ሆስፒታሊቲ ዓውደ ርዕይ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞችም ቢቀጥል !

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቱሪዝም ገቢያ ቸው ከአጠቃላይ ገቢያቸው ከ50 በመቶ በላይ የሆኑ ሀገራት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የእነዚህ አገራት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻ ሲታይ ግን ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት አቅም እዚህ ግባ የሚባል ላይሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡

በተቃራኒው ኢትዮጵያ ሊለማ የሚችል ከፍተኝ የሆነ የቱሪዝም አቅም፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ሆና ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ ከተባለ ምንም ውስብስብ ጥናት ሳያስፈልገው የቱሪዝም ሀብታችንን በአግባቡ አለማወቃችን፤ አለማልማታችንና አለማስታዋወቃችን እንደሆነ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልምዳችን አለማደግም ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳ ነው፡፡

ይህንን ችግር በተወሰነ መልኩ ይቀርፈዋል፤ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምንም ያነቃቃል በሚል ባለፈው መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም በቱሪዝም ሚኒስቴር አዘጋጅነት የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዓውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል፡፡ ይህ ዓውደ ርዕይ ለአንድ ወር ያህል ቆይቶ እነሆ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ ለመሆኑ ዓውደ ርዕዩ በአንድ ወር ቆይታው ምን መነቃቃት ፈጥሮ ይሆን? የሚለውን የዛሬ አጀንዳዬ ማጠንጠኛ ነው፡፡

የዓውደ ርዕዩ የመክፈቻ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መገኛታቸውና፤ መልዕክት ማስተላለፋቸው በራሱ አንድ መነቃቃት መፍጠሩን መገመት የሚከብድ አይደለም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው መገኘት በራሱ ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት አንድ አቅም የሚፈጥር ነውና።

በዓውደ ርዕዩ የተካተቱ የሀገሪቱ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ቅርጾች /በየክልሎች የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ባሕላዊ መገልገያዎች፣ የተለያዩ ባሕላዊ መገለጫዎች፣ የየአካባቢው ታሪካዊ ማስታወሻዎች /፤መልካ ምድራዊ ውበቶች አንድ ሰው አንድ ቦታ ሆኖ ኢትዮጵያን በዘርፉ ያላትን ሀብትና እምቅ አቅም ማሳየት ያስቻለ ነው። ይህ በጎብኝው ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው መገረምና መደመም በስፍራው በመገኘት ብቻ ማግኘት የሚቻል ነው።

በስፍራው ጀጎል ግንብ፣ የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያን የመሳሰሉት ቅርሶች በወካይ ሞዴሎቻቸው ይታያሉ፡፡ የተፈጥሮ መስህቦች (ሜዳና ተራራው) ሳይቀር በአምሳላቸው ይታያሉ፡፡ በእያንዳንዱ ቦታ ላይ ያሉ ማብራሪያ የሚሰጡ ሰዎች ደግሞ ረቂቅ በሆኑ ነገሮች ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡

የመክፈቻው ዕለት እንደተገለጸው፤ የአውደ ርዕዩ ዓላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን፣ የማሕበረሰቡን ታሪክና ልዩ ልዩ ባሕሎች ማስተዋወቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ያህል ተሳክቷል ከተባለ፤ ምንም እንኳን ሙሉ እውነታውን የሚያውቀው አዘጋጁ አካል ቢሆንም እንደ ተመልካች ግን ያስተዋልኩትን መመስከር የምችል ይመስለኛል፡፡

በተለይም እንደተከፈተ በነበሩት ሳምንታት አውደ ርዕዩ ብዙ ታዳሚዎች ነበሩት፡፡ በሁሉም የመጎብኛ ቦታዎች ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩንቨርሲቲ ተማሪ በስፋት ተጎብኝቷል፡፡ ሥራዬ ብለው የሚሄዱ ጎብኝዎች ነበሩ፡፡

መገናኛ ብዙኃን እስከዚህ ሳምንት ድረስ ሲሰሯቸው በነበሩ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ላይ እንዳስተዋልኩት በየቀረጻው ቅጽበት ብዙ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የብዙ ተቋማት ሰራተኞች በቡድን በቡድን ሲጎበኙ ታይቷል፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ፕሮግራም ይዘው ቅደሜና እሁድ ልጆቻቸውን ያስጎበኙ የነበሩ ወላጆች እንደነበሩ አስተውያለሁ፡፡

በእርግጥ በከተማዋ ነዋሪዎች ውስጥ እንዲህ አይነት መነቃቃት የተፈጠረው የቱሪዝም ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ በመሆኑ ነው፡፡ የሳይንስ ሙዚየም በራሱ ለአውደ ርዕዩ ልዩ ውበት መጎናፀፉም አይካድም፡፡

ዓውደ ርዕዩ የፈጠረው ሌላው መነቃቃት ደግሞ ብዙ ሰዎችን ከዋናዎቹ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የመሄድ መነሳሳት መፍጠሩ ነው፡፡ ለማሳያነት የተቀመጡ ቅርሶችን ያስተዋለ ሰው ‹‹ዋናውን ቢያዩት እንዴት ሊሆን ነው?›› የሚል ስሜት የፈጠረበት ይመስላል፡፡ ከዚህ በመነሳትም እስካሁን ቅርሶቹን ባለማየቱ የመጸጸት ስሜት የተሰማቸው እንዳሉም ታዝቤያለሁ፡፡

በነገራችን ላይ በብዙዎች አመለካከት ‹‹ቱሪስት›› ሲባል ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡ ቱሪስት ማለት የውጭ አገር ዜጋ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ዝርዝሩ ይቅርና ቱሪስት ማለት በአጭሩ የሆነን ቦታ የሚጎበኝ ሰው ማለት ነው፡፡ ከሐረር ሄዶ ፋሲል ግንብን የሚጎበኝ ኢትዮጵያዊ ቱሪስት ነው፡፡ ከጎንደር ሄዶ የሐረር ግንብን የሚጎበኝ ጎንደሬ ቱሪስት ነው፡፡ ከወለጋ ሄዶ አክሱምን የሚጎበኝ ሰው ቱሪስት ነው፡፡

እንዲያውም በአንድ የቱሪዝም ውይይት ላይ የሰማሁት አንድ አስተያየት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለው ከውጭ በሚመጡ ዜጎች ነው፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪስት እንቅስቃሴ ባሕል አልተደረገም፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ከአራት ዓመት በፊት የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ የአገር ውስጥ ጎብኚ ሚና በሚገባ አልተጠናም፤ ለዚህ ምክንያቱም አብዛኞቹ ጥናቶች የሚያተኩሩት በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ላይ ስለሆነ ነው፡፡

እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ ፤ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጉብኝት ያለበት ደረጃ ደካማ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ጉብኝት መዳከም ምክንያት ተብለው በጥናቱ ውስጥ ከተጠቀሱት አንዱ የአገር ውስጥ ጉብኝት የስትራቴጂ ዕቅድ አለመኖር ነው፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ አሰራሮች የውጭ አገር ጎብኝዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ነው፡፡

በጥናቶቹ ሌላው እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት፤ አካባቢያዊ ግጭቶች ናቸው፤ እነዚህን ግጭቶች የሚቀሰቅሱ የመገናኛ ብዙኃን /በተለይም የማሕበራዊ ድረ ገጾች/ ግጭቶቹ ብሄር ተኮር ዕይታ እንዲላበሱ ማድረጋቸው ነው፡፡ ስለ ግጭቶቹ የሚፈጠሩ ትርክቶች አንዳንድ አካባቢዎች በመጥፎ እና በአስፈሪ ገጽታ እንዲሳሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ትርክቶቹ የሚፈጥሩት ፍርሃት የአገር ውስጥ ጎብኚ ቁጥር እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

ሌላው በዋነኛነት ጥናቶቹ የሚጠቅሱት ምክንያት የተለመዱት የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ብቻ ሙጭጭ ማለትን ነው፡፡ ይህም አዳዲስ የቱሪስት መደራሻዎችን ከማስተዋወቅ ይልቅ ቀደም ሲል የተዋወቁ ላይ እውቀትን እና ሀብትን የማባከን ችግር ነው።

በአጠቃላይ፤ ለቱሪዝም ያለን አመለካከት አለማደግ እና የአገር ውስጥ ጉብኝት ባሕላችን በጣም ደካማ መሆን በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል። ይህንን ሀገራዊ እውነታ በመቀየር ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ ይቻላል። ለዚህም ለቱሪዝም ያለንን እይታ እናሳድግ፤ ለአገር ውስጥ ጉብኝት ትኩረት እንስጥ። በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የተደረገው የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዓውደ ርዕይ በዘርፉ እየፈጠረ ካለው መነቃቃት አንጻር፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞችም የሚቀጥልበት ሁኔታ ይመቻች!።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2016

Recommended For You