«ሌብነትና ብልሹ አሠራር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተለዩ ከአመራርነት እንዲነሱ ተደርጓል »አቶ ታረቀኝ ገመቹ፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ “ለሚ ኩራ” በሚል ስያሜ 11ኛ ክፍለ ከተማ ካደራጀ እና መዋቅር ፈጥሮ ወደ ሥራ ከገባ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። የክፍለ ከተማው መደራጀት ዋና ዓላማ ደግሞ የአገልግሎት ተደራሽነትና የማስተዳደር አቅምን በማጎልበት ለከተማው ነዋሪዎች ሚዛናዊ በሆነ ርቀት አገልግሎት መስጠት ነው። ይሁን እንጂ በክፍለ ከተማው አሁን ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ በተለይም በመሬት ነክ አገልግሎት ላይ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታዎች እየተነሳበት መሆኑ ይነገራል።

እኛም በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን የክፍለ ከተማውን እውን መሆን ተከትሎ የታዩ ለውጦች፤ የተገኙ ስኬቶችና ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ በማተኮር፤ የሕዝቡን ጥያቄና ቅሬታ ማዕከል በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ምን እየሰራ ነው? የሚለውን ማዕከላዊ ጉዳይ በመያዝ፤ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆኑት አቶ ታረቀኝ ገመቹ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ምንባብ፡

አዲስ ዘመን፡- ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዛሬ ላይ በሕዝብ ዘንድ በመልካምም በችግርም ስሙ ይነሳል። እርሶ ደግሞ በቅርቡ የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል። የዚህ ክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ መሆንዎ ምን ስሜት ፈጠረብዎት?

አቶ ታረቀኝ፡- ይህ ለእኔ አዲስ አይደለም። የክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስጻሚ ስሆን ይህ አራተኛ ክፍለ ከተማዬ ነው። በልደታ፣ ቂርቆስና የካ ክፍለ ከተሞች በዋና ስራ አስፈጻሚነት መርቻለሁ። ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ስመጣ የስራ ጫና እንዳለ በተለይም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ስሰማ ነበር።

ስለዚህ ከመምጣቴ በፊት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ እንዴት አድርጌ አስተካክላለሁ የሚል ሀሳብ ከመፈጠሩ በስተቀር፤ ከአመራሩ፣ ከሰራተኛውና ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቤ ለመስራት ችግር ስለሌለብኝ ብዙ ፍራቻ አልገጠመኝም። ግን ያሉ ችግሮች ውስብስብ ስለሆኑ እንዴት አድርጎ ማስተካከል ይቻላል የሚል ሀሳብ ነበረብኝ።

አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመቅረፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ምን ዕቅድ ነድፈዋል?

አቶ ታረቀኝ፡– ወደ ክፍለ ከተማው ስመጣ ምን ስራ ልሰራ እንደሚገባኝ በከፍተኛ አመራሮች በኩል ‹‹ኦረንቴሽን›› ተሰጥቶኛል። በዚህ መሰረት ዋናው ችግር መሬትና መሬት ላይ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ነው። የመሬት አደረጃጀቱ ብዙ ችግር ያለበት ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ስራዎች ተጀምረዋል።

ከሁሉም በፊት ከፋይል አደረጃጀት ጀምሮ መዝገብ ቤቱ ሲታይ ፋይሎች የሚገኙት ተበታትነው ነው። መዝገብ ቤቱ አራት ቦታ ላይ የሚገኝ ስለሆነ ለቁጥጥርና ለክትትል ምቹ አልነበረም። በዚህ ሳቢያም ባለቤት ስለሌለውና የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ፋይል ወስዶ የመቆየት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ስለሆነም በአሰራርና በአንዳንድ አደረጃጀቶች ላይ ያሉ ችግሮች እንዳሉ በክፍለ ከተማው ካሉ አመራሮች ጋር በካቢኔም በሌላ አመራሮች ጋርም በጠቅላላው ከመላ አመራሩ ጋር ያሉ ችግሮችን በተገቢው መንገድ ገምግመናል።

አንደኛው ችግር፤ ያሉ ፋይሎችን በደንብ ማየት፤ ስንት ፋይል አለው፤ ካሉ ፋይሎች ደግሞ በሕግ አግባብ የትኛው ትክክለኛ ነው፤ የትኛው ትክክለኛ አይደለም፤ የሚለው ከተማ አስተዳደሩ በራሱ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የማጥራት ስራ እየሰራ ነው። ይህም የመረጃ አደረጃጀቱን በማጥራት በኩል አጋዥ ተግባር ነው። ችግር ያለባቸውን ፋይሎችና ችግር የፈጠሩ ግለሰቦችን ጭምር ለይተው በማጠናቀቅ ላይ በመሆናቸው ክፍለ ከተማው በሚሰራው ስራ ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።

ከአደረጃጀት አንጻር ከመዝገብ ቤት ጀምሮ የአግልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እንዲሆንና ያልተፈለገ እንግልትና መመላለስ እንዳይኖር ለማድረግ የአስተዳደር መዋቅሩ ተስተካክሏል። ችግሮችን በመለየት መፍትሔ የማስቀመጥ ስራ እየተሰራ ነው። ያሉ አመራሮች አብዛኞቹ መስራት የሚፈልጉና አቅሙም ያላቸው ናቸው። በዚህም የአመራር ምደባ ማስተካከያ ሥራ ተሰርቷል።

አዲስ ዘመን:- እርሶም እንዳነሱት በክፍለ ከተማው ትልቁ ችግር ሕገ ወጥነት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ረገድ በ2015 በጀት ዓመት ምን ሰራችሁ?

አቶ ታረቀኝ፡- ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አንጻር ብዙ ስራ ተሠርቷል። ከመሬት ወረራ ጋር በተገናኘ ወደ አንድ ሺ 299 ሕገወጦች ተለይተው ሙሉ በሙሉ እርምጃ በመውሰድ 53 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል። ከመሬት ማስፋፋት አኳያ ደግሞ ካላቸው መሬት ጨምረው መሬታቸውን አስፋፍተው የያዙ 52 ሰዎች ተለይተው በተወሰደ ርምጃ አራት ሺ973 ካሬ ሜትር የሚሆን መሬት ተመልሷል። ከግንባታ አንጻር ደግሞ 495 ሰዎች ተለይተዋል።

ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በተመለከተ ደግሞ 99 የሚሆኑ ሕገ ወጥ ደረቅ ቆሻሻ አገልግሎት፣ 277 በሕገ ወጥ እንስሳት እርድ በተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል። በተወሰዱት እርምጃዎች በቅጣት ደረጃ አንድ ሚሊዮን 193ሺ 325 ብር በቅጣት ገቢ ተደርጓል። ሕገወጥ ሲገኝ እርምጃ ወስዶ ማስተካከል ከመሬት ወረራ፣ ማስፋፋት፣ ከሕገወጥ ግንባታ በሌሎች ነገሮች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ከወረዳ በብልሹ አሰራር ውስጥ የተገኘ አመራርም ሆነ ባለሙያ ወደ ክፍለ ከተማ የመመደብ ስራ ሲሰራ እንጂ እርምጃ ሲወሰድበት አይታም፤ ይህ ለብልሹ አሰራር በር እንደከፈተ ስለመሆኑ በሕብረተሰቡ ዘንድ ይነሳል፤ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ታረቀኝ፡- አመራር ሁለት ሚና አለው። የመጀመሪያው ለማረምና ለማስተካከል ራሱ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር ነጻ መሆኑን ይጠይቃል። በሁለተኛ ደረጃ ችግር ውስጥ የገቡ ሰዎችን ለማረምና ለማስተካከል ኃላፊነት አለበት። አመራሩ ከተበላሸ ሁሉም ይበላሻል። ስለዚህ አመራሩን መልሶ ሲደራጅ ችግር ያለባቸው አመራሮች ምን ችግር እንዳለባቸው ተለይቷል። በተደረገው ልየታ መሰረት ብዙ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። የማሳደግ፣ ከቦታ ቦታ መቀየር ሳይሆን፤ ችግር ያለባቸው ከአመራርነት እንዲነሱ ተደርጓል።

ለምሳሌ ወረዳ 13 እና ወረዳ 06 ላይ ኦዲት ተደርጎ በብልሹ አሰራር ውስጥ የተገኙ ብዙ አመራሮች በግምገማ እንዲነሱ ተደርጓል። ሌሎች ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል። አመራሩ በአመራሩ ላይ ባነሳው ሀሳብ ልክ፤ ከሕብረተሰቡ በተገኘው ጥቆማ መሰረት ተደርጎ 26 ሰዎች ከአመራርት እንዲነሱ ተደርጓል። ይህ ሲባል ግን የቀሩ አመራሮች ሁሉም ንጹህ ናቸው ማለት አይቻልም። ይህ በቀጣይም ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው።

እስካሁን ድረስ በሕዝብና በአመራር በሌብነትና ብልሹ አሰራር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተለዩ አመራሮችን ከአመራርነት እንዲወጡ ተደርጓል። በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ለምሳሌ፣ በመቶ ቀን ዕቅድ ውስጥ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የመሬት ወረራን ከመከላከል አንጻር በጸጥታ አስተዳደር የሚመራ ቡድን የተቋቋመ ሲሆን፤ በየሳምንቱ ዋና ስራ አስፈጻሚው በተገኘበት ይገመገማል። ሰባት የሚሆኑ ግብረ ኃይሎች ተቋቁመዋል። ለኑሮ ውድነትን መፍትሄ የሚሹ፤ ፕሮጀክቶችን የተመለከቱ ብልሹ አሰራርና ሌብነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች የራሱ የሆነ ኮሚቴ ተደራጅቷል።

አዲስ ዘመን፡- አመራር ቦታ በማቀያየር ብቻ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለው ያስባሉ?

አቶ ታረቀኝ፡- ችግሮቹን ለማቃለል በዋናነት አመራር መቀየር ሳይሆን፣ አመለካከቱን መለወጥ ላይ መስራት ነው። ባለሙያውንና አመራሩን በማደራጀትና በማቀናጀት በተልዕኮ ስምሪት በመስጠት እየገመገሙ ችግር ካለ ችግሩን በማረም ካልተስተካከለ ሰውን በማንሳትና ሰውን በማምጣት ብዙም ለውጥ ማምጣት አይቻልም።

ዋናው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው። የመሬት አገልግሎት አደረጃጀቱ ችግር እንዳለ ሆኖ ዋናው ጉዳይ ከእጅ ንክኪ ነጻ እንዲሆን ማድረግ ነው። ማንዋል በሆነው አሰራር ከፍተኛ ችግር የሆነው ፋይል መደበቅ፤ ለፋይል

 ማውጫ እጅ መንሻ መጠየቅ እና መሰል ችግሮች ስላሉ ወደ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማምጣት ሁሉም መረጃ ሙሉ በሙሉ ስካን የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁንም ከአመራሩ ጋር ተያይዞ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታዎች ይነሳሉ፤ አመራሩ ችግሩን በልኩ ተገንዝቦ ለማስተካከል ምን ሰርቷል?

አቶ ታረቀኝ፡- ችግሮችን ለመፍታት ዋናው ጉዳይ አመለካከት ነው። ከዚህ ችግር ውስጥ እንድንገባ ያደረገን የአመለካከት ችግር ነው። ሰው አገልጋይ ነኝ፤ ነጻ አገልግሎት እሰጣለው ብሎ በቅንንት ወደ ስራ ከገባ ምንም ችግር የለውም። ስለዚህ የመሬት ልማት አመራሮችን እንዲስተካከሉ ተደርጓል።

ከዘርፎች ቀጥሎ ቡድን መሪዎች አሉ፤ ቡድን መሪዎችን ከተማ አስተዳደሩ ለማስተካከል ኦዲት እያደረገ ነው። የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ እየወጣ ስለሆነ ችግር ያለባቸው ሰዎችንና ችግር የሌለባቸውን ነጥረው እንዲወጡ ተደርጓል። እናም ችግር ያለባቸው ከመሬት ጽሕፈት ቤት እንዲወጡ የሚደረጉ ሲሆን፤ የሌለባቸው ደግሞ ይቀጥላሉ።

አዲስ ዘመን፡- አገልግሎቱን በማዘመን በኦንላይን ለመስጠት የባለሙያውና የአመራሩ ቁርጠኝነት እስከምን ድረስ ነው?

አቶ ታረቀኝ፡- ዋናው የአመለካከት ችግር ስለሆነ ባለሙያዎች የመስራት ፍላጎታቸው በጣም አናሳ ነው። አመራሩም ይህን በደንብ በመያዝ በማንዋል አገልግሎት መስጠት አትችሉም ብሎ አቋም ይዞ ማስተካከል ላይ ችግር ነበር። ከመጀመሪያም ሲስተሙ ከተመረቀ ጀምሮ ስካን ሆኖ ለአገልግሎት ብቁ የሆኑ ፋይሎች አሉ። ባለው በተነሳሽነት አገልግሎት መስጠት ቢጀምር የቀረውም በተፈለገው መንገድ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት መግባት ይቻል ነበር። ነገር ግን ከፍላጎት ማጣት ስለመጣ ችግሩ ውስብስብ እንዲሆንና ለሌብነትና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ እንዲሆን በር ከፍቷል።

መረጃዎችን ስካን በማድረግ ሙሉ በሙሉ ወደ ሲስተም እንዲገባና በኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን፤ ይህም ሌብነትን ይከላከላል። አገልግሎት ፈላጊውም ፋይል ጠፋ ከሚለው አላስፈላጊ እንግልትና ወጭ እንዲድን ያደርጋል። ከዚህም በላይ ዋና ስራ አስፈጻሚውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ባለሙያ ምን እየሰራ እንደሆነ ለመከታተል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ለምሳሌ፣ በክፍለ ከተማው አንዱ ችግር የሆነውን የመሬትና መሬት ነክ ጉዳይ ለመፍታት ዋናውና አንዱ መፍትሔ ሁሉም የመሬት ነክ አገልግሎት ወደ ሲስተም ማስገባት ነው ብለን እየሰራን ነው። እስካሁንም ከእጅ ንክኪ የጸዳ እንዲሆንና ያለው ፋይል ስንት እንደሆነ ልየታ ስራ ተሰርቷል። ሲስተሙ በተመረቀበት ወቅትም ወደ 37ሺህ የሚሆን ፋይል ስካን ተደርጎ ገብቷል።

አዲስ ዘመን፡- አገልግሎት አሰጣጡን ያዘመናል፤ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ይቀርፋል ተብሎ ታስቦ እየተሰራበት ያለው የኦንላይ አገልግሎት ችግሩን ምን ያህል ቀርፏል?

አቶ ታረቀኝ፡- መረጃዎች ስካን ተደርገው ለኦንላይን አገልግሎት መዘጋጀታቸው ለስራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

 ነገር ግን ዋናው ችግር የነበረው የማስቀጠሉ ጉዳይ ነው። ያለውን ፋይል ለይቶ ምን ያህል ፋይል እንዳለ ማሳወቅ አለመቻልም ሌላው ችግር ነው። ለምሳሌ፣ ሲጠየቅ የተወሰነው 54ሺ ሌላው ደግሞ 64ሺ ይላል። ሆኖም ይሄ ሰበብ ነው እንጂ የሚደበቅ ነገር የለም።

ከዛ ውጪ ለዚህ ፍላጎት አለማሳየት ባለሙያው ጋር ያሉ ችሮች ናቸው። ሆኖም አሁን ዋናውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ የሚታሰበው ያለው የፋይል ብዛት ታውቋል። አዲስ ሲገባም እንዴት እንደሚገባ አሰራር ይበጃል። ፋይሉ ከታወቀ ደግሞ በውጭ ፋይል ማደራጀትና እንደፈለጉ ማስገባትና ማስወጣት አይቻልም። ባለቤት ይኖረዋል፤ በመሆኑም ሲስተሙ በዚያ ደረጃ በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ይቀርፋል።

አዲስ ዘመን፡- መረጃው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ሲሰጥ በመሬት ላይ እየተስተዋለ ያለውን ሌብነት መቅረፍ ያስችላል?

አቶ ታረቀኝ፡– ኦንላይንም ቢሆን የሚሰራው በሰው ነው። ስለሆነም ሰው አመለካከቱ ካልተቀየረ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ አይስተካከልም። ነገር ግን የተጋላጭነት መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ለምሳሌ፣ ፋይል ጠፋ የሚባል ወሬ አይሰራም። ለክትትልም ምቹ ስለሆነ አመራሩ የሚሰጠው አገልግሎት ኦንላይን ላይ ስለሚከታተል የቱ ጋር ችግር እንዳለ መለየት ይቻላል። ለማስተካከልና ለመገምገም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው በርካታ ቤቶች ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የላቸውም፤ በዚህ ሳቢያም ለብልሹ አሰራር በር ከፍቷል ተብሎ ይነሳል። ቤቶቹን መመሪያንና ሕግን በተከተለ አግባብ ከማስተዳደር አንጻር ምን ታቅዷል?

አቶ ታረቀኝ፡- የመሬት አገልግሎት አካባቢ ችግሮች አሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ሁሉም አግባብነት ያለውና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መረጃ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር መለየት አስፈላጊ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ የጣሪያና ግድግዳ ግብር ለማስከፈል እንኳን ምቹ ሁኔታ አይፈጥርም። አሁን ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል በዕቅድ ተይዟል። የአርሶ አደሮችም ተለክቶ ካርታ ያገኙ አሉ። ተለክቶ ደግሞ ከለውጡ በፊት ካሳ በልተዋል ተብሎ እየተጣራ ያለም አለ። በዚህም የካሳ ልዩነት መከፈል ያለበትን ለመክፈል ሕጋዊ እንዲሆኑ እተሰራ ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ልኬት ያልወሰዱ እንዲወስዱ፤ ልኬት ወስደው ሁሉንም ነገር ጨርሰው በካሳ አከፋፈል ላይ ተከፍሏል ተብለው የቆዩም የወሰዱትን ወደ ሕግ አግባብ የማስገባት ስራ ይሰራል። ይህ ሲሆን ሕገ ወጥነትን ይከላከላል፤ የመሬት ወረራን ተጋላጭነም ይቀንሳል። ይህን ለማድረግ ከተማ ግብርና እና መሬት ጽህፈት ቤት በቅንጅት እየሰሩ ነው። ካርታ የሌላቸው ግለሰቦች የራሳቸው ይዞታ ከሆነና ይዞታቸው ነው ተብሎ ከተረጋገጠ ካርታ የሚሰጥበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ መልኩ የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ ያለባቸው ቦታዎች እየተመለሱ ይሄዳሉ።

አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማው በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉበት እንደመሆኑ የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከመፍታት አንጻር ምን ታስቧል?

አቶ ታረቀኝ፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የመንገድ፤ የውሃና የመብራት ብዙ ጥያቄዎች አሏቸው። ችግሩን ለመፍታት ከመንገዶች ባለስልጣና ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጋር ውይይት ተደርጓል። ያስቸገሩን በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይቶች ውስጥ አርሶ አደሮች እርሻ እያረሱ፤ ካሳ ይገባናል የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ ነው።

ይህም የተፈጠረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት ላይ መሬት ፆም ማደር የለበትም የሚለው ሀሳብ ሲተገበር ተመልሰው ገብተው ማረስ የጀመሩ አርሶ አደሮች በጊዜ ቆይታ የባለቤትነት ጥያቄ ፍላጎት የመጣ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ቦታዎች በመነጋገርና በመተማመን እየወጡ ነው። መንገድ እንዲሰራ ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በተደረገው ውይይት መሰረት መንገዶች እየተሰሩ ነው። በቀጣይ ይህን የማወያየትና የመተግበር ስራ ከስራ አስፈጻሚው የሚጠበቅ ነው።

አንዴ ካሳ ተቀብለዋል፤ መሬቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት በመሆኑ ሁለተኛ ካሳ የሚከፈልበት አግባብ የለም። በሌላ በኩልም አንዳንድ ኮንትራክተሮች ያለመስራት ፍላጎት አላቸው። መንገዶች ባለስልጣንና ክፍለ ከተማው በማያውቀው ሁኔታ አርሶ አደሮችን የእኔ ነው በልና ከዚህ እንወጣለን የሚል ሀሳብ ያነሳሉ። ይህ ችግር እንዳይደገም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተቋራጮች ላይ እርምጃ እንዲወስድና እንዲስተካክሉ መግባባት ላይ ተደርሷል። ያሉ ችግሮችን ሁሉ በሚገባው ልክ ችግሩን ተረድቶ የራሱን የቤት ስራ በመስራት እንዲቀረፍ የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ስራ እንዲሰራ ማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሕገ ወጥነት ተስፋፍቷል፤ የወንጀለኞች መደበቂያ እየሆነ ነው የሚል ሀሳብ ይነሳልና እርሶ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ታረቀኝ፡- ይህ ጉዳይ በእኛ የሚጣራ አይደለም። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤቶችን የሚሰጠው የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ነው። ሕገ ወጦች የሉም ማለት አይደለም። ከወንጀል አንጻር ግምገማ ተደርጎ በአካባቢው ባሉት ሁለት ሳይቶች ላይ የስርቆት ወንጀል መኖሩ ታውቋል። ስርቆቱ ከውጭ ነው ከውስጥ የሚለውን ከዛው ያሉ ጠባቂዎች ስላሉ እነሱ እያሉ ለምን ወንጀሉ እንደሚፈጸም መገምገም ያስፈልጋል።

ከውጭ ከሆነ ደግሞ እንዴት መግባት ቻሉ የሚለውን ወረዳ አመራሮች ባሉበት ተገምግሟል። በዚህም በተለይም በአካባቢው በጫኝ አውራጅ ላይ የሚስተዋል ከአቅም በላይ የመጠየቅ እንቅስቃሴ ላይ ሰፊ እርምጃ ተወስዷል። ይህን ስራ የሚሰሩትን ወረዳ አደራጅቶ ስላስገባ ኃላፊነቱን ወስዷል።

የጸጥታ ስራውን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያና ሰላምና ጸጥታ ከወረዳዎች ጋር ኃላፊነቱን ወስዷል። የመሰረተ ልማት እንደ ምክንያት ከተነሳም፣ ወሰን ከተከበረላቸው በኋላ በቶሎ መንገዱን የመክፈትና የመስራት ኃላፊነት የመንገዶች ባለስልጣን ነው። ከዛ ውጪ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያሉ ስርቆቶችን ቤቶች እንዲመለከቱና ራሳቸው እንዲያስተካክሉ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

አዲስ ዘመን፡- ለቤተ እምነቶች የሚውሉ ግንባታዎች መበራከታቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን አመራሩ እንዴት ይመለከተዋል?

አቶ ታረቀኝ፡- ከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ወስኖ ለሁሉም ቤተ ዕምነቶች ሕጋዊ ቦታ ተሰጥቷል። ሆኖም ከተሰጣቸው መሬት አልፎ የማጠር ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው። ይህን ችግር ለማስተካከል ስራ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ሁለት ቦታዎች አራት ሺህ ካሬ ሜትር የተሰጠው አንድ ቤተ ዕምነት ስምንት ሺ ካሬ ሜትር ጨምሮ አጥሮ ተገኝቶ በተቋቋመው ግብረ ኃይል እርምጃ ተወስዶበታል።

ሆኖም በመሬት ከተሰጣቸው በኋላ እላፊ መሬት ለማግኘት አንድም ከአርሶ አደሩ ጋር በመነጋገር ሌላም በጉልበት ያጥራሉ። ቤተ ዕምነትን ሽፋን በማድረግ ግልጽ የሆነ የመሬት ወረራ ፍላጎቶች አሉ። ማንኛውም ግለሰብም ይሁን የዕምነት ተቋም ከሕግ በላይ ሊሆን ስለማይችል ሕገ ወጥነትን በምንም መልኩ አንታገስም።

በዚህ ረገድ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሰላም ሰራዊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ እየተሰራ ነው። ከመስከረም ወር ጀምሮ በተደራጀ መልኩ በመሰራቱ ሕገ ወጥነት የለም። ደንብ ማስከበር ብሎክን መሰረት ያደረገ ስምሪት ወስዶ እየሰራ ሲሆን፤ በተመደቡበት አካባቢ ችግር ተፈጥሮ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናሉ። በተጨማሪም በየብሎኮች የወረዳ አመራር ምደባ ተደርጎ ክትትል ያደርጋሉ። ማንኛውም ግለሰብ ከምንም ተነስቶ በሕገ ወጥ መንገድ መሬት አያጥርም፤ አንዳንድ ነገሮች ከጀርባው ስላሉ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማው ከሪል ስቴት አልሚዎችና ከአንዳንድ ድርጅቶች ጋር ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ አርሶ አድሮች ክስ ውስጥ መሆናቸውን አስተዳደሩ ያውቃል?

አቶ ታረቀኝ፡- በአብዛኛዎቹ ላይ እውቅናው ስለሌለኝ ሀሳብ አልሰጥበትም። እስካሁን ወደ እኔ የመጡ ሰዎችም የሉም። አርሶ አደሮች አካባቢ ያለው አንዳንድ ጉዳዮች አብዛኛው ቦታው ለልማት ሲፈለግ የካሳ አከፋፈሉ ሁኔታና የገንዘብ ችግር ሊኖር ስለሚችል የመተማመኛ ደብዳቤ ይሰጣል። ሂደቱ ካለቀ በኋላ ካሳ ይከፈላል። ጥያቄው እውነትም ውሸትም ሊሆን ይችላል። እውነት ከሆነ መጥቶ መጠየቅ ይችላሉ። መሬታቸው ያለምንም ካሳና ምትክ መወሰድ የለበትም። መገፋት ከሆነ ከለውጡ በፊት የተገፉት በቂ ነው።

ያልተከፈለ ካሳ ካለ በሕግ አግባቡ ጠይቆ እንዲከፈል እናደርጋለን። ሪል ስቴት አልሚዎች ጋር የመካሰስና የመጋጨት ሁኔታ አለ። ይህም ሪልስቴት አልሚዎቹ አልፈው የመውሰድ ፍላጎትና በቂ ካሳ ያለመክፍል ችግር ሁኔታ አለ። ከአያት ሪልስቴት ጋር ያለውን ለመፍታት ኮሚቴ ተደራጅቶ ችግሩ የቱ ጋር እንደሆነ ለመለየት ወደ ስራ ተገብቷል። ችግሮች የአርሶ አደሩም ይሁን የሪል ስቴቱ ማስተካከል ኃላፊነት ያለበት የመንግስት ስለሆነ የካሳ ጉዳይን በአሰራሩና በሕግ አግባብ የሚመለስ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው እየተከናወነ ላለው የጫካ ፕሮጀክት የልማት ተነሺዎች አርሷደሮች ከካሳ ክፍያና ከልማቱ ተጠቃሚነት አኳያ ቅሬታ ያነሳሉ፤ ይህን በተገቢው ሁኔታ ከማስተናገድ አንጻር ምን ይላሉ?

አቶ ታረቀኝ፡- 166 የሚሆኑ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች ጫካ ፕሮጀክት ውስጥ ገብተዋል። ጫካ ፕሮጀክቱ ብዙ አርሶ አደሮችን ገፊ ሳይሆን አቃፊ ነው። ይህን የምንልበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ በቂ የሆነ ካሳ ነው የሚከፈለው። ምትክ ቦታም ይሠጣቸዋል። ሦስተኛ ደግሞ የጫኝና አውራጅ ሌሎች ነገሮችም የአንድና የሁለት ዓመት ኪራይ ይሠጣል። እስካሁን ድረስ 35 ሰዎች መጥተው አልወሰዱም እንጂ ካሳ ተሠርቶ ተቀምጦላቸዋል።

ምትክ ቦታን በሚመለከትም ከዚህ በፊት ታይቶ ነበር። አንድ አካባቢ ቢሆኑ፤ ማሕበራዊ መሠረታቸው እንዳይበታተን ተመልሳችሁ እዩ ብየ ነበር። በዚህ መሰረት አንድ ቦታ ተደራጅቶላቸዋል። ቦታቸውም ይሰጣቸዋል። ይህንንም በቶሎ እናስተካክላለን። በጥቅሉም የምትክ ቦታና ካሳ ጉዳይ ላይ ተማምነው ፈርመዋል። በመግባባት ነው ሁሉም ነገር ያለቀው። የመዘግየት ችግር ብቻ ነው ያለው። ይህንንም አፋጥነን ወደ ስራ አስገብተናል።

አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማው ብዙ ጊዜ ስሙ በጥሩ አይነሳም። ስሙን ቀይሮ ሞዴል ክፍለከተማ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ታረቀኝ፡- ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ላይ እንደ ችግር የሚነሳው መሬት ነው። የመሬት ጉዳይን ለማስተካከል ደግሞ ከከንቲባዋ ጀምሮ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። ሪፎርም የማድረግ ስራዎችም ተጀምረዋል። ጉዳዩ የለሚ ኩራ ብቻ ስላልሆነም ከተማ አቀፍ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው። በዚህም እንደ ክፍለ ከተማ እናስተካክላለን የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ ውጪ ክፍለ ከተማው በትምህርት፤ በጤናው ጉዳይ፤ በሕብረተሰብ ተሳትፎ፤ ከፕሮጀክት አፈጻጸም አኳያ በጣም ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የክፍለ ከተማው ሌላኛው ችግር ለሚዲያው ክፍት አለመሆን ነው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ታረቀኝ፡– ትክክል ነው። በክፍለከተማው አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ተብሎ ከተገመገመው ውስጥ የኮሙኒኬሽን ችግር ይገኝበታል። በውስጣችንም ማለት ነው። እኛም የራሳችን ሚዲያ አለን፤ የፓርቲ ሚዲያም አለ። አመራሩም በራሱ ኮሚኒኬተር መሆን አለበት። ከዚያም በተጨማሪ ለሚዲያው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ያለን መረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው። ያለን ዳተኝነት ማቆምም ይገባል።

መስራት እንጂ የተሰራውን ማሳወቅ ላይ በጣም ችግር አለብን። ለምሳሌ አመራሮች የተለያዩ ክልሎች ላይ ሄደው ጉብኝት እያደረጉ ነው። ላልሰማው ብናሰማ የተሰሩ ስራዎች እንዲታዩ ይሆናሉ፤ ሕዝቡ ውስጥ ተስፋ ይኖራል።

አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ እናመሰግናለን።

አቶ ታረቀኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሞገስ ተስፋ እና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You