በኢትዮጵያ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከተነደፉት ስትራቴጂዎች መካከል የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ተጠቃሽ ነው። የመስኖ ልማት ሥራን በማስፋፋት ረገድም በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት በመድረስ በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግን ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ነው።
የመስኖ ልማት ሥራ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት የምግብ ዋስትናን በማሻሻልና የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎችን በመተግበር የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት መለወጥን ዓላማ አድርጓል። ከዚህ አንጻር በተለይም የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በመስኖ ሥራ ያደረገችው ፈርጀ ብዙ ጥረት ከድህነት ለመላቀቅ የሚያስችላትን ትክክለኛ አቅጣጫ መያዝ እንደቻለች ያመላከተ ነው። አገሪቷ ያላትን የመሬትና የሰው ኃብት በመጠቀም ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፋ በመሥራት በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደቻለች መረጃዎች ያመላክታሉ። በአገሪቱ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተመዘገበውን ውጤት መነሻ በማድረግ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።
በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለበጋ መስኖ ስንዴ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። መንግሥት ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሰጠው ትልቅ ትኩረትም ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሃገር ውስጥ ለመተካት ሰፊ ርብርብ አድርጓል። በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገብ ችሏል። እንደ ሀገር ተጠናክሮ የቀጠለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ አሁን በተለይም የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች መስኖ እየሰፋና እየተለመደ መጥቷል። በዚህም በመስኖ እየለማ ያለው የመሬት ስፋት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በሀገሪቱ በአሁን ወቅት ተጠናክሮ የቀጠለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ አበረታች ውጤት እየታየበት እንደሆነ የጠቀሱት የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው እንደሚሉት፤ ከበጋ መስኖ ልማት ሥራ ጎን ለጎን መደበኛ የሆነው የመስኖ ሥራም በአግባቡ እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት እየተሠራ ነው። በመሆኑም በዘንድሮ በጀት ዓመት እንደ ሀገር ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማረስ ታቅዷል። ከሚታረሰው ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥም 117 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።
እሳቸው እንዳሉት እንደ አገር በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካትም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በተለይም ከታች ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሥራት የመስኖ ልማት ሥራ ካለፈው ዓመት በበለጠና በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነና ለዚህም የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የክረምቱ ወቅት እያለፈ የበጋው ወቅት እየመጣ ባለበት በዚህ ወቅት በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መደበኛ የሆነው የመስኖ ልማት ሥራም እየተከናወነ እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት፤ በመደበኛው የመስኖ ልማት ሥራ በአሁን ወቅት ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ጎመን፣ አቦካዶና የመሳሰሉ ምርቶች እየለሙ እንደሆነ ገልጸው፤ በሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የሚለማው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራም ከመደበኛው የበጋ መስኖ ሥራ ውጭ እንደሆነ ነው ያብራሩት።
በአሁን ወቅትም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ አስፈላጊው የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የተሠሩ በመሆናቸው ወደ ተጨባጭ ተግባራት መሸጋገር ተችሏል። ያሉት አቶ ከበደ፤ እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በአፋር ክልል ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የቅድመ እርሻ ሥራ ተሠርቷል። በክልሎቹ የተሠራው የቅድመ እርሻ ሥራን አስመልክቶም የእርሻ ሥራው በዘመናዊና በባሕላዊ መንገድ መከናወኑን ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት 738 ሺ 430 ሄክታር መሬት በባሕላዊ መንገድ የታረሰ ሲሆን፤ በዘመናዊ መንገድ ወይም በትራክተር ደግሞ 193 ሺ 269 ሺ ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚሁ የቅድመ እርሻ ሥራ ውስጥ እስካሁን ባለው 334 ሺ 937 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን እንደቻለም አመላክተዋል፡፡
የቅድመ እርሻ ሥራው በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነና አጠቃላይ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን የጠቆሙት አቶ ከበደ፤ አጠቃላይ የበጋ መስኖ ሥራው ሁሉንም ክልሎች ያማከለ እንደሆነ ነው የገለጹት። ከላይ ከተጠቀሱትና ወደ እርሻ ሥራ ከገቡት ክልሎች ውጭ የሚገኙ ቀሪ ክልሎችም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማከናወን የቅድመ እርሻ ሥራዎች እንቅስቃሴ መጀመር እንደቻሉ ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ካለፈው ዓመት በተሻለ ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ከበደ፤ ከእነዚህም መካከል የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ ትልቁ ሥራ እንደነበር አስታውሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ወደ በጋ መስኖ ሥራ ያልገቡ ክልሎችን በማስገባት፣ በሠርቶ ማሳያ፣ በልምድ ልውውጥ፣ በአርሶ አደር ማሳ ላይ በተደረጉ የመስክ ጉብኝቶችና ሌሎች ጥረቶችን በማድረግ አጠቃላይ የአመራሩንና የአርሶ አደሩ ግንዛቤ በማሳደግ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከዓመት ዓመት ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ሆኗል ነው ያሉት፡፡
የውሃ አማራጮች እና ሰፋፊ መሬቶች እያሉ መሬት ጦም አይደር በሚል በተለይም የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች መሠራታቸውን የጠቀሱት አቶ ከበደ በተለይም ከላይ እስከታች ያለው አመራር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት መሥራት በመቻሉ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ነው የገለጹት። የተመዘገበው ውጤትም አርሶ አደሩን የበለጠ እንዲሠራ ያነሳሳው እንደሆነና ከዚህ በተጨማሪም የአፈር ማዳበሪያ፣ ኬሚካልና ምርጥ ዘርን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ በቶሎ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በቀጣይ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለማሟላት አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም የውሃ አማራጮች ባሉበት አካባቢዎች አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ለአርሶ አደሩ እንዴት ተደራሽ ማድረግ ይቻላል የሚለውን በማጥናት የመለየት ሥራ የሚሠራ እንደሆነ የገለጹት አቶ ከበደ፤ ይህም የበጋ መስኖ ሥራው ከዓመት ዓመት ለማስፋትና ለማሳደግ ጠቃሚ እንደሆነ ነው ያመላከቱት። ለዚህም አርብቶ አደሩን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሙሉ ለበጋ መስኖ ልማት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ያስረዱት።
ከበጋ መስኖ ሥራው በተጨማሪም አሁን ባለንበት የመኸር ወቅት በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የገለጹት አቶ ከበደ፤ ይህም የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ነው ብለዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ የሚደርሰውን ምክረ ሃሳብ መሠረት በማድረግ የደረሱ ሰብሎችን በቶሎ መሰብሰብ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ሜካናይዜሽኖችን ማለትም ኮምባይነሮችን፣ በእጅ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛ የሆኑ አዳዲስና የተሻሻሉ መሣሪያዎችን በመጠቀም እንዲሁም በቡድን፣ በቤተሰብና በልማት አደረጃጀት በመሆን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱንና አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች በሚገጥሙ የዝናብ መቆራረጦች ምክንያት የሚፈጠሩ የምርት እጥረቶችን ለማሸፈን ከሚያስችሉ ሥራዎች መካከል የበጋ መስኖ ሥራ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዝናብ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ከምርት ውጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎችን በመስኖ ልማት ሥራ ለመደገፍ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡
በአሁን ወቅትም ከመኸር ሥራው ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሁለት አይነት ጠቀሜታዎችን የሚያበረክት እንደሆነ ነው ያመላከቱት። አንደኛው በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ በስፋት እየተለመደና ተጠናክሮ መቀጠል ችሏል። ይህ ሁኔታም በምርትና ምርታማነት ላይ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል። ሁለተኛው በተለይም ዝናብ በተቆራረጠባቸው አካባቢዎች ላይ በአካባቢው ያለውን የመስኖ አማራጮች በመጠቀም በቶሎ ወደ ምርት ሥራው ለመግባት አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር በመቻሉ አበርክቶው ጉልህ ነው።
እሳቸው እንዳሉት በሀገሪቱ እየሰፋና ተጠናክሮ የቀጠለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ስለመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በዝግጅት ምዕራፍ ባደረገው ግምገማ ማረጋገጥ ችሏል። በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለመሸፈን ከክልሎች ጋር በመግባባት ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል። በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፈን ይሆናል። ይህም ባለፈው በጀት ዓመት ከተሠራው አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደግ እንደቻለ አስረድተዋል። ይህም እንደ ሀገር በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች እንደሆነና እምርታን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከሚሸፈነው ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 117 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ እንደሆነ ያመላከቱት ሚኒስትሩ፤ ይህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በክረምት ወቅት ከምታለማው የስንዴ መጠን ጋር ሲነጻጸር ተቀራራቢ እንደሆነም ተናግረዋል። ባለፈው በጀት ዓመት ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አካባቢ በመኸር ወቅት የስንዴ ልማትን መሸፈን እንደተቻለ አስታውሰው በዘንድሮ በጀት ዓመት በመኸር ወቅት ብቻ ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።
በበጋ መስኖ እየለማ ያለው የስንዴ ምርት በመደበኛው የእርሻ ሥራ ወቅት ወይም በመኸር ዝናብ ተጠብቆ ከሚሠራው ሥራ ጋር ተቀራራቢ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም ትልቅ እምርታን እያሳየ ያለና በአገሪቱ ያለውን የስንዴ ምርት አስተማማኝ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘውም የተጀመረው የበጋ መስኖ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል በመቻሉ በመስኖ የማምረት አቅምን ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣ መሆኑን እና ዝናብ ባይኖርም በበጋ መስኖ ብዙ መሥራት እንደሚቻል አብራርተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም