ወቅቱን የዋጀ የባሕር በር ጥያቄ

ቀይ ባሕር ከደቡብ ሶርያ ተነስቶ በእሥራኤልና ዮርዳኖስ የሳይናይ በርሃን አቋርጦ ወደ ቃባ ሰላጤ የሚገባና 2ሺ250ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር አካባቢ ነው። ከሕንድ ውቅያኖስ፤ ከኤደን ባሕረ ሰላጤና ከዐረብ ባሕር ጋር ይገናኛል። በሜዲትራንያን በኩልም ሆነ በሕንድ ውቅያኖስ የነዳጅ ዘይት ለሚጭኑ መርከቦች ዋና የባሕር መንገድ ነው። በዚሁ ባሕር ላይ በአመት ከ3ሺ በላይ መርከቦች የተለያዩ ዕቃዎችን ጭነው ይመላለሳሉ።

ቀይ ባሕር ካለው ስትራቴጂክ ስፍራነት በተጨማሪ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም የንግድ ልውውጥ በዚሁ ባሕር ላይ እንደሚከናወን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡ በአሁኑ ወቅትም ሳዑዲ ዐረቢያ፣ የመን፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ እሥራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ኤርትራና ጅቡቲ በጋራ የቀይ ባሕር ባለቤቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ከዚህ መድረክ ከተገለለች ከ32 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ ለሺህ አመታት የቀይ ባሕር ንጉሥ ሆና የኖረች ሀገር ነበረች። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም ‹‹አሰብ የማን ናት? በሚለውና ስለ ቀይባሕርና የወደብ ጥያቄ በስፋት በተነተኑበት መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች በመጀመሪያ የታወቀው ከ100 እስከ 150 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።

‹‹ዘፕሪፐለስ ኦቭ ዘ ኤርትሪያን ሲ›› በተሰኘው መጽሐፍም የአክሱም መጠነ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ዋነኛ የባሕር ባር በነበረው በአዶሊስ ይተላለፍ እንደነበር ያትታል። በወቅቱ የነበረው ንጉሠ ነገሥት አጼ ካሌብ እጅግ የዳበረ የባሕር ኃይል እንደነበረውና ቀይ ባሕርንም ተሻግሮ የመንንና ደቡብ ዐረቢያን ይቆጣጠር እንደነበር ይኸው መጽሐፍ ያብራራል።

ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹‹አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ዘመን በመርከቦቿ ከሕንድ እስከ እየሩሳሌም ከነበሩ አጋሮቿ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበራት። አንዳንዴም ጭቆና የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት የጦር ኃይል በመላክ ሁኔታዎችን ትቆጣጠር ነበር፡›› ሲሉ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ እንደነበረ ያትታሉ።

በዚህ ዓይነት መልኩ ኢትዮጵያ በቀይባሕር ላይ የነበራትን የበላይነት አስጠብቃና የበርካታ ወደቦች ባለቤት ሆና ዘመናትን ተሻግራለች። ሆኖም በኢትዮጵያና በአማጽያን መካከል የነበረው የ17አመታቱ ጦርነት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ለዘመናት ትገለገልበት ከነበረው የቀይባሕር ይዞታዋ ተነቀለች። ወደብ አልባ ሀገርም ሆነች።

ባለፉት 32 አመታትም ወደብ አልባ ሀገር ሆና እና ከቀይባሕር ተገልላ ኖራለች። በዚህም ወደብ አልባ ሀገራት የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመጋፈጥ ተገዳለች። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ፈተናዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የመጀመሪያው ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም ‹‹አሰብ የማን ናት? በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳሰፈሩት እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆኑ ሀገራት ከዋና ዋና የገበያ ማዕከሎች የተገለሉና ከገበያ ማዕከል የራቁ ሲሆኑ ወደብ አልባነት ለኢኮኖሚ እድገታቸው ከፍተኛ ማነቆ ሆኖባቸዋል።

ዶክተር ያዕቆብ፤ ቻውድሪና ኤርዳነቢልግ የተባሉ ምሁር ያደረጉትን ጥናት ጠቅሰው እንደጻፉት፤ አንድ ወደብ አልባና ወደብ ያለው ሀገር በሁሉም ነገር ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ሀገሮች በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ሲነጻጸሩ ወደብ አልባው ሀገር 1በመቶ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ኋላ ይቀራል።

ይህም ማለት ወደብ ያለው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 24 አመታትን ሲፈጅበት ወደብ አልባው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 36 አመታት ይፈጅበታል። በሌላም በኩል ወደብ አልባ መሆን ብቻ የአንድ ሀገር የውጭ ንግድ መጠንን ከ33 በመቶ እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስለ ቀይባሕርና ስለወደብ አስፈላጊነት በሰጡት ማብራሪያም ወደብ የሌላቸው ሀገራት አመታዊ ዕድገታቸው በ25 በመቶ የተገታ መሆኑን አስረግጠው መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ፖል ኮሊየር የተባሉ ምሁር እንዳሉትም፤ ወደብ አልባ ሀገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች በአብዛኛው በአንድና ሁለት ምርቶች ላይ ብቻ የተወሰኑ ናቸው። ስለሆነም ከድህነት የመላቀቅ ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። የውጭ ባለሀብትም አይመርጣቸውም። በወደብ ኪራይ እና በትራንስፖርት ምልልስ ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳረጉም ለሸቀጦች ዋጋ መናርና ለኑሮ ውድነት የተጋለጡ ናቸው።

የባሕር በር ያለው ሀገር ከዓለም ጋር ይገበያያል። ወደብ የሌላው ሀገር ግብይቱ ከጎረቤቱ ጋር ብቻ ነው ሲሉም ፖል ኮሊየር ይገልጻሉ። ስለዚህም ወደብ አልባ ሀገሮች የጎረቤቶቻቸው እስረኞች ናቸው ሲሉም ጽፈዋል።

የባሕር በር አለመኖር ለኢኮኖሚና ለልማት ዋነኛ እንቅፋት መሆኑን ሁሉም ምሁራን ይስማሙበታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮም በየቀኑ ለወደብ ኪራይ ከ3ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ዶክተር ያዕቆብ ያስረዳሉ። ይህንኑ ሀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለወደብ ኪራይ የሚወጣው ወጪ በርካታ የሕዳሴ ግድቦችን ለመገንባት ያስችለን ነበር ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

ሌላኛው የወደብ አልባነት ጉዳት ደግሞ ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያያዝ ነው። ወደብ ያላቸውና የሌላቸው ሀገራት እኩል ተደማጭነት አይኖራቸውም። ኢትዮጵያም ከቀይባሕር ከተወገደች ጀምሮ በዓለም ላይ ያላት ተሰማኒት እየተቀዛቀዘ እንደመጣና በምትኩ ጅቡቲን የመሳሰሉ ትንንሽ ሀገሮች የበለጠ ተሰሚነትን እያገኙ መምጣታቸውን ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም ያስረዳሉ።

ሦስተኛው ችግር ደግሞ ወደብ አልባ ሀገራት እራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ይቸገራሉ። የራሳቸውም ምስጢር አይኖራቸውም። ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር የቀይባሕርና ወደብ ጉዳይን በተመለከተ ቆይታ ያደረጉት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ዶክተር ዳር እስከዳር ታዬ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዋጋ ከፍላለች።

በየአመቱ ለወደብ ከምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ ለሀገር ስትራቴጂክ የሆኑ ዕቃዎችን ለማስገባት ስትፈልግ የግድ ወደብ የሚያከራየው ሀገር ማወቅና መፍቀድ አለበት። ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ምስጢር ነው ብላ የምትደብቀው ነገር አይኖራትም ማለት ነው። እንደሀገር የምትይዛቸው ምስጢሮቿ ሁሉ በወደብ ሰጪው ሀገር ዕውቅና ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ብለዋል።

ለምሳሌ አስፈላጊ የጦር መሣሪያዎች ኢትዮጵያ ማስገባት ብትፈልግ በወደቡ ባለቤት ዕውቅና ማግኘት አለበት። በአጠቃላይ ጉዳቱ ከኢኮኖሚ እስከ ደህንነት ድረስ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል ሲሉ ጉዳቱን አብራርተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እና በየጊዜው እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተሸክሞ እንደሀገር ለመቀጠል ትቸገራለች። ልቀጥል ብትልም አትችልም። ባለፉት 30 አመታት ስትጓዝበት በነበረው ሁኔታ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መኖር ከማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ስለዚህም መፍትሔ መፈለጉ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አልሆነም። ስለዚህም መፍትሔው ምንድነው የሚለው ሁሉንም የሚያሳስብ ጥያቄ መሆን ጀምሯል።

መፍትሔው ደግሞ የሚመነጨው ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ በሚያደርጉት ትብብር ላይ የሚመሠረት ነው። በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ መርህ ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿ በጋራ አሸናፊ የሚሆኑበትን ስልት መንደፍ አለባቸው። አንዱ አትርፎ ሌላው የማይከስርበትን ስልት መንደፍ አለባቸው። አንዱ በአንዱ ላይ ጥገኛ ሆኖ ዘላለም ሲበዘበዝበት የሚኖርበትን አካሄድ መስበር አለባቸው።

መልካም አጋጣሚ ሆኖ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነትን መፍጠር ችሏል። ጎረቤት ሀገራትም ህልውናቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰረ መሆኑን እየተናገሩ ነው። የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ረቡዕ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ መጥተው፣ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ቆይታ አድርገዋል። የኢትዮጵያና የሶማሊያን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶችንም አድርገዋል። ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ሕዝቦች ህልውና የተሳሰረ ነው ሲሉም በወቅቱ ባደረጉት ንግግር አንጻባርቀዋል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ከመግባባት የደረሱባቸውን ጉዳዮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ደግሞ፣ ‹‹ሁለቱ ሀገሮች ለቀጣናዊ ሠላምና መረጋጋት በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ ተስማምተዋል። ይህን ለማድረግም ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውንና የግዛት አንድ ነታቸውን ባከበረ መንገድ በመከባበርና በመግባባት ላይ ተመሥርተው የእርስ በርስ ውይይትና ትብብር ያደርጋሉ፤›› ተብሎ የሠፈረው ነጥብ ትኩረት የሚስብ ነበር።

የሁለቱ ሀገሮች መሪዎች በወቅቱ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ከፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ባለፈ፣ በንግድና በኢኮኖሚ የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት አሳይተዋል፣ በዚህ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተነግሯል። ይህ ሠላምና ፀጥታ ብቻ ሳይሆን ዳቦም ለቸገረው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን በርካታ ተንታኞች ሃሳብ ሰጥውበታል።

ሶማሊያ በሺዎች ኪሎሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ግን ይህ ሁሉ ኪሎሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገልግል የሚችል አይደለም። ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች። ብቻ አማራጩ ብዙ ነው።

ዘይላ ሶማሊያ እንደሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 አመታት ያህል የነበረውን የጠላትነት መንፈስን ሰብረው አዲስ ግንኙነት ከጀመሩ አምስት አመታትን አስቆጥረዋል። እነዚህ ሁለት ሀገራት ላይለያዩ የተጋመዱና የጋራ የሆኑ ዕሴቶች ያላቸው ሀገራት ናቸው። በባህል፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ ትስስርና መሰል ጉዳዮች የሚተሳሰሩ ናቸው። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በአሁኑ ወቅት ወደ 300ሺ የሚጠጉ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ ተሰማርተው ኑሯቸውን በመደጎም ላይ ይገኛሉ።

ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው መልካም የሠላም አጋጣሚ የአሰብን ወደብ በሠላማዊ አማራጭ ለመጠቀም ውይይት ማድረግ ይቻላል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው አቅርቦቶች ይኖራሉ፤ እነሱን በመስጠት አሰብን መጠቀም ይቻላል።

ወደ ሶማሌ ላንድ ስንመጣ የበርበራ ወደብን በጋራ ማልማትና መጠቀም ሌላው አማራጭ ነው። ከዚህ ቀደም የኢምሬት መንግሥት 51 በመቶ፤ የሶማሊላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግሥት 19 በመቶውን በማልማት ወደቡን በጋራ የማልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችል ነው።

በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ማደግ ለጎረቤት ሀገራት ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ሲመጣ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል። ጎረቤት ሀገራትም ወደቦችን በማከራየት፤ በጋራ በማልማት፤ ወይንም ከኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቀይባሕርና በወደብ ዙሪያ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አንዳንዶች የቀይ ባሕር ጉዳይ ከኤርትራ፣ ከጂቡቲ ያጋጫል የሚል ስጋት አላቸው። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በቀይ ባሕር ጉዳይ የማንወያይ ከሆነ በስንዴም፣ በአረንጓዴ ዐሻራም፣ በገቢው ጉዳይ መወያየት ትርጉም የለውም። እንደ ሀገር የሚታሰበውን ሠላም፣ አንድነትና ብልጽግና በቀይ ባሕር ምክንያት የሚታጣ ከሆነ ዋጋ እንደሌለው ገልጸዋል።

በ2030 ዓ.ም 150 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በጂኦግራፊ ታሳሪ ሆኖ መኖር የማይችል በመሆኑ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውሃን የማይወስድ ጎረቤት ሀገር አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ኤርትራ፣ ተከዜን፣ ሱዳን ተከዜንና ዓባይን፣ ደቡብ ሱዳን ባሮን፣ ኬንያ ኦሞን ጨምሮ፣ ሶማሊያ ዋቢሸበሌና ገናሌ ዳዋ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

‹‹አንድ ሀገር ለኢትዮጵያ አንድ ሊትር ውሃ የሚሰጥ ሀገር የለም። ሁሉም ተቀባይ ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹ይገባቸዋል በደንብ አብዝተን እንሰጣቸዋለን ግን የእናንተን እንካፈል የእኛን እንዳትጠይቁን ማለት ግን ትክክል አይደለም›› ብለዋል። አብሮ መኖርና ሠላም ከታሰበ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ በመጋራት መኖር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ከአንዱ ወገን ብቻ የሚጠየቅ ከሆነ ፍትሐዊነት የጎደለው ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አሁነኛው ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ እንደሚፈቅደው። በሰጥቶ መቀበል መርህ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር እና ፍላጎትን ማጣጣም ከተቻለ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ አማራጮች አሉ። ወቅቱ የሚጠይቀውም ይህንኑ ትብብር ነው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You