የወደብ ጉዳይ!

ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ተዳፍኖ የቆየው የኢትዮጵያ የባሕር በር መውጫና የወደብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ዛሬም ከውስጥ የሚመነጭ መፍትሔን የሚሻ ሆኖ ይስተዋላል። የቀይ ባሕር ክልል የዓለማችን አሥራ ሁለት ከመቶ (12%) ልዩ ልዩ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት በባሕር ላይ ንግድ ድርጅቶች በየግዜው ይፋ ከሚያደርጉት መረጃ ለማወቅ ይቻላል። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንስቶ የምዕራብና ምስራቅ አውሮፓ ሀገራት፤ የሩቅና መካከለኛ ምስራቅ ሀገራትን ጨምሮ አሜሪካ በቀጠናው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ብልጫን ለማግኘት ባልተቋረጠ መልኩ ብርቱ ፉክክር እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

የቅኝ ግዛት ዘመንን ጨምሮ ልዕለ ሃያላን ሀገራት የቀይ ባሕር ክልል ሕዝቦችና ሀገራትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ፈጽሞ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንቅስቃሴ በቡድንና በተናጠል በስፋት ሲያደርጉ ይስተዋላል። በአካባቢው በሁሉም ረገድ በልጦ ለመውጣት የሚያደርገው ፍትሃዊነት የጎደለው ፉክክርና ፍጥጫ የቀጠናው ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን እንዲያጡ እያስገደደ ያለ ከመሆኑም ባለፈ ለብሔራዊ የፀጥታ ስጋት ተጋላጭ እንዲሆኑም አድርጓቸዋል።

በቀጠናው እየተደረገ ያለው የልዕለ ሃያላኑ ሁሉን አቀፍ በየደረጃው የሚገለጽ ብርቱ ጫና የቅኝ ግዛት አርተፊሻል ድንበር፣ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብና በቀጠናው አገራት ሕዝቦች መካከል ኃይማኖትን ጨምሮ ያሉ ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን በአሉታዊ መንገድ አጉልቶ አንዱን ለሌላው ስጋት አስመስሎ በማሳየት የሚደረግ ነው። አንዱ ለሌላው የሁለንተናዊ ጥንካሬው ምንጭ መሆኑ ቀርቶ ጠላት እንደሆነ በማስመሰል፤ ከፋፍሎ አቅም በማሳጣት ላይ የተመሰረተ የራስን ጥቅም ብቻ ማዕከል የሚያደርግ የተበላሸ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ የሚከተሉ መሆናቸውን የአካባቢው የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪዎች አጽንኦት ሰጥተው በየመድረኩ ሲናገሩ ይደመጣል።

ይህም ነጣጥሎ ኃይልና ተደማጭነትን የማሳጣት የልዕለ ሃያላኑ እንቅስቃሴ የቀጠናው ሀገራቱ ጠንካራ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ውህደትና የፖለቲካ መተማመን እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለው የሚናገሩ ምሁራንም እጅግ በርካታ ናቸው። በፈረንጆች ኖቬምበር 17/1869 በግብጽ የባህር ክልል በኩል የተሰራው፣ ቀይ ባሕርን በቀጥታ ከሜድትራኒያን ባሕር ጋር የሚያገናኘው ሰው ሰራሽ “ስዊዝ ካናል “የተሰኘ የውሃ ውስጥ መሿለኪያ መገንባቱ ደግሞ የአካባቢውን የስበት ማዕከልነት በእጅጉ ከግዜ ወደ ግዜ እያሳደገ እንደሚገኝ በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቀጠናው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተጨባጭ ሁኔታና ታሪክ መረዳት ይቻላል።

የመሿለኪያው መከፈት አፍሪካን እንዲሁም የምስራቁን የአህጉሪቱን ክፍል ከመካከለኛና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት፤ ከምዕራብና ምስራቅ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም አሜሪካ በቀላሉ የሚያገናኝ መሆኑ የአካባቢውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በእጅጉ ከፍ ያደረገም ነው።፤ ከቀጣናው ውጭ የሚገኙ ልዕለ ሃያላን ሀገራት በየደረጃው የሚገለጽ የኢምፔሪያሊዝምና የኒዮ ኮሎኒያሊዝም መልክ ያለው ቀጠናውን ለፖለቲካ አለመረጋጋትና ለሽብር አደጋ ስጋት የሚዳርግ ፉክክር እንዲያደርጉም ምክንያት የሆነ ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ ፕሮጀክት ነው።

ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ረገድ የመሿለኪያው መከፈትን ጨምሮ ቀይ ባሕር በመርከብ ልዩ ልዩ ነዳጅና ዘይቶችን፤ ሃይድሮካርበን፣ ልዩ ልዩ ሸቀጥና የፍጆታ ምርቶችን፤ ሌሎችንም የጦር መሳሪያን ጨምሮ ግዙፍ ቁሳቁሶችን ወደ ሦስቱም አቅጣጫ 193 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው መሿለኪያ አማካኝነት በፍጥነት ማለትም ወደ አውሮፓ፣ ኢዥያና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ማጓጓዝ እንዲቻል አቅም የፈጠረም ነው። መሿለኪያው በዓመት 30 ኮንቴይነር ምርቶች ግብይት እንዲከናወን በማስቻሉ USD $1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማመንጨት የሀገራቱን ኢኮኖሚ ከመደገፉም ባሻገር የቀጠናው እስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ጎልቶ እንዲታይም አድርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ግብጹ የስዊዝ ካናል አስተዳደር መረጃ በፈረንጆች 2020 ከ19,000 በላይ መርከቦች መሾለኪያውን ተጠቅመው በቀጠናው ጉዞ ማድረጋቸው ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በቀን 50 መርከቦች እንዲሁ መሿለኪያውን ተጠቅመው ወደ መዳረሻቸው በማቅናት 3-9 USD $ ቢሊዮን የካርጎ ግብይት የምስራቅ አፍሪካ የባህር ክልልን ጨምሮ የተፈጸመ መሆኑን አመላክቷል።

በ1983 በሀገሪቱ የተደረገውን የመንግሥትና የፖለቲካ ስርዓት ለውጥን ተከትሎ ሕዝብን ለውይይት ባልጋበዘ/ ዕድል ባልሰጠ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሀገሪቱ በታሪክ የእርሷ እንደነበሩ በግልጽ ተመዝግበው የተቀመጡና ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የነበሩ ሁለት ወደቦቿን ጨምሮ የባሕር በር መውጫዋን እንድታጣ ያስገደደ ብሎም የመጪው ትውልድን ጥቅም ያላገናዘበ አሳዛኝ ውሳኔ ተላልፏል። በወቅቱ ተላልፎ የነበረው የፖለቲካ ውሳኔ የሁለቱን ሀገራት ዘላቂ ጥቅም የማያረጋግጥ የጥቂት ተፋላሚ ቡድኖች ፍላጎት ብቻ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ ተደጋግሞ ሲነሳ የሚስተዋል ነው። በሁለቱም ሀገራት ለሚኖሩ ወንድማማች ሕዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ቀጠናዊ ትብብር ተጨባጭ አቅም ይሆን ዘንድ ከግጭትና ጦርነት በመለስ ያሉ ሌሎች የመፍትሔ አማራጮችን በመፈለግ ዘላቂ ሰላምን በቀጠናው ማረጋገጥ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን በቀይ ባሕር የውሃ ክልሏ ላይ አቋቁማው የነበረው የባሕር ኃይል በቀጠናው ያላትን ተደማጭነትና ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር እንዲያስችላት ሲያበረክት የነበረው አስተዋጽኦ በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገር ቢሆንም ከ1983 የፖለቲካ ውሳኔ በኋላ እንዲፈርስ በመደረጉ ሳቢያ በአጠቃላይ ሰላምና ደህንነቷ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ በቀጠናው የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ አዳዲስ ክስተቶችን ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሆነባትም ተያይዞ ይነሳል።

ከሦስት አሥርት ዓመታት ለሚበልጥ ግዜ ምንም ዓይነት አማራጭ መፍትሔ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ባልተገኘበት ሁኔታ ሀገሪቱ በር ተከርቸም ተዘግቶባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት የጅቡቲን የወደብ አማራጭ እየተጠቀመች የምትገኝ መሆኗ የሚታወቅ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ምሽት፤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈውና ‹‹ከጠብታ ውኃ እስከ ባሕር ውኃ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ማብራሪያ፤ “ዓባይና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ተደርገው መወሰድ እንደሚኖርባቸው ያመላከቱት “ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፍጥነት እየጨመረ ካለው የሕዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ የባሕር በር መውጫ የግድ እንደሚያስፈልጋት ዝርዝር እውነታዎችን ለምክር ቤት አባላት ለቀጣይ ውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ማብራሪያ መስጠታቸው የሚታወስ ነው ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በማብራ ሪያቸው፤ “የቀይ ባሕርን ጉዳይ እኛ እንዴት ነው የምንመለከተው? ምንድን ነው እሳቤያችን? ይሄ እሳቤያችን ትክክል ነው ወይስ አይደለም? ያዋጣል ወይስ አያዋጣም? መሆን አለበት ወይስ መሆን የለበትም? በሚለው ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከስሜት ነጻ በሆነ መንገድ አስልቶ፤ ለልጆቹ መልካም ነገር መተው አለበት” ያሉ ሲሆን፤ “በሕዳሴና በተከዜ ጉዳይ እየተወያየን በቀይ ባሕር ጉዳይ አንነጋገርም ማለት የሚቻል አይሆንም” በማለት የምክር ቤት አባላት ወርደው በየደረጃው ሕዝብን የማወያየት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁ መሆናቸውም አይዘነጋም።

የኢፌዴሪ መንግሥት ከለውጡ ማግሥት አንስቶ የባሕር ኃይል እንደገና ማደራጀትን ጨምሮ ሀገሪቱ የወደብ አማራጭና የባሕር በር መውጫ/መተንፈሻ ማግኘት በምትችልበት ሁኔታ ላይ ከጋዜጠኞች፣ ከባለሀብቶች፣ ከፖለቲከኞችና ምሁራን እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከውስጥ የሚመነጩ አማራጭ የመፍትሔ አሳቦች ዙሪያ ተደጋጋሚ ምክክሮችን ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በአንዳንድ አካላት መንግስት የውስጥ ጉዳዮችን በዚህ ለመተካት እንዳመጣው አጀንዳ ተደርጎ የሚናፈሰው መሰረተ ቢስ አሉባልታ ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም ።

ከቀይ ባሕር ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና በጋራ መልማት ጋር በተገናኘ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው አጀንዳ መነሻው ውይይት፤ መድረሻው የጋራ ተጠቃሚነት ነው። ታሪክና አስቀድሞ የነበረን መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ መሠረት ባደረገ መልኩ በአገር ወስጥ የሚደረግ ውይይትን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው ወሰን ተጋሪ ሀገራት በጋራ በሚያደርጉት አካታች ንግግር የቀጠናውን ሁለንተናዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችል መፍትሔ ማዋለድ እንደሚቻል በብዙሃን ተቀባይነት ይኖረዋል።

በቀጠናው እውን እንዲሆን የሚፈለግ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ በአንድ ሀገር የበላይነት ወይንም በተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሁሉንም ወሰን ተጋሪ በቀጠናው የሚገኙ ሀገራትን ማዕከል በሚያደርግ አብሮ በወንድማማችነት የመልማት መርህ የሚወሰን ይሆናል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር አንስቶ እስካሁን ባለው ከታችኛውና ላይኛው የተፋሰስ አገራት ጋር በዘላቂነት እያደረገች ያለው ውይይት ሀገሪቱ በጋራ ተጠቃሚነትና መርህ የምታምን መሆኑን የሚያሳይና በቀጠናው እንደአብነት ልጥቀስ የሚችል ሁሉንም አካላት የሚያግባባ ምሳሌያዊ ተግባርም ጭምር ነው።

አስቀድሞ የሀገሪቱ ሉኣላዊ ግዛት ከነበሩ ሀገራት ጋር በየደረጃው የሚገለጽ ለፖለቲካዊ ውህደት መንገድ የሚጠርግ የኢኮኖሚያዊ ውህደት ሥራዎች- ማለትም እንደ አብነት የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ሥራ አብሮ ልታይ የሚገባ ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ክልል ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ሶማሌ ላንድና ኤርትራ ወደቦችን መመልከትን ጨምሮ ከኤደን ባህረ -ሰላጤ ሀገራት ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር በቀጠናው መልማት የሚችሉ የወደብ አማራጮችን አቅም በሚፈቅደው ሁሉ መጠቀም እንድትችል መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ እንጂ ለመንግሥት ብቻ በአደራ የሚተው አይሆንም።

በውይይት የዳበሩ አዋጭ አማራጮች በየደረጃው ተግባራዊ በማድረግ አገሪቱ በቀጠናው አስቀድሞ የነበራትን ተቀባይነትና ተጽዕኖ እንዲሁም የባሕር -በር ወሰን ወደነበረበት እንዲመለስ ለማስቻል የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ከጠመንጃ በመለስ በሁሉም ረገድ የንግግር ባሕል እንዲዳብር በጋራ መስራትን ጨምሮ ጥንት በአገሪቱ ታሪክ ዜጎች በወንድማማችነት መፈጸም እንደቻሉት አኩሪ ገድል ሁሉ ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን መከበር በዓለም አደባባይ በአንድነት መቆም እንደሚጠበቅብን ቀጠናዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ።

እንደ መውጫ

ለዓመታት ከዐባይ ግድብ ግንባታ መጀመር ጋር በተጓዳኝ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስናደርግ እንደነበረው ድርድር ሁሉ የቀይ ባሕር መውጫና የወደብ አማራጮችን አስፍቶ የመመልከት ጉዳይን በሚዲያ፣ በየደረጃው በሚደረጉ የሕዝብ፣ የምሁራንና የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት በሁሉም ዘንድ አጀንዳው ጎልቶ እንዲታይ ማስቻልን ጨምሮ በቀጠናው የሚገኙ ወንድማማች ሕዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች መፍትሔ ማዋለድ እስኪቻል ድረስ በሁሉም ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። አጀንዳው አድጎና ጎልብቶ ከቀጠናው አልፎ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ይታይ ዘንድ በየደረጃው አካታችና አዋጭ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመከተል ሀገራት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማግባባት አብሮ ሊከናወን የሚገባው ሌላኛው ዋነኛ ተግባር ነው !

 ላንዱዘር አሥራት

ጋዜጠኛ እና ሲኒየር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You