ኮንታና ዳውሮ፤ ድንቅ የተፈጥሮ እጅ ሥራ

መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም ማለዳ ከአዲስ አበባ የተነሳው የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያደርገውን ጉዞ ጀምሯል። በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና በቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው የሚዲያዎች ጉዞ፤ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ ዓላማው አድርጎ ወሊሶን ተሻግሮ፣ ወልቂጤን አቋርጦ፣ ጅማ አረፍ ብሎ በአመያ አዳሩን አድርጓል።

የጋዜጠኞቹ ቡድን በማግስቱ ጥቅምት 17 ደግሞ የግማሽ ቀን ጉዞ አድርጎ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን በመጎብኘት በኮንታ ዞን የሚያደርገውን ቅኝት ጀምሯል። በቀጣይ ቀናት ደግሞ ጨበራ ጩርጩራ ፓርክን፣ የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደትን፣ የዳውሮ ዞን ሙዚየምን፣ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ፣ የሃላላ ኬላ ግንብና መዝናኛ ሎጅን ለተከታታይ አምስት ቀናት ተጎብኝተዋል። በዚህ የጉዞ ማስታወሻ የኮንታና ዳውሮ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦችን ከብዙ በጥቂቱ እንቃኛለን።

የተፈጥሮ ግርማ ሞገስ

ተፈጥሮ ጥበቧንና ግርማ ሞገሷን የምትገልጥባቸው ጥቂት ሥፍራዎች አሉ። ጫካው ሳይመነጠር፣ ወንዞች ሳይበከሉ፣ ተራሮች ሳይናዱ፣ የዱር እንስሳት ሳይጠፉ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ሳይዳቀሉ፣ ንፁህ የተፈጥሮ ውበትና ማራኪ ገፅታ ለማግኘት በተለይም በዚህ ዘመን አዳጋች ነው።

ዓለም በተፈጥሮ ሀብቶች ውድመት ምክንያት በተፈጠረ የአየር ንብረት መዛባት እየተጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ኮንታና ዳውሮ ዞኖች ድንግል የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን ይዘው “ኑ ተደመሙብኝ” ይላሉ። በእርግጥም በተፈጥሮ ውበት መማረክ የሚፈልግ ሰው ኮንታና ዳውሮ ዞኖችን ሊጎበኝ ይገባል።

በእነዚህ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲደርሱ በአራቱም አቅጣጫ በተራሮች ይከበባሉ። ከፊትዎ፣ ከኋላዎ እና ከጎንዎ አስደናቂ የተራሮች ሰንሰለት ይከብዎታል። ኮንታና ዳውሮ ፈጣሪ በተራራ ክምሮች የጻፋቸው ምድሮች ናቸው። በእነዚህ ማራኪ የተራራ ክምሮች መካከል መገኘት መንፈስን ያድሳል። ተራሮቹ የተላበሱት ጥብቅ ደን በወፎች ዝማሬ ጆሮዎትን ይማርካል፣ አረንጓዴነቱም የዐይን ምግብ ነው።

የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ

በኮንታና ዳውሮ ዞኖች ከሚገኙት አስደማሚ ቦታዎች የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ እንዱ ነው። ኮንታና ዳውሮን የሚያጎራብተው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ አያሌ ወንዞች፣ ሀይቆችና ፏፏቴዎችን አቅፎ ይዟል። ይህም የሞቃታማውን አካባቢ ግለት እረስተው የመቀዝቀዝ ፋታ ለማግኘት ያስችላል። ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ከ137 በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎችን፣ በቁጥር 57 መካከለኛና ትልልቅ አጥቢ የዱር እንስሳት አይነቶችን፣ ሀገር በቀል ጥንታዊ ዕፅዋትን፣ የተፈጥሮ ፍልውኃዎችን፣ ሐይቆችን፣ ፏፏቴዎችንና ሌሎች የተፈጥሮ መስህቦችን በውስጡ ይዟል። በፓርኩ የሚገኙ ፍልውኃዎች ለተለያዩ ህመሞች ፍቱን መድኃኒት ናቸው።

ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምዕራብ ክልል በኮንታ እና በዳውሮ ዞኖች ውስጥ ይገኛል። ወደ ፓርኩ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ በወላይታ ሶዶ ታርጫ ኢሰራ አልያም በአዲስ አበባ ጅማ አመያ መጓዝ ይቻላል።

ከአዲስ አበባ በጅማ 465 ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሚያገኟት አመያ ከተማ የብሔራዊ ፓርኩ ደጀን ከሚባሉት ከተሞች አንዷ ናት። አመያ የኮንታ ዞን መዲና ስትሆን በደን የተሸፈነች፣ አስደናቂ የመልከዓ ምድር አቀማመጥ ያላት ለቅንጡ ሎጆች ምቹ በሆነ መልከዓ ምድር ላይ ያረፈች ከተማ ናት።

አስደማሚው የሃላላ ኬላ ሪዞርትና የኮንታና ዳውሮ ታሪካዊ መስህቦች

የአካባቢውን የቱሪስት የስበት ማዕከላዊነቱን ወደ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻ የቀየረው አዲሱ የሃላላ ኬላ ሪዞርት የተገነባው በዚህ በጨበራ ጩርጩራ ፓርክ አቅራቢያ ነው። የኦሞ ወንዝን ተንተርሶ የተገነባው ሃላላ ኬላ ሪዞርትም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ወደ አካባቢው የሚስብ ሌላኛው የገበታ ለሀገር ትሩፋት ነው።

ይህ ሪዞርት ምቹ ማረፊያዎች፣ መዋኛ ገንዳዎች፣ ሬስቶራንት፣ ባሕላዊና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ፣ የጀልባ ላይ ሽርሽር፣ ማራኪ ገፅታን የሚያመላክቱ ቴራሶች፣ በንጉሥ ሃላላ አማካይነት ከድንጋይ የተሠሩ ግንቦችን ጥበብ የሚያንፀባርቅ ግንባታ ወዘተ ያለበት ምቹ የቱሪዝም ሥፍራ ነው። ሪዞርቱ ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስተናገድም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የተገነባ መኾኑ የመስህብነቱ ተጨማሪ ኃይል ነው።

በመስከረም ወር የሚከበሩት “ሀንግጫ” እና “ቶኪ በአ” የተሰኙት የኮንታና የዳውሮ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ተጨማሪ የአካባቢው የቱሪዝም ሀብቶች ሲኾኑ፤ በዓላቱን በአካል ተገኝቶ ማክበርም ልዩ ትዕይንትና ትዝታ የሚሸመትበት ነው። በእነዚህ በዓላት የአካባቢዎቹ ጥንታዊና ባሕላዊ እሴቶች ከምንግዜውም በላይ የሚደምቁበት ነው።

ሃላላ ኬላ፡ የኢትዮጵያ ታላቁ ግንብ

ከሃላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ ጋር የተካተተው የንጉሥ ሃላላ ግንብ በአካባቢው ያለ ሌላኛው ታሪካዊ ቅርስ ነው። የንጉሥ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) የተገነባበት ዋና ዓላማ ዳውሮን ከአጎራባች የፈረሰኛና እግረኛ ጦር ጥቃት ለመከላከል እንደሆነ ይነገራል። የድንጋይ ካቡ የጠላት መግቢያና መውጫ እንደሚሆኑ በሚገመቱ አካባቢዎች የጦር በሮች በማዘጋጀት፣ በእያንዳንዱ የጦር በር ጠባቂ ሹም (Miis’aa Iraasha) ሹመት በመስጠት፣ የግዛት ወሰንና የሕዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ ነበር።

የካዎ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ኬላ) መገኛ በዳውሮ ዞን ኦሞ ወንዝን ተከትሎ ነው። ከዳውሮ ዞን ወረዳዎች መካከል ኢሠራ፣ ዲሳ፣ ሎማ፣ ዛባ ጋዞ፣ ጌና፣ ታርጫ ከተማ አስተዳደርና ታርጫ ዙሪያ ወረዳዎችን በማካለል ጋሞ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ከምባታ ጠንባሮ፣ ጅማ ዞኖንና ኮንታ ዞን መሻገሪያ ድንበሮችን ያካለለ ታሪካዊ የዳውሮ ንጉሥ ጥንታዊ የኪነ-ሕንፃ ግንባታ ጥበብና የዳውሮ ሕዝብ የጥንካሬ መገለጫ ነው። የሃላላ ኬላ ግንብ ከ1532 እስከ 1822 ዓ.ም. በሀገር በቀል ዕውቀት የተገነባ ነው።

“ሃላላ” የዳውሮ ንጉሥ መጠሪያ ሲሆን፤ “ኬላ” የሚለው የድንጋይ ካብ (የመከላከያ ካብ) የሚል ትርጓሜ አለው። ካዎ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ሀላላ ኬላ) በአንድ ረድፍ 175 ኪ.ሜ. እና አጠቃላይ ርዝመት በሰባት ረድፍ 1225 ኪ.ሜ. ይሸፍናል። ከ2.5 እስከ 5 ሜትር ስፋትና ከ2.5 እስከ 3.8 ሜትር በላይ ከፍታ አለው። በውበቱ አግራሞትን የሚፈጥረው ይህ ኪነ-ሕንጻ የዳውሮ ሕዝብን ጥንታዊ ሥልጣኔ የሚያሳይ ነው።

የግንባታው ሂደት 350 ዓመታት የፈጀው ሃላላ ኬላ ግንብ፤ ከ15ኛው እስከ 18ኛው ክ/ዘመን ዳውሮ ዞንን ያስተዳድሩ የነበሩ 14 ነገሥታት በቅብብሎሽ የገነቡት ነው። ከቻይናው ‘ታላቁ ግምብ’ እና ከፐርሺያው ‘ባቢሎን’ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የድንጋይ ካብ አፍሪካ ውስጥ መኖሩ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን ሰፋ ላለ ጥናት ይጋብዛል።

ሃላላ ኬላ የሚገኝበት የዳውሮ ዞን ከአዲስ አበባ በሻሸመኔ ወላይታ ሶዶ 455 ኪ.ሜ.፤ ከአዲስ አበባ በጅማ ደግሞ 479 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል።

የኮንታና ዳውሮ ባሕላዊ መስህቦች

የኮንታና ዳውሮ አካባቢዎችን የቱሪዝም መስህብነት ከሚያጎሉ ጉዳዮች ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ነው። በአካባቢዎቹ የሚገኘው ማኅበረሰብ እንግዶችን በደስታና በእንክብካቤ ይቀበላል። ልክ እንደ ተፈጥሯዊ ንፁህ ውበቶቹ ኹሉ፤ የኮንታና ዳውሮ አካባቢ ማኅበረሰብም ከልብ በመነጨ አክብሮት እንግዶችን ተቀብሎ ያስተናግዳል። ይህም ጎብኚዎች ያለምንም ስጋት በአካባቢዎቹ ተገኝተው ለቀናት አሊያም ለሳምንታት በአካባቢው እንዲቆዩ ያደርጋል።

ኮንታና ዳውሮ ደርሰው የአካባቢውን ውብ ዜማና ውዝዋዜ መታደም ተጨማሪ ገፀ በረከት ነው። በባሕላዊ መሣሪያዎች የሚቀነባበረውን ሙዚቃ ከኦርጂናል ውዝዋዜ ጋር መመልከት ተጨማሪ የደስታ ምንጭ ይፈጥራል።

“ቴመናይ ቴማ

ኤ ኮንታ ሎሜ”

“ዳውሮ ባና ዳውሮ ባና

ኤሰ ባና ኑኒ ባና”

የሚሉትን ስንኞች በውብ ዜማ የማጣጣም ዕድል የሚገኘው በኮንታና ዳውሮ ምድር ሲገኙ ነው። ከእንሰት፣ ከቅቤና ከአይብ የሚሠሩ የአካባቢዎቹ ባሕላዊ ምግቦችም ሰውነትን የሚገነቡ፣ መልክን የሚያስውቡ ስለመኾናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በኩራት የሚመሰክሩት ሀቅ ነው። በዳውሮ ዞን የተገኘ የሥጋ አፍቃሪ የኾነ ሰውም ብርንዶ ሥጋ ከመኻል ከተማ በግማሽ በሚቀንስ ዋጋ መመገብ ይችላል።

የድንጋይ ከሰልም ሌላው የዳውሮ ዞን ተፈጥሯዊ ሀብት ነው። በድንጋይ ከሰል ልማት ለመሰማራት ለሚፈልግ ባለሀብት ዳውሮ ተመራጭ ቦታ ነው።

በኮንታና ዳውሮ ዞኖች ያለው እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር ልማትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ አካባቢው ያለው አቅም የመጪው ጊዜ የቱሪዝም ልማት መዳረሻ የሚኾን ነው። መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው አምሥት የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዘም መኾኑ ደግሞ፤ በአካባቢዎቹ ላይ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ላሉ እና ወደፊትም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኹሉ አበረታች ዜና ነው።

ውብ የተፈጥሮ ፀጋ የተጎናፀፈው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፤ በገበታ ለሀገር ፕሮጀከት እየተገነቡ ካሉ የመዝናኛ ሎጆች ጋር ተዳምረው የአካባቢውን መስህብነት የበለጠ የሚያጎሉ ናቸው። ወደ ፓርኩ የሚያደርሱ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እና የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በተሟላ ሁኔታ ሲጠናቀቁ ለጎብኚዎች እጅግ ምቹ መዳረሻ ይኾናል።

እንደ ኮንታና ዳውሮ ኹሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ያላቸውን አካባቢዎች በስፋት ማስተዋወቅ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በብዛት መዘርጋትና መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት እንዲሁም ለሀገር ገፅታ ግንባታ መሠረት ነው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ የቱሪስት መስህብና መዳረሻዎች በስፋት ቢታወቁና ሊጎበኙ እንደሚገባ ሥፍራዎቹን የጎበኙ ኹሉ ይመክራሉ። በአካባቢዎቹ የተገኙ ጋዜጠኞችም ይህንኑ ሀሳብ ይጋራሉ።

ኢትዮጵያ ተነብባ የማታልቅ መጽሐፍ፣ ተጽፋ የማትጨረስ ድርሳን ስለመኾኗ የደቡብ ምዕራብ አካባቢ ስነምህዳር የቱሪዝም ሀብቶች ምስክር ናቸው። በእነዚህ ሥፍራዎች ተገኝቶ ጉብኝት ማድረግ ከመዝናናትም በላይ ነው። ከንፁህ ተፈጥሮ ጋር መገናኘት፤ እንቁ ባህል ውስጥ መገኘት፣ የሀገርን አንድ ገፅ ማወቅ ለሚፈልግ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እጃቸውን ዘርግተው ይጠብቃሉ።

ከመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ኤልያስ ጌትነት እና እዮብ ሰለሞን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You