ልጆች ስለጤና አጠባበቅ…

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ልጆች ሀገራችን በርካታ ምሳሌዊ አነጋገር፣ ተረት እና ምሳሌ እንዲሁም የተለያዩ አባባሎች እንዳሏት ታውቃላችሁ አይደል? በእርግጥ ልጆችዬ ዛሬ ስለ አባባሎቻችን እንዲሁም ተረት እና ምሳሌ ልንነግራችሁ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዛሬ ርዕሰ ጉዳያችንን ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› በሚለው አባባል ለመጀመር ስለወደድኩ ነው። ልጆችዬ የዚህን አባባል ትርጉሙን ታውቁታላችሁ? ለምታውቁት ሳይሆን ለማታውቁት ምን መሰላችሁ? አንድ ሠው ከመታመሙ በፊት አስቀድሞ ቢጠነቀቅ እና ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ሁሉ ቢያደርግ ራሱን ከበሽታ መከላከል ይቻለዋል እንደማለት ነው። በተጨማሪም በበሽታው ምክንያት ጉዳት እንዳይገጥመው እና እንዳይንገላታ ይረዳዋል ማለት ነው። ልጆችዬ ጠቃሚ ምክር ነው አይደል? ‹‹በሚገባ›› እንዳላችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ልጆችዬ አስተውላችሁ ከሆነ ከሰሞኑን ራሳችሁን ወይም ቤተሰባችሁን፣ ጓደኞቻችሁን ወይም መምህራኖቻችሁን ብቻ በቅርብ የምታውቋቸው ሰዎች ጉንፋን ወይም መሰል ነገር ተይዘው ታመው ተመልክታችሁ ይሆናል። የጤና ሚኒስቴርም ከሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተስተዋለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት መግለጹን ሰምታችኋል ብዬ እገምታለሁ።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ መከሰታቸውን አረጋግጧል። በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ-ኃይል ዋና አስተባባሪ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ ተከስቷል። የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን በሁለት ሺህ ያህል ናሙናዎች ላይ ባደረጉት ምርመራም የበሽታውን መከሰት ማረጋገጣቸውንም መገናኛ ብዙኃን መረጃውን ለሕዝብ እንዲደርስ አድርገዋል።

የትንፋሽ አቅም ማነስ፣ የሰውነት መቆረጣጠምና የድካም ስሜቶች ከሕመሙ ምልክቶች መካከል እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ቫይረሱ ሳምባ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ደረጃ ሲደርስ ሳል፣ ከፍተኛ የሆነ የትንፋሽ ማጠርና ሌሎች ምልክቶች እንዲስተዋሉ ያደርጋል። ስለዚህም ምልክቶቹ የታየበት ሠው በአፋጣኝ በጤና ተቋማት ሕክምና ማግኘት እንዳለበት የሕክምና በላሙያዎቹ ይመክራሉ። ልጆች በሽታው ሕዝብ በሚበዛባቸው በትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ሥፍራዎች፣ የእምነት ቦታዎች በስፋት የመሠራጨት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባችኋል። እንዲሁም በከተሞችና ከፍተኛ መቀራረብ ባለባቸው የመኖሪያ ሥፍራዎች ጭምር የመስፋፋት አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል ስለሚታመን፤ ልጆችም ሆኑ ወላጆች ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

እጅ በመታጠብ፣ አፍና አፍንጫን በመሸፈን በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል እና በበሽታው የተያዙ ሰዎች በቂ እረፍት በመውሰድ፣ ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች በመጠቀምና ተገቢውን ሕክምና በማግኘት ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ባለሙያዎቹ መክረዋል። የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረሃሳቦች በመተግበር፣ በርና መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ የኢንፍሌንዛ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የሕመም ምልክት ከታየባቸው አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል። በትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ እና ሠዎች በሚበዙባቸው ስፍራዎች በቂ አየር እንዲኖር በማድረግ እና ለተማሪዎች በተከታታይ ግንዛቤ በመፍጠር በሽታው ከሚያደርሰው ሕመም ራስን ብሎም ሌሎችን ለመከላከል ያስችላል።

ልጆችዬ ምንም እንኳን አሁን ላይ በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አናሳ እና የሚያደርሰውም ጉዳት ቀንሷል ቢባልም፤ ኮቪድ በተቀሰቀሰበት ወቅት ይደረግ የነበረውን ጥንቃቄ አሁንም መተግበር ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪም በየመንገዱ ያለው መጥፎ የቱቦ ሽታ እንዲሁም በየመንገዱ የሚጣሉ ቆሻሻዎች ለጉንፋን እና መሰል በሽታ አጋላጭ መሆናቸውን በመረዳት ማስክ አድርጎ መንቀሳቀስም ተገቢ ነው።

ሌላው ደግሞ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ጉንፋን የያዘው ተማሪ ካለ ወደ ሌላ ተማሪ በተለያየ መንገድ ሊተላለፍ እንደሚችል በመገንዘብ፤ ማስክ በማድረግ፣ እጅን በሳሙና ቶሎ ቶሎ በመታጠብ (ሳኒታይዘር በመጠቀም) ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ሲሆን፤ ሳል፣ ራስ ምታት እና ሌሎች ምልክቶች ካልጠፉ ግን ቸል ከማለት ይልቅ ለቤተሰብ በማሳወቅ ወደ ሕ ክምና ጣቢያ ማምራት ያስፈልጋል።

በተለይም በዚህ ዓመት ትምህርት የጀመሩ ሕፃናት እንዲሁም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን የጤና ሁኔታ በመከታተል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መምከር ብሎም እገዛ ማድረግ ከመምህራን እና ከወላጆች (አሳዳጊዎች) የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ስለዚህም ልጆችዬ ታማችሁ ከትምህርታችሁ እንዳትስተጓጎሉ እና በበሽታው ምክንያት ጉዳት እንዳይረስባችሁ አድርጉ የምትባሉትን የጥንቃቄ ምክሮች በመስማት እና በመተግበር ራሳችሁን ከበሽታ እንድትከላከሉ ያስችላችኋል። በሉ ልጆችዬ ለዛሬው በዚህ እናብቃ። ሁሌም እንደምንላችሁ ትምህርታችሁን በሚገባ ተማሩ፣ አጥኑ፣ የግል ንጽህናችሁን ጠብቁ።

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2016

Recommended For You