የቡና ሰንሰለት ተዋናዮችን ወደፊት ለማራመድ!

 ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ነች። ለፈጣሪ ምስጋና ይግባውና ለቡና ተስማሚ የሆነ ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአየር ንብረት ችሯታል። ወደ 90 በመቶ የሚጠጋው የኮፊ ዐረቢካ ዝርያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን እየተካሄዱ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ገና ተጨማሪ ዝርያዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። ምርቱ የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ከመሆን ባለፈ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ኑሮም ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

አሁን ላይ የቡና የምርት ሰንሰት ውስጥ፤ በመበጠስ፤ በመልቀም፤ በማጓጓዝ በመገበያየት፤ በማቀነባበር እንዲሁም በጥሬውም ሆነ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በመላክ 20 ሚሊዮን የሚያህሉ ዜጎች ኑሯቸውን መሰርተዋል። ከእነዚህ ዜጎች መካከል አብላጫውን ቁጥር የያዙት ሴቶች ናቸው። ሙያውን በቀለሙ ትምህርትም ሆነ በልምድ ደህና አድርገው እንዳካበቱትም በተጨባጭ በመስክ የሚታይ እውነታ ነው።

ተሳትፏቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ አሁን ላይ ከ75 በመቶ በላዩን የሚሆነውን እንደያዙት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ሆኖ ግን አሁን ድረስ እንደተሳትፏቸው በዘርፉ እየተጠቀሙ አይደለም። በተለይም ከፍ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።

ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቡናን ወደ ውጭ በመላኩ በኩል የሚሳተፉት ሴቶች ቁጥር ከ10 በመቶ አይበልጥም። አብዛኞቹ ሴቶች ታች ካለው ከለቀማ ጀምሮ በትንንሽ የቡና እሴት ሰንሰለት ሥራዎች የሚሳተፉ ናቸው።

ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሯቸውም ዋናው ተግዳሮት የካበተ የፋይናንስ አቅም አለመኖር ነው። ይህንን አቅም ለማካበት የቱንም ያህል ቢጥሩም በመስኩ ጥቂት ወንዶች የደረሱበት እድገት ማማ ላይ የመድረሱ ጉዳይ ሊሳካላቸው የቻለ አይደለም። ችግሩን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት መፍታት የሚያስችል ዕድል ቢኖርም በተቋማቱ የሚታየው ቢሮክራሲ ተጨባጭ ሊያደርገው አልቻለም።

በዘርፉ ሰፊ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ አንጋፋውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ በሀገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ባንኮች ገንዘብ የሚያበድሩት ትልልቅ ሕንፃ ላላቸውና በቂ ሀብት ላካበቱ ባለሀብቶች ብቻ ነው።

በቡና ላይ ዕውቀት ኖሯቸው በዚሁ ዕውቀታቸው ለሀገራቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ለሚችሉ በዘርፉ ለተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች አይደለም። እነዚህ ሴት ነጋዴዎች ለባንኮቹ ጥያቄ የሚሆን ሀብት የሌላቸው በመሆኑ በዘርፉ የማደግ ህልማቸውን እየቀጨጨ ሄዷል።

ዘርፉ ትልቅ የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ መሆኑ፤ ከተከላ እስከ ለቀማ ያለው ሂደት ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የሚወስድ መሆኑ፤ በዘርፉ ያለውን የሴቶች ኢንቨስትመንት በእጅጉ ፈታኝ አድርጎታል። በዚህም በህልማቸው ልክ በዘርፉ ተሰማርተው የሚጠብቁትን ጥቅም ማግኘት አልቻሉም።

አብዛኞቹ በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ህልም ቡናን በሰፋፊ እርሻ ላይ የማልማት፤ ለውጭ ገበያ ማቅረብ በዚህም ከፍተኛ የዕድገት ማማ ላይ መውጣትና የሀገራቸውን ስም ማስጠራት ቢሆንም በገንዘብ እጦት ህልማቸው መክኗል።

በአጠቃላይ በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች፣ የንግድ ተቋም ባለቤቶችና መሪዎች በተደራረቡ ችግሮች እየተፈተኑ ያሉ ናቸው።

ችግሮቻቸው ከብድር አቅርቦት፣ ከወለድ ምጣኔና ከእፎይታ ጊዜ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር በመሆናቸው ፈተናውን በእጅጉ አበርትተውባቸዋል።

ለሥራቸው የሚያስፈልጓቸውን ሥልጠናዎች በበቂ ሁኔታ ከማግኘት ጋር የተገናኙ ተግዳሮቶቻቸውም ብዙ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የመረጃ ተደራሽ አይደሉም። ይህም ባሰቡት ልክና ፍጥነት ተቋሞቻቸውን እንዳያሳድጉና በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ትልቅ ማነቆ ሆኖባቸዋል።

በቅርቡ በስካይላይት ሆቴል የተከፈተውና በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የሀገራችን ሴቶችን ያሳተፈው የቡና ኮንፈረንስ ይሄንን ችግራቸውን ይፈታል ተብሎ ታምኖበት ሲካሄድ ቆይቷል።

ኢንተርናሽናል ውመን ኢን ኮፊ አሊያንስ ቻፕተር አባል በሆነው ውመን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማኅበር ሃሳብ አመንጪነትና አስተባባሪነት የተዘጋጀው ኮንፈረንሱ በፋይናንስ ተግዳሮት ሳቢያ በሥራቸው ለውጥ ባለማምጣት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንቅስቃሴ ያሉ ሴቶችን በመታደግ ረገድ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ነው።

በርግጥ ሴቶች በመረጡት መስክ መሥራት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው መብቶቻቸው ከተከበሩላቸው፣ ችግሮቻቸው ከተቀረፉላቸው፣ ጥረታቸውን ካበረታቱላቸው፣ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ተገቢው ዕውቅና ከተቸራቸው ፈጣን ለውጥም ያመጣሉ።

ያላቸውን እምቅ አቅምና ተሰጥዖ፤ እውቀትና ክህሎት በሚገባ አውጥተው በመጠቀምም የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ከመለወጥ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥና ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። ይህንን ታሳቢ በማድረግም፤ በመንግሥት በኩል በኢኮኖሚው መስክ ሴቶችን ለማብቃት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ለሴቶች መብት መከበር ብሎም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብሎ ማጽደቁ ለዚሁ ማሳያ ነው።

በኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩልም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፓኬጆችና ሌሎች የማስፈጸሚያ ስልቶች ተቀርፀዋል። ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩም ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ከዚህ ባሻገርም መንግሥት የተቀረጹት ሀገራዊ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎች ስኬታማ እንዲሆኑ የደጋፊነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ሆኖም እንስቶቹ በመስኩ እየገጠሟቸው ያሉ የፋይናንስና ሌሎች ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በመንግሥት ብቻ የሚደረግ ጥረት በቂ አይደለም። በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮችን ጨምሮ የልማት አጋራት፣ የግል ባለሀብቶችና የሌሎችንም የጋራ ትብብርና ርብርብ ይጠይቃል።

ከዓለም የተውጣጡ 33 ሀገራት የተሳተፉበትን ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ዓላማም ይሄ እንደሆነ ውመን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማኅበር መረጃ ያሳያል። ማኅበሩ የኮንፈረንስ ዝግጅት ሃሳቡን ያመነጨና የተገበረው በብዙ ምክንያት ነው።

አሁን ላይ በመስኩ እየታየ ያለውን መልካም ጅማሮ ዘላቂነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ፍትሐዊ ተሳትፎና የላቀ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን፤ በዚህም የሴቶች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ብሎም ሴቶች ለማኅበረሰባቸውና ለሀገራቸው ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚጠበቅባቸውን ወደር የለሽ ሚናቸውን በሚገባ እንዲጫወቱ ማስቻል ቀዳሚው ትኩረቱ ሊሆን ይገባል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You