ኤርትራ ለግብጽ ወታደሮች መስፈሪያ መሆኗን ተከትሎ የግብጽ መንግሥት ወደ ኤርትራ ድንበር ወታደሮቹን ማስጠጋቱ እና ድንበር መዝጋቱ በቀጥታ ከቱርክ ፍላጎት የመነጨ ውጥረት ነበር። ስለዚህም ኤርትራ ከቱርክ ጋር የነበራት ግንኙነት እንዲሻክር በር ከፍቷል።
ቱርክ በኤርትራ ሙስሊም ሊቃውንት እና በኤርትራ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መነሻ በማድረግ እጇን ለማስገባት ፈጥናለች። ቱርክ ለሙስሊም ወንድማማቾች ቅርበት አለው የሚባለውን የኤርትራ ሙስሊም ኡላማ ሊግ በኢስታንቡል ቢሮ ከፍቶ እንዲሠራ በጥር 2019 ላይ ማስጀመሯ ነገሩን የተካረረ እንዲሆን አድርጎታል።
በዚህም ምክንያት የኤርትራ ነፃነት ካገኘችበት ከ1991 /እ.ኤ.አ/ ጀምሮ የነበረው እና ቱርክ ኤምባሲዋን በአሥመራ በ2013 /እ.ኤ.አ/ በከፈተችበት ጊዜ የበለጠ ተጠናክሮ የቆየው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ፈተና ውስጥ ገብቷል።
ቱርክ እና ኤርትራ የንግድ ግንኙነታቸውን እያሳደጉ የቆዩ ሲሆን፣ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ዓመታዊ የግብይት መጠን ላይ ደርሰው ነበር። ቱርክ የኤሌክትሮኒክስ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስን፣ የምግብ ምርቶችን እና ጨርቃ ጨርቅ ወደ ኤርትራ ታስገባለች። ከትብብር አንፃርም ቱርክ ለኤርትራ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ስኮላርሺፕ በመስጠት የሰው ኃይል ልማት ላይ ስታግዝ ቆይታ ነበር።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011