ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ባሻገር

የዲጅታል ዘመን፣ ዓለምን ወደ አንድ በማምጣት የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል። ጊዜን፣ ጉልበትንና አላስፈላጊ ወጪን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችም ጥቅም ላይ ውለው በዓለም ዙሪያ ያሉት የሰው ልጆች በቀላሉ በበይነ መረብ አማካኝነት በማስተሳሰር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ እንደመሆኑ በፍጥነት እያደገ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ መጓዝንም የግድ ይላል፡፡

ዛሬ ላይ የበለጸጉ የዓለም ሀገራት ወደ ተራቀቀ ቴክኖሎጂ እየተጓዙ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ታዳጊ ሀገራት ደግሞ ከዓለም ጋር አብሮ መጓዝ የሚያስችላቸው ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ዓለም የደረሰበት የቴክኖሎጂ ጥግ ለመድረስም ያላቸው አቅም ተጠቅመው ወደ ፊት በመገስገስ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም የዲጅታል ዓለም ለመቀላቀል የሚያስችላት ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይሄን እውን ለማድረግ ‹‹የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ነው፡፡ ይሄ የዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ፈጣንና አበረታች ለውጥ እየተመዘገቡበት ነው፡፡

ለአብነት በሀገራችን ያለውን የዲጅታል የመሠረተ ልማት ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ተወዳዳሪነት ለመፍጠር ከኢትዮ-ቴሌኮም በተጨማሪ፤ ሳፋሪ ኮም ተሳታፊ ማድረግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሄም እያደገ ከመጣው ተደራሽነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለውን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር 69 ሚሊዮን ሲሆን፤ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ23 ሚሊዮን በላይ መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተመሳሳይ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የታየው ውጤት፣ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች ተግባራዊ መሆን መጀመራቸው ነው፡፡ ይሄም በዘርፉ አበረታች የሚባሉ ለውጦች እንዲመጡ ያስቻለ ነው፡፡

ለዚህ ተብለው ጥቅም ላይ የዋሉ ዘመናዊ የገንዘብ ልውውጥ መንገዶች ውስጥ እንደ ቴሌ ብር፣ ኤ.ቲ.ኤም፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ፖስ ማሽኖችን፣ ሲቢኢ ብርና ሌሎች በርካታ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች ጥቅም ላይ ውለው በርካታ መጠን ያለው የገንዘብ ልውውጥ ተደርጓባቸዋል፡፡ ለአብነት በቴሌ ብር አማካኝነት በ2015 ዓ.ም ብቻ የተፈጸመን የገንዘብ ዝውውር ብንመለከት 679 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሌሎች የክፍያ አማራጮችም በ2015 ዓ.ም ብቻ ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር በዘመናዊ ግብይት የገንዘብ ልውውጥ መደረጉን መረጃዎች ያመላክታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ በዓመት አራት ትሪሊየን ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እየተዘዋወረ ይገኛል። መረጃው የዲጂታል ክፍያ አማራጭ በሀገሪቱ መስፋፋቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲቀነስ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ያሳያል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ግብይቶች በዲጂታል እንዲከናወኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከ170 በላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸውንም የሚያመላክት ነው፡፡ ይህም የዲጅታል ሥርዓቱ ያለበትን ደረጃና ዲጅታል ኢትዮጵያ እውን የማድረጉ ሂደት አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ ለመሆኑ በማሳያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

እነዚህ መልካም ጅምሮችና እየተገኙ ያሉ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ግን፤ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረጉ ጎን ለጎን መሰራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች ለመኖራቸው አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂን መስፋፋት ተከትሎ የሚከሰቱ የሳይበር ጥቃቶችን የመመከት ዝግጁነትና ንቁ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠርን የግድ ነው፡፡ ይሄን ጥቃት መቋቋም የሚያስችሉ ዘመኑ የሚመጥኑ፣ ከዘመኑ ጋር አብረው መጓዝ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅን ይገባል፡፡

በዚህም ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማትም ሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤውን የሚጨምሩ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል። በተለይ አሁን ላይ በዲጅታል ክፍያ ሥርዓቶች ላይ እየታዩት ያሉ አብዛኛውን የሚባሉት ችግሮች ስንመለከት ከግንዛቤ እጥረት እና ከአጠቃቃም ጋር ተያይዘው የሚነሱ የዳታ መሰረቅ፣ የመጭበርበር እና የመሳሳሉ ችግሮች መሆናቸው፤ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና የሚጨምሩ በርካታ ሥራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ማሳያ ናቸው፡፡

እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከወዲሁ መሥራት እስካልተቻለ ድረስ የዲጅታል ሥርዓታቱን በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ እንቅፋት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዲጅታላይዜሽን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በተቋማትም ሆነ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ (የሚሰዘነሩ) የሳይበር ጥቃቶች ለመቀነስ የሚችለውን ጠንካራ የሳይበር ጥቃት መመከት የሚያስችል አቅም መገንባት ይጠይቃል፡፡

የሳይበር ጥቃት ሆነ ተብሎ ያልተፈቀዱ የኮምፒውተር ሥርዓቶች፣ መሰረተ ልማቶች፣ ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ ዳታዎችን፣ መበዝበዝና አገልግሎት በማስተጓጎል የሚፈጸም ጥቃት እንደመሆኑ መጠን፤ ጥቃቱ መመከት ሳይቻል ቀርቶ ከተከሰተ የሚያስከትለው ውድመት እንደ ሀገር ከፍተኛ ነው። ይሄም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ከባድ ነው፤ ከፍተኛ ሀገራዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችልም ነው፡፡

በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የሳይበር ጥቃት 96 በመቶ መከላከል የተቻለበት ቢሆንም፤ ያልተገመቱ ጥቃቶች ሊያስከትል የሚችሉበት አጋጣሚ በርካታ ስለሆነ ተገቢው የጥንቃቄ እርምጃው መውሰድ የግድ ይሆናል፡፡

የሀገሪቱን ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃት በመከላከል የሀገሪቱን ዲጅታል ሉአላዊነት በማስጠበቅ ኃላፊነት ያለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የሳይበር ጥቃቶች በአመዛኙ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች፣ የፋይናንስ ዘርፉ፣ የሚዲያ ተቋማትን፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትና የመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት ትኩረት አድርጎ የሚሰነዘሩ ናቸው፡፡

በመሆኑም ችግሩን ከመከላከል አኳያ ተቋማቱ ሊታጠቁ የሚገባቸውን ዘመኑ የሚፈልገው አይነት ቴክኖሎጂ በማስታጠቅ ረገድ ጥቃቱን የመከላከል ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ሊያሳደጉ የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎችን መስራት ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም የዲጅታላይዜሽን እውን እንዲሆን በቴክኖሎጂው ሆነ በሰው ኃይል ብቁ ሆኖ መገኘትን የሚጠይቅ፤ ከዚህም በላይ እንደ ሀገር በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ተቋማትም ሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀምም፤ የጉዳቱ ሰለባ ላለመሆንም ዘመኑ የሚፈልገው ቴክኖሎጂ ታጥቆ ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ ለነገ የሚባል ሳይሆን አሁናዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆንም ደግሞ ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ ባይ ነኝ፤ ቸር እንሰንብት፡፡

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You