በግብርናው ዘርፍ የታዩ ውጤቶች የስኬታማነት ማሳያዎች ናቸው!

ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 120 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ የሚመግብ ዘርፍ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ 96 ሚሊዮን ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮው ቀጥታ ከግብርና ስራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሬ አንጻርም ብንመለከተው አብዛኛው ገቢ የሚገኘው ከዚሁ ዘርፍ ነው፡፡

ይህንኑ ሃቅ በመገንዘብ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡ የሀገሪቱን መልክዓ-ምድርና የአየር ጻባይን መሰረት ያደረጉ ስራዎች በመሠራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪኳ አምርታቸው የማታውቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችለዋል፡፡

ጤፍ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ የሚመገበው እና አብዛኛውን የእርሻ መሬት የሚሸፍን ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ይሄ ነው የሚባል የምርት ዕድገት ሳያሳይ ቆይቷል፡፡ የለውጡ መንግስት እውን እስከ ሆነበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በክላስተር ማረስ በመቻሉ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአዲስ የልማት ጎዳና እንድትራመድ ካደረጓት የግብርና እንቅስቃሴ አንዱ የስንዴ ልማት ነው፡፡ ቀደም ሲል በጥቂት መጠን፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፤ በክረምት ብቻ ይመረት የነበረውን የስንዴ ልማት ወደ በጋም በማሸጋገር የስንዴ ምርትን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም ላይ ተደርሷል፡፡

የስንዴ ምርት በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በሄክታር ሁለት ቶን ይገኝ የነበረው የስንዴ ምርትም ወደ አራት ቶን ማሳደግ ተችሏል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2016 ምርት ዘመን ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች፡፡ በ2015 ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከተውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡ በተለይ በአማራ ፎገራና በጅማ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል፡፡ 500ሺ የነበረው ዓመታዊ ምርትን ወደ 800 ሺህ ማሳደግ ተችሏል፡፡ በዚህም 700ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ገቢ ወደ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ችሏል፡፡ የሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለሀገሪቱ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የማምጣት አቅም ላይ ደርሷል፡፡

ከዚህ በሻገርም በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል። በማር፤ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽዖ፣ በጓሮ አትክልትና በፍራፍሬ ምርት ላይ የጎላ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ዜጎች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ብሎም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏል።

በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ያለው መሻሻል ስንዴን፤ ሩዝንና አቦካዶን የመሳሰሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም እንዲቀርብ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር የተመሰከረለትና ኢትዮጵያም በግብርናው ዘርፍ እምርታ እያሳየች መምጣቷን የሚመሰክር ነው !

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2016

Recommended For You