የባዮቴክ አስፈላጊነት የቀሰቀሳቸው የፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች

ድሮም ቢሆን፣ እድሜ ለሥነቃል ሀብታችን ይሁንና፣ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” ነው የሚባለው። ለፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች መነሻ የሆነውን ሀሳብ ተንተርሰን፣ ፕሮፌሰሩ መነሻ ስለሆናቸው ጉዳይ የሰጡትን ሀሳብ ተደግፈን፤ ያነሷቸውን ጥያቄዎች ጠቃቅሰን የሚከተለውን እንላለን።

ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት (በአፍሪካ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ መድረክ – OFAB ያዘጋጀው) የዓመታዊ ጉባኤ መድረክ፤ መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ∙ም በኢንስቲቲዩቱ ዋና ምስሪያ ቤት፣ ሕሩይ አዳራሽ አካሂዶ ነበር። ጉባኤው በግብርናው፣ በተለይም በባዮቴክኖሎጂ ግብርናው ዘርፍ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ዘርፉን የተመለከቱ ስራዎችን ለሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥበት ነበር።

በጉባኤውም በግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ አሉ የተባሉ ልሂቃን፣ የግብርናው ዘርፍ ስትራቴጂስቶች፣ ዓለም አቀፍ እውቅና፣ ዝናና ተሳትፎ ያላቸው ምሁራን በጥናት አቅራቢነት፣ አወያይነትና ታዳሚነት የተገኙበት፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

ከእነዚህ ምሁራን መካከል አንዱና አንጋፋው ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ ሲሆኑ፣ “የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያለው ሚናና ተግዳሮት” (Ad­vances in Agricultural Technologies and Agricul­tural Challenges) በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናትም ሆነ ጥናቱን በሚያቀርቡበት ሰዓት ሲያስተላልፏቸው የነበሩት መልዕክቶች ሙሉ ለሙሉ የሁላችንም በመሆናቸው ምክንያት ወደዚህ ገጽ ላመጣቸው ወደድሁ።

ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ ይባላሉ። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፣ በግብርናው ዘርፍ የሌሉበት ቦታ (የሙያ ማሕበር፣ ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ፎረም፣ የጥናትና ምርምር መድረክ ወዘተ) የለም።

ፕሮፌሰሩ ቁፍጥናቸው ከምሁርነታቸው ይፈጥናል። ጨዋታ አዋቂ ናቸው። አንደበታቸው ትንታግ ነው። ያልሄዱበት አገር፣ ያልረገጡት ምድር፣ ያላዩት የልማት እንቅስቃሴ፣ ያልጎበኙት የስኬት ተግባር የለም። ልምዳቸው ተዝቆ አያልቅም። ተሞክሯቸው የትየለሌ ነው። “ለምን ተራብን?” ውስጣቸው ድረስ የዘለቀ ጥያቄ ነው። “መፍትሄውስ?” የሚለው እንዳደከማቸው፣ ሁሌም እረፍት እንደ ነሳቸው አለ። በጥያቄ መልክ ወደሚሰነዝሯቸው አስተያየቶቻቸው እንሂድ።

አንዱና ቁልፉ ጥያቄያቸው፣ “ለድህነታችን፣ ለመራባችን፣ ከአገራት በታች ለመሆናችን ተጠያቂው ማን ነው?” ካሉ በኋላ፤ “ማን ነው ተጠያቂው፣ ገበሬው?” የሚል የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ሰው ጥቂት እንዲያስብ፣ እንዲያሰላስል፣ እርስ በርሱ (የጎንዮሽ) እንዲመካከር እድል ከሰጡ በኋላ “ተጠያቂዎቹ ሁላችንም ነን፤ ሁላችንም።” በማለት ራሳቸው መልሱን ሰጥተዋል።

ሌላኛው ጥያቄያቸው፣ ድህነት አዋራጅ መሆኑን፣ አንገት የሚያስደፋ መሆኑን ብዙ ብዙ ነገር ማለት መሆኑን ከጠቀሱ በኋላ፤ “ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣት ማን ነው፣ ማን ነው ከድህነት የሚያወጣት? ትምህርት ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር?” የሚል ጠጣር ጥያቄን ካቀረቡ በኋላ፤ “ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከድህነት የሚያወጣት ግብርና ነው፤ ግብርና ሚኒስቴር።” የሚል መልስን ሰጡ።

አክለውም “ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣት ግብርና ሚኒስቴር ከሆነ እንደገና መጠናከር (ሪብራንድ መደረግ) አለበት።” በማለት መልሰዋል። ግብርናን እንደ አንድ ተራ ተቋም ማየቱ ሳይቀረፍ፣ ወደ ግብርና የጥናት መስክ እንኳን መግባት የሚጠየፍ ሰው ባለበት ወዘተ አገር በግብርና ከድህነት እወጣለሁ ማለት አይቻልም። በመሆኑም “ሪብራንዲንግ ያስፈልጋል” ሲሉም ነው ተቋሙን ለመሰረታዊ ለውጥ የጋበዙት።

ሌላው ጥያቄያቸው፣ አገራችን በ“የውሀ ማማ ናት” አገላለፅ ትታወቃለች። ይሁን እንጂ ይህንን ሁሉ ውሀ ታቅፋ ከመቀመጥ ያለፈ የሰራችው ስራ የለም። “ለምን?” ሌላው አገር አርተፊሻል ውሃ እያመረተና ግድብና ወንዝ እየሰራ (ምስሉን በስክሪን እያሳዩ) ከድህነት ሲወጣ እኛ ተፈጥሮ የሰጠንን ፀጋ ይዘን ለምድን ነው የምንራበው፣ ለምንድን ነው ውሃችንን በአግባቡ ተጠቅመን ከድህነት የማንወጣው? ወዘተ ነበር። ይህም የሁላችንም ጥያቄ ስለ መሆኑ መጠራጠር ባይቻልም ለተግባሩ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል።

ሌላኛው አስገራሚ ጥያቄያቸው ትንሽ ለየት ያለና ብዙም ተሰምቶ የማያውቅ ሲሆን፤ እሱም “የአደጉት አገራት አንድ ገበሬ 400 ሰዎችን የመቀለብ አቅም አለው፤ የእኛ አንድ ገበሬ አራት ሰው እንኳን መቀለብ አልቻለም። ለምን?” የሚል የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ለመውጣትና ሌሎች የደረሱበት ለመድረስ የግብርና ባዮቴክኖሎጂን የመሳሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እነዚህ የፕሮፌሰሩ ጥያቄዎችና መልሶች፣ ምናልባት መልሶቹ ካልሆኑ በስተቀር፣ የሁላችንም ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ላይ የሚጥል አይሆንም። በመሆኑም እነዚህም ሆኑ ሌሎቹና እዚህ ያልጠቀስናቸው የፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ አግኝተው ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያሻግሩን የሁላችንም ምኞትና ተስፋ ነው። ለዚህ ደግሞ እሳቸው ጥናታቸውን ያቀረቡበት መድረክ አንዱና ፊት መሪው ሊሆን እንደሚገባ ሲነገር ተሰምቷል።

ይህ አህጉር አቀፍ፣ የማሕበረሰቡን ግንዛቤ ከማሻሻል፣ በዘርፉ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አከላትና ፖሊሲ አውጪዎችን በማገናኘትና ተቋማትን በማስተሳሰር ከግብርና ባዮቴክኖሎጂም ያለፈ ከፍተኛ ጠቃሜታ ያለው፤ የተለያዩ ምክክር፣ የውይይትና ስልጠና መድረኮችን የሚያመቻች ፕሮጀክት መሆኑ የተመሰከረለት የግብርና ባዮቴክኖሎጂ መድረክ (OFAB-Open Forum on Agricultural biotech­nology) ይህንን አገራዊ ችግር በመቅረፍ ከፍተኛ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ በመድረኩ ተነግሯል።

ከ200 ያላነሱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የመስኩ ባለሙያዎችና የማሕበሩ አባላት በተሳተፉበትና በየሁለት ዓመት በሚካሄደው 19ኛው የኢትዮጵያ ሰብል ሳይንስ ባለሙያዎች ኮንፈረንስ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና መስሪያ ቤት፣ እዚሁ ሕሩይ አዳራሽ ከየካቲት 17 እስከ 18፣ 2015 (ወይም እአአ ፌብሪዋሪ 24 እስከ 25፣ 2023) በተካሄደበት ወቅት ፕሮፌሰር ፍሬው “የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያለው ሚና” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ላይ “በአገራችን ድህነትን ለማስወገድ ከተፈለገ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፍላጎቱ ካለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ጉዳይ ሊታለፍ የማይችል ብቻ ሳይሆን የግድ ነው” ማለታቸው በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።

ከጥናቱም ሆነ ከአጥኚው አጠቃላይ ማብራሪያና “ጥያቄዎች” መረዳት እንደሚቻለው፣ ከድህነት አረንቋ ለመውጣትም ሆነ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አገርና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሲሆን፤ የግብርና ባዮቴክኖሎጂን መጠቀም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ መሆኑ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You