
አዲስ አበባ፡- የነዳጅ ግብይትና ስርጭትን በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት መከናወኑን ለመከታተልና ሕገወጥ ተግባራት ተፈጽመው ሲገኙም ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል የነዳጅ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በባለሥልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ገበያ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እስካሁን ድረስ ከነዳጅ ግብይት፣ ማጓጓዝና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሚያጋጥሙ ሕገወጥ ተግባራት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አንድ ወጥ ሕግ አልነበረም፡፡
አሁን ላይ የነዳጅ ግብይትና ስርጭት በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት መከናወኑን ለመከታተልና ሕገወጥ ተግባራት ተፈጽመው ሲገኙም ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የነዳጅ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡
በነዳጅ ግብይት ሂደት ላይ ነዳጅን ከተፈቀደለት ቦታ ውጭ መውሰድ፣ ከተፈቀደ መስፈሪያ ውጭ መሸጥ፣ ከተፈቀደለት ዋጋ በላይ መሸጥና ሌሎችም የተከለከሉ ተግባራት እንደሚፈጸሙ ጠቅሰው፤ እስካሁን ድረስ እነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ እርምጃ የሚወሰደው የተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎችን በመጠቀም ነበር፡፡ አሁን የነዳጅ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ መሰል ተግባራትን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ወጥ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ተጠናቆ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ሥርዓትን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እየተሠጠ ነው ያሉት አቶ ለሜሳ፤ ነዳጅ ከትዕዛዝ እስከ ሽያጭ ያለው ሂደት በሲስተም እንዲተሳሰር በመደረጉ ነዳጅ ከየት ተነስቶ የት እንደገባ፣ የትኛው ማደያ ምን ያህል ነዳጅ እንዳለ መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
ለአሽከርካሪዎች የትኛው ማደያ ነዳጅ እንዳለ የሚያመላክት የሞባይል መተግበሪያም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም አሽከርካሪዎች ነዳጅ ፍለጋ ከመዘዋወር ይልቅ በመተግበሪያው ነዳጅ የት እንዳለ አይተው በቀላሉ ግብይት ለመፈጸም እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል፡፡
የተጀመሩ የቴክኖሎጂ አሠራሮች እንዳሉ ሆነው የተቀመጡ የአሠራር ሥርዓቶችን በአግባቡ በማይተገብሩና ነዳጅ እያላቸው የለንም የሚሉ አካላትም ረቂቅ አዋጁ አንድ ሰው ነዳጅን ከተፈቀደለት የግብይት ሥርዓት ውጭ ሲሸጥ ሲገኝ የሚቀጣበት፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ መንገዶችን አሟልቶ የሚያስቀምጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ትግበራ ሲገባ የነዳጅ ሪፎርሙ ላይ የተካተቱትን ግብይቱን ማዘመን፣ ቁጥጥሩን ማጠናከር፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ አቅርቦትና ስርጭቱን ማሳደግና ፍትሐዊ ማድረግና ተያያዥ ሥራዎችን በአግባቡ ለማስፈጸም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም