አቶ ጥላሁን ከበደ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ባሉ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በአዲስ መልክ በተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመው ሥራ ጀምረዋል፡፡ አዲስ ዘመንም አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አወቃቀሩን በተመለከተ እና በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታን አስመልክቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መቀመጫ እንዲሆኑ መደረጉ አንድም ለከተሞቹ እድገት አንድም ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲኖር ታስቦ እንደሆነ ይነገራልና በእርስዎ አተያይ ይህ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጥላሁን፡- በቅርቡ ምሥረታውን ያካሔደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ማዕከል እንዲኖረን ታስቦ የተወሰነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በቀድሞው የደቡብ ክልል ውስጥ የነበሩ ዞኖች በክልል እንደራጅ ጥያቄያቸው ከዕለት ወደዕለት እየጎለበተ መምጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በበርካታ ዞኖች የተነሳ ጥያቄ የራሱ የሆነ ገፊ ምክንያት ኖሮት ወደፊት የመጣ መሆኑ እውን ነው፡፡
በተለይ የክልል ተቋማት በአንድ ማዕከል ላይ መሰባሰባቸው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሮም ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የከተሞች እድገት ላይም ሆነ የተጠቃሚነት ጉዳይ ላይ ችግር ፈጥሮ በመክረሙ ዞኖች በክልል እንደራጅ የሚለውን ጥያቄ አጉልተው ሲጠይቁ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በተደጋጋሚ ከሕዝቡ ይነሳ የነበረው ሌላው ምክንያት የቀድሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አልጠቀመንም፤ አላሳተፍንምም የሚል ጭምር ነበር፡፡ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሁም በቅርበት አገልግሎት ለማግኘት አልቻልንም የሚልም ቅሬታ ነበራቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት በክልል እንደራጅ የሚለው ጥያቄ አይሎ ሊመጣ ችሏል፡፡ በወቅቱም በየመድረኩ ሲነሳም ነበር፡፡
ይህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ምን መከተል ይሻላል በሚል ከሁሉም አካባቢ ከተውጣጣ ምሁር ጋር እንዲሁም የሕዝብ እንደራሴዎች በተገኙበት ምክር ቤት ውይይት አድርገናል። ውይይቱን ስናደርግ ሰብሰብ ብለን እንደራጅ፤ በየዞኑ ክልል እንዲሆን ያልነው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ስንመለከት ብዙም አቅም ያለው ስለማይሆን ኅብረት ፈጥረን ብንደራጅ የበለጠ አቅም ይኖረናል በሚል ተነጋገርን፡፡
ከዚህ ቀደም በቀድሞው በደቡብ ክልል የነበሩ የታዩ ግድፈቶችን በሚያርም አግባብ ክልሉን ብናደራጅ መልካም ነው ወደሚለውም መምጣት ቻልን፡፡ ይህ በመሆኑም በክላስተር ሰብሰብ ብለን እንደራጅ፤ ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎቻችን እንዲፈቱ የሚለውን ሕዝቡ ይሁንታ ስለሰጠው ክልሉን ስናደራጅ በመርህ ደረጃ ክልሉ ብዝሃ ማዕከላት እንዲኖር፤ ማለትም የብዝሃ ማዕከላት ከተሞች ደረጃም እኩል ደረጃ ያላቸው እንዲሆኑ በሚል ተስማማን፡፡
በእርግጥ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት ማዕከላት እንዲኖር ማድረግ ብለን ስንስማማ ቀድሞም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ ብዝሃ ማዕከላት ያለው ክልል እንደሆነ የሚታወቅ ነው። አንቀጽ ስድስት ላይ የክልሉ መቀመጫ ወይም
ደግሞ የክልሉ ከተሞች ብዝሃ ማዕከል ያልናቸው ስድስት ከተሞች ናቸው ብለን ለይተናል፡፡ ከተሞችንም እንዴት እንምረጥ፣ መስፈርታቸውስ ምን መሆን አለበት ብለን ተወያይተንና ተነጋግረን ከተሞችንም መርጠናል፡፡
ከተሞቹ ሲመረጡ የክልሉ መቀመጫ ስድስቱም ከተሞች በእኩል ደረጃ የክልሉ መቀመጫ እንዲሆኑ ስንወስንም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ለከተሞችም ሆነ ለመላ ሕዝባችን ጠቃሚ ይሆናል ብለን በስፋት ገምግመን ነው፡፡
በዋናነት የሕዝቡ ተጠቃሚነት ለከተማ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ለሚገኙ ለአጎራባች ዞኖችም ጭምር ነው፡፡ በፊት አገልግሎት ወደተጠቃሚው ሕዝብ ማዳረስ ብዙም የሚቻል አልነበረም፡፡ ከዚህ የተነሳ በአንድ ማዕከል መሆኑን ለብዙ ነገር ሕዝቡ ርቆብናል ሲል ነበር፤ የክልል አመራሮች ሳናውቃቸውና ሳናያቸው ጊዜው ያልፋል በማለትም ሲናገር ነበር፡፡ ስለዚህ ወደአካባቢያችን ቀረብ ይበል፡፡
በቀድሞው ክልል አንድ ከተማ የክልል መቀጫ ሲሆን፣ ሁሉ የሚሰበሰበው ወደ አንድ ሴክተር ነው፡፡ አሁን ግን በስድስት ማዕከል ሲሆን፣ በዚህም ወደመላ ሕዝባችን በመድረስ ቀረብ ያለ አገልግሎት እንዲኖር አድርገናል፡፡ በዚህም አግባብ ይርቅብናል የተባለውን ችግር በዚህ መልኩ መፍታት ችለናል፡፡
ሁለተኛው የከተሞች ቁጥር ስድስት ስናደርግ ለከተሞች እድገትም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። የክልል ማዕቀፍ ስለሆነ በልዩ ሁኔታ የዞንም፣ የወረዳም የከተማ አስተዳደርም በሦስትዮሽ ከተሞች እንዲያድጉ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ስለዚህ የከተሞች እድገት በጣም የተራራቀ መሆን የለበትም፤ የተቀራረበ እንዲሆንም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለብን፡፡ እነዚያ የክልል ማዕቀፍ የሆኑ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው ያሉ ከተሞች ሁሉ እንዲያድጉ ይደረጋል፤ ስለዚህ የከተሞች እድገትና የከተሞችን ሁኔታ ከመቀየር አኳያ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እነዚህ የሚታዩት በተለይ ከኢኮኖሚ አኳያ ነው፡፡
በማኅበራዊ ደረጃም በተለይ ስድስት ከተሞች የክልሉ መቀመጫ ሲደረጉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በበለጠ እንዲጠናከር ያደርገዋል፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 32 ብሔረሰቦች ያሉበት ነው፡፡ መላ ኢትዮጵያውያን የሚኖርበት ክልል ነው ማለትም ይቻላል፡፡ የክልላችን መርህ ብለን ያስቀመጥነው የሠላም ተምሳሌት፣ የእድገት ተምሳሌት የብልጽግና ተምሳሌት ብለን ነው፡፡
ብልጽግና ስንል የወንድማማችነትና የሠላም ነው፡፡ ክልላችን ደግሞ በርካታ ሕዝብ የሚኖርበት ክልል ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የምንወስዳት ትንሽዋ ኢትዮጵያ በሚል ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የመቻቻል፣ ወንድማማችነት፣ መከባበርን በአግባቡ የምናይበት ክልል ነው፡፡ ስለሆነም ብዝሃ ማዕከልን ስናደርግ ይህንን በክልሉ ስም በተለይ አንድ ማዕከል ላይ ከሚሆን በርካታ ማዕከላት ማድረጋችን ሁሉም ሰው በአግባቡ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ይህ የበለጠ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክር እንደሆነ የተማመንበት ሁኔታ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህን ስታደርጉ ማዕከላቱ የተለያየ ከተማ እንደመሆናቸው ለአገልግሎት አሰጣጣችሁ ችግር አይፈጥርም?
አቶ ጥላሁን፡- ማዕከላቱ በተለያየ ከተማ መሆናቸው እንደተባለው የተለያየ ጥያቄ ሲነሳ እናስተውላለን፡፡ በተለይ ከአቅም ጋር በተያያዘ ወጪ እንደሚያስወጣም ይነገራል፡፡ እኛ ከዚህ ጋር በተያያዘ አስቀድመን የተለያየ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ምክንያቱም በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ላይ ማዕከላትን ማድረጉ ሙከራው አዲስም ስለሆነ እንዴት አድርገን ነው በአንድ ማዕከል ላይ ሲሰጥ የነበረውን አገልግለሎት ስድስት ማዕከል ላይ ማድረግ የምንችለው? ተገልጋይ ሳይጉላላ አቅማችንን አሟጥጠን እና ወጪን ቆጥበን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ምን ዓይነት መንገድ እንከተል? የሚለውን ለማወቅ የተለያዩ ጥናቶችን እያጠናቀቅን ነው፡፡
በእነዚህ ስድስት ማዕከላት ላይ ተገልጋይ ብዙ ሳይጉላላ በተለይ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ የምንከተልበትን የአሠራር ሥርዓት ልናስኬድ ይገባል፡፡ ለዚህ አሠራር ያዘጋጀነው ሕግና ደንብ ጭምር ነው። ስድስቱም ማዕከላት የማዕከል አስተባባሪዎች ወይም ደግሞ በምክትል ርዕሰመስተዳድር ማዕረግና ምክትል ርዕሰመስተዳድሩ የሚመሩት ማዕከላትን ነው ያዘጋጀነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ማዕከላት አንድ ተገልጋይ አንድ ጊዜ ቢመጣ እዚያው ሆኖ ስድስቱን ማዕከላት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችልበትን ሥርዓት እንዘረጋለን ብለናል፡፡
ይህ በቴክኖሎጂም የታገዘ እንዲሆን ሥራውን ማቃለያ ዘዴ ተጠቅመን ለመሄድ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ዓለም ዘምና የደረሰችበትን ደረጃ መረዳት እምብዛም አይከብድም፡፡ ግሎባላይዜሽን ላይ ናት፡፡ ምክንያቱም እዚሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን በመላ ዓለም ሥራዎችን ማካሄድ ተችሏል። ከዚህም በላይ ውስብስብ የሆነውን የጤናን ሁኔታ በዚሁ በኦንላይን የሚካሔድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ደግሞም ሥርዓት ያለው እና በሕግ አኳያ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት ዘርግተን በዚያ አግባብ እንዲካሄድ ወስነናል፡፡
ስለዚህ በተቻለ መጠን ወጪ ቆጥበን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አድርገን በዚያ መንገድ እየተንቀሳቀስን ነው። ለዚህ ደግሞ በጋራ ሊሠሩ የሚችሉ አካላት እና አመራሩ ይህን መንገድ ተከተትለን እየሠራን እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአምስት ዓመት ወዲህ ከተመሠረቱ አዳዲስ ክልሎች መካከል ከሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትቀስሙት ተሞክሮ አሊያም የምትማሩበት አካሔድ ይኖር ይሆን?
አቶ ጥላሁን፡- እንደሚታወቀው የቀድ ሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምንም እንኳን የሲዳማ ቀጥሎም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደየቅደም ተከተላቸው ቀድመው የተደራጁ ቢሆንም እነሱን ጨምሮ ክልሉ በአሁኑ ወቅት አራት ክልል ሆኖ ተደራጅቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተደራጀነው በአንድ ቀን አንድ ላይ ነው፡፡ ቀድመው የተደራጁት ክልሎችን በወቅቱ አደራጅተን ወደሥራ እንዲገቡ አድርገናቸዋል፡፡ ከእነዚህ ቀድመው ከተደራጁ ክልሎች ከትምህርት አኳያ የወስድናቸው አንዱና ትልቁ ነገር ሕዝብን በማነቃነቅ በተለይ ቃል የተገቡ ሥራዎችን በአግባቡ ያለመፈጸም፣ ሊሳካ የማ።ይችለውን ጉዳይ ቃል የመግባትና ክልል መሆን ማለት ሁሉ ነገር የተሟላ እንደሆነ ማሰብ ላይ ነው፤ ይህ ደግሞ በኋላ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጥጠው ሲመጡ መልስ መስጠት የሚከብድ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምክንያቱ ከሕዝቡ በኩል የክልልነት ጥያቄን ያቀረብነው ለዚህ ነው ወይ? የሚል ነገር መምጣት ይጀምራልና እነዚህንም ጉዳዮች ጭምር መፍታት የሚቻለው የማንደርስባቸውን ሥራዎች እንደምንደርስባቸው አድርገን ከመናገር መቆጠብ ነው፡፡ ከልምድ አኳያ በጋራ ሕዝብን አስተባብረን ሕዝቡ ባለቤት ሆኖ ከመሥራት ያለፈ ሌላ የተለየ ነገር እንደሌለ በደንብ ይዘን ቀሪ የልማት ሥራዎችን የራሳችንን አቅም ራሳችን አንቀሳቅሰን መሄድ እንደሚገባን ነው፡፡
ከዚያ ውጪ የምንለው ነገር ቢኖር የክልል ምስረታ ብለን በዚያ ላይ መላ ኢትዮጵያውያን እና መላ የንግዱ ማኅበረሰብም ይሁን እንዲሁም ደግሞ መንግሥታዊ ድርጅቶች በሃሳብም ሆነ በሌላ ሌላውም የተወሰነ ድጋፍ በማድረግ ይህን ጊዜ እንሻገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ጸጋዎቻችንን ማየት እና ከዚህ ቀደም ያልታዩ አቅሞቻችን ማየት ላይም እንሠራለን፡፡
ከደቡብ ምዕራብ የወሰድነው ልምድ ብዝሃ ማዕከላትን ቀድመው የጀመሩት እነርሱ ናቸው፡፡ ብዝሃ ማዕከላት በሕዝቡ ውስጥ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችል መንገድ በመሆኑ ትክክል ነው ብለን ወስደናል፤ በመሆኑም ይህን ተሞክሮ እኛም መቀመር ችለናል፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ደግሞ ለማሳካት በየጊዜው አቅማችንን እያጎለበትን እንሄዳለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ አዲስ ሆኖ እንደመዋቀሩ ይህንኑ ተከትሎ አዳዲስ ዞኖችም ከወረዳ ደረጃ ከፍ ብለው ተካተዋል፤ በመሆኑም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምናልባትም ከአጎራባች ክልሎች ጋር የተፈጠረ የወሰን ችግር አጋጥሟችሁ ከሆነ? ከሆነስ ለመፍታት እየሠራችሁ ያለው እንዴት ነው?
አቶ ጥላሁን፡- የደቡብ ብሔር፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ በነበርንበት ጊዜ ክልል ሆነን የተደራጀነው አብዛኞቻችን ዞኖች ነን፡፡ በወቅቱ ዞኖች በክልል ስር በነበሩበት ጊዜ በተወሰነ መልኩ የወሰን እንዲሁም የግጦሽ መሬት ጉዳይ ጥያቄዎች አሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ለእኛ በተለይ ከወሰን ጋር ተያይዞ ለአራቱም ክልል በጣም ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ ነገር ግን የተነሳ ነገር የለም፡፡ ይሁንና ቢነሳ እንኳ የቀድሞው የደቡብ ክልል የሆንን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደአራት ክልል የተደራጀን በጋራ ተቀምጠን የምንፈታው ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሀብት ክፍፍልን እንኳ በተመለከተ ኮሚቴ ተቀምጦ እያየው ስላለ ይህ ነገር ቢከሰት የጋራ መድረክ ፈጥረን የምንፈታው ይሆናል፡፡ ለጊዜው ወጣ ያለ ከወሰን ጋር ተያይዞ የመጣ አጀንዳ ብዙም የለም፡፡ ይሁና ወደፊት ሊኖሩ ስለሚችሉ ሳይባባሱ ከወዲሁ እየተነጋገርንበት የምንሄድበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው ዞኖች ከዚህ ቀደም የተደራጁ ናቸው። ስለሆነም አዲስ የሚፈጠርላቸው የወሰን ጉዳይ አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ለተያዘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያልዎ አተያይ እንዴት ይገለጻል? እንደ ክልልስ የሚኖራችሁ ድጋፍ ምንድን ነው?
አቶ ጥላሁን፡– በብሔራዊ ደረጃ እና ኢትዮጵያውያንን ብዙ አንድ የሚያደርጉን እና የምንጋራቸውን ነገሮች አሉን፡፡ ሊያግባቡን የሚችሉ ጉዳዮችም በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጥቂት የሚያለያዩን ጉዳዮች ትልቅ ቦታ ይዘው እርስ በእርስ ለመናቆር ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡
እንደ ሰውኛ ባህሪ እኛ አሁን ፈተና የሆነብን እጅግ በጣም ብዙ አንድ የሚያደርገን ጉዳይ እያለ በጣት የሚቆጠር ጥቂት ነገር የግጭት እና ያለመግባባት መንስዔ እየሆነ መምጣቱ ነው፤ ታዲያ ለምን ይሆናል የሚለውን መፍታት የሚቻለው በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲሆን፣ እንደ ሀገር ተቋቁመው ወደሥራ መግባታቸው የሚታወቅ ነው፤ እኛ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንደ መንግሥት ከእኛ የሚጠበቅንና የሚያስፈልግ ነገር በተለይም በጉዳዩ የሚሳተፉ አካላትን መልምለን እንዲሳተፉ ማድረግ አንዱ ሒደት ነው። እንዲሁም አጀንዳ ሊሆኑ ይችላሉ የምንላቸውን ጉዳዮች በማቅረብ ላይም እንሠራለን፡።
ዋናው ድጋፍ ማድረግ እና የማያግባቡን ጉዳዮች ላይ ሰው በነቂስ ወጥቶ ተወያይቶና ተመካክሮ እንዲፈታው ድጋፍ ማድረግ ነው። እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከቀበሌ ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ ሊሠሩ የሚችሉ አካላት ጋር ውይይት ቢጀመር የሚለውን እየተነጋገርን እንገኛል፡፡ በጥቅሉ በችግሮቻችን ላይ እና በልነቶቻችን ላይ ያሉ አለመግባባቶች ካሉ ተነጋግረን እንፈታለን የሚል እምነት ስላለን መልክ የሚይዝ ይመስለኛል። በመሆም በተቻለን ሁሉ ደግፈን ወደተግባር ፈጥኖ እንዲገባ የበኩላችንን እንደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ከጥቂት ሳምንት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ለፓርላማ አባላት ስለ ቀይ ባሕር እና ስለ ባሕር በር ጉዳይ ገለጻ ማድረጋቸው ይታወሳል፤ በባሕር በር ጉዳይ አጀንዳ ላይ የእርስዎ አተያይ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጥላሁን፡- ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው በጣም ትልቅ ሀገር ናት፡፡ የምንገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይም ድርሻዋ ጉልህ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በሕዝብ ብዛትም ደረጃችን ከፍ ያለ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ያለን የተፈጥሮ ሀብትም በተመሳሳይ ከፍተኛ በመሆኑ በጥቅሉ በአካባቢያችንም ሆነ በቀጣናችን ተጽዕኖ ፈጣሪነታችን ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡።
ነገር ግን ትልቅ ፈተና የሆነው ከዚህ ቀደም የባሕር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደብ አልባ ሆናለች፡፡ ግን ደግሞ ለብዙ ሀገራት የተፈጥሮ ጸጋ የሆነውና በጣምም ውድ የሆነው ውሃ በወንዞቿ አማካይነት ስትገብር ትስተዋላለች። የእኛን ወንዝ የሚጠቀሙ በጣም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አሉ፤ እኛ ግን ከእነሱ የምንጠቀመው ነገር ብዙም የለም፡፡
የባሕር በር ቢኖረን የሚለው ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ ለሕዝብ መቅረቡ እንደእኔ ጊዜውን ጠብቆ በትክክኛ ወቅት የመጣ እና እንዲሁም ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ኖሯት የውስጥ ልማቷንም ሆነ አጠቃላይ በቀጣናው በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ያላትን ተጽዕኖ ልታሳይ ይገባል ባይ ነኝ። በመሆኑም ጉዳዩ ዋና አጀንዳ ሆኖ በፍጥነት ከጫፍ ጫፍ መነጋገር፣ መወያየትና መግባባት የሚገባን ጉዳይ ነው ብዬ እወስዳለሁ። የባሕር በርና የወደብ ጉዳይ ጊዜውን ጠብቆ የመጣ ትክክለኛ አጀንዳ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ መንግሥት ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ተነጋገሩበት መባሉ ትክክለኛ ነው የሚል አተያይ አለኝ።
መንግሥት አጀንዳ አድርጎ ሲያቀርብም የባሕር በርን በጉልበት እንውሰድ ማለቱ አይደለም። አጎራባች ከሆኑ ሀገራት ጋር በስምምነት፣ በውይይት በመነጋገር እና በመግባባት ለሁሉም ሕዝብ ጠቃሚ በሚሆን መልኩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰው ጉዳዩን እያነሳ ከኤርትራ ጋር ሲያገናኘው ይስተዋላል። በተመሳሳይም ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያገናኘዋል። ዋናው ሁለቱ ሕዝቦች የባሕር በር ያላቸው ብዙ መጠቀም ወይም ደግሞ መገልገል ያልቻሉትን እኛ የጋራ አድርገን መገልገል ስላለብን የሁለት ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ መርህን ተከትለው በጋራ እንገልገል፤ አጀንዳ አድርገን እንወያይበት፤ የተለያዩ ስልቶችን ነድፈን ተግባቦት እየፈጠርን እንሂድበት የሚል አመለካከት አለኝ። ደግሞም አጀንዳ መሆኑ ማንን ይጎዳል፤ የባሕር በርም ደግሞ ያስፈልገናል። ስለዚህ አጀንዳ አድርገን ጀምረናል፤ በሒደት ደግሞ ተጠቃሚ ስንሆን አጀንዳው ይቋጫል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት አጀንዳ ሆኖ ጥንስሱ እንዲጠነሰስ መደረጉ ተገቢም ወቅቱን የጠበቀም ነውና ትክክለኛም ውሳኔ ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርዕሰመስተዳድርነት ለመምራት በተሰጥዎ ኃላፊነት ከሌሎች አመራር ጋር በመሆን ምን ዓይነት ደረጃ ላይ ለማድረስ አስበዋል? ክልሉ ባለሀብቶች መጥተው እንዲያለሙበት የሚያስችልስ ምን ምን ነገር አለ?
አቶ ጥላሁን፡- በታሪክ አጋጣሚ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያው ርዕሰመስተዳድር ሆኜ እንድመራ ድርጅትም መንግሥትም መርጦ ሕዝቡ ደግሞ ይሁንታውን ሰጥቶኝ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡ ፓርቲዬ ይህንን ክልል ምራ ብሎ ሲሰጠኝ እንደሚታወቀው ክልሉ በጣም ትልቅ ክልል ነው፡፡ በተፈጥሮም ጸጋ በጣም የበለጸገ ነው። ብዙ ያልለማ፤ ግን ደግሞ መልማት የሚችል ነው፡፡
ከእኔ ጋር በመሆን አብሮ ለመሥራት እና ሕዝብ ለመምራት የተቀመጥን አመራር አለን፡፡ በዚያ ልክ ደግሞ ክልሉን ለመቀየር በሙሉ ሞራል እና በሙሉ ኃላፊነት ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ አደራ ወስደን መምራት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊም አመራር ጭምር ነን ብዬ አስባለሁ፡። ይህን ጊዜ በተለይ አመራር ሆነን በምንመራበት ወቅት ትልቁ ግባችን እና ርዕያችን በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተው ክልል በኢኮኖሚም፣ በፖለቲካም የብልጽግና ተምሳሌት በመሆን ራሱን ችሎ ለሌላው የሚተርፍ እንዲሁም ደግሞ የእድገት እና የብልጽግና ተምሳሌት የሆነ ክልል እንዲሆን ነው።
ዋና ግባችን የሠላም ተምሳሌ፣ የወንድማ ማችነት ተምሳሌት የሆነ ክልል እንፍጠር ነው። ስለዚህ ክልላችን በሠላም ተምሳሌትነት እንዲታወቅ እንሠራለን፤ ከዚህ ጎን ለጎን ክልላችን የፈተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ነው፡፡ ከደቡብ ኦሞ ዳሰነች ጫፍ እስከ ወላይታ ሶዶ አረካ ጫፍ ድረስ ያለው የተፈጥሮ ጸጋ ብዙ ያልተነካ እና ብዙ ያልተበላ ነው፡፡ ስለዚህ በትንሹ ከተረባረቡበት በጣም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የሚያስችል ጸጋ ያለው ነውና በሰው ኃይልም በተፈጥሮ ጸጋም በከርሰ ምድርም ይሁን በገጸ ምድር ሀብት የበለጸገ ክልል ነው፤ ይህንን አቅም እና ጸጋ በአግባቡ ለይተንና አውቀን በጊዜ የለንም መርህ ወደልማት ገብተን ከሠራን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝባችንን ጥያቄ መመለስ እንችላለን፡፡
ይህንን ሁኔታ ተገንዝበን ወደሥራ መግባት በጣም ወሳኝ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማስተላለፍ የምፈልገው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናም ይሁን፣ በማኅበራዊም ይሁን በተለይ ደግሞ በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣ ነው፡፡ ደቡብ ላይ የቱሪስት መዳረሻዎች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የለሙ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሊለሙ የታቀዱ አሉ፡፡
በቱሪዝሙ ዘርፍ ሠላማችን የክልላችን አንዱ መገለጫ ነው። በግብርናም የተመቻቸ ሁኔታ አለ። የማዕድናት ሀብት ስላለን ባለሀብቶች ለራሳቸው ተጠቅመው ክልሉንም እንዲጠቅሙ ማድረግ መልካም ነው፡፡ ማንኛውም ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጣ አካል በራችን ሁልጊዜ ክፍት ነው፡፡ ሁኔታዎችን አመቻችተን ለማስተናገድ ዝግጁዎች ነን። ክልላችንም ሆነ ሀገራችን የበለጠ ሊያድግ የሚችለው ከግሉ ሴክተር ጋር ተነጋግረን ስንሠራ ነው፡፡
መላ ሕዝባችንም ደግሞ ከአመራሩ ጋር በምስረታ ጊዜ እኛን ደግፎ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲሁም ደግሞ ምስረታ ወቅትም አለን በርቱ ብሎ ያሳየውን ድጋፍ አሁን ወደሥራ ስንገባም በተመሳሳይ መልኩ ድጋፉን እንዲቀጥል እንሻለን፡፡ ጥሪም እናቀርባለን። በተለይ ሠላሙን በማስጠበቁ በኩል፣ ልማቱንም በማሳለጡ ረገድ ከእኛ ጋር በመቀናጀት ይህንን ክልል የሠላም፣ የብልጽግ እና የወንድማማችነት ተምሳሌት እንዲሆን አግዙን እንላለን፡፡ አጋዥ የሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎችን አቅም በሚሰጥ እገዛችሁ ከእኛ አይለይ እላለሁ፡፡
በእስካሁኑ ሒደት ድክመቶቻችንንም ሆነ ጥንካሬዎቻችንን በግልጽ እየነገራችሁን እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡ በቀጣይም ይህ እንዳይለየን እጠይቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ጥላሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም