ከሀገራዊ ምክክሩ ሁላችንም እናተርፋለን

አበው የምክርን ወይም የመመካከርን አስፈላጊነት ሲያስረዱ ‹‹ምከረው… ምከረው ፤ እምቢ ካለ መከራ ይምከረው›› ይላሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባሕሎችና ወጎች ያሉን ሕዝቦች ነን። በአባቶቻችን ምክር ተግሳጽና ቁጣ እየታረቅን/ እየተስተካከልን ፍቅራችንን እና አንድነታችንን ጠብቀን የኖርን ሕዝቦች ነን። ዥንጉርጉር ማንታችንን ጸንቶ የሚኖር፣ ፈጣሪያችንን የምንፈራና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች መሆናችንም በታላላቆቹ የክርስትና እና የእስልምና ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ አስቀድሞ የተነገረልን ነን።

ከረዥም ዘመን አብሮነታችን የተነሳ ቋንቋዎቻችን፣ ባሕሎቻችን፣ ወጎቻችንና አኗኗራችን ተወራርሰዋል። ከዚህ አለፍ ሲልም እርስ በእርሳችን በደም ተሳስረናል። በዚህ የተነሳ የአንዱ ብሔረሰብ ባሕልና የአኗኗር ሥርዓት ይነስም ይብዛም በሌላው ብሔረሰብ ውስጥ ይንጸባረቃል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ብሔረሰብ ራሱንም ሌላውንም ብሔረሰብ ሆኖ ተሳስቦና ተፋቅሮ ኖሯል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር አንዱ ብሔረሰብ ከሌላው ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆኖ ይኖራል ማለት ነው፡፡

ይህ ሁለንተናዊ የተወራራሽነት ባሕሪ የአንድነ ታችንን ካስማ እያጠናከረ እዚህ ድረስ አዝልቆናል። ወደፊትም አብሮን ይኖራል። ብሔረሰባዊ ማንነታ ችንና ኅብረ ብሔራዊ አንደነታችን ሳይጋጩብን ብዙ ዘመናትን ተሻግረን እዚህ የደረስንባቸው ምስጢሮቻችን ብዙ ናቸው። ከነዚህም ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቻችን ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛሉ።

በረዥሙ የአብሮነት ጉዟችን ውስጥ መንገዶቻችን ሁሉ አልጋ በአልጋ ነበሩ ማለት አይቻልም። በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደትም ይሁን በሌላ ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ የትኞቹም የዓለም ሀገራት ማኅበራዊ ግጭቶች ሳይከሰቱባት እዚህ የደረሰች ሀገር አይደለችም፤ እንኳንስ በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ይቅርና በአንድ ብሔረሰብ ውስጥም ግጭቶች ተከስተው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ እንደ ዘመነ መሳፍንት አይነቶቹንና በየአካባቢው በነበሩ ገዢዎች መካከል የተፈጸሙ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ እንደሀገር ይገጥሟት የነበሩ ወለምታዎችን ሁሉ በነባሩ ባሕላዊ ሕክምናዋ እየጠገነች ሕዝቦቿ ሰምና ወርቅ ሆነው እንዲዘልቁ አድርጋለች።

ሆኖም ኢትዮጵያ ዛሬ ወለም ብሏታል። እንደከዚህ ቀደሙ ወለምታዋን ጠግኖ በሁለት እግሯ ለማቆም የሚጥር ሀገር ወዳድ ዜጋ፣ ምሑር፣ ሽማግሌና የሃይማኖት አባቶች አሏት። ዛሬም ቢሆን እነዚህ አካላት ስለሀገር ሰላም ስለአብሮነትና ወንድማማችነት ያልመከሩበት ያልዘከሩበት ጊዜ አልበረም። የሚሰማቸው ጠፍቶ እንጂ ዛሬም እየተጣሩ ነው። ጥሪያቸውን ሰምቶ ባሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ቁጭ ብሎ ከመነጋገር ይልቅ ወለምታዋን ወደ ውልቃት፤ ውልቃቷን ወደ ስብራት የሚያባብሱ ቡድኖችና ግለሰቦች እየበረከቱ መጥተዋል። ነገር ግን እነዚህ የጥፋት መንገዳቸው የትም አያደርሳቸውም፡፡

ነባሮቹ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የአንድነት እና የሰላም እሴቶቻችን በሐሰት ትርክት ተሸርሽረው በማኅበራዊ መስተጋብራችን ላይ የሚፈጠረውን ወለምታ የማከም ሚናቸው እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል።

ዋናው ጉዳይ ግን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአባገዳዎች እና የሌሎችም ቀና ምክር፣ ተግሳጽና አስታራቂነት ጸንቶ ያለው ነባሩ እሴት፤ በፖለቲከኛ፣ በነፃ አውጪና በምሑር ነን ባዮች፣ በአክቲቪስቶችና በዩቲዩበሮች አፍራሽ አስተሳሰብ የተጠለፈው ኢትዮጵያዊ መገለጫችን ዛሬ አደጋ ላይ መውደቁን ያዙልኝ፡፡

ለሐሰተኛ ትርክቶች ጆሯቸውን እየሰጡ ስንበደል ኖረናል፣ መብታችን እና ጥቅማችን አልተከበረልንም፣ ሕልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል፤ እንደሕዝብ ልንጠፋ ነው፣… የሚሉ ቡድኖች በሚፈጥሩት አሉባልታ የተጋመድንባቸውንና የተሳሰርንባቸውን ክሮች ለመበጣጠስ ብዙ ተሞክሯል። ይህ ታዲያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያናጉና ኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠሏን ነገር ፈታኝ ያደረጉ ማኅበራዊ ቀውሶች እዚህም እዚያም እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።

እያንዳንዱ ብሔረሰብ የሚያነሳቸው በርካታ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ይኖራሉ። አንዳንዶቹን ብንመለከት እንኳ ‹‹ለወሰን እና ለማንነት ጥያቄዬ መልስ ይሰጠኝ››፣ ‹‹በዚያኛው ሥርዓተ-መንግሥት ተበድያለሁ››፣ ‹‹በዚህኛው ሥርዓተ-መንግሥት ተገፍቼያለሁ››፣ ‹‹ይሄኛው እንጂ ያኛው ባንዲራ አይወክለኝም››፣ ‹‹ያኛው እንጂ ይሄኛው ባንዲራ አይወክለኝም››፣ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ ይሻሻልልኝ››፣ ‹‹ሕገ- መንግሥቱ እንዳይነካብኝ›› የሚሉና እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ጥያቄዎች ሀገራችንን አዙሪት ውስጥ ከከተቱ ምክንያቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በአንድ ጉዳይ ላይ የሚንጸባረቁ የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስታረቅ የሚቻለው ደግሞ በመነጋጋርና በሀሳብ ልዕልና እንጂ በጠብ መንጃ አፈሙዝ ሊሆን አይችልም። በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚረጋገጥ አሸናፊነት ወቅታዊ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሔም አይሠጥም። እርግጥ ነው ጥያቄዎቹ ሁሉ አግባብነት የላቸውም ማለት ግን አይደለም። ችግሩ እነዚህንና መሰል የሀሳብ ልዩነቶችን መነሻ እያደረጉ ነፍጥ ማንሳቱና ጉልበተኝነት አሸናፊ የማያደርግ መሆኑን አለመረዳቱ ላይ ነው።

ጠብመንጃ እንደስሙ ሁሉ ጠብን ከማባባስ፣ ትውልድን ከመብላትና ሀገርን ከማፈራረስ ባለፈ የሚነሱ ጥያቄዎችን ሲመልስ አልታየም። ከተሞክሮዎች መረዳት እንደሚቻለው ጦርነት ካጸናቸው ጉዳዮች ይልቅ ሰላማዊ ንግግር ያጸናቸው ጉዳዮች ይበልጣሉ። ለዚህ ደግሞ የሌላ ሀገራትን ወይም የሩቅ ዘመን ታሪክን መጥቀስ ሳያስፈልገን ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲደረግ የነበረውን ጦርነት መጥቀስ እንችላለን። የጦርነቱ መቋጫ ያገኘው ሰላማዊ ድርድርና ንግግር ነው። ሆኖም በርካታ ዜጎቻችንን አሳጥቶናል። ከፍተኛ የሀገር ሀብት ባክኗል፤ መሠረተ ልማት ወድሟል።

ገና ከትናንቱ ችግር ሳንወጣ፣ የተጣባን በጠመንጃ አፈሙዝ የመፍታት አባዜ ዛሬም በዚሁ አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር አድርጎናል። የራሱን መከላከያ ሠራዊት የሚወጋ፣ የራሱን ሕዝብ ለችግር የሚዳርግ ነፃ አውጪነኝ ባይ በየመንደሩ መሽጎ በገዛ ወገኑ ላይ መተኮስን እንደ ትግል ስልት ሲመለከተው ስናይ ወደየት እየሄድን ነው? ያስብላል። የዛሬው ስሜታዊነትና ተራ ጀብደኝነት ልክ እንደትናንቱ ጥሎብን ከሚያልፈው መከራና የኢኮኖሚ ድቀት በዘለለ ጠብ የሚል ፋይዳ እንደማያመጣ ለሁላችንም ግልጽ ነው።

በመሆኑም አሉን የምንላቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ በጉዳዩ ላይ መከራከርና በሀሳብ ልዕልና ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ዓለም የሚከተለው የሠለጠነ መንገድ ነው። ከዚህ አንጻር መንግሥት በያዝነው ዓመት ሀገራዊ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ይህ አጋጣሚ ማዶና ማዶ ሆነው የየራሳቸውን ሀሳብ የሚሠነዝሩ ኢትዮጵያውያን ተቀራርበው እንዲነጋገሩና ለጋራ ሀገራቸው የጋራ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ያግዛል። ልዩነቶቻችንን ማስወገድ የምንችለውና ለሀገራችን እና ለሕዝባችን የሚበጅ ቁምነገር መሥራት የምንችለው በሀሳብ የበላይነት እንደመሆኑም፤ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ‹‹ፈረሱም… ሜዳውም…›› እንዲሉ ለሁሉም በሩን ክፍት ያደረገ ነውና ሀሳብ ያለን ወደ ሜዳው ብንመጣ ብዙ የምናተርፍበት ይሆናል፡፡

ሜላት ኢያሱ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You