ኢትዮጵያን የሚወክል የአትሌቲክስብሔራዊ ቡድን ሊኖር ይገባል!

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በበጎ ከታወቀችባቸው ጉዳዮች መካከል አትሌቲክስ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ይህ ስፖርት የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም ከፍተኛ ሚናም አለው። ቀደም ባለው ጊዜ በጥቂት አትሌቶች ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያስቻለ ድል ሲመዘገብ ቆይቷል።

በሂደትም የአትሌቶችን ቁጥር መጨመር ተከትሎ የአሰልጣኞች፣ የውድድሮች፣ የክለቦች እና የማናጀሮች ቁጥርም አድጓል። በዚህም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች ኢትዮጵያን በክብር እያስጠሩ እዚህ ደርሰዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቀድሞ ይታይ የነበረው ስሜት እየተሸረሸረ፤ በተለያዩ ውድድሮች ላይም የውጤት እጦት ቀውስ እና በኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ያልተለመደ እጅ መስጠት እየተስተዋለ ነው። በተመሳሳይ አትሌቶች ወጥ ባልሆነ አሰለጣጠን በማለፋቸው እንዲሁም በተለያዩና በግል አሰልጣኞች መሰልጠናቸው ባልተቀናጀ የአሯሯጥ ስልቶች የተቃኙት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ሀገር የምትወከልባቸው ውድድሮች ሲካሄዱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚታወቁበት የቡድን ስሜት እየተመናመነ መምጣቱ ታይቷል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚታወቁበት የመረዳዳት እና በቡድን የመስራት ልማድ በአንዳንድ ርቀቶችና አትሌቶች ዘንድ ይታይ እንጂ፤ በአመዛኙ እየቀረ መሆኑን በቅርብ የተካሄዱ ውድድሮች ምስክሮች ናቸው። በአንድ ብሄራዊ ቡድን እና ርቀት እየተሳተፉ በተለያየ የአሯሯጥ ስልት እርስ በእርስ በሚያደርጉት ፉክክርም ሀገር ዋጋ መክፈሏ በተደጋጋሚ ታይቷል።

ግለሰብ ሳይሆን ሀገር በምትወከልባቸው በእነዚህ የውድድር መድረኮች የኢትዮጵያን መለያ እና ባንዲራ ይዘው እየተሳተፉ ተፎካካሪን አዳክሞ ውጤት ከማስመዝገብ ይልቅ፤ እርስ በእርስ በሚደረግ ውድድር ክፍተቶች ተፈጥረዋል። ተቀናቃኝ ቡድኖችም ይህንኑ ክፍተት ተጠቅመው ውጤታማ ሆነዋል። በዚህ የኢትዮጵያውያኖች ስሜት መዳከም ምክንያትም ከጎረቤት ኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ባለፈ አውሮፓውያን አትሌቶች ጭምር ምን ያህል እንደተጠቀሙ በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

የቀደመው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማ ዘመን ሲታወስ የሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን፣ ደራርቱ ቱሉ እና ጌጤ ዋሚ፣… በመም ላይ የነበራቸው መናበብና ጥምረት አስደናቂ እንደነበር ከስፖርት ወዳጆች ሕሊና በቀላሉ አይሰረዝም። እርስ በእርስ ባላቸው መከባበር፣ መተባበር እንዲሁም ከአሰልጣኞቻቸው የሚሰጣቸውን መመሪያ ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ አስደናቂ ብቃት ነበራቸው። በዚህ ዘዴም በመላው ዓለም የናኘ እና እስካሁንም ከከፍታው ዝቅ ሊል ያልቻለ ዝናን መገንባት ችለዋል።

በእርግጥ አሁንም ይኸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስኬታማነት ምስጢር የሆነው የቡድን ስራ በትልልቅ ቻምፒዮናዎች ላይ እንደሚፈለገው ባይሆንም መታየቱ አልቀረም። ለአብነት ያህል በቅርቡ በተካሄደው የቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ የደገሙበት ሁነት በቡድን ስራ የተገኘ ነው።

በሌሎች ርቀቶችም በቡድን ለመስራት ጥረት የተደረገ ቢሆንም ስኬታማ ባለመሆኑ ከሽፏል። ሩጫን የሚያውቁ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ለዚህ ምክንያት ነው የሚሉት የቡድን ስራ ራሱን የቻለ ችሎታ የሚፈልገው መሆኑን ነው። ሌላኛው ደግሞ የአሯሯጥ ስልቱን የሚነድፉት ባለሙያዎች የተለያዩ እንደመሆናቸው በቀላሉ ሊተገበር የማይችል እንደሆነ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቋሚ የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የላትም። ኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮና እና መሰል ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲካሄዱም ጊዚያዊ ብሄራዊ ቡድን የሚቋቋም ሲሆን፤ አሰልጣኞችም ባስመረጧቸው አትሌቶች መጠን ይመረጣሉ። ታዲያ የዝግጅቱ ወቅት አልፎ ወደ ውድድር ሲገባ እንደ አንድ ሃገር ሳይሆን እንደ ግል ውድድር አንዱ አትሌት ሌላኛውን ለመርታት የሚያስችለው የአሯሯጥ መመሪያ የሚሰጠው በመሆኑ በውድድሩ ወቅት አለመግባባት ይፈጠራል። ይህን የእርስ በእርስ ፉክክር ከተቀናቃኝነትም አልፎ አለመግባባቶች ሲፈጠሩና በይፋ እስከመተናነቅ የሚደርስ መሆኑንም በተለያዩ መድረኮች ለመታዘብ ችለናል።

ከዚህ ባለፈ አትሌቲክስ የብቃት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የቤተዘመድ አሰራር የተንሰራፋበትም ሆኗል። ታዋቂ የሚባሉና ስኬታማ አትሌቶችን ማፍራት የቻሉ አሰልጣኞች ወንድሞቻቸውን፣ ልጆቻቸውን እንዲሁም የቤተሰብ አባላቶቻቸውን በአሰልጣኝነት ስም ቀድመው በስራቸው ሳይታወቁ በድንገት ብሄራዊ ቡድኖችን እንዲመሩና ሌሎች የለፉበትን እንዲቀራመቱ እያደረጉ ይገኛሉ። በተመሳሳይ ሴት አትሌቶች በባሎቻቸው መሰልጠንን የሚመርጡ በመሆኑ አግባብነት የሌለውና በቡድን ውስጥም የስነምግባር መጓደል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህም አደጋውን የሚያንረው ሲሆን ብዙዎች ባልተጠበቀ መልኩ ያለ እድሜያቸው በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ከውድድር ውጪ መሆናቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ በዚህ ከቀጠለም በልምድም ሆነ በትምህርት ዝግጅት ባልተገኘ ስልጠና በርካታ መመሰቃቀሎች እንደሚደርሱም ግልጽ ነው።

በመሆኑም በእነ አበበ ቢቂላ፣ ዋሚ ቢራቱ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣… ተገንብቶ ለዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፤ ከጊዜ በኋላ የገጠመውን ስብራት የሚጠግን ወጌሻ አስፈላጊ ነው። ይኸውም ወጌሻ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ቋሚ የሆነ ብሄራዊ ቡድን በመገንባት ውድድሮች ሲደርሱ ከመሯሯጥ እንዲሁም በተለያየ መንገድ የተቃኙ አትሌቶችን ወደ አንድ መንገድ ለማምጣት ከሚደረገው አላስፈላጊ ጥረት የሚያድን ይሆናል። በእርግጥም እነ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ የገነቡትን ብሄራዊ ቡድን ፍሬ ዞር ብሎ ማየት መፍትሄው ይህ ብቻ መሆኑን ያመላክታል።

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለውጤት ማጣትና የቡድን ስሜት መጥፋት ምክንያቱ ይህ መሆኑን በማመን ብሄራዊ ቡድን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ ነበር። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ በመቅረቱ አሁንም ድረስ ተግባራዊ ስላልሆነ ውጤትና ኢትዮጵያ እየተራራቁ ሕዝቡም ልቡ እየቆሰለ ቀጥሏል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ነገር በማድረግ ብሄራዊ ቡድን በማቋቋም በተመሳሳይ ስልጠና ሀገርን ብቻ ብለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን መፍጠር ይገባዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያውያን አትሌቶችና በጎረቤት ሀገራት አትሌቶች መካከል ያለው የብቃት ደረጃ እየተለያየ እንደመሆኑ ጠንካራ ስራ ይፈልጋል። ጊዜው በሄደ ቁጥር ሁኔታዎችም መለወጣቸው አይቀርምና በሁለቱም ርቀቶች ከ15 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የነበሩ ክብሮችን አጥተናል። ይህ የሆነው በሂደት ነገሮች ዘመናዊ መልክ እየያዙ እና ጠንካራ አትሌቶችም እየተፈጠሩ ስለመጡ ነው። በመሆኑም የተወሰደብንን ክብር ወደ ሀገሩ ሊያስመልስ የሚችል ብቃት ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ አትሌት ማፍራት የግድ ነው።

ስለዚህም ቋሚ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድንን በመመስረት የተበተነውንና ባለመግባባት እየባከነ የሚገኘውን የአትሌቶች ብቃት መሰብሰብ ያሻል። ይህንንም ሃሳብ ፌዴሬሽኑ በዚህ ወር መጨረሻ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አጀንዳ አድርጎ በማቅረብ ውሳኔ እንዲያገኝ ጥረት መደረግ አለበት። ዛሬ ነገ ሳይባልም በአፋጣኝ ወደተግባር ተገብቶ ወራት ብቻ ለሚቀሩት የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ብቻ የሚወክሉ ውጤታማ አትሌቶች እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You