ኢትዮጵያ ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፦ በደን ልማት ዘርፍ እየተከናወነ ባለው ሥራ ኢትዮጵያ እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ደን ልማት ብሔራዊ የ”ሬድ ፕላስ” ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደለጹት፤ የካርበን ሽያጭ ደንን ከጭፍጨፋ በመከላከልና በማልማት የካርበን ልቀትን በመቀነስ ለሚከናወነው ሥራ የሚከፈል ዓለም አቀፍ ክፍያ ነው።

ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፍ እያከናወነች ባለው ውጤታማ ሥራ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዓለም ባንክና ኖርዌይን የመሳሰሉ ሀገራት በሚያከናውኑት ክፍያ አማካኝነት በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው የደን ልማት ሥራ ባለፉት 10 ዓመታት በተለያየ መልክ ከዘርፉ 150 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማምጣት እንደተቻለ አስታውቀው፤ በቅርቡ ኖርዌይ የ25 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማቷን ጠቁመዋል፡፡

ከተለያዩ የዓለም ኩባንያዎች ጋር በጋራ በመሥራት ላይ እንገኛለን ያሉት ዶክተር ይተብቱ፤ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ በሚገኘው የደን ጥበቃ ከዓለም ባንክ ጋር የ40 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።

የካርበን ሽያጭ ክፍያ የረጅም ጊዜ የደን ልማት ሥራን የሚጠይቅ ሲሆን፤ ካርበን እንደማንኛውም እንደበቆሎ ወይም ቡና ዋጋ ወጥቶለት እንደ ገበያው ሁኔታ የሚሸጥና ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ከዘርፉ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል አንድ ሚሊዮን ሄክታር ደንን በመከለል በአካባቢው ለሚኖረው ማኅበረሰብ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ በመስጠት እንዲያስተዳድሩት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሀገሪቱ ከካርበን ሽያጭ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ የካርበን ማዕከልን በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ባለሙያዎችን አደራጅታ መሥራት ብትችል በየዓመቱ ከዘርፉ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ማግኘት የምትችልበት ዕድል እንደሚፈጠር አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ በፓሪስ የገባችውን ቃል ከመፈጸም ባለፈ በደኖቿ አማካኝነት ለቀጣናውና ለዓለም ሀገራት የምታበረክተው ንጹሕ አየር የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ በይበልጥ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ይተብቱ ገለጻ፤ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዓለም ሙቀት መጠን ለመቀነስ ያደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ላሉና በደን ልማት ዘርፍ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ሀገራት የካርበን ሽያጭ ክፍያ ያከናውናሉ።

ክፍያውም ደን ለአካባቢውና ለአየር ንብረት ሚዛናዊነት ጥበቃ በያዘው የካርበን መጠን በቶን ተለክቶ የሚከናወን ነው ያሉት ዶክተር ይተብቱ፤ ኢትዮጵያም በተለያዩ ጥብቅ ደኖቿ አማካኝነት ካርበን ለዓለም ባንክ እየሸጠች ገቢ ታገኛለች ብለዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You