጋር አብሮ እንዲኖር የማስገደድ ያህል የከፋ ወንጀል ነው። በማኅበረሰብ ዛሬና ነገዎች ላይ መፍረድም ነው።
ይህንን የከፋ ወንጀል ለመከላከል ሆነ ለማስቆም ከሁሉም በላይ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕልን ማበልጸግ ወሳኝ ነው። በተለይም በለውጥ ማግስት የሚፈጠሩ ልዩነቶች የለውጡ አካል ብቻ ሳይሆኑ፤ ለለውጡ ማግስት ተግባራት ስኬትም አቅም መሆናቸውን ተገንዝቦ ልዩነቶችን በሆደ ሰፊነት ማየት፣ ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶችን መዝጋት የግድ የሚያስብል ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ለመለወጥ ካለን ከፍ ያለ መሻት አንጻር በተለያዩ ወቅቶች ሀገራዊ ለውጥ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ንቅናቄዎችን መፍጠር ችለናል። በነዚህ የለውጥ ንቅናቄዎቹ የየዘመኑ ትውልድ ብዙ ተስፋዎችን ሰንቆ ስለተስፋዎቹ እራሱን መስዋዕት ማድረግ በሚያስችል ቁርጠኝት ተሰልፏል።
ይህም ሆኖ ግን ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት የሚያስችል ሀገራዊ/ ማኅበረሰባዊ አቅም ባለመፍጠሩ ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች ከተከናወኑ ለውጦች የተገኘው የተጠበቀው/ተስፋ የተደረገው ሳይሆን ያልተጠበቀው ሆኗል። ይህም በየወቅቱ የፈጠረው ሀገራዊ ስብራት ከፍ ያለ ነው።
ከነዚህ የትናንት የለውጥ ታሪክ ስብራቶቻችን መማር ባለመቻላችንም በዚህም ዘመን እንደ ሕዝብ የተፈጠረው የለውጥ መነቃቃት በተነሳበት ልክ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችልበትን ፍጥረታዊ ጉዞውን አደነቃቅፈናል፤ ከዛም ባለፈ በሀገሪቱ የቀደሙ የታሪክ ምዕራፎች ባልታየ መልኩ የሀገርን ሕልውና/እንደ ሀገር የመቀጠል ተስፋ አደጋ ውስጥ በሚከት ያልተገባ መንገድ ላይ ተገኝተናል።
ማንንም አሸናፊና ተሸናፊ በማያደርግ፤ ከሁሉም በላይ ሀገርና ሕዝብን ማቅ ያስለበሰ ትርክት ለመጻፍ የተገደድንበት የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ግጭት እንዳይከሰት ብዙ የሰላም እጆች ከፍ ብለው ቢውለበለቡም፤ ሰላም የአንድ አካል ፍላጎት ብቻ ባለመሆኑ ሊሳካ አልቻለም።
የዛሬውን ጥቅምት 24 ስናስብም፤ ከሁሉም በላይ የሰላምን ዋጋ በማጤን፤ ችግሮችን በድርድርና በውይይት የመፍታትን ሁለንተናዊ ጥቅም በማሰላሰል፤ ተመሳሳይ ችግር በቀጣይ ትውልዶች እንዳይደገም መሠረታዊ የአሰተሳሰብ ለውጥ ለመፍጠር ከራሳችን ጋር ቃል በመግባት ሊሆን ያስፈልጋል።
አለመግባባቶችን በኃይል ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፤ አለመግባባቶችን በሀገርና በሕዝብ ስም በኃይል ለመፍታት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖችን በቃችሁ የሚል የጋራ አስተሳሰብ በመገንባት፤ ሰላማችንን አስተማማኝ በሆነ መንገድ መጠበቅ የሚያስችል ሀገራዊ ማንነት በመፍጠርና ለመጪው ትውልድ በጠንካራ መሠረት ላይ በማዋቀር ጭምር ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2016