መነጋገር – ሃብትን በጋራ ለማልማትና በጋራ ለመበልጸግ ጥሩ መሰረት ነው!

 መነጋገር፣ መመካከር፣ መወያየት፣… የሰው ልጆች በማስተዋል ተሞልተው በስክነት ተራምደው፣ በዕውቀትና ብልሃት የሚከውኑት ተግባር ነው፡፡ ሰክነው ሲወያዩ፣ አውቀው ሲመካከሩ፣ በመረዳት ውስጥ ሆነው ሲነጋገሩ የመግባባት አቅማቸው ከፍ ይላል ፡፡ የማድረግ አቅማቸውም ይጨምራል፡፡

በመግባባት የተጀመረ መንገድ ደግሞ ድካሙ ይቀንሳል፤ በመነጋገር የተጀመረ ሥራም ውጤቱ ያምራል፤ በመወያየት የተነደፈ እቅድም ለፍጻሜ ይበቃል፡፡ ይሄ በግለሰቦች፣ በማኅበረሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ሃቅ ነው፡፡

የጋራ ጉዳይ ኖሯቸው የመከሩ፤ መክረው የተግባቡ፤ ተግባብተውም በጋራ ወደ ተግባር የተራመዱ ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦችና ሀገራት ዛሬ ላይ ከፍ ብለው የሚታዩ፤ የበለጸጉ ተብለው የሚገለጹና የሰለጠኑ ተብለው የሚጠሩ ሆነዋል፡፡

ይሄ የመሰልጠን፤ የመበልጸግና ከፍ የማለት መንገድ የሆነው የመነጋገር ባህል ታዲያ፣ ዛሬ ላይ ሀገራት በጥቅሉም ዓለማችን በእጅጉ የሚያስፈልጋት ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜው አብሮ መቆምን፤ መተባበርን፤ በጋራ ሠርቶ መበልጸግን የሚጠይቅ ነውና፡፡ አብሮ ለመቆም፣ በጋራ ሰርቶ ለመበልጸግና ለመላቅ ደግሞ የጋራ የሆኑ ሃብትና አቅሞችን ማቀናጀትን ይፈልጋል፡፡

ምክንያቱም፣ አንድ ሀገር በሁሉ ነገር ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ አንዱ ጋ ያለ ነገር ሌላው ጋር ላይኖር ይችላል። አንዱ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሌላው ጋር የተትረፈረፈ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ በራሱ አንዱ የአንዱን ጉድለት እንዲሞላ ሆኖ የተሰራ እንደመሆኑ፤ ሀገራት በጋራ መቆምና በጋራ መልማት የሚችሉበትን ዕድል እንዲፈጥሩ ያስገድዳቸዋል፡፡

ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጓት ዐቢይ ጉዳዮች አንዱ ወደብ/የባህር በር ነው፡፡ ይሄ የባህር በር ደግሞ በተለያየ ምክንያት ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በእጇ የሌላትና አጥብቃ የምትሻው ነገር ነው፡፡ በተቃራኒው የባህር በር/ ወደብ ያላቸው ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ የሚፈልጓቸውና ማግኘት የሚችሏቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡

የአንዳቸው ጉድለት ሌላኛቸው ጋር የመገኘቱ ምስጢር ደግሞ፤ በሀገራቱ መካከል መገፋፋት ሳይሆን መተባበር፤ መነቃቀፍ ሳይሆን መነጋገር እንዲፈጠር የግድ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ይሄንኑ እውነት ትገነዘባለች፡፡ መገንዘብ ብቻም ሳይሆን ያላትን አካፍላ፤ የሌላትን ተካፍላ በመልማት መርህ ታምናለች፡፡ ይሄን ሃብትን በጋራ አልምቶ የመጠቀምና በጋራ ለምቶ የመበልጸግ እሳቤዋንም በተለያዩ መንገዶች እየተገበረች ቆይታለች፤ ትገኛለችም፡፡

በተለይ በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ አተኩራ መስራቷም ለዚህ ዐብይ ማሳያ ነው፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፤ የባቡር፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል እና በሌሎችም የሚገለጸው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተሳስሮ የመጠቀም ተግባሯም ከዚሁ በጋራ ከመልማትና ከማደግ እሳቤዋ የመነጨ ነው፡፡

አሁንም የወደብ/የባህር በር ጥያቄዋን ይዛ ስትነሳ፤ ወደብ ያላቸውን ሀገራት ወርሮ ወይም በጦር አሸንፎ የወደብ/የባህር በር ባለቤት የመሆን ፍላጎት ኖሯት አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕዝቦቿን የመልማትና የደኅንነት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችላትን አቅም ከመፍጠር አኳያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሃብትን በጋራ አልምቶ በጋራ ለመጠቀም በማሰብ እንጂ፡፡

ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተመሰረተበት 116ኛ ዓመት በዓል በተከበረበት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ኢትዮጵያ በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም፡፡ ለጋራ ጥቅም፤ ለጋራ ዕድገት እና ለጋራ ብልፅግና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ከወንድሞቻችን ጋር ተወያየተን የጋራ ጥቅም የምናስከብር እንጂ፤ በኃይል ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት ወንድሞቻችን ላይ ቃታ የምንሰነዝር እንዳልሆንን በአፅንኦት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤” ሲሉ ያረጋገጡትም ይሄንኑ ነው፡፡

ለጋራ ጥቅም፤ ለጋራ ዕድገት እና ለጋራ ብልፅግና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ለመወያየትና የጋራ ጥቅም ለማስከበር ደግሞ ዋናውና ብቸኛው መንገድ ቁጭ ብሎ መነጋገር እንደሆነ ኢትዮጵያ በማያወላዳ መልኩ አስቀምጣለች፡፡ ይሄን ለማድረግ ግን ቅንነት፤ ስለ የጋራ ተጠቃሚነትና መልማት መርህ መረዳት፤ ያለን አቅም አውቆ በዚያ ላይ እንዴት አልምቶ በጋራ መጠቀም እንደሚቻል መገንዘብ፤ መነጋገርም ሃብትን በጋራ አልምቶ ለመጠቀምና ለመበልጸግ መሰረት መሆኑን ከልብ አምኖ መቀበል ከሁሉም አካል ይጠበቃል

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You