የግብርናው ዘርፍ ዕቅድም ውጤትምያማረ ነው!

 በተያዘው 2016/17 የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብቻ 117 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል:: ልማቱ በሦስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄድ ሲሆን፣ ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ እንደ ግብአት አቅርቦትና የማሳ ዝግጅት ያሉ ስራዎች በሁሉም ክልሎች እየተፈጸሙ መሆናቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱትም፤ ክልሎች በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዕቅዳቸውንና ዝግጁነታቸውን እያረጋገጡ ናቸው፡፡

አሁን የበጋው ወር እንደመያዙ የተጠቀሱት መረጃዎች ወቅታዊ ናቸው፡፡ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ በስፋት መሥራትና መነገር በሚጀመርበት በዚህ ወቅት ይህን ዜና መሰማት ሥራው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በክልሎችም በፌዴራል መንግስት ደረጃም እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሰጠውን ትኩረት በሚገባ ያመላክታሉ፡፡

እንደሚታወቀው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚሸፈነው ማሳና የሚገኘው ምርት መጠን በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ የመስኖ ልማቱ ከሦስት ዓመት በፊት በቆላማ አካባቢዎች የተጀመረው በ117 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ በወቅቱ የተገኘው ምርትም 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ነበር፡፡ በቀጣዩ ዓመት 24 ነጥብ 5 ሚሊየን ተመርቷል፤ ባለፈው ዓመት 53 ሚሊየን ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ 47 ሚሊየን ኩንታል አካባቢ ተገኝቷል፡፡

ዘንድሮ በመስኖ ልማቱ የሚሸፈነው መሬትም የሚጠበቀው ምርትም በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ በልማቱ ለማግኘት የታቀደው 117 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ከተገኘው ምርት ከእጥፍ በላይ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓመት ለማግኘት የታቀደው የምርት መጠን ባለፈው ዓመት በመኸርና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አንደሚገኝ ይጠበቅ ከነበረው 107 ሚሊዮን ኩንታልም ይበልጣል፡፡

የሚታረሰው የመሬት መጠንም እንዲሁ ከአምናው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ሶስት ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የሚታረሰው መጠን በቀደሙት ዓመታት በመኸር ወቅት በስንዴ ይለማ ከነበረው መሬት የሚበልጥበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

እነዚህ ሁሉ መረጃዎች በራሳቸው ብቻ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ግዙፍ ዕቅድ መያዙን ያመለክታሉ፡፡ እየተደረገ ያለው ዝግጅትም ዕቅዱን ለማሳካት ይመጥናል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሥራው እየሰፋ ዝግጁነቱም እየላቀ እንደመጣ ሁሉ፣ ክትትልና ድጋፉም በዚያው ልክ የተጠናከረ ሊሆን ይገባል፡፡

ዝግጁነቱ፣ ክትትልና ድጋፉ በሁሉም የልማቱ ምዕራፎች ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን የሚጠበቀውን ማሳ በዘር መሸፈን፣ የሚጠበቀውን መጠን ምርትም በእርግጠኝነት ማግኘት ይቻላል፡፡

የፌዴራል መንግስት ባለፉት ዓመታት በማዳበሪያ አቅርቦቶች ላይ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት የማዳበሪያ አቅርቦቱን ከአሁኑ መጀመሩ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም የራሱን አሰተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ዘንድሮ የተያዘው ዕቅድ ሰፊ ነው፤ ይህም ግብአት በስፋት ማቅረብንም ይጠይቃል፡፡ ማዳበሪያ አስቀድሞ መገዛቱና መጓጓዝ መጀመሩ ለተያዘው ሰፊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ለምርት ዘመኑ ከተገዛው ማዳበሪያ የተወሰነው በዚህ ወር መጨረሻ ጅቡቲ ወደብ የሚደርስ መሆኑም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም የበለጠ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ማሳ ማስፋፋት አንዱ መንገድ ነው፤ ብቸኛው መንገድ ግን አይደለም፡፡ በስንዴ ዘር የሚሸፈነው ማሳ መጨመሩ ከዚህም ለማግኘት የታቀደው ከፍተኛ መሆኑ አንድ ነገር ሆኖ በሄክታር የሚገኘው ምርታማነት መጨመር ላይም በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡ የበጋ መስኖ ሲጀመር በሄክታር 35 የነበረው ምርታማነት በፈረንጆቹ 2022 ወደ 40 ኩንታል አድጎ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የምርታማነት ዕድገት እንዲመጣ መሥራት የዘንድሮው ዐብይ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬታማ ተሞክሮዎች እቅዱን ለማሳካት ጥሩ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ በስንዴ ልማቱ ሀገርንም መንግስትንም በስኬት ያስጠራ ተግባር በዓመታቱ ማከናወን መቻሉ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱን ለሌሎች ልማቶቿ ልታውለው ከሚገባት ውስን የውጭ ምንዛሬ ላይ አንስታ ስንዴ ትገዛ ከነበረበት ሁኔታ ማውጣት ተችሏል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ከሀገራዊ ፍጆታዋ የተረፋትን ስንዴ ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመላክም የውጭ ምንዛሪም አግኝታለች፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ከስንዴ እርዳታ ጥገኝነት መላቀቅ ተችሏል፤ በስንዴ ምርት ሉአላዊነት ተጠብቋል፡፡

ዘንድሮም ይህን ታሪክ በሚገባ መድገም የሚያስችል ዕቅድና ዝግጁነት ተይዞ ወደ ልማቱ ተገብቷል ማለት ይቻላል፤ የግብርና ሚኒስቴርም የክልሎችም ዝግጅት ይህን ያመለክታል፡፡ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አጋርነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴርና በክልል የሚገኙ ተመሳሳይ ተቋማት ለመስኖ ስራ የሚያስፈለገውን ውሃ መሰረተ ልማት በመዘርጋት፣ እክል ሲገጥም በመጠገንና በመሳሰሉት ምክር በመስጠት ኃላፊነታቸውንም አጋርነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባዋል፡፡ ከዕቅዱ ስፋት አኳያ የመላው ሕዝብና ሌሎች የልማት ኃይሎች ድጋፍም ወሳኝ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You