የኢትዮጵያ ስምና ገጽታ ደምቆ ከሚገለጽባቸው አቅሞች መካከል አንዱ የመከላከያ ተቋምና የመከላከያ ሠራዊቱ ነው።ይሄ ተቋምና ሠራዊት በታሪክ ሂደት ሳይለዋወጥ፤ በሥርዓት ለውጥ ሳይለወጥ 116 ዓመታትን በብቃትም በጽናትም የሀገር ጠበቃና ኩራት ምንጭ ሆኖ የዘለቀ ነው።ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ1900 ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማቋቋም እና ለተቋሙም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ኃላፊ/ሚኒስትር አድርገው መሾም የተቋሙም፣ የሠራዊቱም አይለዋወጤነት መሠረት እንዲይዝ ያደረገ ነበር፡፡
በዚህም በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሠራዊት መሆኑን ከ1900 እስከ 2016 ዓ.ም ባሉ 116 ዓመታት አሳይቷል።ይሄ እየተፈተኑ መጽናት፤ እየጸኑ ማሸነፍና ድል ማድረግ ታዲያ እንደ ትናንቱ ዛሬ፤ እንደ ዛሬውም ነገ ጸንቶ የሚቀጥል የመከላከያ ሠራዊቱ ታላቅ ተልዕኮ ነው።ይሄ ተልዕኮ ደግሞ ሀገራዊውን እውነት አውቆ፤ ዓለምአቀፋዊውን ሁነት ተገንዝቦ ለሁሉም በሁሉም ቦታ መገኘትን፤ አለኝታና ጋሻ፣ የሠላምና ደኅንነት ዋስትና መሆንን በተግባር መግለጥን አጠናክሮ ማስቀጠልን የሚሻ ነው፡፡
መከላከያ ከምንም በላይ የሠላም ኃይል ነው።ይሄ የሠላም ኃይልነቱ ደግሞ አንድም ያለን ነገር እንዳይጠፋ በማድረግ ውስጥ ይገለጻል።ሁለተኛም ከእጃችን ያመለጠንና ያጣነውን ሠላም በመመለስ ውስጥ ይገለጻል።ሦስተኛም፣ የመጣ ሠላምን በማጽናት ውስጥ የሚገለጽ ነው።እነዚህን ሦስት ነገሮች ማለትም፣ በእጅ ያለ ሠላም እንዳያመልጥ በማድረግ፤ ያመለጠ ሠላም እንዲመለስ በማድረግ፣ እንዲሁም የመጣ ሠላም ጸንቶ እንዲኖር በማድረግ ሂደት ውስጥ በሚገለጸው የሠላም ኃይልነት ውስጥ መከላከያ ሠራዊቱ ከፍ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡
እነዚህ ደግሞ ትናንት ሲያደርጋቸው የነበረ፤ ዛሬም እያደረጋቸው፤ ነገም በልበ ሙሉነት የሚፈጽማቸው የእሱነቱ መሠረቶች ናቸው።ምክንያቱም ሠላምን መጠበቅ፣ መመለስና ማጽናት እንደ ትናንቱና ዛሬው ሁሉ ለነገ ብርቱ ትግልን ይሻል።ምክንያቱም፣ ሠላም ከወትሮው በተለየ ፈተናዋም፣ ፈታኟም በርክቷል፤ በርትቷልም።ይሄ የሠላም ጸር ኃይል ደግሞ በጊዜውና በሁኔታው ውስጥ ራሱን እየቃኘና እያስማማ ለመሄድ እረፍት የሌለው ፀረ ሕዝብና ሀገር ስብስብ ነው፡፡
መከላከያ ደግሞ ይሄንን ፀረ ሕዝብና ሀገር ስብስብ አደብ በማስያዝ፤ ሀገር እንድትረጋጋ፣ ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንድትዘልቅ፤ ዜጎችም ሠላምና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ለሁለንተናዊ ብልጽግናቸው እንዲተጉ ያለ እረፍት ላብና ደም እያፈሰሰ፤ ሕይወቱን እየገበረ ዘብ የቆመ ኃይል ነው።በውስጥ ሆነው ሀገር የሚያምሱ ቡድኖችን በዱር በገደሉ ገብቶ አደብ የሚያስይዝ፤ ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የሚቋምጡ ኃይሎችን ደግሞ በድንበሯ ላይ ቆሞ አጥር ሆኖ የሚያስከብራት ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር እንደ ሀገር ጎረቤቶች ሠላም ሲያጡ፤ የዓለም ሀገራት በጦር ሲናጡ ደጀን ሆኖ የደረሰ፤ ለሠላማቸው አለኝታነቱን እያረጋገጠ የዘለቀ ኃይል ነው።በዚህም የሥርዓቶች መለዋወጥ እሱነቱን ያልለወጡት፤ የሀገሩንም ሠላምና ሉዓላዊነት አስጠብቆ፤ የሌሎችንም ሠላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተሰጠውን ግዳጅ ከሩቋ ኮሪያ እስከ ጎረቤቷ ሶማሊያ በብቃት እየፈጸመ ያለ የሀገርም የወገንም ኩራት ነው፡፡
በፈተና ውስጥ እየጸና፤ በመጽናት ውስጥ እያሸነፈ በድል ከትናንት ዛሬ ላይ የደረሰው የመከላከያ ሠራዊት፤ ከዛሬ ባሻገር ያለው ነገ ብዙ መሥራትን የሚጠይቀው ስለመሆኑ አያሌ ማሳያዎች አሉ።ይሄም መከላከያ ሠራዊቱ ከትናንቱም ከዛሬውም የላቀ ግዳጅ እንዳለበት የሚያመላክት፤ ግዳጁን የሚመጥን ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት እንደሚሻው የሚጠቁም፤ ከዘመኑ ጋር የሚዘምን ማንነት እንዲኖረውም የሚያስገድድ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ትናንት የመከላከያ ሠራዊት ቀን በተከበረበት ወቅት የተላለፉ መልዕክቶች፣ የታዩ ትርኢቶች፣ አጠቃላይ የሁነቱ ድባብ ሠራዊቱ ከትናንቱም ሆነ ከዛሬው ይልቅ ስለ ነገው መንገዱና ግዳጁ በእጅጉ ትኩረት መስጠቱን መመልከትም፣ መረዳትም ይቻላል።የሠራዊቱ ሰብዕናና ሥነልቡና፣ የሰው ኃይሉ ብቃት፣ የቴክኖሎጂው ግብዓት፣ የትጥቅ አቅሙና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ለጦር ኃይል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በጊዜውና በዘመኑ ተለክተው የተደራጁ ናቸው፡፡
ይሄ ደግሞ ሠራዊቱ እንደ ሀገር የሀገርና ሕዝብን ደህንነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ፤ እንደ ዓለምም ዓለምአቀፋዊ የሠላም ማስከበር ግዳጅን ለመወጣት የሚያስችል ምሉዕነት እንዳለው ያረጋገጠ ሆኗል።በሁነቱ ሀገር ባላት አቅም እንድትኮራ፤ ሕዝብም በተፈጠረለት አስተማማኝ ደጀን እንዲመካ ያስቻለም ነው።በውስጥ ባንዳዎች፤ በውጭም በኢትዮጵያ ላይ መልካም ነገርን የማይሹ ኃይሎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ብቻ ሳይሆን እጃቸውን እንዲሰበስቡ፤ ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ የሚያስገድድ ትዕይንትም ነበር፡፡
ይሄ ደግሞ ከ116 ዓመት የጸና መሠረት ካለው የአንድ የመከላከያ ተቋምና ሠራዊት የሚጠበቅ ነው።ምክንያቱም ይሄ የመከላከያ ተቋምና ሠራዊት ታሪኩን የሚያውቅ ከታሪኩ የተማረ፤ አባቱን የሚያከብር ከጀግኖች አባቶቹ እሴትን የወረሰ፤ ሕዝብን የሚያከብር ብልሃትንና ብርታት የቀሰመ፤ ራሱን በልኩ የተረዳ በውስጡ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ መጠቀም የቻለ፤ ነገውንም ቀድሞ በመተንበይ ስለ ነገው አስቦ ራሱን በልኩ ያዘጋጀ የሀገር መከታ፣ የሕዝብም መመኪያ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016