በፉክክር ሳይሆን በምክክር የጋራ ቤታችንን እናጽና

ሀገር የማንነት አውድ ናት፤ ሕዝብ ደግሞ የዚህ እውነት መገለጫ። በአንድ እጅ ላይ እንዳሉ እንደ መዳፍና አይበሉባ እኩል የሚጠሩ፤ እኩል የሚወሱ። ይሄ ሁሉ የማንነት ጉራማይሌ መልክ ብዙሀነትን ታቅፎ በእያንዳንዳችን ማንነት ላይ እንዲንጸባረቅ የሆነው በሀገርና ሕዝብ ስም ነው። ይሄ ሁሉ የታሪክና የባሕል፣ የስርዓትና የሉአላዊነት ውሕድ ሕብረብሄራዊት ሀገር የሰራው ተለያይተው በተመሳሰሉ፣ ተመሳስለው በተለያዩ ብዙ አይነት መልኮች ነው።

መነሻችን ፍቅር ነበር። ጥንት በእያንዳንዳችን የመንፈስና የስነልቦና ባሕር ውስጥ ኢትዮጵያዊነት መሰረቱን ሲጥል ፍቅርን ተንተርሶ ነው። ፍቅር አንድነትን ወለደ፣ አንድነት ብዙሀነትንና ባለታሪክነትን፤ ጀግንነትንና ሉአላዊነትን ሰጠ። በስተመጨረሻም የነጻነት ፋና ወጊ፣ የፍትሕና የሚዛናዊነት በኩሮች ሆንን። ብዙና ገናና፤ እልፍና ኃያል ተብለን ለአፍሪካ ትንሳኤ ለዓለም ምልክት ሆንን።

ዛሬም ድረስ አፍሪካ በእኛ ጥንተ ፍቅር፤ ጥንተ አንድነት የምትጠራ ናት። ዛሬም ድረስ ዓለም በእኛ የታሪክ እና የጀግንነት ጀብድ የምትደነቅ ናት። ይሄ ስም፣ ይሄ ማንነት እንዴት መጣ? ብለን ስንጠይቅ ፍቅርን የቀየጠ፣ አንድነትን የለወሰ የሰላም ባለቤትነትን እናገኛለን። አብሮነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር የገመደ፣ የቋጠረ ማንነትን እናገኛለን።

ይሄ የድሮ መነሻችን ነው። አሁናዊ እኛነታችን መልኩን ቀይሮ ብቻነትና እኔነትን የሚያቀነቅንበት ሆኗል። የዛሬ ስሞቻችን እንደ ድሮው መልከ ደማም ወይም ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የደመቀባቸው አይደሉም። በብሔርና በጎሳ፣ በጎጥና በእኔነት ወይበው ደብዝዘዋል። ለዛም እኮ ነው እንደጥንቱ አይነት ሀገር መፍጠር ያቃተን። ለዛም እኮ ነው ተቀራርበን የተራራቅ ነው፣ አንድ ሆነን የተለያየ ነው።

የታሪኮቻችን መሀሉ የብዙሀነት ምሰሶ የቆመበት ነው። ለብቻ አስበን፣ ለብቻ ተራምደን ያቆምነው መሰረት የለም። የኢትጵያዊነት ጣሪያ በአብሮነት ክንድ የተደገፈ ለመሆኑ ማስረጃ አያስፈልገውም። ተያይዘንና ተቆላልፈን የመጣንባቸው የታሪክና የማንነት ዳናዎች ዛሬም ሳይደበዝዙ ምስክሮች ናቸው። ወደ ኋላ ባየን ቁጥር እነዛን ብዙ አንድ አይነት እግሮች የረገጧቸውን፣ ብዙ አንድ አይነት እጆች የጨበጧቸውን የማንነት ማሕተሞች ነው የምናገኘው።

እነዚህ ክንዶች አሁን ላይ ዝለዋል። ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን እኔነትን የሚናገሩ ሆነው ፈርጥመዋል። ወደ ተውነው ወደ ጥንቱ የፍቅርና የአብሮነት መዐድ እስካልተመለስን ድረስ ትንሳኤአችን ሩቅ ነው። በመነጋገር ቤት ካልሰራን፣ በውይይት ወደ እርቅና ወደ አብሮነት ካልተሸጋገርን መጪው ጊዜ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አይደለም በጥላቻና በመለያየት ቀርቶ በፍቅር ተጉዘን እንኳን ሩቅ በማንደርስበት ጊዜና ዘመን ላይ ነን።

በብሔራዊ የምክክር ኮምሺን አስተናጋጅነት ላለፉት ዓመታት ዝግጅት የተደረገባቸው የምክክር መድረኮች እየጠበቁን ነው። በሰከነና በረጋ መንፈስ ሀሳብ ሰጥተን ሀሳብ በመቀበል፣ ችግሮቻችን ወደማያንሰራሩበት ደረጃ ማሸጋገርን ቀጣይ እጣ ፈንታችንን የሚወስን ጉዳይ ነው። ሀገራችንን በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ የፖለቲካ ርዕዮት ማረቅ ካልቻልን ከድጡ ወደማጡ የሚታደገን አይኖርም። የትውልዱ ተስፋ ያለው በእጃችን ውስጥ ነው።

ማንም ከዳር ቆሞ የሚስቅብን በእርስ በርስ ሞታችን ነው። ትላንትና ለዓለም ሰላም አስተዋጽኦ ያደረገች ሀገር፣ ትላንትና ለአፍሪካ መነሳት መንገድ የጠረገ ሕዝብ ዛሬ ሰላም አጥቶ፣ ፍቅርና አንድነት፣ እርቅና ተግባቦት ርቀውት ሰላም ፈላጊ ሲሆን ማየት ይገርማል። የቱጋ ነው የተበላሸ ነው? የቱ ጋ ነው ርካብ የሳትነው? የቱ ጋ ነው ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጥነው? ተጋምደን ተሳስረን የመጣን ሕዝቦች አይደለን? ማን ለያየን? ማን አቧደነን? እኚህን ጥያቄዎች በመንተራስ ወደ መፍትሄዎቻችን እንጠጋ።

ጦር ተማዘን፣ ተገዳድለንና ደም ተቃብተን ኖረናል። በሰላም እጦት፣ ባለመግባባት፣ በስልጣን ሽኩቻ ብዙ ትላንትናዎች አልፈውናል። በዘረኝነት፣ በመገፋፋት፣ በኃይል እና በእልህ እሳቤ እልፍ ትናትኔዎች አሉን። ታሪክ በማጣመም፣ ያለፈን በማስታወስ እልፍ ቁርሾዎችን ፈጥረናል። አብሮነትን በማኮሰስ፣ እኔነትን በማንገስ በውበታችን ላይ መለያየትን ዘርተናል። የቀረን ምንድ ነው? የቀረን በመነጋገር መግባባት ብቻ ነው። በእርቅና በምክክር ወደ ተውነው መመለስ ነው።

በእርቅ የአብሮነቱን ቤት መስራትና ማጽናት የዚህ ትውልድ የቤት ስራው ነው። መፍትሄ አዘል ሀሳቦቻችን ለፈረሰ ጎጇችን፣ ላዘመመ አብሮነታችን ዋልታና ማገር ነው። ያን ማንም የሌለውን የፍቅርና የአንድነት ጥንተ ጠዋታችንን ለመመለስ ከእያንዳንዳችን የሚዋጣ የሀሳብ መዋጮ አለ። ያን ማንም የሌለውን የብኩርና ፊተኝነት ለመመለስ ከሁላችን የሚጠበቅ የይቅርታና የመተው ምንዳ አለ።

ሀገርና ሰው፣ ሰውና ሀገር የታሪክ መልኮች ናቸው። በፍቅር ካልሆነ በእንዴትም አያብቡም። አሁናዊ ፉክክራችን የከረመ ፍቅራችንን እንዳያደበዝዝብን ኢትዮጵያ የምትቀድምበት የታሪክና የፖለቲካ ምሕዳር ያስፈልገናል። በታሪክ ውስጥ ትልቁ የትውልድ ክስረት የፉክክር ፖለቲካ ነው። ከመውደቅ ባለፈ ተፎካክረን ያላሸነፍንባቸው ብዙ የታሪክ ገጾች አሉን። አሁንም በዛ መንፈስ ውስጥ መሆናችን ነገን እንድንሰጋ ያደርገናል።

የውይይት ትልቁ ጸጋ ፉክክርን ማስቀረት ነው። እኔነትን መሻር ነው። ፍርሀትና ስጋት ባንጃበቡባት ሀገር ላይ ዝምታና ድንግርታ ጥቅም የላቸውም። ትኩሳቶቻችን እንዲበርዱ፣ የሰላም መቅረዞቻችን ሩቅ እንዲያበሩ ስለሰላም የሚያወሩ አፎች፣ ስለ አንድነት የሚሰብኩ አንደበቶች መብዛት ግድ ይላቸዋል። ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ፤ ከማንም ምንም ሳንጠብቅ ያለንን ትንሽ ነገር በማዋጣት ትልቁን ጋን ማቆም እንችላለን።

ይሄ በሀገራችን ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊነት እኩል ተጠቃሚነትን ያመጣል። መነሻችን ብዙሀነት እንደሆነ መድረሻችንም ህብረብሔራዊነት ነው። በጋራ ካሰብን የጋራ መፍትሄ አናጣም። በወቅታዊ ችግሮቻችን ላይ እንደትልቅ ተግዳሮት የሚነሳው የትብብር መንፈስ ማጣት ነው። ኢትዮጵያ የአንድና የሁለት ሰዎች ንብረት የምትመስለን አለን። ታሪክ ስናወራ ስለ አንድና ሁለት ሰው የምንመሰክር የሚመስለን አለን። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት። ታሪኩ፣ ባህሉ፣ ስርዓትና ወጉ የጋራችን ነው። በችግሮቻችንም ላይ በጋራ መክሮ በጋራ መፍትሄ ማምጣት ግዴታችን ይሆናል።

የሀገራዊ ምክክርም ዋና ዓላማ በጋራ ምክር ኢትዮጵያዊነትን መመለስ ነው። በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ መድረክ አንድነትን መፍጠር ነው። የደበዘዙ ማንነቶቻችንን ማድመቅ፣ የፈዘዙ ጸዳሎቻችንን መመለስ ነው። ውይይቶቻችን አንድነትን እንዲሰጡን፣ በአንድነታችን ኢትዮጵያዊነትን እንድንመልስ ሰላም ፈጣሪ በሆነ የተግባቦት ሀሳብ ማዋጣት አለብን።

እነ ሶቅራጥስን ጨምሮ የዚህና የዛኛው ዘመን ታላለቆቹ ፈላስፎች ሰላምን የምንም ነገር መጀመሪያ አድርገው ነው የሚናገሩት። በመንፈሳዊ አስተምህሮትም ብናይ ተመሳሳይ ነገርን እናገኛለን። በተቃራኒው እንደጥላቻና መቧደን፣ የእኔ የአንተ እንደመባባል በሰው ልጅ መካከል አስከፊ ደዌ እንደሌለ የሚናገሩም ጥቂቶች አይደሉም። በታላቋ ሀገር ስም ስለታላቁ ሕዝብ ስንል ስለ ፍቅር አብሮ መቀመጥ ያስፈልገናል። ያልተደማመጥንባቸው እነዛ የእልህና የማንአለብኝነት ጊዜአቶች ዛሬን ወልደው ትውልዱን መከረኛ አድርገውታል። ከዚህ መዳኛችን ደግሞ ፍቅር ነው። መዳኛችን የችግሮቻችንን ምንጭ በማድረቅ ሌላ አዲስ የተሀድሶ ቦይ መቅደድ ነው።

ሀገር ሰውና ትውልድ በፍቅር ጀምረው በፍቅር ካላበቁ ትላንት እንጂ ነገ የሌለው ግማሽ ባለታሪኮች ነው የሚኮነው። ሙሉ ታሪክ ከሙሉ ገድል የሚጀምር ነው። ሙሉ ገድል ደግሞ ፍቅርና አብሮነት፣ እርቅና ውይይት የታጨቁበት የመንፈስ ከፍታ ነው። ሰውነት ፍጹምና አልተሰጠውም። የሆነ ቀን በሆነ ምክንያት ቅያሜ ሊኖር ይችላል። ቅያሜዎቻችን ጦር እስኪያማዝዙንና ሌላ ቅያሜን እስኪፈጥሩ መጠበቅ ሳይሆን ለምን? በሚል ምክንያታዊ መጠየቅ መልስ መስጠቱ ነው ባለሞገስ የሚያደርገው።

ፍቅር የሰላም ቤት ነው። ማቆሚያ የሌላቸው ረጃጅም ቅያሜዎች በዚህ ቤት ውስጥ ስፍራ የላቸውም። በአጭሩ የሚቀጩ እንጂ ወደ ነገ የሚሻገሩ የሕዝብ ጥያቄ፣ የፖለቲካ ትኩሳቶች በዚህ ቤት ውስጥ አይኖሩም። የታሪክ ዶሴዎቻችን ምንም ገድል እንዳልጻፉ ኦይናቸውን መታየታቸው፣ የአብሮነት ሰንደቆቻችን ምንም ጀብድ እንዳልተሰቀለባቸው ባዷቸውን መቆማቸው በእኛ ተለያይቶ መቆም ነው። የታሪክ ምኩራቦቻችን ምንም ገድል እንዳልሰሩ መታየታቸው፣ የነጻነት አልፋ ደሴት አድማሶቻችን ድር አድርቶባቸው መታየታቸው በእኔና በእናተ ይዋጣልን ነው።

ትውልዱ ፍቅር የሚማርባት ኢትዮጵያ ወዴት ትሆን? ለብሔር ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነት የምንዘምርበት መድረክ የት ይሆን? ጥያቄዎቻችን ሩቅ የሉም። መሻቶቻችን ከነ መልሶቻቸው መዳፋችን ስር ነው ያሉት። እስከተመካከርን ድረስ፣ ለውይይት በራችንን እስከከፈትን ድረስ የትኛውም ተንኮል፣ የትኛውም ጥላቻ ዝቅ አያደርገንም። ባለመነጋገር ደጃዝማነታችንን ከተነጠቅን ቆይተናል። ለዛውም የሀገርን፣ ለዛውም የትውልዱን ደጃዝማችነት። መቼ ነው በዝምታ ማርጎምጎም የሚበቃን? መቼ ነው ቆይ ካልሰራሁለት የሚለቅቀን? እንደ ሀገር የመቀጠል እጣ ፈንታዎቻችን በእጃችን ውስጥ ነው። ለዚህ ደግሞ እንነጋገር፣ እንወያይ፣ በጋራ ለጋራ እንትጋ።

የጥበብ መጀመሪያ ፈጣሪን መፍራት እንደሆነ ሁሉ የሕይወት መጀመሪያም ተነጋግሮ መግባባት፣ ተግባብቶ አብሮ መኖር ነው ባይ ነኝ። በሰላም እጦት የከፈልነው መስዋዕት ዳግም እንዲመጣ በማይሻ መንፈስ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አለ። ጀግኖች የትም አሉ። በሰላም ውስጥ እንደሚወጣ ጀግና ግን ብኩርና የለም። አሁን ላይ እንደሀገር ስለሰላም እየከፈልናቸው ያሉ መስዋዕትነቶች የሚበረታቱ ቢሆኑም ረጅም ርቀት እንዲጓዙ ከመስራት አኳያ ግን የሚቀረን አለ።

ብሔር ከኢትዮጵያዊነት የበለጠባት ሀገር ለትውልድ የሚሆን የሞራል ስንቅ የላትም። ትውልዱ በሀገሩ አፉን እንዲፈታ እውነት ያነገበ የብዙሀነት ፖለቲካ ያስፈልጋል። እንደሀገር በብዙ የልዩነት እሳቤ ውስጥ ነን። ልዩነቶቻችን ደግሞ ሞትና መፈናቀልን፣ ጥላቻና ጥርስ መንከስን ካልሆነ የሰጡን በረከት የለም። ካለፈው ተምረን አዲስ የአብሮነት ጎዳና አለማቅናታችን በአንድ ሕመም ለሁልጊዝ እንድንሰቃይ አድርጎናል። በሀገራዊ ምክክሩም ሆነ ስለ አብሮነት በተከፈቱ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ ሰሚና ተናጋሪ፣ አድማጭና ተጋሪ ሆነን ስለሀገራች አዲስ ተስፋን የምንፈነጥቅበት ይሁን።

ሀገር እንደሰው ናት፤ ሕክምና ያስፈልጋታል። በእኔና በእናተ መግባባት ውስጥ እንድትሽር እና እንድትታመም ሆና የተሰራች ናት። የሀገር ሽረት፣ የትውልድ ተስፋ በእኔና በእናንተ አሁናዊ አስተሳሰብ ውስጥ የተቀመጠ ነው። ስንስማማ እያከበርናት ነው። ስንግባባ እያነገስናት ነው። በተቃራኒው ስንገፋፋና ስንጠላላ ለማናችንም እንዳትሆን እያደረግናት ነው።

ይሄ ሁሉ ማሕበራዊ ጉስቁልና፣ ይሄ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ድቀት የመጣብን ባለመነጋገራችን ነው። የለመድነው ጠመንጃ መወልወል እንጂ ጉሮሮ መሞረድ አይደለም። መከራዎቻችን እንዲያበቁ ገዳይ መሳሪያዎቻችን አፈሙዛቸውን አዘቅዝቀው ቀና ወደማይሉበት ያሸልቡ። በጦርነት ውስጥ የሚገኝ ሰላም የለም። ሰላም ስፍራው በውይይት ውስጥ ብቻ ነው። በታሪክ የሚባላ ትውልድ፣ በብሔር ካባ የተደበቀ ፖለቲከኛ ሀገር ማቅናት አይችልም። ሁሉም የእኔ፣ ሁሉም የእኛ ስንል እንነሳ።

ሀገር ከጎደፈች ሕዝብ ነው የሚጎድፈው። ሕዝብ ከጎደፈ ሀገር ነው የሚጎድፈው። ችግሮቻችን ሳይገድሉን በእርቅ የምንፈታበት ጥንተ ጥበብ ያስፈልገናል። ለአንድነት እንትጋ፤ ምክንያቱም በሸንጎና በሽምግልና፣ በጎሜና በይቅር ለእግዜር ስንቱን ያረቀ ማንነት ፍርድና ሚዛናዊነት ይርቁታል ተብሎ አይታሰብም።

የዚህ ዓለም ታታላቅ እውቀቶች መነሻ ስፍራቸው ሀገርና ሰው ነው። ሀገርና ሰው..ሰውና ሀገር ከየትኛውም ምድራዊ ኃይል በላይ ጉልበታም ናቸው። በየትኛውም ሊቃውንትና ፈላስፋ ዘንድ ቅቡልነት አግኝተው ከትላንት ወደ ዛሬ የመጡ ሁለት ማንነቶች ናቸው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቁርሾ ሳይፈጥር ያለፈ ፖለቲከኛ የለም። ባይፈጥር እንኳን ትርክት ፈጥረን ስም ማጥፋት እንችልበታለን። እኛም ፖለቲካውም መስተካከል ያስፈልገናል።

የትኛውም ሀገራዊና ማሕበራዊ ተግዳሮት ከውይይት በላይ አይሆንም። በሀገራችን ገላ ላይ ከዛም ከዚም የተለጣጠፉ የዘርና የብሔር፣ የጥላቻና የመለያየት ቅርሻቶች እንዲጠሩ፤ ከምንም በላይ እርቅ ተኮር የውይይት መድረክ በስፋትና በጥራት ያስፈልጋሉ። ችግሮቻችንን በጋራ ቀርፈን ወደፊት እስካልሄድን ድረስ ቀና የሚያደርገን ኃይል አይኖርም። እናም የጋራ የሆነች ሀገራችንንና ቤታችንን ለማጽናት ከፉክክር ይልቅ ምክክርን እናስቀድም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You