የእሁድ ገበያን በማጠናከርና አዳዲስ ስልቶች በመተግበር የዋጋ ንረት የሚፈጥረውን ችግር ማቃለል ይገባል!

 የሸቀጦች ዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል። ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሀብት ምክንያቶች እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው ሲገለፅ ቆይቷል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋጋ ግሽበቱ ክፉኛ ተጎጂ ሆነዋል።

መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት በርካታ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጦ መተግበር ከጀመረ ሰነባብቷል። መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከውጪ ሲገቡም ሆነ ሀገር ውስጥ ሲገበዩ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆኑ በመወሰን መንግሥት የሚያገኘውን ትልቅ ገቢ ትቶ የዋጋ ጫናውን ከሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ ለማቃለል ጥረት ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች ምርት ያለአግባብ በማከማችትና እጥረት ያለ በማስመሰል የሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለሽ የዋጋ ንረት እንዲሁም በደላላዎችና ሕገ-ወጥ የንግድ ተዋንያን አማካኝነት ያለው የተንዛዛ የግብይት ሂደት በምግብ ሸቀጦች ላይ እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና በሚፈለገው መልኩ ለማቃለል አልተቻለም።

ከዚህ አንጻር የቅዳሜና እሁድ ገበያ በተለይም ያለ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እየጨመረ ያላውን የዋጋ ንረት በማርገብ ረገድ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። አምራቾች ሰፊ የገበያ ዕድል፣ ሸማቾች ደግሞ ያለደላላ ጣልቃ ገብነት ባጠረ የግብይት ሂደት በተመጣጠነ ዋጋ እንዲሸምቱ አስችሏል።

የቅዳሜና እሁድ ገበያ በቅርበት ባለባቸው አካባቢዎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች በአጭር የግብይት ሂደት ከአምራቹ በቀጥታ ለሸማቹ በተመጣጠነ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ በዋጋ ንረቱ ቀጥተኛ ተጎጂ ለሆነው የማኅበረሰብ ክፍል የተወሰነ እፎይታን ፈጥሯል። በመሆኑም ግብይቱ ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ቅናሽ በበለጠ ተስፋፍቶ መቀጠል አለበት። ጥረቱና ጅምሩ መልካም ሆኖ ሳለ ግን የግብይት ቦታዎቹ ውስን ከመሆናቸው የተነሳ ኅብረተሰቡ ርቀት ያለው መንገድ የታክሲ ትራንስፖርት ከፍሎ በመሄድ የሚያገኘው ገበያ እምብዛም ተጠቃሚ አያደርገውም። ስለሆነም መልካምን ጅምር በማስፋት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ግን አሁን ካለው በተጨማሪነት በየአካባቢው የግብይት ማዕከላት በመክፈት መስፋፋትና መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

ምክንያቱም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ መንግሥት ከቀየሰው የመፍትሔ አማራጭ በተጨማሪ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች ይበልጥ ተደራሽ የሚሆኑበትን አዳዲስ ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ ይገባል። በዚህ ረገድ ለገበያ የሚያቀርቡትን የምርትና አገልግሎት አይነት ለማስፋትና የግብርና ምርቶችን ከገበሬው ማሳ ላይ ገዝቶ ለማቅረብ የሚታይን የፋይናንስ ችግር ለማቃለልም የበለጠ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።

መንግሥት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የፋይናንስ ችግር ለማቃለል እየሠራ ቢሆንም ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንፃር ባለው አቅም ሁሉ ብዙ መጨመርን ይጠበቃል። የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሕዝብ አገልጋይ እንደመሆናቸው መጠን አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ብድር የሚሰጡበትን ቢሮክራሲ በማቃለልና ብድር በመስጠት ተቀራርበው በመሥራት ሊደግፉ ይገባል፡፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ የዋጋ ንረትን በማርገብ ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ወደሌሎች ክልሎች ተደራሽነቱን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን አዲስ ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ የግድ ይላል። ከዚህ ጎን ለጎን አቅርቦቱን ለማሳደግ እና ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ እድል ለመፍጠርም ማሳ ላይ ሰፊ ሥራ ሊሠራ ይገባል።

የከተማ አስተዳደር፣ የክልልና በየተዋረዱ ያሉ የዘርፉ አስፈፃሚ አካላትም የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም መንግሥት የዘረጋው የእሁድ ገበያ ሊበረታታና በሌሎች አማራጮች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You