ድህነትን ታሪክ፣ ብልጽግናን እውን የማድረግ ስኬታማ ጉዞ!

ኢትዮጵያ ሃብታም እና ባለፀጋ ሀገር ስለመሆኗ ይነገራል። እርግጥ ነው ሃብቱም ፀጋውም በጉያዋ ያለ፤ ነገር ግን በወጉ ታውቆና ለምቶ “ድሃ” እና “ተረጂ” ከሚለው የስንፍና መጠሪያዋ ሊታደጋት ሳይችል ዘመናት ተቆጥረዋል።

ምክንያቱም ሃብታም በምትባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦቿ፤ ለም አፈር ላይ ተቀምጠው እየተራቡ ለምፅዋት እጃቸውን ዘርግተዋል። በውሃ ላይ እየኖሩ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እንኳን አጥተዋል። የብርሃን ምንጭ የሚሆኑ አያሌ ሃብቶችን ታቅፈው በጨለማ ውስጥ ተመላልሰዋል።

ዛሬ ግን ይሄ ሁሉ ታሪክ ሊሆን መልካም ጉዞ ተጀምሯል። አንዳንዱም ከኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ላይ መራገፍ ጀምሯል። የጨለመው እየበራ፤ ለልመና የተዘረጋውም እጅ እየታጠፈ፤ የተጠማውም ጉሮሮ እየራሰ ማደር ጀምሯል። ይሄ ደግሞ ሀገር ያላትን ሃብት ከማወቅና ወደ ልማት እንዲቀየር ከማድረግ የጀመረ የመሪዎች አርቆ የማየትና የማሰብ ልዕልና የመነጨ ነው።

ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ በልቶ ከማደር ባሻገር የምትገለጥበት አቅም አንዱ ግብርና ነው። በዚህ ረገድ እንደ ሀገር የበጋ ስንዴ በጥቅሉም የስንዴ ልማት ጅማሮው እጅጉን የሚደነቅ ነው። ለምሳሌ፣ አምና አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት መታሰቡን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሄ ደግሞ ከአምናው አንጻር ከእጥፍ በላይ (በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር) ብልጫ ያለው ነው። የበጋ እና የክረምቱ ደምሮ ማየት ከተቻለም፤ በመሬት ዝግጅትና በዘር የመሸፈን ሂደቱ ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር አልፏል። ይሄ አፈጻጸም ለውጥም፣ ዕድገትም የታየበት ሂደት ነው።

ይሄ በመሬት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ በምርት ደረጃም እንዲሁ ይጠበቃል። ለምሳሌ፣ አምና በጋ ላይ 47 ሚሊዮን ያህል ኩንታል መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ዘንድሮ ደግሞ በበጋ ብቻ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

እዚህ ጋ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ እየተገኘ ባለው ጅምር ውጤት መርካት እና የጉዞ ግለትን ማቀዝቀዝ ፈጽሞ የሚታሰብ ጉዳይ አለመሆኑን ነው። በመሆኑም፣ የክረምት ምርት ውጤት አስገኝቷል ብሎ ሳይዘናጉ፤ ቶሎ የበጋ ሥራን መጀመር አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚታረሰውን ሰፊና ለም መሬት፣ ዓመቱን ሙሉ ከሚፈስሱ ወንዞች ጋር በማስተሳሰር ወደሥራ መግባት የተገባ ነው።

ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፋር ክልል የበጋ ስንዴ ልማት ሥራ መርሐ ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት ያስገነዘቡትም ይሄንኑ ነው። በወቅቱም እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር በዚህ የበጋ ስንዴ ልማት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት እቅድ ሲያዝ፤ ይሄን ማድረግ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለ በማመን ነው።

ለምሳሌ፣ በአፋር ክልል ሰፊ የሚታረስ ለም መሬት አለ፤ በዛው ልክ የውሃ ሃብት አለ። እነዚህን ሁለት ለሥራው የሚያስፈልጉ አቅሞች በተገቢው መልኩ ማገናኘት እና ሥራው የሚጠይቀውን ማድረግ ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል። በዚህ መልኩ ደግሞ የበጋው ሥራ ውጤት ሲያስገኝ እና በክረምቱ ከተገኘው ውጤት ጋር ሲደመር፤ ቀድሞ ከሚመረተው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ስለሚሆን እንደታሰበው ለወጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን ለሌላም ጉዳይ ማዋል የሚቻልበትን እድል ይሰጣል፤ አቅምም ይፈጥራል።

ይሄንን ለማድረግ ደግሞ እንደ አፋር ክልል ሁሉ፣ በሁሉም አካባቢ ያለውን ሃብት ፈልቅቆ ማውጣትና መጠቀም ያስፈልጋል። ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ እጅግ የማደግ አቅም ያላት ሀብታም ሀገር ናት። ሊታረስ የሚችል መሬት፤ ያልወጣና ወደ ገንዘብ ያልተቀየረ ማዕድን ያላት፤ ሰፊ ጉልበት እና መማር መሥራት የሚችል የሰው ኃይል ያላት ሀገር ናት። የአፋር ክልል ደግሞ የዚህ አባባል አንዱ ማሳያ ነው።

በአፋር ምድርም እርሻ ሲታሰብ መልክዓ ምድሩም ሆነ የአየር ጠባዩ የሚጠይቀውን ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት፤ ለዚህ የሚሆን አቅም፤ ለዚህ የሚሆን ሥራና ትጋትን ይጠይቃል።

ምክንያቱም ልመናን ታሪክ ማድረግ እና በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር መፍጠር የሚቻለው፤ ከዚህ የተሻገረ አቅም ፈጥሮም ጅምሩ ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እውነት ወደ ከፍታ የሚሸጋገረው፤ በቃል የሚነገረው የኢትዮጵያ ብልጽግና ተጨባጭ የሚሆነው፤… በአንድ ወቅት ወይም ክረምት ላይ ብቻ በተንጠለጠለ ግብርና ሳይሆን፤ በበጋውም ጭምር ውሃ እና አፈርን በማገናኘት በሚከወን ከፍ ያለ ተግባር ነው!

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You