የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በአዲስ አበባበ ከተማ ‹‹በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ መልዕክት የፊታችን ቅዳሜ ለአስራ ሦስተኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን ብሄረሰባዊ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጣጥሞ በመሄድ ረገድ ክፍተቶች እየተስተዋሉ መጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ የኔሁን ብርሌ ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሕብረ ብሔር ሀገራት ከሀገራዊ እና ከብሄረሰባዊ ማንነት አንዱን ብቻ መምረጥ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከደርግ በፊት በነበረው የሀገር ግንባታ ሂደት ብሄረሰባዊ ማንነት ተጨፍልቆ ሀገራዊ ማንነት እንዲንጸባረቅ ትልቅ ጥረት ተደርጓል የሚሉት የሕግ መምህሩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማግዘፍ አንድ ቋንቋ ፣አንድ ባህል እና አንድ ሀገር የሚሉ አስተሳሰቦች ሥራ ላይ ውለው ነበር ይላሉ፡፡
ሆኖም ግንባታው ግቡን ሳይመታ ሀገራዊ ግንባታ የሚባለው ነገር የአንድ ወይም የተወሰኑ ብሔሮችን የበላይነት በሌሎች ላይ ለመጫን ነው ተብሎ ስለታሰበ የብሔር ግጭቶች ከመነሳታቸው አልፎ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች እንዲመጡ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ከኃይለ ሥላሴ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ በደርግ ዘመን በብሔር የተደራጁ አካላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን የሚገልጹት አቶ የኔሁን፤ በብሔር ተደራጅቶ ፖለቲካ መስበክን የትግል መስመር ማድረግ የተማረውንም ያልተማረውንም በቀላሉ በመሳብ ቶሎ ውጤት የሚያስገኝ ስልት በመሆኑ በተለይ በደርግ ዘመን በጣም አቆጥቁጦ በትግራይ፣ በኦሮሚያ ፣ በደቡብ እና በብዙ ቦታዎች ተስፋፍቶ ነበር ይላሉ፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላም ኢህአዴግ የትግላችን መነሻ የብሔር ጭቆና ነው ብሎ ስላሰበ ብሔረሰባዊ ማንነትን በማግዘፍ ተጠምዶ መቆየቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ብሄረሰባዊ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጣጥሞ መሄድ ያልተቻለው ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በተሠራ ሥራ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም እኛ የምናውቀው ሁሌ ከዜሮ መጀመርን እና አንዱን ጽንፍ መያዝን ነው፡፡ ፖለቲካችን ማቻቻል አያውቅም ብሔር ሲባል ብሔርን ብቻ የሚደግፍ በሌላ በኩል ደግሞ የለም የብሔር ፖለቲካ ያጠፋናል ብሎ ጀርባውን የሚሰጥ ነው ያለው ይላሉ፡፡
‹‹አሁን የደረስንበት ደረጃ በአንድ ቀን የተሠራ አይደለም›› የሚሉት አቶ የኔሁን ስልጣኑን እና ሚዲያውን ይዞ በቆየው አካል በተካሄዱ በአንዳንድ እውነትነት ባላቸው በብዛት ግን ውሸት በሆኑ ሰበካዎች እዚህ ደርሰናል ባይ ናቸው፡፡ ብሄረሰባዊ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጣጥሞ መሄድ እንዲቻል መጀመሪያ ሰው ነኝ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ያሉት መለያዎች ብሔር እና ዜግነት ብቻ አይደሉም ይላሉ፡፡
እንደ አቶ የኔሁን ማብራሪያ፤ በተለይ የሃይማኖት አባቶች ሰው በሃይማኖቱ ግብረ ገብ ሆኖ ተለውጦ የሚኖርበትን መንገድ መስበክ አለባቸው፡፡ ሕፃናትን በግብረ ገብ ትምህርት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ሚዲያዎች ኃይል ካለው አካል ጋር መወገን ትተው ገለልተኛ በመሆን ብሄረሰባዊ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጣጥሞ መሄድ እንዲቻል ትልቅ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በመቋቋም ላይ ያሉት የወሰን እንዲሁም የዕርቅ እና የሰላም ኮሚሽኖች በትክክል ሊሠራባቸው ይገባል፡፡
ከፖለቲካ ነፃ እንዲሆኑም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት የብሔር ማንነትን የሚያጠፋ አለመሆኑን የብሔር ማንነትም ኢትዮጵያዊነትን ጨርሶ የሚውጥ አለመሆኑን በዘመቻ ሳይሆን ወጥነት ባለው መልኩ በማስገንዘብ በተደጋጋሚ በሚሠራ ሥራ ሁለም የድርሻውን ሲወጣ በሚቀጥሉት ሃያ እና ሠላሳ ዓመታት ሁለቱን ማንነቶች አቻችለን መሔድ እንችላልን፡፡
በአሰላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የፖለቲካው ምህዳር ከ1983 ዓ.ም በኋላ በብሔር ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ እና በሕገ መንግሥቱም ሥልጣን የብሔር ብሄረሰቦች መሆኑ መደንገጉ ቀደም ሲል ከነበረው ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ጋር ግጭት ፈጥሯል፡፡ ሁለቱ ማንነቶች ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ መሆናቸውን ከሚያምነው አስተሳሰብ በተጻራሪ አዲስ የተነሳው ኃይል ብሔርን መሰረት ላደረገ አደረጃጀት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ እና ቀደም ሲል የነበረው የኢትዮጵያዊት አስተሳሰብ ለብሔር ብሔረሰቦች ቦታ ያልሰጠና ፋይዳ ያላስገኘ ተደርጎ እንዲቀርብ በመደረጉ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ተደፍቆ ቆይቷል ይላሉ፡፡
ዶክተር ዳግማዊ ኢትዮጵያ የሦስት ሺ ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ ስርዓቶች ይቀያየራሉ፡፡ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፤ የተፈጠሩ አለመግ ባባቶችን በተፈጥሯዊ መንገድ መፍታት፤ የፌዴራል ስርዓቱ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት ጥናት እና ምርምር ማድረግ፤ በዚህ ሂደት ያለፉ ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ እና ኢትዮጵያውያን በገነቧት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰከነ መንገድ ቁጭ ብለው ተነጋግረው የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማስረጽ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡