ቱርክ የአሁኑ ዘመን እንደ ትናንቱ አለመሆኑን የተገነዘበች አገር ነች። ይሄንን ለማለት የሚያስደፍረውም በምስራቅ አፍሪካ፣ በጥቅልም በአፍሪካ በተግባር የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በቅድሚያ በአፍሪካ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራት ከመፈለግ የሚመነጭ እንጂ የአፍሪካን ባህል በእሰላማዊ መሠረት ላይ ለማስኬድ በመቋመጥ አይደለም። በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ብርቱ የኢኮኖሚ ጥቅም ትስስር ከብርቱ ወታደራዊ እና ባህላዊ ትብብር በላይ አስፈላጊ መሆኑ የሚታይበት መሆኑ ለቱርክ ግልጽ ነው።
ቱርኮች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ከትብብር እና ከድጋፍ ጋር አጣምሮ ለመቀራመት ከሚተጉ ቻይናን ከመሰሉ አገራት ጋር ተጋፍተው አብላጫ ድርሻውን ለማንሳት እጅግ ብረቱ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። አንዳንድ ፖለቲከኞች የቱርክ የአፍሪካ ቅርምት /Turkey scrambles for Africa/ እያሉ እስከ መጥራት ለደረሱበት ብርቱ ፉክክር ተሰልፋ ተገኝታለች።
ዛሬ ላይ ቱርክ በአፍሪካ የ44 ኤምባሲዎች ባለቤት መሆኗን ስንረዳ በአፍሪካ ላይ ዓይኗን የጣለችበትን ደረጃም እንረዳለን። ቁጥሩ ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት አንፃር ሲታይ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን ይነገራል። ቱርክ በአፍሪካ እስልምናን የማስፋፋት ፍላጎት አላት የሚሉ አካላት ቢኖሩም፤ የቱርክ ፍላጎት ግን በዚህ ላይ ብቻ የተመሰረተ አለመሆኑን በተግባር ይታያል የሚለው ሙግት ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል።
ቱርክ ከፍተኛ የቢዝነስ መሰረት ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሁሉም የአፍሪካ አገራት ጋር በሚባል ደረጃ መስርታለች። ከ15 ዓመታት በፊት ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች በንቃት ክትትል፣ ተሳትፎ፣ ጣልቃ ገብነት፣ ትብብር ወዘተ… ስለሚያደርጉ አካላት ሲታሰብ አሜሪካ፣ ቻይና እና ራሺያ ጎልተው ይመጣሉ። ድምፃቸው ከልኩ በላይ ይሰማል። ቱርክ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የእግራቸው ኮቴ ሳይሰማ በአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት ካላቸው እና እርምጃ ውስጥ ከገቡ አገራት መካከል ያላት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አሌ አይባልም።
እስከ አሁንም በአፍሪካ ውስጥ የስድስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አላት። ከፍተኛ የሚባለውን የቻይና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለመጋራትም እየጣረች ነው። የወቅቱ ፕሬዚዳንት ራሴፕ ታዪፕ ኤርዶጋን ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ እንኳን በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ከ30 ጊዜ ያላነሰ የጉብኝት መርሐ ግብር ነበራቸው። ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ የአፍሪካ ጉዳዮች መድረክ ላይ ‹‹አዲሱ የዓለም ሥርዓት እየተገነባ ባለበት በዚህ ወቅት ቱርክ አካሄዷን ከአፍሪካ ጋር ታሳምራለች።›› ሲሉ ተደምጠዋል። እንደ Middle East Eye ዓነቶቹ ሚዲያዎች ይሄንን ፈጣን እንቅስቃሴ አዲሱ የኦቶማን ተስፋፊነት /Neo Ottomans Expansionism / በማለት ይጠሩታል።
ቱርክ በአፍሪካ ያላት የኢኮኖሚ ፍላጎት የሰብአዊ እና የልማት ድጋፍንም አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ፤ በአጭር ጊዜ እየተመነደገ እንዲሄድ በር ከፍቷል። ለዚህም የቱርክ ዓለም አቀፍ የትብብር እና ጥምረት ኤጀንሲ / TIKA/ ተግባራት ይጠቀሳሉ። ይህ ኤጀንሲ በ28 የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚተገበሩ ከ200 የማያንሱ ፕሮጄክቶችን ይመራል። ቱርክ ለአፍሪካ አገራት የምትሰጠውን ትብብር እና ድጋፍ በዚህ ኤጀንሲ በኩል ታስፈጽማለች። ከዚህ የልማት ትብብር እና ድጋፍ ጎን ለጎን ግን ቱርክ በአፍሪካ ያላት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ድርሻ እጅግ አነጋጋሪ በሆነ ደረጃ አይሏል።
በዐረብ አቢዮት የተናጠው የውጭ ግንኙነት ወቅታዊው የቱርክ የግንኙነት ፖሊሲም በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ለውጦችን መነሻ ማድረጉ ባይካድም በምስራቅ አፍሪካ የውጭ ግንኙነት እና የደኅንነት ፖሊሲዋ ግን ነባሩን የታሪክ እና የባህል ግንኙነት የገደፈ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል።
ቱርክ ሁለት ቁልፍ የደኅንት ሥጋቶች አሉባት። አንዱ ከምዕራባውያን ጋር የጎሪጥ የምትተያይበት የቱርክ የተገንጣይ ኩርዶች እንቅስቃሴ ነው። ተገንጣይ ቡድኖቹን አሜሪካ እና ሸሪኮቿን ለመደገፍ የሚያሳዩት ዝንባሌ እና ተግባር በአፀፋው ቱርክ በምስራቅ አፍሪካ እና በሌሎች አካባቢዎች የተቻላትን ያህል በጥቅሞቻቸው ላይ የእጅ አዙር ትንኮሳዎች / ጫናዎች የማሳደር ዝንባሌ ያለው ፖሊሲ አላት። ሁለተኛው ቁልፍ ሥጋት አረባዊ ሙስሊሞች አረብ ባልሆኑ ሙስሊሞች ላይ ያላቸውን ፖሊሲ የሚገዳዳር ነው። ለዚህም አረባዊ እስልምናን ሳይሆን ሙስሊም ወንድማማችነትን መሰረት ያደረገ እስላማዊ ጫና እንዲስፋፋ ትፈልጋላች። ለዚህም ግብጽን ከመሰሉ አገራት ጋር የጎሪጥ የመተያየት እና የመገዳዳር ፖሊሲ አላት።
በምስራቅ አፍሪካ ያለው ወቅታዊ የቱርክ የውጭ እና የደኅንት ፖሊሲ የሚቀዳበት አንዱ ምንጭ እነዚህ ሁለት ሥጋቶችን የመቅረፍ አቅጣጫ ነው።
ከዐረብ አቢዮት ተከትሎ በግብጽ የሙ ስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በምርጫ የበላይነትን ባገኘ ጊዜ ለቱርክ ከፍተኛ ፈንጠዝያ ተፈጥሮ ነበር። አፀፋዊ በሆነ አቢዮት ሙርሲ ከሥልጣን መንበራቸው ወርደው ወደ እስር መምጣታቸው ግን ቱርክን በከፍተኛ ደረጃ አስቆጥቷታል። ስለዚህም በምሥራቅ አፍሪካ የምትከተለው የግንኙነት አቅጣጫ የአልሲሲን መንግሥት ጫና ውስጥ የሚከት እንዲሆን በጥበቅ መሥራት ቀጥላለች።
የቱርክ አንዱ እርምጃ ‹‹የዘላለሜ ነሽ›› ከምትላት ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ጠበቅ በማድረግ በቀይ ባህር በሱአኪንደሴት ላይ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከሱዳን መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሻለሁ ብላ ይፋ አድርጋለች። ይኸው ደሴት በሊዝ ግዥ ዓይነት በቱርክ እጅ መውደቁ ለግብጽ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል። በሱዳን በኩል የተዘረጋው የቱርክ ፀበ ጫሪ እርምጃ በምሥራቅ አፍሪካ ውጥረት ሊፈጠር እንደሚችል ለየትኛውም የፖለቲካ ተንታኝ ግልጽ ነበር። እንደተሰጋውም የግብጽ መንግሥት ኤርትራ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ ገነባችው ወታደራዊ ሠፈር በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ልካለች። ያንን ተከትሎም ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላትን ድንበር ዘግታለች። በሺህዎቸ የሚቆጠሩ ወታደሮቿንም ወደ ኤርትራ ድንብር አስጠግታ ነበር። የቱርክ እርምጃ ሁለቱን የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ኤርትራን እና ሱዳንን አፋጠጠ።
እንደ ሱዳን ትሪቢዩን ዘገባ ደግሞ ቱርክ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ጠንካራ ፈተና የሚያመጣው በወታደራዊ መስክ ያላቸው ትብብር ነው። ቱርክ በሱዳን ወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ለመክፈት እና መከላከያ መሥሪያ ቤቷን ለማጠናከር ያደረገችው ስምምነት ከጎረቤት አገራቱ በተለይም በግብጽ በዓይነ ቁራኛ የሚታይ ሆኗል።
ቱርክ ለአፍሪካ ወታደራዊ ሹማምንት (መኮንኖችም) ስልጠና ለመስጠት መትጋቷ ቢታወቅም፤ በመሥራቅ አፍሪካ ደግሞ በተለይ ለሱዳን፣ ለሶማሊያ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለኡጋንዳ እና ለኬኒያ በዚህ ረገድ የምትሰጠው ድጋፍ ጠንካራ ነው። ቱርክ ይሄንን በምስራቅ አፍሪካ የምታደርገው በቀይ ባህር፣ በባብኤል ወደብ የባህር ወሽመጥ እና በኤደን ባህረሰላጤ ሊኖራት የምትፈልገውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ነው።
ሱዳን ከቱርክ ጋር ለመሥራት ያላትን አቋም እንድታጠናክርም የቱርክ ፕሬዚዳንት በታህሳስ 2018 ላይ በሱዳን ባደረጉት ጉብኘት መልዕክት አስተላልፈዋል። ሱዳን እስከ አሁንም መፍትሔ ልትዘይድለት ብትቸገርም ኢኮኖሚዋን የበለጠ በመደገፍ እንዳታፈገፍግ ለማድርግ ቱርክ ወሳኝ እርምጃ ወስዳላች። ቱርክ ለነዳጅ ፍልጋ እና የነዳጅ መስክ ልማት የሚውል 100 ሚሊየን ዶላር ለመመደብ እና ሱዳን ለቱርክ ኩባንያዎች በሺዎች በሚቆጠር ስኩየር ማይሎች ያህል የግብርና መሬት ለቱርክ ባለሀብቶች እንድታቀርብ የሚያደርግ ሰምምንት ተፈራርመዋል። በግብርና መሬቱም ለቱርክ እና ለሱዳን የምግብ ዋስትና በሚበጅ ደረጃ እንደሚለማ ታቅዷል። የንግድ ግንኙነታቸውንም በዓመት ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ተስማምተዋል።
የቱርኩ Ziraat Participation Bank ቅርንጫፉን ካርቱም በመክፈት ከሱዳን ጋር ያለውን የገንዘብ ሴክተር ግንኙነት ለማሣለጥ አልሟል።
ሱዳን ያለባትን የምንዛሪ እጥረት ግን በጊዜው መፍታት በላመቻሏ ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ ማምራት ግድ ሆኖባታል። በዚህም ምክንያት ህዝባዊ ተቃውሞ በመንግሥት ላይ ተነሥቷል።
ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ቱርክ የነበራት ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት ከ2 ቢሊየን ዶላር በተሻለ በስፋት በሱዳን መሬት የማሳደግ ዕቅድ ፈተና ሊገጥመው ይችላል። ቱርክ ራሺያ እና ኳታር በሱዳን ወቅታዊ ችግር ‹‹ከጎንሽ ነን›› ባሉት አግባብ ቱርክም በተመሳሳይ ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታትም የኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ ትብብሯን ገልፃለች።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011 ዓ.ም
በማለደ ዋስይሁን