ዓለም የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በየቀኑ እየተመለከተች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ መከራዋና ሰቆቃዋም እየበዛ ነው። በየቦታው የሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ነዋሪዎቿን ለስቃይና መከራ መዳረጋቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ችግሮች ከሚፈጥሯቸው ማኅበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የጎዳና ተዳዳሪነት ነው። የጎዳና ተዳዳሪነት ችግር በኢትዮጵያም ተንሰራፍቶ የሚታይ ማኅበራዊ ቀውስ ነው።
በኢትዮጵያ በ11 ዋና ዋና ከተሞች ከ89ሺ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ ከ55ሺ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ከአራት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገ መረጃ ያሳያል። ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችም ስር ነቀል ለውጥ ማስመዝገብ አልቻሉም። በችግሩ ምክንያት የሚፈጠሩ ቀውሶች ቤተሰብን፣ ኅብረተሰብንና ሀገርን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ነው።
ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከመታደግ አኳያ በአንድ ወቅት መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በመንግሥት ጥረት ወደ ተለያዩ ማዕከላት በማስገባትና ሥልጠና ይሰጥ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል፤ በሌላ ወቅት ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ወደ ትውልድ ቀዬቸው የመመለስ ሥራዎች ይከናወኑ እንደነበር ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት አረጋውያንን፣ የአእምሮ ህሙማንን፣ ለመታደግ የሚያስችሉ ጥረቶች በዜጎች፣ በተለያዩ ተቋማትና በመንግሥትም ትብብር እየተካሄዱ ቢገኙም የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመታደግ ጥረቶች በተለይ በአሁኑ ወቅት ብዙም ጎልተው አይታዩም። ሙከራዎቹ የችግሩን ስፋት በፍጹም የሚመጥኑ አይደሉም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ችግሩ እየሰፋ መጥቷል።
ይህ አደገኛ ችግር ያሳሰባቸው በጎ አሳቢ ዜጎች፣ ችግሩ ከዚህ የበለጠ ቀውስ እንዳያስከትል በየጊዜው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል። የ‹‹በርተሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ምግባረ ሰናይ ተግባራት ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ ነው።
‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ከመመስረቴ በፊት ሕይወቴ የተዛባ ነበር፤ የጎዳና ተዳዳሪም ነበርኩ›› የሚለው የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ገዛኸኝ ሲሳይ፣ የአባቱን ማንነት ሲጠይቅ ከእናቱ ጋር በተፈጠረ አለመስማማት ወደ ጎዳና እንደወጣ ያስታውሳል። ገዛኸኝ የጎዳና ሕይወት ብዙ አስከፊ የሕይወት ገጽታዎችን አሳይቶታልና በዚህ ሕይወት ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለመታደግ የበኩሉን ዐሻራ ማሳረፍ እንደሚኖርበት አመነ። ለጎዳና ተዳዳሪዎች ድጋፍ የማድረግ ምኞቱን ተቋማዊ ለማድረግ ‹‹በርተሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት››ን መሠረተ።
‹‹በርተሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› የተቋቋመው በጥቅምት 2014 ዓ.ም ቢሆንም፣ ገዛኸኝ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፍ ተቋም ለመመስረት ማሰብ የጀመረው ግን በ2011 ዓ.ም ነው። ለጎዳና ተዳዳሪዎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ በጎዳና ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን የመታደግ ዓላማን ይዞ የተመሠረተው ድርጅቱ፣ አቅምና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንንም አይዟችሁ ባይና ደጋፊ ነው።
ገዛኸኝ እንደሚገልፀው፣ ድርጅቱ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን ንፅህና በመጠበቅ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ያደርጋል። ድጋፍ የሚያደርግ አካል (ስፖንሰር) ሲገኝ ደግሞ፣ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ልጆች አሳዳጊ እንዲያገኙ ዕድሎችን ያመቻቻል። አቅም ለሌላቸው አረጋውያንም ድጋፍ ይሰጣል። መውለድ የማይችሉ (መካኖች) እና በኤች አይ ቪ/ኤድስ የተጠቁ ወገኖችም በድርጅቱ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ለ150 ሰዎች (100 አረጋውያንና 50 ሕፃናት) ቋሚ ድጋፍ ያደርጋል። በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ድርጅቱ በመሄድ የንፅህና፣ የምገባና የአልባሳት አገልግሎት ያገኛሉ። ቤት ለቤት በመሄድ ለዕለታዊ ፍጆታ የሚውሉ ድጋፎችን እናደርጋለን። በበዓላት ወቅት አቅም በፈቀደ መጠን ዶሮ፣ እንቁላል፣ ዘይትና በርበሬ እንሰጣለን። የቤት ኪራይ ክፍያ መክፈል ላልቻሉ ሰዎችም የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል። በሌላ በኩል በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ከሱሳቸው እንዲያገግሙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ይሠራል። በበጎ አድራጎቱ ሥር በሚገኙ አባላት በኪነ ጥበብ ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። ከጤና ጣቢያዎች ጋር በመሆን ብዙ ሰዎች የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ እንዲያደርጉና የአባላዘር በሽታ ኮርስ መስጠት ማድረግ ችለናል›› በማለት ድርጅቱ ስለሚያደርጋቸው ድጋፎችና ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ይገልፃል።
የ‹‹በርተሎሚዎስ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ምግባረ ሰናይ ተግባራት በርካታ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ወቅታዊ ችግሮቻቸው እንዲቃለሉላቸው አስችለዋል። ‹‹መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ያልቻሉ ዜጎች በተደረገላቸው ድጋፍ ፍላጎቶቻቸው ተሟልተውላቸዋል። ለመመገብም ሆነ ለመልበስ አቅም ያጡ ወገኖች ምግብና አልባሳት አግኝተዋል። አቅመ ደካማ አረጋውያን በሚደረግላቸው ድጋፍ ደስ ተሰኝተዋል። በሥራችን ብዙ አበረታች ስኬቶችን አስመዝግበናል…›› በማለት የድርጅቱ ተግባራት ስላስገኟቸው ውጤቶች ያስረዳል።
ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው ከኪነ ጥበብ ሥራዎች ከሚገኝ ገቢ እንደሆነ ገዛኸኝ ይናገራል። የኪነ ጥበብ ተሰጥዖ ያለው ገዛኸኝ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ከማቋቋሙ በፊት ‹‹ዞ ኪነጥበብ›› በተሰኘ የኪነ-ጥበብ ቡድን ውስጥ ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ያዘጋጅ እንደነበር ያስታውሳል። ይህም ለበጎ አድራት ድርጅቱ ሥራ በእጅጉ እንደጠቀመውም ይገልፃል።
‹‹የገንዘብ ምንጫችን የኪነ ጥበብ ሥራዎች ናቸው። ትያትሮችን እናዘጋጃለን፤ መነባንቦችንና፣ ውዝዋዜዎችን እናቀርባለን። እኔ ትያትሮችን እፅፋለሁ፣ አዘጋጃለሁ። ሌሎች ወጣቶችን አሰልጥኜ ከእነርሱ ጋር በጋራ እንሠራለን። እነዚህን የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ በማቅረብ በሚገኝ ገቢ ድጋፍ እናደርጋለን። ከዚህ በተጨማሪ አሮጌ ጫማዎችን በመጠገንም ገቢ እናገኛለን። ዋናው ገንዘብ ምንጫችን የሕዝቡ ድጋፍ ነው›› ይላል።
ድርጅቱ መስራቹን ጨምሮ ስምንት አባላት ባሉት ቦርድ የሚተዳደር ነው። እስካሁን 150 አባላትን ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ተጨማሪ አባላትን ለማፍራት ተከታታይ የቅስቀሳና ምልመላ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይሁን እንጂ የአባልነት መዋጮን በተገቢው ሁኔታ በማዋጣትና በድርጅቱ ተግባራት ላይ በንቃት በመሳተፍ ረገድ ሰፊ ውስንነቶች እንዳሉ ገዛኸኝ ይናገራል። 150ዎቹ አባላት ‹‹አባል›› ቢባሉም የአባልነት መዋጮ እያዋጡ እንዳልሆነ ይናገራል። ‹‹አንድ ሰው አባል ለመባል የአባልነት መዋጮ ማዋጣት አለበት። ከ150ዎቹ መካከል በንቃት የሚሳተፉትም አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። በእርግጥ ጊዜውና ኑሮው የሩጫና የውጣ ውረድ ነው። ባለን አቅም የድርጅቱን ሥራ ለማስቀጠል እየታገልን ነው›› ይላል።
ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት የሚገልፀው ገዛኸኝ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረት ዋናው ችግር እንደሆነ ይናራል። ይህም ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ በእጅጉ የፈተናቸው ችግር እንደሆነ ያስታውሳል። ‹‹ድርጅቱ ሲቋቋም የቢሮ ኪራይ የመክፈል አቅም አልነበረውም። አንዳንድ ድርጅቶችን ‹የሕንፃችሁን የመጨረሻ ፎቅ ላይም ቢሆን ቢሮ ስጡን› ብለን በደብዳቤ ስንጠይቃቸው ፈቃደኛ አልሆኑም፤ እንዲያውም ቅድሚያ ክፍያ ጠየቁን። የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንደምንሠራ ነግረናቸው ገንዘብ ስናገኝ እንደምንከፍል ብናስረዳቸውም በጎ ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል። ኮምፒዩተር አልነበረንም፤ አንዲት ግለሰብ ናቸው ኮምፒዩተር የሰጡን። ደብዳቤዎችንም ሆነ ሌሎች ጽሑፎችን የምንጽፈው በክፍያ አልያም በየቢሮው ትብብር እየጠየቅን ነበር›› በማለት ስለችግሩ ያብራራል።
‹‹ድርጅቱ የራሱ ቢሮም ሆነ ቦታ ስለሌለው ሥራችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ዋና ቢሮውን በወጣት ማዕከል ውስጥ አድርጎ እየሠራ ቢሆንም፣ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ቦታ እየፈለገ ይገኛል። በተለይም ከአንድም ሁለት ጊዜ የቦታ ይዞታ እንዲሰጠን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ለመጠየቅ ስንሄድ በጎ ምላሽ አላገኘንም። ተቋሙ ሕጋዊ ፈቃድ ቢኖረውም፣ እስካሁን ግን የራሱ የሆነ ንብረት ስለሌለው በሥራው ላይ ጫና ፈጥሮበታል። የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ያገለገሉ ኮምፒዩተሮችንና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎችን ቢያደርጉልን የተሻለ ሥራ መሥራት እንችል ነበር። ከየተቋማት ተርፈው የተመለሱ አልባሳትና አሮጌ ጫማዎች ለእኛ ተቋም እንዲሰጡ ጥያቄ ብናቀርብም፣ መልስ ልናገኝ አልቻልንም። በተለይ መንግሥት የቦታ ጥያቄያችንን ቢመልስልን በሥራችን ለውጥ ማምጣት እንችላለን›› በማለትም ይገልፃል።
እነ ገዛኸኝ የድጋፍ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ለጥያቄያቸው በቂና አዎንታዊ ምላሽ የሰጠ አካል አልተገኘም። ከግለሰቦችም በቂ ድጋፍ አልተደረገላቸውም። ተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚመድቡት ገንዘብ ቢኖርም፣ በአብዛኛው ድጋፍ ሲደረግላቸው የሚስተዋሉት ድርጅቶች ታዋቂ የሆኑት ናቸው። ‹‹እኛም በሚገባ ብንታወቅ ኖሮ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉልን ይመስለኛል። ብዙ የድጋፍ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ያላገኙት ገና አዲስ ተቋም በመሆናችን ነው ብዬ አምናለሁ›› በማለት ይገልፃል።
ድጋፍ ካለማግኘት በተጨማሪ በሥራቸው ሂደት የሚያጋጥሟቸው ሌሎች ችግሮችም አሉባቸው። ከድጋፍ እጥረት በተጨማሪ የግንዛቤ ችግርም ሌላው ፈተና እንደሆነ ገዛኸኝ ያብራራል። ‹‹እኛ ሕጋዊ ፈቃድ ያለንና በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ የተሰማራን ድርጅት እንደሆንን ብንናገርም እኛን ማዳመጥ ትተው ለመጣላትና ለመተቸት የሚጣደፉ አካላት አሉ። ዘለፋዎችና ሰብዕና የሚነኩ ንግግሮች ያጋጥሙናል።›› ሲል የደረሰባቸውን ችግር ጠቁሟል።
ብዙ አባላት ሥራውን የተዉት በመሰል ንግግሮች ምክንያት ነው የሚለው አቶ ገዛኸኝ፣ አስፈላጊ ማስረጃዎች (የድጋፍ ደብዳቤ፣ የእውቅና የምስክር ወረቀት፣ ደረሰኝ…) እየቀረቡላቸው ሥራን የሚያሰናክሉ እንዲሁም ጉቦ የለመዱና ብር እጅህ ላይ ይዘህ ካዩህ ብሩን መንጠቅ የሚፈልጉ አንዳንድ አካላትም አሉ። አንዳንዶቹ ፈተናዎች እኛ ተስፋ ቆርጠን ሥራውን እንድንተው ለማድረግ ጫና የሚሳድሩ ናቸው። መልካም ነገር ሲደረግ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥማሉ ብለን በማሰብ ፈተናዎቹን ተቋቁመን ሥራችንን ለማስቀጠል እየጣርን ነው›› ይላል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስትና ወረዳ ዘጠኝ ወጣት ማዕከላት ቢሮ ሰጥተዋቸው እየሠሩ እንደሚገኝ ገልፆ፣ የከተማ አስተዳደሩ ቦታን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን እንዲያደርግላቸው ያደረጉት ሙከራም እንዳልተሳካ ያስረዳል። ከዚህ ቀደም ጥያቄያቸውን ይዘው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ ሄደው መግባት ሳይችሉ እንደተመለሱና አሁንም በድጋሜ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ይገልፃል።
ድርጅቱ በቀጣይ የበጎ አድራጎት ሥራውን በስፋት ማከናወን እንደሚፈልግ የሚናገረው ገዛኸኝ፣ ስለድርጅቱ ቀጣይ እቅዶች ሲናገር ‹‹የበጎ አድራጎት ሥራችንን በስፋት ማጠናክር ስለምንፈልግ ቦታ እንዲሰጠን ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ እናቀርባለን። ጎዳና ላይ የሚለምኑ ሕፃናትንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን መንከባከብ እንፈልጋለን›› በማለት ይናገራል።
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጋስ ነው፤ የበጎ አድራጎት ሥራችንን እየሠራን ያለነው ከሕዝቡ በሚገኝ ድጋፍ ነው፤ ለዚህም ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና አለን›› ሲል አቶ ገዛኸኝ ይገልጻል። ድርጅቱ ያለኅብረተሰቡ ድጋፍ መንቀሳቀስ እንደማይችል ጠቅሶ፣ ኅብረተሰቡ ድጋፉን እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም