በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ጉዳቶችን ለመከላከል በቂና ወቅታዊ መረጃ ያስፈልጋል

አዳማ:- በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ጉዳቶችን ለመከላከል በቂና ወቅታዊ መረጃ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን ለማፅደቅና ወደ ክልሎች በማውረድ ተፈፃሚ ለማድረግ ያለመ የክልሎችና የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ምክንያት ዓለም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመሆኗ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ጉዳቶችን ለመከላከል በቂና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ ወሳኝነት አለው።

የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍን በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በአግባቡ መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመከላከል መረጃን በተገቢ ሁኔታ ማጠናቀርና መተንተን እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ አስቀድሞ የአየር ንብረት ለውጥን መረጃ አለመሰብሰብና በመረጃው አለመጠቀም የተፈጥሮ ውሃ ሀብትን በመጉዳት ዜጎችን ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ አስገንዝበዋል።

በሀገራችን የሚስተዋለውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለመቀነስም የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ሳይንሳዊ መረጃ በማቅረብ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን የአየር ጠባይ ሁኔታን በመተንበይ መረጃ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ መረጃውን የሚመለከታቸው አካላት ጥቅም ላይ ሊያውሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷን የአየር ሁኔታ መረጃዎችንም በክልል ደረጃ ወርዶ በመሥራት የጥንቃቄ ርምጃዎች እንዲጠናከሩ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል።

የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ አስቀድሞ መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You