በዜጎች ጎርፍ የሚጥለቀለቀው ኢሚግሬሽን

«ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ!?»

ይህ ጸሐፊ ከአንድ ደራሲ ወዳጁ ጋር በሀገሩ ጉዳይ የማለዳ ቡና ፉት እያሉ ሲጨዋወቱ የወረወረለት አንድ አባባል በእውነቱ ከሆነ ከስለታም ጦር የሰላና የውስጥ ስሜትን ዘልቆ የሚወጋ ኃይል ነበረው። ያ ደራሲ ወዳጁ እንዲህ ነበር ያለው፡- “በደራሲ ምናብ ምልከታዬ ስመረምረው እያንዳንዱ ዜጋ ነግቶ በጠባ ቁጥር ማለዳ ማለዳ ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሰላምታ የሚያቀርብላት ‹ጤና ይስጥልኝ ኢትዮጵያዬ!› እያለ ብቻ ሳይሆን ‹ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ› በማለት እያነባ የሚያስተዛዝናትና የሚያላቅሳት ይመስለኛል፡፡” አባባሉ ጊዜያችንንና ሕመምተኛዋን ሀገሬን በሚገባ ስለሚገልጽ “አበጀህ ደራሲው!” ብዬዋለሁ፡፡

“ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ፤ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ” የሚለው ብሂል የተለምዶ ንግግር ብቻ ሳይሆን የኑሯችን ዘይቤ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በደራሲው ወዳጄ ወግ የጀመርኩትን መንደርደሪያ በጉምቱው ነፍሰ ሄር ባለቅኔያችን የጣር ጩኸት አጎላምሼ ወደ ዋናው የመነሻ ጉዳዬ እፈጥናለሁ።

«እሳት ወይ አበባ” የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ዘመን አይሽሬ የግጥም መድበል መሆኑ ለትንሽ ለትልቁ የታወቀ ስለሆነ ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለንም፡፡ “ሰቆቃው ጴጥሮስ” የሚለው ግጥሙ ልክ የዛሬ 55 ዓመት ተጽፎ በ1965 ዓ.ም በታተመው መድበል ውስጥ የተካተተው ይህ የጣር ድምጽ የፋሽስት ኢጣሊያ የግፍ ሰለባ የሆኑትን ብፁእ አብነ ጴጥሮስ በጠንካራ ምናባዊ ዕይታ የገለጻቸው በሚከተሉት ሞጓች ስንኞች አማካይነት ነበር፡፡

”አዬ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?

ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?

እስከ መቼ ድረስስ እንዲህ መቀነትሽን ታጠብቂባት?

ልቦናሽን ታዞሪባት?

ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?

አላንቺ እኮ ማንም የላት?

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈታኝ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ዜጎች እንደየእምነታቸውና እንደየቀኖና ሥርዓቶቻቸው ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ጸሎትና ዱዓ አድርጉ ቢባሉ ወደ ፈጣሪያቸው የሚቃትቱ ጳጳሱ በተገለጹበት የስሜት ስብራትና ሀዘን ተውጠው እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ስለምን? ቢባል ሀገራዊ መከራዎቻችን፣ አሳሮቻችንና ዕንቆቅልሾቻችን ብዙ ስለሆኑ – መልስ ይሆናል፡፡

ውሱን ቃላት በሚስተናገዱበት በዚህ አንጋፋ ጋዜጣ ገጽ ላይ “ሆድ ያባውን” ሁሉ ለመግለጽ መሞከር የሚቻል ስላልሆነ ትኩረት የሚሻ አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ብቻ ነቅሰን እንደተለመደው “በሆድ ይፍጀው” ትዝብት ለማለፍ ሳይሆን በሚመለከተው ያገባኛል ባይ ተቋም የተግባር እርምጃ እንዲወሰድበት ብዕራችንን ጠንከር አድርገን ማናገሩን ምርጫ አድርገናል፡፡ ያለበለዚያ “አለባብሰን ብናርስ በአረም መመለሳችን ስማይቀር” የችግሮቻችንን ቁስሎች ከማጀል ይልቅ ጨከን ብለን ማፍረጡ ለፈወስ እንደሚያግዝ እናምናለን፡፡

የዜግነት ፓስፖርትን ለማግኘት የእምባ ክፍያ!?

የፌዴራል ኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ስሙ በየሥርዓተ መንግሥታቱ የተለዋወጠ ቢሆንም፤ ከሀገሪቱ አንጋፋ ተቋማት አንዱና ከፍ ያለ ኃላፊነት የተሸከመ እንደሆነ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ይህ ተቋም ከዓመታት በፊት ለተገልጋዮች በሚሰጠው ፈጣንና ቀልጣፋ የፓስፖርት አሰጣጥ አገልግሎቱ “ከክፉ የቢሮክራሲ ዓይንና ወጥመድ ይታደግህ” ተብሎ በዜጎች እንዳልተመረቀና እንዳልተወደሰ ሁሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “የዜጎች አስከፊ የእምባና የሮሮ” ምክንያት መሆኑ በእጅጉ ወዴት እየሄድን ነው ብለን እንድንጠይቅ ተገደናል፡፡

ይህ ጸሐፊ እንደማንኛውም ዜጋ በዚህ ተቋም ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ተገልግሏል፡፡ በተቋሙ ውስጥ በአርአያነት የሚጠቀሱና በኃላፊነት ቦታቸውም አንቱታም ሆነ ምሥጋና የሚገባቸው ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞችና ኃላፊዎች መኖራቸውን ጸሐፊው ዳግላስ የሚመሰክረው ኅሊናውን ዳኝነት አቁሞ ነው፡፡

ህፀፅን መንቀስ ብቻ ሳይሆን እንደነዚህ ዓይነቶቹ “ኅሊና ስንቁ” ታታሪና ትጉህ ኃላፊዎችም በምስጋና ቃልና በአክብሮት መበረታታቸው ይደገፋል። በአንጻሩ ደግሞ በዜግነት ክብር ላይ የሚሳለቁ፣ ለተገልጋዩ ሕዝብ አክብሮት የሌላቸው እጅግ ብዙ “ምንተዳዬ ባዮች” እንዳሉም ለመመስከር ወደ ተቋሙ ብቅ ማለት ብቻ በቂና ከበቂ ባላይ ይሆናል፡፡

በቅርቡ ጸሐፊው ወደዚሁ ተቋም ለግል ጉዳዩ አገልግሎት ለማግኘት ብቅ ብሎ በነበረበት ወቅት እጅግ በርካታ መታረም የሚገባቸው ችግሮችና መጉላላቶች እንዳሉ ተገንዝቧል፡፡ ያስተዋላቸውን መተረማመሶችና መጉላላቶች ያስተውል የነበረው በእግረ መንገድ ትዝብት ብቻ ሳይሆን “የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል” ተብሎ ሀገር ኃላፊነት እንዳሸከመው እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ጭምር የባለጉዳዮችን ብሶት ያደምጥ የነበረው ልብ ተቀልብ ሆኖ ነበር፡፡

ከተወሱኑ ወራት በፊት መሥሪያ ቤቱን በዳይሬክተርነትና በከፍተኛ ኃላፊነት ሲመሩ የነበሩ ሦስት ከፍተኛ የሥራ መሪዎች ከአንድ ዓመት ተመንፈቅ የአገልግሎት ቆይታ በኋላ ከኃላፊነት መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ ሰሞኑንም “…42 የሚሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች በሙስናና በብልሹ አሠራር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ” የሚል ዜና አድምጠን ‹ይብላኝልሽ ኢትዮጵያ!› በማለት በውስጣችን አልቅሰናል፡፡

ከበርካታ አገልግሎት ሰጭ የሀገራችን ተቋማት መካከል ዜጎች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ወደ ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት እየተሳቀቁና እየተሸማቀቁ ጎራ የሚሉት ሀገራቸውን እየረገሙ ጭምር መሆኑን ማስተባበል አይቻልም፡፡ በተቋሙ ደጃፍ ላይ ቆመው በእምባና በብሶት እየተንሰቀሰቁ የሚያለቅሱትም መሰደድን በልባቸው እያውጠነጠኑ ይመስላል፡፡

በእንግልትና በመጉላላት ብዛት ከዚህ መ/ቤት በልጦ ሌላ ተቋም ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ “እሳት ካየው ምን ለየው” እንዲሉ ዜጎች አገልግሎት በሚጠይቁባቸው በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የባለጉዳይ መጉላላት ባህል ሆኖ እስኪቆጠር ድረስ ሥር የሰደደ ቢሆንም የኢሚግሬሽኑ መ/ቤት ግን ከሁሉም ገዝፎ የሚታይና በአደባባይ ጮክ ተብሎ የሚመሰከርለት ጭምር ነው፡፡

በኢሚግሬሽን መ/ቤት ዋና በር ላይ የተኮለኮሉትንና ጉዳያችሁን እናስጨርስላችኋለን እያሉ እንደ ንብ በመውረር በግላጭ የሚደራደሩ ደላሎችንና አጭበርባሪዎችን ማየት እንግዳ አይደለም። ይህን መሰሉ ችግር የተቋሙ መለያ ሆኖ ሥር ከሰደደ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አልፎም ተርፎ የተለመደ ባህል እንዲሆን እውቅና የተሰጠው እስኪመስል ድረስም በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ የ42ቱ ሠራተኞች የክስ ዜና አየሩን ሞልቶ መነጋገሪያ በሆነበት በትናንትናና በዛሬ ዕለታትም ሳይቀር ደላሎቹና አጭበርባሪዎቹ ፍርሃት ይሉት ስሜት አስደንግጧቸው ከተቋሙ በራፍ ላይ ዞር ሊሉ አልቻሉም፡፡ “ሚስትህ አረገዘች ያሉት እውነት ነው?” ተብሎ የተጠየቀ ምስኪን አባዋራ “ማንን ወንድ ብላ” ብሎ እንደመለሰው ብጤ መሆኑ ነው፡፡

ይህንን መሰሉን የደላሎች ወረራና ከበባ “አይዟችሁ ባይ ጀግና” ከጀርባቸው ከሌለ በስተቀር የተቋሙ ኃላፊዎችም ሆኑ የጸጥታ አካላት አያውቁትም ብሎ መደምደም በፍጹም አይቻልም፡፡ ከዜግነት ማረጋገጫ ፓስፖርት አሰጣጥና ከተጨማሪ ሌሎች ብሔራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘውን ይህንን ወሳኝና እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ኃላፊነት በአግባቡ ያለመወጣት ምን ስም ሊሰጠው እንደሚገባ ይቸግራል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ42 ተጠርጣሪ ሠራተኞች ፋይል ምን ያህል ተጨማሪ 42ቶችን ስቦ እንደሚጎትት ወደፊት በፍርድ አተገባበር ሂደቱ ማስተዋላችን የሚቀር አይሆንም፡፡

ወደ ተቋሙ ግቢ ውስጥ ከተገባም በኋላ የሚታየው የሕዝብ ትርምስምስና እንግልት ይህ ልኩ የሚባል ዓይነት አይደለም፡፡ በተጠና ስልትና አግባብ ተገልጋዩን በአግባቡ ለማስተናገድና ዜጎች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ተገቢ አቀባበል ተደርጎላቸው “አዎንታዊም ሆነ አይቻልም” የሚል መልስ ስለምን በአግባቡ እንደማይሰጣቸውም ግራ ያጋባል፡፡ በርግጥ ይህን ችግር የተቋሙ ኃላፊዎች መፍታት ተስኗቸው ይሆን? አዲስ የተመደቡት ሹሞች ወደፊት “ለመከራው ማብቂያ” መድኅን እንደሚሆኑ ተስፋ ማድረጉ ለመጽናናት ያግዛል፡፡

ይህ ጸሐፊ በኢሚግሬሽን ግቢ ውስጥ በተመላለሰባቸው ቀናት ጠጋ ብሎ ያነጋገራቸው በርካታ ተገልጋዮች ፓስፖርት ለማውጣት የፈለጉት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከሀገራቸው ለመውጣት ግድ ስለሆነባቸውና “በመከረኛዋ ሀገራቸው መከራ ከመግፋት ይልቅ በአንድ ቁርጡ ስደት ይሻላል” የሚል ውሳኔ ወስነው መሆናቸውን በድፍረት ሲናገሩም ተደምጧል፡፡

ዜጎች በነፃ ፈቃዳቸው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ሕገመንግሥታዊ መብታቸው መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም እንደዚህ ዘመን “ተስፋቸው ተራግፎባቸው” ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ የተነቃቁበት ጊዜ ይኖር ይሆንን? ብለን ብንጠይቅ ተገቢ ይመስለናል። ስለምን ስደት ለዜጎች ተቀዳሚ ምርጫ ሊሆን ቻለ? ኢትዮጵያ ዜጎቿን ወደ ሥራ ለማሰማራት ስላልቻለች ወይንስ ልጆቿን ማኖር አቅም ስለሌላት? በውይይት፣ በልምምጮሽም ሆነ በቅስቀሳ ውይይት ተደርጎበት እልባት ሊያገኝ ላልቻለው ለዚህን መሰሉ ብሔራዊ ፈተናችን መፍትሔው ከማን ዘንድ እንደሚገኝ ለጊዜው አፍ ሞልቶ “ከእከሌ ዘንድ” ለማለት ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡

እጅግ የሚያስደነግጠው ደግሞ ብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ለስደት ምርጫቸው ተቀዳሚ የሚያደርጓቸው የራሳቸው ሀገር ችግር ገዝፎ መከራ ላይ በወደቁ የቅርብና የመካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት መሆኑ ነው፡፡ “መላእክት ሊራመዱበት በሚፈሩት ጎዳና እግረኛ ምን ሊሠራ ተገኘ” የሚለው የባህር ማዶዎቹ የተለመደ አባባል ከላይ የጠቀስነውን ሃሳብ በሚገባ ያጎላምስ ይመስለናል፡፡

የቀደምት ዜጎቻችን የስደት ታሪክ እንዴት፣ ወዴትና ምን ይመስል እንደነበር በሚቀጥለው ሳምንት የአንድ የደቡብ አሜሪካ ሀገርን ታሪክ በመንደርደሪያነት ተጠቅመን የዳሰሳ ያህል ለማሳየት ስለምንሞክር ለጊዜው ርዕሰ ጉዳዩን በይደር አቆይተናል፡፡ ለመሆኑ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋ የማያስቆርጥ ምን ነገር ይኖራል?

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ታሞና መድኃኒት ጠፍቶለት አልጋ ላይ ከዋለ ሰነባብቷል፡፡ የኑሯችን ብሂል “ከእጅ ወደ አፍ” መሆኑ ቀርቶ “ከዐይን ወደ አፍ” እስከ መባል ተደርሷል፡፡ ግጭትና ሁከትን ክፉ የመጠፋፊያ ስልት በማድረግ ደም እየተቃባን “ይዋጣልን!” ማለትን የባህል ያህል ተቀብለን የደም ሸማ መጣጣል የዕለት ተግባራችን ከሆነም ሰነባብቷል።

ስለምን በመነጋገርና መመካከር ችግሮቻችንን መፍታት እንደተሳነን እንኳን ለእኛ ቀርቶ ልብን ለሚመረምረው አምላክም ሳይቀር “ተሰውሮበት ይሆንን?” ብለን እስከመጠየቅ ደርሰናል፡፡ ፖለቲካው “ከቃየል እርግማን” መንጻት ተስኖት ተቅበዝባዥ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሰማያዊ ጽድቅና የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚደረግበት የሃይማኖት ጉዳይም እርቃኑን ተራቁቶ በምድራዊው እንካ ሰላንትያ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ያለቦታው ቦታ መፈለግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የማሕበራዊ መስተጋብር አቋማችን ተነቃንቆ “አብሮነት” ወደ “ለእኔ ብቻነት” ዝቅ ካለም ጊዜው ነጉዷል፡፡ ሩቅም ይሁን ቅርብ ብቻ በጥቅሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ብርቅም ድንቅም ሆኖብን እግራችን ተሸብቧል፡፡ አየሩን የሞላው የአብሮነት አድናቆት ሳይሆን የመለያየት ትርክት ነው፡፡ ያለምንም ፍርሃት ኢትዮጵያ ተደራራቢ በሆኑ ክፉና ወቅት ወለድ ደዌዎች ተለክፋ በማቃሰት ላይ ነች ብንል ያስማማናል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የችግሮቿ መፍትሔዎች በሙሉ በልጆቿና በመሪዎቿ እጅ መሆናቸው ነው፡፡ “ግዛዋ ሳለ ከደጅሽ ለምን ሞተ ልጅሽ!?” ያለው ጥንታዊ ብሂል እዚህ ቦታ ቢጠቀስ ተገቢ ይመስለናል፡፡ ምን ነካን? ከሰላም እንድንኳረፍስ አዚም ያደረገብን ማነው?

ሀገሪቱን እጅ ከወርች ጠፍንጎ ያሰረው ቢሮክራሲ፣ በሙስና የመልከስከስ ክፉ ነቀርሳና እርስ በእርስ የመጠፋፋታችን አባዜ ከኢትዮጵያ ገላ ላይ ተፈውሶ ነፃ የምንሆንበት ጊዜ መቼ ይሆን!? ሀገሬ ሆይ የቱን ትቼ በየቱ ጉዳይሽ ይማርሽ ልበልሽ? መፍትሔው በእጃችን ላይ እያለ አንድም በንግግር፣ አንድም በይቅርታ፣ አንድም በካሳ፣ አንድም “ከእኔ ይቅር” በማለት ወደ ቀልባችን እንዳንመለስ ልባችንን የዘጋው ክፉ የብረት መጋረጃ ምን ይሆን? ሀገሬ ሆይ! ወገኔ ሆይ! በዚህ አካሄድ የት ደርሰን ምን ላይ እንደምንወድቅ መገመት ስለማይከብድ ዜጎችም ሆኑ መሪዎች ወንበር ስበን እንመካከር፤ ጆሮ ተሰጣጥተን እንደማመጥ፡፡ የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You