እኔ ውብሊቀር ተበጀ ነኝ። ሰካራሙ…. ስካር የአባቴ ነው። የሰካራሙ ተበጀ ልጅ ነኝ። አባቴ ተበጀ የጉለሌው ሰካራም፤ ዶሮ ነጋዴው፤ ነፍሱ ከአሳማ ያነሰው የተበጀ ልጅ ነኝ እኔ ውብሊቀር… እጠጣለሁ፤ ጠጥቼ ያየሁትን እናገራለሁ። ማን ሊከለክለኝ ይችላል? ማንም!!
እኔም ግራ ይገባኛል… ኧረ አሁንስ ”በጋራም” አልገባ ብሎኛል። ሰው መሀል ተፈጥሬ ሠላም የማገኘው ጃምቦ (መጠጥ) መሀል ስለሆነ ነው። ለምን? እኔ እንጃ! ይሄ እኮ ነው በግራም በቀኝም አልገባ ያለኝ። የሰው ወሬ ሁሉ ፍግ ፍግ ይላል…. ፍግ ምንድን ነው? የከብቶች እዳሪ!… እሱን እሱን ይለኛል። አንድ ቀን እኔ ዘና (ፏ) ብዬ እየጠጣሁ… አንዱ መጣና፤ አንተ ሁል ጊዜ የምትጠጣው ”ሜቴክ” ነህ እንዴ አለኝ። የሜቴክ ኃላፊዎቹን ማለቱ ነው። ይህ አባባሉ በሁለት ነገር አናደደኝ። አንደኛ እኔ የምጠጣው እንደሱ ሀሳብ የዘረፍኩት ገንዘብ ስላለኝ አይደለም። ባገኝ፣ ቢደላኝ ለምን እጠጣለሁ?! እየጠማኝ መሰለው እንዴ የምጠጣው? አይደለም!! መጠጣት ስላለብኝ ነው። ለምን ቢባል? እኛ እናውቃለን!!
ሁለተኛው ”ሜቴክ”ን ካነሳ አይቀር ለምን ገንዘቡ ብቻ ትዝ አለው? በተቋሙ ውስጥ ገንዘብ ብቻ ነው እንዴ የሚዘረፈው?! ኧረ ስንቱ…። ይልቅ ከዚህ ሁሉ ለምንድን ነው የምትጠጣው? ተገርፈህ፤ ተኮላሽተህ ወይስ ተጠቅተህ ነው? ለምን አላለኝም? የቱ ነው የሚያስጠጣው? ገንዘብ መኖር ወይስ መጠቃት ነው የሚያስጠጣው? አውቃለሁ መራብ መጠማት እንደ መጠቃት ቁስሉ አይጠናም እንጂ ለመጠጣት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
መጠቃት ግን በጣም ያስጠጣል፤ ያከሳል፤ ዝቅ ያደርጋል፤ ያስከፋል፤ ስለዚህ የዚህ ሁሉ ማርከሻዬ መጠጥ ነው። እጠጣለሁ….. ካልጠጣሁ ምን እሆናለሁ?! ሲዖል እገባለሁ፤
ቂ ቂ ቂ….iii
ዛሬ አይ…ደለም ትናንት ነው እንጂ…. አንድ ጓደኛዬ ደብዳቤ ገምግምልኝ አለኝ። ለማን ልትልከው ነው? ለሚስትህ ወንድም ወይስ ለልጅህ ክርስትና አባት አልኩት። ”አይደለም አለኝ።“ ታዲያ የምንድን ነው? ስለው “የፍቅር!“ ነው አለና ደብዳቤውን አቀበለኝ። ተቀበልኩ እና አነበብኩት። “እቴዋ እኔ ላንቺ ያለኝን ፍቅር ለመግለፅ ቃላት ያጥሩኛል“ ብሎ ይጀምር እና አራት ገጽ ጽፏል። ቃል ባያጥረው ስንት ገጽ ሊጽፍ ኖሯል?! ኧረ…. ሀፍረት ማጣት፤ ሚስቱን እና ልጁን አስቀምጦ ለኮረዳ የፍቅር ደብዳቤ መጻፍ! የእንደዚህ ያለ ሰው ጭንቅላት እንኳንስ ለዕውቀት ለተባይም አይመች፤ ቅል ራስ!!
ጽግዬ ውዷ ባለቤቴ መጣሁልሽ…. እግዜር ንዝነዛሽን አቅርቦ ዘነዘናሽን ያርቀው… ይሄው አልጠጣም ብየሽ ነበር። ግን ላንቺ ብዬ ነው የጠጣሁት። አትጠጣ ያልሽኝ እንዳልሞትብሽ አይደለም? አዎ እንዳልሞትብሽ ብዬ ነው የጠጣሁት…. አልጠጣም ብዬ ቁጭ ብዬ ነበር። ነፍሴ ግን ትታኝ ልትወጣ ቁጥር ትቆጥርልኝ ጀመር… አንድ አለችኝ… ሁለት ቀጠልኩ፤ ሦስተኛው ላይ ልትወጣ ስትል አንቺ ትዝ አልሺኝ….. ከዚያ ጉሮሮዬ ላይ ደርሳ የነበረችውን ነፍሴን እንደ ክኒን በአንድ ጃምቦ ድራፍት መልሼ ዋጥኳት!! ላንቺ ስል።
እኔ ሰካራሙ ውብሊቀር ተበጀ እጠጣለሁ….. ለምን? በል! ፖለቲካው እሳት፤ ኑሮው እሳት፤ አየሩ እሳት ነው። በዚህ መሀል እኔ ማገዶ ነኝ…ተቃጠልሁ እኮ!….. ስቃጠል ጠጣሁ።
‹‹አስማት ነው ኑሯችን አይታመን ከቶ፤
ወጫችን አንድ ሺህ ደሞዛችን መቶ››
አለ ኤዲያ!!
“እኛ ኤትዮዽያውያን የችግራችን መደራረብ በበርገር መሀል ያለ የሰላጣ ቅጠል ያስመስለናል” አለ ቢሻው። ወዳጄ ቢሻው ሞተ። እናንተ እንደፈለጋችሁ ብሎ ሞተ። ሚስቱ ደውላ አረፈ አለችኝ። ሞተ አይደለም አረፈ ነው ያለችኝ ቂቂቂ…. ከርታታው፤ የዋሁ እና ባካኙ አንድ ቀን ሳያልፍለት፤ አንድ ቀን ሳይተነፍስ እንደ ፊኛ ታፍኖ ተቀበረ። አይ አንቺ ምድር… አይጠረቃ! ስንቱን በምስጢር ደፈርሺው? ስንቱን በእንቅፋትሽ ጥለሽ ሰለቀጥሺው። ዕድሜ ላንቺ ታድሎ፤ ለእኛ ተነፍጎ ደረትሺን ነፋሽብን፤ ቅስት አድርገሽ በእኛ ሥጋ ደረትሺን ነፋሺብን።
“ኢትዮዽያ ቁማር ተበላች” ይል ነበር… ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ እና ከምዕራብ አገራት ተሰባሰቡና ጠጅ እና ጃንቦ ድራፍት እየጠጡ ቁማር ጨዋታ ገጠሙ አሉ። ኢትዮዽያ ጠጇን ትታ ደብል ጃንቦ እየለጋች ቁማሩ ተጀመረ። መጀመሪያ በሃምሳ ዶላር በላች፤ ቀጥላ በመቶ በላች። ከዚያ በአምስት መቶም ደግማ በላች። ይሄኔ ዓፄ “እኛ ስዩመ እግዚአብሔር ነን” ብለው እግዜርን የቁማር ተባባሪ አደረጉት።
ከዚያም በተከታታይ ዕድል ስለቀናት ባላት አስይዛ ጨዋታዋን ቀጠለች። በዚህን ጊዜ ተበላች። ለማስቀጠል የሚያስችል ስላልነበራት እያበደሩ ይበሏት ጀመሩ። ይኼው እስከ ዛሬ ስትለምን አለች። “አዕምሮዋን፤ ዕውቀቷን ቁማር ተበላች” ይል ነበር ቢሻው። አዬ ቢሻው እንደ ሰንደል ጭስ ጭሶ አለቀ። ይቺ አትጠረቃ ምድር በላችው። ጠጥተን ስናየው፤ ይቺ ምድር ለእሷ ያለን የመብላት አባዜ አለባት።
ጠጥታችሁ ስታዩት ሁሉ ነገር ምስጢር ነው። ስካር ምስጢር ነው፤ ትዳር ምስጢር ነው፤ ኑሮ ምስጢር ነው። ምስጢር የሆነው በምክንያት ነው። ዓለም ከድንጋይ ቀጥላ የተሞላችው በምስጢር ነው። ሰው በየቦታው ይገደላል። ገዳዩ አልሸባብ ወይም አይኤስ አይኤስ ይባላል። አለዚያ በተፈጠረ ግጭት…. ባልታሰበ አደጋ ቅብርጢሴ ቅብርጢሴ ይባልልኛል። ሰው በድንገት የሚሞተው በትራፊክ አደጋ ብቻ ነው።
ያውም ከስንት አንድ ጊዜ። ስም አይጠቀስ እንጂ እያንዱ ነገር የሚደረገው ታቅዶበት እና ታስቦበት ነው። ለምን ብትሉ ምስጢር ነው!! ይህን ለማወቅ እና ለማውራት መጠጣት ያስፈልጋል። ጠጅ እና ጃንቦ ድራፍት መቀላቀል ያስፈልጋል። ኤዲያ….. ስካር እና ህልም አያሳዩት የለም። አይ ጽግዬ….
ጽግዬ ይቅርታ አርጊልኝ፤ እኔ የምጠጣው እንዳልሞትብሽ ብዬ ነው።
እኔ የምጠጣው እንዳልሞትብሽ ብዬ ነው። እኔ የምጠጣው ጃንቦ ድራፍት ጠምቶኝ አይደለም፤ ጠጅ ስለምወድ አይደለም። መስከር ስለምፈልግ ብቻ ነው። ይሄ እኮ ነው ፅግዬ እኔ ውብሊቀር ተበጀ ሰካራም ነኝ… ሰካራም የሚለው ማዕረጌ ሎሬት ወይም ክቡር ኢንጅነር ዶክተር ከሚባሉት የማዕረግ ስሞች ይበልጣል… ምክንያቱም በሥራዬ ስለተሰጠኝ፤ ትክክለኛ ስለሆነ፤ እኔን ስለሚገልጠኝ ማዕረጌን እወደዋለሁ፤ እኔ ሰካራሙ ውብሊቀር ተበጀ።
ለምንድን ነው የምናደደው? ሰው ሆኜ እንደሰው መኖር ስላቃተኝ?፤ ትዳር ይዤ ቤት ስለሌለኝ?፤ ልጅ እና ሆድ ይዤ ምግብ ስለሌኝ? ወይስ ግጥሜን ስላጣሁ ነው? ግጥሙን ሲያጣ እንኳን ሰው እስክርቢቶ ይገነፍላል።
ድሀ አትሁን፤ ድህነት መጥፎ ብቻ ሳይሆን ጅብ ነው። አፈሩ ይቅለለውና ወዳጄ ቢሻው አንድ ቀን በጧት ፊቱ በልዞ መጣ። ምን ሆነህ ነው ፊትህ የበለዘ? ከማን ጋር ተደባደብህ? ስለው “ማታ በህልሜ ኑሮ የሰው ሥጋ ለብሶ ሲደበድበኝ አደረ” አለ። ኑሮ ረቂቅነቱን ትቶ እንደ አውሬ እያስፈራራን ነው። እኔማ አንዳንዴ ፌዴራል መጥራት ያምረኛል። ኡ..ኡ… እልና “ምን ሆንክ?” ሲሉኝ፤ ኑሮ ጥቃት አደረሰብኝ እለዋለሁ። እሱ ምን ይለኛል?! “ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ነው” ይለኛልii
ቆይ ጥበቃ ሊደረግበት የሚገባ ሰው ነው ወይስ ኑሮ?! ብዙ ሰው የፈጀው ኑሮ አይደለም እንዴ? ጠጥተንም ሆነ ሳንጠጣ ስናየው ጨካኙ ኑሮ ነው። ፖሊስ ከኑሮ ከለላ ሊያደርግልን ይገባል። ሰው ነው ጨካኝ አትበሉ። ሰውን ጨካኝ ያደረገው ኑሮ ነው። መንግሥት ቀድመህ ጅብህን እሰርልን። በርግጥ “የቀኖችን ጅቦች” አስረሃል። ይኸኛው ጅብ ግን የቀንም የሌሊትም ስለሆነ መታሰር አለበት። ወዳጄን በላ፤ እኔ እና ጽግዬን ሊበላን እያሳደደን ነው።
ጽግዬ የእኔ ውድ፣
የኔ ጥቁር አዝሙድ፤
የኔ ማር፣ የኔ ‘ጣን፣
ተነስቶብሽ ይሆን፣
የነከሰሽ ሰይጣን? ለማንኛውም መጣሁልሽ ራዲዮን ከፍተሸ ጠብቂኝ አሽሙርሽ ናፍቆኛል።
ሁለት
ኧረ አሽሙር፤ አሽሙር ሊደፋን ነው። ሰውዬው ምን አለ… ማለቴ ራዲዮኑ ሰውማ እንዴት ይህን ይላል? “በ2030 ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ከሀገራችን እናጠፋለን።” ይህን ስሰማ እንዴት ቢሆን ብዬ አሰብኩ። አዎ! ሊሆን ይችላል፤ ሊቆም ይችላል። ግን የሚቆመው አጥፍተነው ሳይሆን አጥፍቶን ሊሆን ይችላል አልኩ። አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት ሰዓትን አሳልፎ “ጥሙን” ሲለጋ እያደረ ኤች.አይ.ቪን በ2030 እናስቆማለን! አፈር ሁን እና ሐውልት ይቁምልህ! ይህን እኔ ሰካራሙ ውብሊቀር ተበጀ ስምንት ጃምቦ ድራፍት ጠጥቼ እንኳ አልናገረውም።
ውሸታም ዝም ብሎ ይቀደዳል! አሁንማ ራዲዮኟ ራሷ የምትሰማው ነገር እያስገረማት ኧረረረ…ሩሩሩ ትላለች። ለምን አይገርማት! ትናንት በከርሷ “ሀገሪቱን ለማፈራረስ እና ወደ የዕርስ በዕርስ ጦርነት ለመውሰድ፤ ሕገ መንግሥቱን ለመጣስ የሽብር ወንጀል የሠሩ ሰዎች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው ብሎ ዜና ያነበበ ጋዜጠኛ (ሰው)፤ ዛሬ እነዚያን ሰዎች ስለ ዕውነት እና ስለ ሕዝብ በመቆማቸው ምክንያት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች ከእስር ተፈቱ ብሎ ተናገረ። እውነት ይህ የዜና አንባቢ የራዲዮኔን ያህል ሞራል የለውም። እሱ ላወራው ራድዮኔ አፈረች። ስንቱን ታዘብነው?!
አይዘመን ማሠሮው አይዘመን መንገዱ ከጠበንጃ በልጦ
አገላብጦ አሳየን ቃል እንደ ሽልጦ።
እኔ እና ራድዮኔ አንታለልም። እኛን ማታለል ከባድ ነው። አንድ ሰው ሊያታልል ይችላል። ሀገር ካልጠጣች ትታለላለች። የእኛ ሀገር ጠጅ ትጥላለች፤ አረቄ ታወጣለች ግን ጠጥታ አታውቅም። እናም ትታለላለች። ዋ! ዛሬ! ዋ! አሁን! እየተታለለች ከሆነ? ዋ! ደግሞ ‘ኮ ይመስላል። ጠጥታችሁ ስታዩት ይመስላል። ሰው ሲታለል ሳቅ፤ ሀገር ስትታለል ምስራች ይበዛል። አንድ ሰጥቶ ሁለት ከወሰደ ይሄ ማታለል ነው። አንድ ስቶ ሁለት ከገደለ ይሄም ማታለል ነው። ”ፖለቲካ ቆሻሻ የመሃይሞች ዋሻ ነው። ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ሳትፈርስ ቤተ መንግሥቴን አልገነባም“ አለ አሉ ሰይጣን። የጠጣ ነው የነገረኝ።
ጽግዬ መጣሁልሽ! የኩኩዬ እናት፤ ጽግዬ ኤዲያ ወዲያ ተይው ኑሮ እና ኪስ ሞልቶ አያውቅም።
ልሙትልሽ! ጽጌ ሁሌ ከምታዝኚ
አንስቼ እንድጠጣሽ እስኪ ጠጂ ሁኚ
እቴ የእኔ ጽጌ አንድ ጥያቄ አለኝ
አንቺን እኔ ጣልሁሽ እኔን ማነ ‘የጠላኝ?
ስካር እንዳትይኝ! ያንገዳግዳል እንጂ ሰው አይጥልም። ካልሽ ደግሞ እዚያ መንገዱ ላይ የወደቁት አርባ፣ ስልሳ…እ.. ሰዎች ጠጥተው ነው? አይደለም። የሚጠጡበት አተው ነው የወደቁት። መጠጣት ሳይሆን ማጣት ነው ሰው የሚጥለው። አንድ ቀን ማታ ፈታ ብዬ ቤቴ ገባሁ። ፅግዬ እሳት ሳትጎርስ እሷ እሳት ሆና ጠበቀችኝ። የተቀመጠችበት ሶፋ ሲጨስ አይቸዋለሁ። “እራት የለም“ የለም አለችኝ። እኔ ያንቺ ባል አልኳታ እና ኩኩዬን ወዲህ አልኩና ለሦስታችን አንድ እንጀራ እንድትገዛ ድፍን አምስት ብር ሰጠኋት። ጀግና አይደለሁ?! አዎ! ጀግና ነኝii
ጽግዬ እኔ ያንቺ ጽግዬ
መጣሁልሽ የትም ውዬ
ጃንቦ ከጠጅ ቀላቅዬ
ካለመጠጣት ይሻላል ብዬ።
መቸለት ነበር? ኢትዮጵያ አምስት ሺህ ሰው በማጎራረስ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጂኔየስ ቡክ) ላይ ተመዘገበች አሉ። ባተሌ የሆነች ሀገር የተራቡ ዜጎቿን አጉርሳ በሰው ልብ መመዝገብ ይበልጥባት ነበር። አልሆነም ብሬን መልሽ አለ ወስላታ! እነማን ናቸው እንዲህ ያደረጉ? እህህ… እነስም አይጠሬ፤ እነ እንትን አይምሬ…. ኧረረረ……ኧረረረ…
ሆዴን ሽቅብ ሲለኝ አረቄው ነው ብዬ
ሆዴ ሲጥወለወል ጠጁ ይሆን ብዬ
በሎሚ ስቆጣው
ለካ በደል ኑሯል አልፈጭም ብሎ የሚገላበጠው።
እኔ እኮ የሚገርመኝ፤ ሱፍ የለበሰ ምሁር፤ ቁሞ የሄደ ሁሉ ፍጡር መባሉ ነው። ሀገሩን ሳያውቅ የፊዚክስ ቀመር ቢያውቅ ትርጉሙ ምንድን ነው? የዓለምን ታሪክ ቢያውቅ የራሱን ማንነት ካላወቀ ምን ይጠቅማል? ጠፈሩን እያጠና እኔ ለምን እንደምጠጣ መመርመር ካልፈለገ ምኑ ላይ ነው ምሁርነቱ? ርሀብን ማጥፋት ትቶ በርሀብ ለሚመጣ በሽታ መድኃኒት ‘ሚሠራ፤ ብርዱን ማስወገድ ትቶ በብርድ ስለሚመጣ ቲቢ የሚደሰኩር ምሁር ምኑ ላይ ነው ምሁርነቱ? ተማርኩ፣ አወቅሁ፣ አጠናሁ ወይም መረመርሁ
ካለ የተሻለች ዓለም መፍጠር አለበት። ግን ጠጥተን ስናየው ይህ ሲሆን አላየንም። ውሸት፣ ክህደት፣ ስግብግብነት፣ ዝርፊያ…. ግርፊያ ነው ያየነው፤ ዘረኝነት፣ ሰይጣናዊነት ነው ያየነው።
ከመንግሥት ይልቅ ነፃነት የሚሰጠኝ ጠጅ ነው። ሕግ ሳይሆን የልቤን እንድናገር ያደረገኝ ጃምቦ ድራፍት ነው። ክብር እና ዘላለማዊነት ለጃምቦii ተሳስቼ ከሆነ ይቅርታ….ጽግዬ መጣሁልሽ ጽግዬ
ቤታችን የኪራይ አለ…..
ቤታችን የኪራይ ምግባችን ልቅምቅም
ሞቶ መቀበርን ሸሽተነው አናውቅም።
ሦስት
ሠላም ሠላም እኔ ሰካራሙ ውብሊቀር ነኝ። ዛሬ ምን አየሁ መሰላችሁ። ፈረንጂ… ፈረንጂ ሲለምን አየሁ!!
እንዳው ጥሎብኝ እኔ ጥቁር ሆኜ ጥቁር ሰው አልወድም። “ሰይጣን” ይመስለኛል የዳቢሎስ ወንድም። እያለ ራሱን የሚረግጥ ሀበሻም ለምፅዋት እጁን ሲዘረጋ አየሁ። እውነት ለመናገር ያሳዝናሉ። ፈረንጂ ልጅ ታቅፎ ሲለምን በውኔ አየሁ። ግን ለምን? ማን ነው እንደዚያ ያደረጋቸው?
እነሱ ናቸዋ! መጀመሪያ ከፋፈሏቸው….. ከዚያ የየራሳቸው ማንነት ሰጧቸው፤ ከዚያ እሳት ለኮሱና አፋጇቸው። አድኑን ሲሏቸው ለሁለቱም ጠመንጃ ሰጧቸው። ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ተታኮሱ፤ ተጋደሉ ከተማቸውን አፈራረሱ…… ወገናቸውን ፈጁ። ጨካኞች በገዛ ሀገራቸው እንደ ውሻ እግራቸውን አንስተው ሸኑባቸው። ክቡር የሆኑትን የሰው ልጆች ቤተ ሙከራ አደረጓቸው። ዋይ! ዋይ!… አስባሏቸው። ሞት እያባረራቸው ወደ ጠላቶቻቸው ሲሸሹ እንደ አውሬ በር ዘጉባቸው።
እና ባለቤቱን ያጣ ባል ጨቅላ ልጁን ታቅፎ ሲኦል አድርገው ሲያሳዩዋቸው ወደነበረችው ኢትዮጵያ መጡ። እና ግን እንደሚሉን አይደለንም። ምን ብናጣ… ምንም ድሀ ብንሆን የምንሰጠው አናጣም። እናም ድሀ አይደለንም። ድሀ የማይሰጥ፤ የማያካፍል ነው። ድሀ እነሱ ናቸው። የሰው ሀብት እና ፀጋ ፣ ሠላም እና እረፍት የሚዘርፉት። ሐበሻ ድሀ አይደለም። ታሪኩን አዛብተውበት፤ ማንነቱን ገሽልጠውት፤ ስብዕናውን አጭበርብረውት ነው እንጂ ሐበሻ ኩሩ ነው። ጠጅ እንኳን ጨልጦ አይጠጣም!i
እኔ ምን አገባኝ ሶርያ ብትደማ
እኔ ምን አገባኝ የመንስ ብትደማ
እኔ ምን አገባኝ ሶማሌ ብትደማ
አይልም ሐበሻ
በእነሱ የሚያየው የእሱን መጨረሻ።
አንዱ ጅል ”ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ተብሏል ሲለው፤ ለዚያ ነዋ እየተቀባበሉ ያጨሷት አላለም!! ሰውየው ግን እውነቱን ነው። ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖብን ነው‘ንጂ የምንኖረው መሞት እኮ አቅቶን አይደለም። በዚህ ዘመን ካለምንም መንከራተት፣ ካለምንም “CV” እና ልምድ ባቅራቢያ የሚገኘው ነገር ሞት ነው።
በባለፈው አንድ የመንግሥት ተቋም የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ አሉ። ሌላውን እንተወውና ማሳሰቢያው ምን ይላል መሰላችሁ?
የሥራ መደቡ በዘርፉ ተቀጥሮ አምስት ሰው ያኮላሸ፤ በመልካም ሥነ ምግባሩ ሰይጣን የሚፈርምለት ይላል። ጉድ ነው። ብለን ብለን የሰይጣን ማህተም እንጠይቅ! ዕድሜ ጎታታው አያሳየን የለ!!
በዓለም በአንድ ዓመት አንድ ሚሊዮን ሰው ራሱን ያጠፋል አሉ። ስድስት ሰዎች የዓለምን 60% ሀብት ጥርግ አድርገው ይዘው ለምን አይሞት!? እንዲያውም ትንሽ ነው። በነገራችን ላይ ራሱን አጠፋ በሚል ነገር አልስማማም። አንድ ወዳጄ ነበር። አንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። ማታም አይተኛም፤ ጥበቃ ይሠራል። በአንድ ቀን የሁለቱም ደመወዝ 3‚000 ብር ገባለት። ቤቱ እንደገባ ለአስፔዛ ሚስቱ 400 ብር ተቀበለችው። ከዚያም ሲጨቀጭቁት ለነበሩት አከራዩ 500ውን ከፈለ። ጥዋት ወደ መሥሪያ ቤት ሲሄድ በግራ ኪሱ የነበረውን 500 ብር ሌባ ወሰደበት። መሥሪያ ቤቱ ሲገባ ያበላሸው ዕቃ ስለነበረ ሁለት መቶ ብር ከፈለ። በበነጋው መታከሚያ እንዲልክላቸው ሲለምኑት የነበሩት አባቱ ማረፋቸውን ሰማ። ቀትር ላይ በተረፈችው ብር በረኪና ገዝቶ ጠጣና ሞተ። አሁን ይሄ ሰው ራሱን አጠፋ ነው የሚባለው?! እንዴት ሆኖ አከራዩ፣ ኑሮው፣ መሥሪያ ቤቱ፣ ሌባው እና ሀገሩ ተባብረው ነው እንጂ የጨፈጨፉት።
እንዲህ ነዋ! መተንፈሻ፣ መውጫ መግቢያ እያሳጡ ሕዝባቸው ራሱን በገመድ ሲያስገባ ራሱን አጠፋ የሚሉን። ገደልን ላለማለት! ስም ማሳመራቸው እኮ ነው። ነፍሰ በላ ሁሉ! ጠጥተን ስናየው ሁሉም ሌባ ነው።
አንድ እርጉም፤ ሁለት፣ ሦስት አራት ጃምቦ ድራፍት ሳብ አድርጌ ዓለም ኮከብ ስትሆን… መጣና ”ጌታን ተቀበል፤ ጌታ ያድናል“ አለኝ። ምነው የጌታን ማዳን ሰበር ዜና አደረግኸው። ዛሬ ነው እንዴ የሰማኸው? አልኩት።
እሱን ጌታ ሳይሆን ይኸኛውን ጌታ ነው ያልኩህ። የሀብት፣ የፀጋውን ጌታ፣ የኃይለኛውን፣ የዕውቀቱን አምላክ ነው ያልኩት አለኝ። ብታምኑም ባታምኑም ሰይጣንን ተቀበል አለኝ።
ለምን እቀበለዋለሁ? ለምን የት ሂዶ? እኔው ጋ አይደለም እንዴ የሰፈረው? ማን ሆነና ነው እንዲህ የሚያደርገኝ ኧ!? ማን ሆነና ነው? ወስደህ ለሌላው ስጠው አልኩት። ሰውየው ማለት የፈለገው የገባኝ ግን ዘግይቶ ነው። እዝጌርን ካደው ነው ያለኝ። እኔ ሰካራሙ! ውብሊቀር ተበጀ! እኔ ሐበሻው! እኔ ኢትዮጵያዊዩ! እቀምሰው ባጣ አንጠፈጥፈው ባይኖረኝ ይህን አደርገዋለሁ እንዴ!?
ይህን ሆኜ ቢሊየነር ከምሆን የጀመረኝ ድህነት እንደ አሞራ ተቀራምቶ ይብላኝ። እንዳሞራ! እንዳሞራ! ቆርጦ ይብላኝ።
ደሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዚያ አይደለም እንዴ አንድ ሺህ ዓመት ከዓለም ተለይተን ወደ ኋላ የቀረነው?! ሰይጣንን ውጊያ አይደለም እንዴ ዕድሜያችንን፣ ሀብታችንን የጨረስነው? እስቲ ከሰራችሁ የሚለን ማን ነው?
አገሬ ወይን ናት አበባ የዋጣት
ሊበሉ ከበቧት አጥር አልታያቸውም አወይ ዓይን ማጣት
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል
የለህም እንዳልል ይዘንባል ያባራል
የለህም እንዳልል ያብባል ይረግፋል
አለህም እንዳልል ሰይጣን በመቅደስህ ዙፋኑን ይሠራል።
እግዜር ሆይ ዝም አትበል አፍ እንደጎደለው
በጦሩ ሳይገድለን በቃልህ ግደለው።
አይ ጽግዬ አልቀርም መቼም እመጣልሻለሁ። ዛሬ ንዝነዛሽን ትተሸ ዘነዘናሽን እንዳታመጪ። ኑሮ በእየአቅጣጫው መትቶኛል። ትንሽ ብትነኪኝ ሰበብ እሆንብሻለሁ። እንዳትነኪኝ።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011
በሐብታሙ አያሌው