ለአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት፤ ልማት እና ብልጽግና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለንተናዊ አበርክቶ ከፍ ያለ ነው። ከሁሉም በላይ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚኖራቸው የጋራ ኃላፊነት መተኪያ የሌለው ነው፤ የስኬታማነታቸው ዋነኛ መመዘኛም ይህንኑ ኃላፊነታቸው በአግባቡ የመወጣታቸው እውነታ እንደሆነም ይታመናል።
በተለይም ለረጅም ዘመናት አምባገነናዊ በሆኑ የፖለቲካ አስተዳደሮች ውስጥ ያለፉ፤ በዚህም ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ ሕዝቦች፤ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያደርጓቸው የሽግግር ጉዞዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህም ልዩነትን የሚያሰፉ፤ ቁርሾና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ትርክቶች ወጥተው፤ እንደ ሀገር ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ፤ ሕዝቡ የለውጥ አስተሳሰቦችን ተቀብሎ ዋነኛ የለውጥ ኃይል የሚሆኑበትን የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት፣ አስተሳሰባዊ ልዕልና እና ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።
ትናንቶችን ከውዥንብሮች ማጥራት፤ ከጠሩ ትናንቶች መማር፤ ዛሬን የተሻለ፤ ነገን ደግሞ ባለ ብዙ ተስፋ ማድረግ የሚያስችል አዲስ ለውጥ ተሸካሚ ትርክት መፍጠር፤ በዚህ ትርክት የተፈጠረና የተገዛ አንድ ሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ።
ይህም እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብም ሆነ የማኅበረሰብ ክፍል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ፤ እንደ ሀገር ለሁሉም ዜጎች ለኑሮ የተመቸች ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ትልቅ አቅም የሚፈጥርላቸው ነው ።
በተለይ እንደኛ ባሉ፤ ብሔራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ የተዛቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትርክቶች በበዙባቸው፤ በተዛቡ ትርክቶች ምክንያት ሰላምና መረጋጋት እያጡ ባሉ ሀገራት፤ አንድ ሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች በብዙ ፈተናዎች የተሞሉ ስለመሆናቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ከሁሉም በፊት እነዚህን ትርክቶች ማጥራት ወሳኝ ነው፤ ትርክቶችን በማጥራት ሂደትም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ፤ ትናንቶችን በሁለንተናዊ መልካቸው ተገንዝቦ፤ ለዛሬ ሀገራዊ የልማትና የብልጽግና ጉዞ አቅም ፤ ለነገ ደግሞ የተጨባጭ የተስፋ ምንጭ የሚሆኑበትን ዕድል መፍጠር ይኖርባቸዋል ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ትናንቶችን የማጥራትና የማከም ሁኔታ ከአሁናዊ የሥልጣን ጥያቄ ያለፈ ሀገርን የማቆምና የማጽናት አጀንዳ መሆኑን መረዳት፤ ይህንኑ አጀንዳ ከየትኛውም ሀገራዊ አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ እና ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊከናወን እንደሚገባ ሊያጤኑት ይገባል።
የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት ለዚህ ሀገራዊ አጀንዳ ቅድሚያ በመስጠት የቀደሙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትርክቶቻችንን ማጥራትና ማከም እንችል ዘንድ ነፃ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አዋቅሯል ። ኮሚሽኑም ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ተስፋ ሰጭ መንገድ ላይ ይገኛል።
እንደሚታወቀው፤ ኮሚሽኑ ሲቋቋም አብረውት ለመሥራት ፈቃደኛነታቸውን ያሳወቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ሦስት ነበር፤ ይህ አኃዝ ደግሞ ብዙዎችን ያሳሰበ እንደነበር የሚታወስ ነው ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት ከነበራቸው አዎንታዊ አስተዋፅዖ አንጻር በርግጥም መረጃው አስደንጋጭ ነበር ፤ ይሁንና ኮሚሽኑ ደረጃ በደረጃ ባከናወናቸው ሥራዎችና በፈጠረው ቅርርብ በአሁኑ ጊዜ በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ 47ቱ ከኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመሥራት የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራርመው እየሠሩ ነው፡፡
በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ትናንቶችን በማጥራት፤ ከትናንት ተገቢውን ትምህርት ወስዶ ዛሬ ላይ አዲስና ዘመኑን የሚዋጅ የፖለቲካ ሥርዓት እና እሱን የሚሸከም ትርክት በውይይት/በንግግር ለመፍጠር የደረሱበት ድምዳሜ ከፍ ያለ ዕውቅናና ከበሬታ የሚሰጠው ነው። እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብና የማኅበረሰብ ክፍል ከዚያም በላይ ለጋራ ለሆነችው ሀገራቸው ብሩህ ነገዎች ያላቸውን ቀናኢነት ያመላከተ ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም