ስትራቴጂውን ለመተግበር ጠንካራ ዲሲፕሊን፣ ቁርጠኝነት እና በቂ ዝግጁነት ያስፈልጋል

 ሀገራችን ሰፊ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ የሚገኝባት፤ ለእንስሳት ልማት የሚሆን ተስማሚ አየር ፣ የግጦሽ መሬት እና ውሃ ያላት፤ ከዚህ የተነሳም ከ165 ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብት ባለቤት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ካላቸው የመጀመሪያዎቹ አስር የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

ይህም ሆኖ ግን ሀብቱን በአግባቡ በማልማትና በመጠቀም ረገድ ካለው ክፍተት የተነሳ የሀብቱ ተጠቃሚ ሳትሆን ዛሬም ድረስ ዘልቃለች። ሀብቱን ለመጠቀም በየወቅቱ የተደረጉ ጥረቶችም የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሳይሆኑ ችግሩ አሁንም ሀገራዊ አጀንዳ እንደሆነ ነው።

በተለይም በቆዳና ሌጦ ምርት ዙሪያ ያለው እውነታ ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ብዙ ጥቅም እያሳጣ ነው ፤ በቅርቡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት ከሚገኘው 41 ሚሊዮን በላይ የቆዳና ሌጦ ምርት አገልግሎት ላይ የሚውለው ግማሹ ብቻ ነው።

ለዚህም እንደ ችግር የሚጠቀሱት፤ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን አለመቻሉ፣ የዓለም የቆዳ ምርቶች ገበያ መቀዛቀዝ፣ የመጓጓዣ እጥረት፣ የጥሬ ቆዳ አሰባሰብ ችግር፣ ምርቶች የሚቀርቡበት ሰፊ ገበያ አለመኖርና የግብዓት አቅርቦት እጥረት ዋነኛ ናቸው።

በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ የሚፈጠሩ የጥራት መጓደሎች፣ ለቆዳ ምርት ግብዓት የሚውለው ጨው በሚፈለገው መጠን አለመቅረብ ፣ አምራች ፋብሪካዎች የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ኬሚካሎች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡና ከፍያለ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ መሆናቸው ደግሞ ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ከዚህ የተነሳም በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትና አምራች ኢንዱስትሪ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ ተገድደዋል። አንዳንዶችም ከዘርፉ ለመውጣት የተገደዱበት፤ ፋብሪካዎችም ለመዘጋት የተዳረጉበት ሀገራዊ ሁኔታ ተስተውሏል። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶችን የበለጠ ፈታኝ አድርጓቸዋል።

በአንድ ወቅት ሰፊ የሰው ኃይል በመሸከም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የነበረው ይኸው ዘርፍ ፤ በሀገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረውን ደማቅ ቀለም በየጊዜው እያጣ ከፍ ላለ ኪሳራና ብክነት ተዳርጓል።

ሆኖም ዘርፉ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ላለፉት ሁለትና ሦስት አመታት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል። በዚህም በዘርፉ መነቃቃት እየተፈጠረ ነው። ማምረት ካቆሙ የቆዳ ፋብሪካዎች የተወሰኑት ወደ ሥራ ተመልሰው የሀገር ውስጥ ገበያ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉበት የተመቻቸ ሁኔታም ተፈጥሯል።

ከዚህም ባለፈ ችግሩን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለዘለቄታው ለመፍታት ሰሞኑን ከ2016 እስከ 2025 ዓ.ም የሚተገበር የ10 ዓመት የቆዳ ልማት ስትራቴጂ ይፋ ተደርጓል፡፡ ስትራቴጂው በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የጥሬ ቆዳ አቅርቦትና ጥራትን ለማሳደግና ሌሎች ሀገራት በቆዳ ውጤቶች ያደጉባቸውን መንገዶች ለመቅሰም ጥረት የሚያደርግ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የቆዳና ቆዳ ውጤት መዳረሻ ሀገራትን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ገበያን መጠቀም፣ ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን በሀገር ውስጥ ማምረትና ሌሎች የመፍትሔ ሃ ሳቦች በስትራቴጂው የሚተገበሩ ስለ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ የሚፈጠሩ የጥራት መጓደሎችን ለማስቀረት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፣ ለቆዳ ምርት ግብዓት የሚውለውን የጨው አቅርቦትን የማሳደግ እና ቆዳ ለሚያዘጋጁ አካላት ሥልጠና መስጠት በስትራቴጂው ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

መንግሥት ዘርፉ ያጋጠመውን ችግር ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ከአምራች ኢንዱስትሪ ጋር በመሆን ለመፍታት የጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው። በተለይም ከዘርፉ እንደ ሀገር እያጣነው ካለው ከፍ ያለ ሀብት አንጻር ለዘርፉ በዚህ መልኩ የተሰጠው ትኩረት ሊበረታታ የሚገባ ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ ዘርፉ ከመጣበት ውስብስብ ችግር አንጻር ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት ለማስመዝገብ ፤ በጠንካራ ዲሲፕሊንና ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ፤ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You