ዓለማችን በጦርነት ያልተንበረከኩ ጀግኖችን በፍቅረ ነዋይ፤ በፍቅረ ሥልጣን እና በፍቅረ ብእሲት ስታንበረክካቸው ኖራለች። ፈረንሳዊቷ ሜሪ ሮዝ ጆሴፊኔም ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን የነበራት ሴት ባትሆንም ታላቁን ጀግና ናፖሊዮን ቦናፓርትን በፍቅር አንበርክካ ለንግሥና የበቃች ብላቴና ናት። ፍሬ ነገሩም እንዲህ ነው። ጆሴፊኔ ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለች አንድ ኮከብ ቆጣሪ ቄስ ትኩር አድርጎ ይመለከታታል። ጆሴፊኔም ‘’አባቴ ለምንድን ነው? እንደዚህ አትኩረው የሚመለከቱኝ’’ በማለት ትጠይቃለች። ኮከብ ቆጣሪውም የህፃኗን ኮከብ ቆጥሮ እና ወደፊት ምን ልትሆን እንደምትችል አስቦ እና ገምቶ «ይህ የማይታመን እና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ነገር ነው» አለ ለራሱ። ቀጥሎም “የልጅቱን ኮከባዊ ዕድል ወይንም ትንቢት ልነግራት ይገባል’’ ብሎ ወሰነና ‘’ጆሴፊኔ ወደፊት ዘውድ ትጭኛለሽ ማለት የፈረንሳይ ንግሥት ትሆኛለሽ። የምትነግሽው ግን በባለቤትሽ አማካይነት ነው እንጂ በራስሽ ውሳኔ አይደለም» በማለት እንደ ብሥራታዊ መልአክ አበሠራት። ነገር ግን ትንቢቱ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር።
ምክንያቱም ጆሴፊኔ ከአደገችም በኋላ የቤት እመቤት ሆና ስለነበር ነው። ከዚህም ባሻገር ጆሴፊኔ በቁንጅናዋ ተጠቅማ ወንዶችን ከማጥመድ እና ከማማለል ውጭ ስለፖለቲካ ብዙ የምታውቅ እና የምትጨነቅ ሴት አልነበረችም። የቤት እመቤት ደግሞ ከመሬት ተነሥታ የፈረንሳይ ንግሥት ለመሆን ትችላለች ብሎ በጊዜው ማሰብ የዋህነት፤ አሊያም ቂልነት ነው። ለእርስዋም ትንቢቱ ቀልድ እንጂ እውነት ይሆናል ብላ አላሰበችም። ነገር ግን ጉዳዩ የጆሴፊኔን እናት በእጅጉ አሳሰባቸው እና ኮከብ ቆጣሪውን ፈልገው ሲያነጋግሩት እንዲህ አላቸው። ‘’እመይቴ በደንብ ያስተውሉ፤ እኔ የምናገረው እርስዎን ለማስደሰት ብዬ አይደለም። ለዚሀ ደግሞ ግድ የለኝም። የደረስኩበትን እውነተኛ ነገር እናገራለሁ። ልጅዎ ንግሥት ትሆናለች። ቢሆንም እድሜ ልኳን ንግሥት ሆና አትዘልቅም’’ በማለት ኮከብ ቆጣሪው እና ስለወደፊት ዕድል ነጋሪው ሰው ሐሳቡን ደመደመ።
ሉዊስ 16ኛ መላ ፈረንሳይን ይገዛ የነበረ ንጉሥ ሲሆን፤ እጅግ ሸጋ የነበረቺው ባለቤቱ ማሪየ አንቶይኔቴ በፈረንሳይ የቦርቦን ሥርዎ መንግሥት ወራሾች የሆኑ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወልደውለታል። ጆሴፊኔም በጊዜው የተወለደቺው ከአንዲቱ የቤተ መንግሥት ሠራተኛ ሲሆን፤ አባቷ በዌስት ኢንዲስ ማለት በፈረንሳይ የባሕር ማዶ ግዛት የሮማርቲኒክ ደሴት መስፍን ነበር። የጆሴፊኔ አባት በወቅቱ የንጉሡ የሉዊስ የመጀመሪያ ልጅ ሲነግሥ ጆሴፊኔን እንደሚያገባና አብረው እንደሚነግሡ እምነት ነበረው። ነገር ግን ይህ ሐሳብ ተሠረዘ እና ልጁን ቪስካውንት አሌክሳንደር ቢዩሐርናይስ ለተባለ እና በጆሴፈኔ ፍቅር ለተነደፈ ሌላ የፈረንሳይ መስፍን ዳረለት። ጆሴፈኔም አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ ከመስፍኑ አሌክሳንደር ወልዳለታለች።
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ማለት እ.ኤ.አ. በ1789 በፈረንሳይ የደም ፍጅት ያስከተለው ሕዝባዊ አብዮት (በታሪክ የፓሪስ ኮሚዩን ተብሎ የሚታወቀው) ሲካሄድ ሉዊስ 16ኛ፤ ንግሥት ሜሪ አንቶይኔቴና ሌሎች መሳፍንት እና መኳንንት ተገደሉ። ንግሥት ሜሪ አንቶይኔቴ የፈረንሳይ ድሆች “ዳቦ ራበን” ብለው በፈረንሳይ አደባባዮች ሰላማዊ ሰልፍ በወጡበት ወቅት በመስኮት ላይ ብቅ ብላ “ድሆች ዳቦ ራበን ከሚሉ ለምን ኬክ አይበሉም” በማለት መልስ በመስጠቷ እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካ ፌዝ እና ጨዋታ ትጠቀሳለች።
የጆሴፊኔ ባለቤት የነበረው መስፍኑ ቪስካውንት አሌክሳንደርም አብሮ በሞት ተቀጣ። ጆሴፊኔ ደግሞ ታሠረች። ለአራት ወራት ያህል ከታሠረች በኋላ በወዳጇ /በፍቅረኛዋ/ በጄኔራል ፓውል ባራስ አማካይነት ከእሥራት ተፈታች። ጆሴፊኔ ከጄኔራል ፓውል ባራስ በተጨማሪ ጄኔራል ሆክ የተባለ ሌላ ፍቅረኛም ያዘች። ጆሴፊኔም የሆክ ወዳጅነት አልበቃ ስለአላት «እባክህን ሆክየ ወጣት ነኝ የምትለውን እና ገና ያልበሰለችውን ሚስትህን ፍታና እኔን አግባኝ» በማለት አሽቧቧቺው (አግባባችው) ። ጄኔራሉ ግን «አንድ ሰው እንዳንቺ ዓይነቷን ቆንጆ የምሥጢር ፍቅረኛ አድርጎ ቢያስቀምጥም የሕግ ሚስቱን ግን መፍታት የለበትም’’ በሚል ጆሴፊኔን ከማግባት ተቆጠበ። በዚህ ዓይነት ጆሴፈኔ ሀብታም እና በሌሎች ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚችል ባል ለማግባት በመፈለግ ላይ እንዳለች አንድ ታማኝ ጓደኛዋ ‘’ጀግናው ናፖሊዮን በፈረንሳይ ትልቅ ሰው የሚሆን እና ገና ሚስትም ያላገባ ሰው ነው’’ ብሎ ነገራት። በዚህም ጆሴፊኔ ጀግናው ናፖሊዮን እየተጋበዘ ወደሚሄድበት የምሽት ፓርቲ አምራ፤ ተውባ እና ደምቃ፤ ተሸቀርቅራ እና ተኳኩላ ለመሄድ ተገደደች። ወደ ምሽት ፓርቲ ከሄደች በኋላ ‘’ ውድ ናፖሊዮን ለአንተ ልዩ ክብር የምትሠጥህ ጓደኛህን ፈጽሞ አትጎበኛትም ‘’ ብላ ደብዳቤ ጻፈችለት። ቀጥላም «አንተ እምቢ ብለህ ቀርተሃል። ነገር ግን ተሳስተሃል። ስለሆነም ነገ ናና ምሳ አብረን እንብላ። አንተን ለማየት እፈልጋለሁ። ስለአንተ ፍላጐት ከአንተ ጋር ለመወያየትም እሻለሁ» በማለት ሌላ ደብዳቤ ጽፋ እና ፈርማ ላከችለት።
የጆሴፊኔ ግብዛ ከልክ በላይ መሆኑን የተረዳው ናፖሊዮን ደብዳቤውን እንዳነበበ በምሽት ፓርቲ ላይ አምራ፤ አሸብርቃ እና ደምቃ ያያት ሴት ወይዘሮ መሆኗን አስታወሰ እና ‘’ደብዳቤ በተከታታይ የጻፍሽበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻልም። ይህንን ስል ግን ያንቺን ጓደኝነት ባለመፈለግ እንዳልሆነ እንድታምኚ እለምንሻለሁ። ይህንን ጉዳይ ከምንጩ ለማረጋገጥ እንደ እኔ ስሱ የሆነ ሰው ያለ አይመስለኝም። እንደተመቸኝ እኔ በአካል መጥቼ መልዕክቱን አስተላልፋለሁ» ብሎ ጻፈላት። በቃሉ መሠረትም ናፖሊዮን እና ጆሴፊኔ ተገናኙ። በቀጠሮው ቀን ጆሴፊኔ ቤቷን እጅግ በጣም አስውባ እና ራሷም ተውባ ጠበቀቺው። አቅሟ በፈቀደ መጠን ናፖሊዮንን ሊማርክ በሚችል ዝግጅት ለመቀበል እና መልካም ምሳ አዘጋጅታ ለመጋበዝ በአደረገቺው ጥረት ለእርሱ ያላትን አክብሮት እና የፍቅር ስሜት ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም። በዚህ ዓይነት ናፖሊዮን የጆሴፊኔ ቤተኛ ከሆነ በኋላ ሁለቱም በፍቀር ተሣሠሩ። በዚሁ ሁኔታ ላይ እያሉ ናፖሊዮን ውድ እና ንዑድ የሆኑና በውድ ዋጋ የተገዙ ስጦታዎችን ሲያበረክትላት የቀድሞ ፍቅረኛዋ ጀኔራል ባራስ ተመለከተና እንዲህ ሲል ናፖሊዮንን መከረው።
‘’ለማዳም ቡሜይስ የምታወጣውን ገንዘብ ለቤተሰብህ ጠቀሜታ ብትልከው ይሻላል። ጆሴፊኔን የተንከባከብከው ከወታደሮችህ ውስጥ ምርኮ እንደሚካፈል እንደ አንዱ ተዋጊህ አድርገህ ነው።’’ ናፖሊዮን ግን ይህንን የጀኔራል ባራስን ምክር ከመጤፍ ሳይቆጥር «ይህ ያበረከትኩላት ውድ ስጦታ ለሠርጋችን የተዘጋጀ ቢሆንስ ምን ትላለህ?’’ ብሎ ፓውል ባራስን አሳፈረው። ጄኔራል ባራስ በወቀቱ ጆሴፊኔ ናፖሊዮንን ለማግባት በመዘጋጀቷ ውስጥ ውስጡን ቢናደድም «ጆሴፊኔ እንኳን ደስ አለሽ። ጥሩ ባል ልታገቢ ነው’» በማለት መልካም ምኞቱን ገለጠላት። ጆሴፊኔ ግን ነገሩን እያቃለለች እና የአዞ ዕንባ እያፈሰሰች ‘’ባራስየዬ እኔ‘ኮ ከልቤ የማፈቅረው አንተን እንጂ ቦናፖርትን አይደለም። እኔ እርሱን የማገባው አፍቅሬው ወድጄው ሳይሆን፤ ማኅበራዊ ክብር እና ልዕልና ለማግኘት ስል ብቻ ነው» በማለት ተናዘዘች። በተቃራኒው ከናፖሊዮን ጋር በነበሩበት ጊዜ ደግሞ «ውድ ናፓሊዮንዬ! ናፕየዬ! ይህን ሽማግሌ ጄኔራል ባራስን (ሼባው ባራስን) አላፈቅረውም። ምክንያቱም ያለ ጥፋቴ አሥሮ ለአራት ወራት ያህል አጉላልቶኛል። ከዚህም ባሻገር ባለቤቴንም አስገድሎብኛል’’ አለቺው።
ጆሴፊኔ በእንደዚህ ዓይነት ድብብቆሽ / ድራማዊ ጨዋታ/ የምታፈቅረው መስላ ናፖሊዮንን ድል ከመታች በኋላ እ.ኤ.አ. መጋቢት 9 ቀን 1796 በማዘጋጃ ቤት ተፈራርመው ጋብቻቸውን ፈፀሙ። በጋብቻቸው ላይ ከአብዮቱ ማለት ከፓሪስ ኮሚዩን በፊት በፈረንሳይ መንግሥት ውስጥ ታላቅ ተሰሚነት የነበረው ጄኔራል ባራስ እና ዕቁባቱ እመት ታሊየን ተገኝተዋል። በወቅቱ ናፖሊዮን ማዘጋጃ ቤት ለመድረስ ከያዘው ቀጠሮ ለሁለት ሰዓት ያህል ስለዘገየ ‘’ጆሴፊኔ የማይረባ ሰው ለጋብቻ መረጠች። ምናልባትም ሐሳቡን ቀይሮ ሊሆን ይችላል’’ ብላ በእጅጉ ተበሳጭታበት ነበር። ነገር ግን ዘግይቶም ቢሆን ናፖሊዮን በጥቂት ጓደኞቹ ታጅቦ መጣና የቀለበቱ ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ። ከተጋቡ ከሦስት ቀናት በኋላ ግን ግዳጁን ለመፈፀም ሲል ውድ ባለቤቱን ተሰናብቶ ወደ ኢጣልያ ጦር ግንባር ዘመተ።
ናፖሊዮን ከፈረንሳይ ወደ ኢጣልያ ከሄደ በኋላ ከረዳቶቹ አንዱ የሆነውን እና ጃኖት የተባለውን ደብዳቤ አስይዞ ለጆሴፊኔ እንዲያደርስ ወደ ፈረንሳይ ላከው። የደብዳቤው መልዕክትም ‘’ ጃኖት አንቺን ሳይዝ አይመለስም። እዚሁ ኢጣልያ ውስጥ ከእኔ ጋር ትሆኛለሽ። በልቤ ውስጥ፣ በክንዴ ላይ በከንፈሬ ላይ ስለማኖርሽ ክንፍ አውጥተሽ እና በርረሽ ነይልኝ የሚል ነው። ነገር ግን ጀሴፊኔ ወደኢጣልያ ለመሄድ ፈቃደኛ ስለአልሆነች ጃኖት ብቻውን ተመለሰ። ምክንያቱም ናፖሊዮን ከልቡ አፍቅሯት ጆሴፊኔ ግን ማኅበራዊ ዕውቅናን ለማግኘት ብቻ ስትል ስለተጋቡ ነው። በመሆኑም ባለቤቷ ወደ ጦር ግንባር ከመሄዱ ጀምራ ፍቅር በመሥራት ያሳበደቺውን እና ሂፓሊቴ ቻርለስ የተባለውን ወጣት መኮንን አፍቅራ ፓሪስ ውስጥ በደስታ መኖር ጀመረች።
ናፖሊዮን በየዕለቱ ደብዳቤ ቢጽፍላትም አልፎ አልፎ ጥቂት መስመሮች ከመጻፍ ውጭ የሞተ ያህል ረሳቺው፤ ዘነጋቺው። በሌላ ጊዜም በታማኝ ጄኔራሉ በሙራት እጅ ሌላ ደብዳቤ እንዲህ ብሎ ሰደደላት ‘’ለኑሮ ምቹ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እዚህ ኢጣሊያ ውስጥ ታገኛለሽ። አሽከሮች፣ ውድ ልብሶች፣ የምትዝናኚበት ብርቅየ ውሻ—- ’’ ጆሴፊኔ ደብዳቤውን ከአነበበች በኋላ ‘’ ለካ ናፖሊዮን በጣም ቀልደኛ ነው» ብላ ፈገግ አለች። በመሆኑም ማስመሰያ ሐሳብ በማሰብ እርጉዝ እንደሆነች እና ከባድ መንገድ እስከ ኢጣልያ ድረስ ለመሄድ እንደማትችል ለጄኔራል ሙራት ነግራ ይቅርታ ጠየቀቺው። ሙራትም እውነት መስሎት የምሥራቹን ተቀብሎ ወደ ኢጣሊያ ተመለሰ እና ለናፖሊዮን አበሠረው። ናፖሊዮንም ባለቤቱ እርጉዝ መሆኗን ከጄኔራል ሙራት ሲሰማ በደስታ ሠከረ። ጆሴፊኔ ወደ ኢጣሊያ ያልሄደቺው በእርግዝና ምክንያት መሆኑንም ተገነዘበ።
ጀግናው ናፖሊዮን በሚያካሂደው ጦርነት በድል ላይ ድል እየተጎናጸፈ ቢሄድም፤ የፍቅረኛው የጆሴፊኔ ምስጢራዊ ባሕርይ በእጅጉ አሳስቦት ነበር። ይህንኑ በተመለከተ ዮሴፍ ለተባለው ወንድሙ ደብዳቤ ሲጽፍ ‘’እኔ ተስፋ ቆርጫለሁ። በዓለም ላይ እንደ እርሷ ያፈቀርኳት ሴት አትኖርም። የጆሴፊኔ ሁኔታ ግን የሚያሣዝን ነው። አዕምሮዬን ስቻለሁ። ያለ እርሷመኖር አልችልም።’’ ጆሴፊኔ ዮሴፍ በሙራት በኩል ናፖሊዮን የጻፈላትን ደብዳቤ ለጄኔራል ባራስ ሰጠው። ባራስም ጆሴፊኔ በአስቸኳይ ወደ ናፖሊዮን እንድትሄድ አዘዛት።
ጆሴፊኔ የጀኔራል ባራስን ሐሳብ ተቀብላ ከፍቅረኛዋ ከቻርለስ ጋር ወደ ሚላን /ኢጣልያ/ በሄደችበት ጊዜ ናፖሊዮን ከልቡ ከመደሰቱ የተነሣ ምድር ጠበበችው። ስሜቱን ለመቆጣጠር ካለመቻሉም ባሻገር ዕንባውም በጉንጩ ሳይፈስ። በዚያው ምሽት ጆሴፊኔ ለፍቅሩ አፀፌታ እንዳልሰጠቺው፤ ከልቧ እንዳላፈቀረቺው እና እንደረሳቺው ግን ለራሷ ደስታ ብቻ እንደተፈጠረች ዓለምም እርሷን ለማስደሰት እንደተፈጠረች እርሱ ግን በጭንቀትና ደስታ ርቆት እንደሚኖር የሚያስረዳ ደብዳቤ ጻፈላት። (ከተገናኙ በኋላ እንዴት በደብዳቤ!!)
በኢጣሊያ ጦር ሜዳ በሚያዋጋበት በዚያ ወቅት ናፖሊዮን ፎቶ ግራፏን በየቀኑ ከኪሱ ቦርሳ እያወጣ ሲመለከተው እና ሲስመው ነበር። በጆሴፊኔ ምክንያትም ራሱን ጥሎ ታይቷል። አይበላ፣ አይጠጣ፣ አይተኛ፤ አያስተኛ ከቀን ወደ ቀን ሰውነቱ እየቀነሰ /እየቀጠነ/ መጣ። ጆሴፊኔ አታፈቅረኝም ብሎም ከልቡ አለቀሰ።
ጆሴፊኔ ሚላን ውስጥ በእንግድነት እንዳለችም ፍቅረኛዋን ቻርለስን ይዛው እንደመጣች ስለተረዳ በእርሷ ላይ ፈጽሞ እምነት አጣ። ጆሴፊኔ እና ቻርለስ ሁለት ቀናት ሚላን ውስጥ ከቆዩ በኋላ ወደ ፓሪስ ተመለሱ። እ.ኤ.አ. ሐምሌ 13 ቀን 1798 የውጊያውን አድማስ አስፍቶ ወደ ግብፅ እንደመጣ ዘጠኝ ዓመት ከሚያንሳት እና ልቧን ከበላው ከወጣቱ ፍቅረኛዋ ከኮሎኔል ሂፖሊቴ ቻርለስ ጋር ለመጋባት እንደወሰኑ ናፖሊዮን ቦናፓርት ከታመኑ የዜና ምንጮች አረጋገጠ። ከዚህ በኋላ ከጆሴፊኔ ጋር መፋታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተረዳ። ‘’በቅንዓት ከመቃጠል መፍታት መፍታት በስንት ጣሙ’’ ሲልም ለራሱ አጉመተመተ። (አጉተመተመ)
የሁለቱ ማለት የቻርለስ እና የጆሴፊኔ ፍቅር የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ26 ሠኔ 1796 ነው። ናፖሊዮንም ከአንድ ዓመት የጦር ሜዳ ቆይታው በኋላ ማለት እ.ኤ.አ. ኅዳር 11 ቀን 1799 ዓ.ም በድል አድራጊነት ወደ ሀገሩ ተመልሶና በፈረንሳይ የመጀመሪያው ኮንሱል ሆኖ በሉግዘምበርግ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተቀመጠ። መላ የፈረንሳይ ዕድልም በእርሱ ቁጥጥር ሥር ሆነ። ባለቤቱ ጆሴፊኔ ለእርሱ ታማኝ እንዳልሆነች እና እንደማታፈቅረው አውቆ ፍቺውን ቢፈልግም ፍቅሩ የተለየ ስለነበር፤ ከፍተኛ ጫና አደረገበት እና እንደገና በስሜቱ ፈለጋት። ነገር ግን በወቅቱ ጆሴፊኔ በምትኖርበት ቤተ መንግሥት ውስጥ የቁም እሥረኛ ሆና ነበር።
ናፖሊዮን በፈረንሳይ የመጨረሻው የጦር መሐንዲስ እና አርቢትር ስለሆነ፤ እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 2 ቀን 1804 ዓ.ም ‘’ ግርማዊ የፈረንሳይ ንጉስ’’ ተብሎ ነገሠ። ሥርዓተ ንግሡን የኖትሬ ዳም ቤተ ክርስቲያን እጅግ ደማቅ በሆነ እና በአማረ ሁኔታ አክብራዋለች። ናፖሊዮን በሰረገላ ላይ ሆኖ እና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ዘውድ በደፋበት ዕለት የንግሥናውን ሥነ ሥርዓት ብቻውን ማከናወን ስለአልፈለገ ጆሴፈኔ አብራው ‘’የፈረንሳይ ንግሥት’’ ተብላ እንድትነግሥ አደረገ።
ቆንጆ፣ ለግላጋ፣ ሸንቃጣ እና ወገበ ቀጭን የሆነቺው፤ ገና ከ25 ዓመት ያላለፈቺው እና መቀነቷን ያልፈታች ልጃገረድ የመሰለቺው ጆሴፈኔም በቤተ መንግሥት ዘውዳዊ አለባበስ ተሽቀርቅራ እና ተንቆጥቁጣ በአልማዝ እና በወርቅ የተሠራውን ዘውድ ናፖሊዮን በራሷ ላይ ሲያደርግላት ከጽርሐ አርያም የወረደች ዕንቁ መሰለች። የንግሥናዋ ትንቢትም በዚሁ ተፈፀመ። ንግሥቲቱ ግን በናፖሊዮን ላይ የፈፀመቺው ድርጊት ደስታ እና ሰላም አልሰጣት አለ። የእርሱም አዕምሮ ሰላም አጣ። በመጨረሻ ተፋቱ። ጆሴፊኔም እስከ መጨረሻ በንግሥትነት ቆይታ እንደማትሞት አስቀድሞ ከኮከብ ቆጣሪው ቄስ ስለተረዳች ከናፖሊዮን ጋር በመፋታቷ ብዙም አላስጨነቃትም ። እርሱም ሜሪ ሉዊስን አግብቶ የተመኘውን ልጅ ለመውለድ በቃ። ነገር ግን ጆሴፊኔን ሊረሳት አልቻለም። እ.ኤ.አ. በ1814 በሕዝብ አመፅ ከሥልጣን እንዲወርድ ተደርጎ «ኢልባ»በተባለ ቦታ ውስጥ ታሠረ።
ነገር ግን ከእሥራት አምልጦ ወደ ፓሪስ መጣ እና ጆሴፊኔ ትኖርበት ወደነበረው ማልሜይሰን ቤተ መንግሥት ገባ። ሽጉጡን ተኩሶም ራሱን በራሱ አቆሰለ። በዚህ ጊዜ ጆሴፊኔ ተደናግጣ ‘’ናፖሊዮን ኢልባንኦ (ወይኔ ናፖሊዮን)» በማለት እሪታዋን አቀለጠቺው። እንደገናም ተይዞ ተጋዘ። እ.ኤ.አ ግንቦት 1821 ዓ.ም ከመሞቱ በፊትም ‘’ጆሴፊኔን ጥሩልኝ’’ ብሎ ዓይኑን ዘጋ፤ ከንፈሩን ገጠመ፤ የመጨረሻ እስትንፋሱንም ዋጠ!
ምንጭ ፡-Naimisharan Mittal,(1994) World Famous Romances of Great People.
ዘመን መጸሄት መጋቢት 2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)