ስህተትን በተጨማሪ ስህተት ለመካስ የሚደረግ ስሌት አያተርፍም!

ይብዛ ይነስ የተሳሳተ ስልት ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው። በተለይም ለራስ የሚሰጥ ያልተገባ ግምት ከራስ አልፎ ለሌሎች ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ከሚባል ተሞክሮው ተነስቶ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚከብደው አይሆንም። ሰብአዊ ማንነቱን ለዚህ እውነት ብቁ ያደርገዋል።

ይህም ሆኖ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች ለጥቅሞቻቸው በሚፈጥሯቸው የተሳሳቱ ስሌቶች በማኅበረሰብ፣ በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ትላልቅ ውድመቶች እና ጥፋቶች ተከስተዋል። በዚህም የሰው ልጅ የከፈለው ያልተገባ ዋጋ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ብዙ ታሪኮችን፤ እስከ ዛሬ ጠባሳቸው ያላገገሙ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል።

ከሁሉም በላይ የግለሰቦች ያልተገራ ማንነት እና ማንነታቸው የሚፈጥረው ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ ሊያስከትሉት ስለሚችለው ጥፋት የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶችን እና በጦርነቶቹ የደረሰውን ስብዕና ቁሳዊ ውድመት መጥቀስ ይቻላል። በነዚህ ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሙት እና ቁስለኛ ሆነዋል። የዘመኑን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ የጨመረ ጥፋት አድርሰዋል።

ከነዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ጦርነቶች ውጪም በተመሳሳይ የስሌት ችግር በሀገራት መካከል በተካሄዱ ጦርነቶች ብዙ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ተከስተዋል። በሀገራት ሕዝቦች መካከል ጠላትነትን እና አለመተማመን የፈጠሩ የግጭት እና የጦርነት ትርክቶች ዛሬም ድረስ የሚሰሙ፤ የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋል።

ግለሰቦች እና ቡድኖችም በተመሳሳይ መንገድ በአንድ ሀገር ውስጥ በሚፈጥሩት የስሌት ስህተት፤ ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ያፈረሱበት አጋጣሚ ጥቂት የሚባል አይደለም። ዛሬ ላይ የሀገርነት መልካቸውን አጥተው በብዙ ሁከት እና ትርምስምስ ውስጥ የሚገኙ ሀገራትን መመልከት በራሱ በቂ ነው።

እራስን በአግባቡ ካለማወቅ፤ ወቅታዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን አለመረዳት፤ ከሁሉም በላይ ሆኖ ለማየት በሚፈልጉት ነገር ውስጥ ፍፁም ሰጥሞ መገኘት፤ ለሌላ አማራጭ ሀሳብ እና እይታ እራስን አለማስገዛት፤ ትምክህት እና እብሪት፤ ደንታቢስነት እና ዳተኝነት፤ ጸልመተኝነት እና እራስ መዳድነት ለስሌት መዛባት እና ችግሩ ለሚያመጣው መልከ ብዙ ችግር እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው።

ለዚህ ደግሞ የሩቁን ዘመን ትተን ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር የመጣንበትን መንገድ እና የመንገዱን መንገጫገጭ መመልከት ይቻላል። አንዳንዶች በግለሰብ ደረጃ የለውጡን መንገድ እና አካሄድ ባለመረዳት፤ ለውጡን ለግል መጠቀሚያ አቋራጭ አድርገው በመውሰድ ለለውጡ ፈተና ሆነዋል።

የነሱ የስሌት ስህተት እንደ ሀገር መላው ሕዝባችንን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል። በሕዝባችን መካካል ለዘመናት ተጠብቆ በኖረው መከባባር እና መቻቻል፤ ወንድማማችነት እና አብሮነት ላይ ጥላ ሆኖ አልፏል። የግርግር እና የሁከት ምንጭ በመሆንም ሀገርን እና መላው ሕዝባችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ዛሬም እያስከፈለ ነው።

በቡድን ደረጃም ቢሆን አንዳንዶች የትናንት ያልተገራ የከፍታ ትርክት በፈጠረው እብሪት፤ በተፈጠረ የስሌት ስህተት በራሳቸው ላይ መከራ እና ሞትን ጠርተዋል። ችግራቸው ከእነርሱ አልፎ ሀገርን ወደ ከፋ የግጭት አዙሪት በመክተት፤ በዚህ ዘመን ወደማይጠበቅ ተጨማሪ የጦርነት እና የግጭት ታሪክ ውስጥ እንድንገባ አስገድደውናል።

ለውጡ ይዞት የመጣውን አዲስ የፖለቲካ ባሕል የማነስ ምልክት አድርገው፤ የማነስ ታሪክ ውስጥ ገብተዋል። በዚህም ከራሳቸው አልፈው እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ለከፋ አደጋ አጋልጠዋል። ሀገርን እንደ ሀገር የማፍረስ የታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ በመሆንም የሀገርን ሕልውና ተፈታትነዋል።

እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከትናንት ስህተታቸው ለመማር ከመፍቀድ ይልቅ፤ የቀደመውን ስህተታቸውን በሌላ ተጨማሪ ስህተት ለመካስ ዛሬም ባልተገባ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ይህ የጥፋት መንገዳቸው እንደ ትናንቱ ራሳቸውን ለከፋ አደጋ፤ እንወክለዋለን፣ እንታገልለታለን የሚሉትን ሕዝብ ለተጨማሪ ጥፋት የሚጋብዝ ነው።

ከትናንት ጥፋት ተምሮ ራስን መግራት ሰብአዊ መንገድ ነው። ነገዎችን እንደግለሰብ ሆነ ቡድን ከዚም በላይ እንደማኅበረሰብ እና ሀገር የተሻለ ለማድረግም ትልቅ አቅም ነው። ከዚህ ውጪ ትናንትን እንዳልተፈጠረች አድርጎ በሌላ የተሳሳተ ስሌት ነገን ተስፋ ማድረግ በተለመደው ጥፋት ውስጥ ከመንደፋደፍ ያለፈ አንዳች አያተርፍም። በተሳሳተ ስሌት የሚታደስ ተስፋም የለም።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You