ቦር- የፈውስ ተራራ

ኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የቅርስ ሀብቶች በስፋት ከሚገኝባቸው ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ትመደባለች። ይሁን እንጂ እነዚህን ሀብቶች በሚፈለገው መጠን የማስተዋወቅ፣ የማልማትና ከሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አቅም አሁንም ድረስ እንዳልጎለበተ ይታመናል። ሀገሪቱ ለዓለም በኪነ ጥበብ፣ ባህልና ባህላዊ ሕክምና፣ በተፈጥሮ፣ በኪነ ሕንፃና ሥነ ጽሑፍ እውቀት ያበረከተች መሆኗም እሙን ነው። ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ቀደም ያሉ የሥልጣኔ ዐሻራዎች ናቸው።

አሁን ላይ በዓለም የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙ ኪነ ሕንፃዎች፣ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች፣ ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም ታሪካዊ ክስተቶች ሀገራችን ለመላው የሰው ልጆች ዛሬ ላይ የመድረስ ምክንያት እንደነበረች ህያው ምስክር ናቸው።

በተለይ በቀደምት ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከሕክምና ጥበብ ጋር ተያይዞ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ያስቀመጧቸው የምርምር ውጤቶችና ግኝቶች በብዙኃን ዘንድ በእግር በፈረስ የሚፈለጉ ናቸው። ታላላቅ ሀገራት በብራና መጽሐፍት ላይ የተከተቡ ጥበቦችን ለመረዳት የግዕዝ ቋንቋን ጭምር በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻቸው እንደ አንድ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እስከመሥራት ደርሰዋል።

በሀገራችን ከቀደምት ጥበቦች እንዲሁም ከሀገር በቀል እውቀቶች መካከል የባህል ሕክምና ከፍተኛ ትኩረት እንደተነፈገው ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ የባህል ሕክምና ጥበብ ከሁሉም የዓለም ሀገሮች በፊት የተጀመረና ዓለም ሰልጥኖ ዘመናዊ ሕክምና ከመጀመሩ በፊት በዘርፉ የተሰማሩ ጠበብት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉንም ዓይነት በሽታ የሚፈውሱበት መድኃኒት እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ መድኃኒቶቹንም ከተለያዩ ዕጽዋት በመመራመርና በመቀመም ለታማሚው መጥኖ በመስጠት በሀገሪቱ በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

እንደ አለመታደል ሆኖ ዓለም በሕክምናው ዘርፍ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ቢደርስም በእኛ ዘንድ ግን የውጭውን ሥልጣኔ ተመልካች በመሆናችን ሀገር በቀል የሆነውን ባህላዊ እውቀት በአግባቡ ባለመረከባችን ቀደምት የሆነው የባህል ሕክምና ተንቆና ተረስቶ እንዲኖር ተፈርዶታል፡፡

ይህ እውቀት ወደ ዘመናዊው የሕክምና ሥርዓት አይግባ እንጂ ዛሬም ድረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ የፈውስ መንገድና ዘዴ ተደርጎ ይወሰዳል። ጅምርና ያልጎለበተ ቢሆንም ባህላዊ የሕክምና ዘዴዎችን ከዘመናዊው ጥበብ ጋር አስተሳስሮ ለማስኬድ ምርምር የሚያደርጉ ውስን ተቋማት አሉ። ከሁሉ በላይ ግን የቀደመውን ባህላዊ ሥርዓትና እሴት ጠብቆ በማቆየት ረገድ ማኅበረሰቡ የማይተካ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የ «የም» ማኅበረሰብ ተጠቃሽ ነው።

የም- ባህላዊ እሴቶች የመጠበቅ ምሳሌ

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው የየም ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴቶችን እና ጠቃሚ ልማዶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ጠብቆ በማስተላለፍ ከሚታወቁት መካከል አንዱ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት «የም» የሚለው ስያሜ የብሔረሰቡ መጠሪያ ሲሆን «የምሳ» ደግሞ የብሔረሰቡ መደበኛ ቋንቋ ነው። ብሔረሰቡ ከአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ታዋቂና ጠንካራ መንግሥት መስርቶ ይኖር እንደነበርም የጥናት መዛግብት ያስረዳሉ። የየም ብሔረሰብ አሰፋፈሩን በኮረብታማና ወጣ ገባ መልከዓ ምድር ላይ ያደረገ ነው። ከጊቤ ወንዝ አንስቶ እስከ ቦር ተራራ ያለው አቀማመጥም ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ የሚሄድ በመሆኑ ለመኖሪያነት አመቺ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከመዛግብትና ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያዎች መረዳት እንደተቻለው፤ ብሔረሰቡ የሰፈረበት አካባቢ የአየር ንብረት ደጋና ወይናደጋ ሲሆን፣ ምሥራቃዊው ክፍልና የጊቤ ተፋሰስ በቆላነት ይመደባል።

ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ ባህል፤ ቋንቋ፤ ታሪክና ወግ አለው። በአካባቢው ታሪካዊ ቤተ መንግሥት፣ የእምነት ስፍራዎች፣ ዕድሜ ጠገብ ደኖች፣ ትክል ድንጋዮች፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ዋሻዎች በብዛት ይገኛሉ። በርካታ ትክል ድንጋዮች የሚገኙበት ስፍራ «ዞፍካር» ይባላል። ይህ ስፍራ የየም የመጨረሻ ንጉሥ በነበረው አባቦግቦ ዘመን ቀብር ይፈፀምበት ነበር፡፡ አካባቢው በታሪካዊነቱና በአንጋፋነቱ ከሌሎች የተመረጠ በመሆኑም በፓርክ ክልልነት እንዲለይ ተደርጓል። «አንጋሪ» የተባለው ጥንታዊ ቤተ መንግሥትም በጥቅጥቅ ደኖችና በሀገር በቀል ዛፎች የተከበበ በመሆኑ በመስህብነት ያገለግላል።

የየም ብሔረሰብ የቤት ውስጥ መገልገያዎች፣ የንጉሣውያን አልባሳት፣ ከዝሆን ጥርስ የተሠሩ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎችና የሸክላ ውጤቶች ዕድሜ ጠገብ ከመሆናቸውም በላይ የብሔረሰቡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ናቸው፡፡ በብሔረሰቡ በዋንኛ ምግብነት ከአስር የማያንሱ ምግቦች ከእንሰት ውጤቶች ይዘጋጃሉ። በልዩ ማኅበራዊ ግንኙነት ወቅት የሚዘጋጅ የቆጮ ድፎ «ኮባና» ይባላል። በገንፎና በቂጣ መልክ የሚዘጋጀው ቡላም «ኬዳኦ» የሚል መጠሪያ አለው። የቆጮ ገንፎ «ናቱ» ሲባል ከጎመንና ከቆጮ የሚዘጋጀው ፍርፍር ደግሞ «ዎቶ» ይሰኛል። «ፈጨ» የሚባለውም ለሕፃናት ምግብነት የሚዘጋጅ ነው።

ከብሔረሰቡ ባህላዊ መጠጦች ዋናው «ቦርዴ ማኡሻ» ይባላል። የሚዘጋጀውም ከገብስ፣ ከዳጉሳ፣ ከቀይ ጤፍና ከብቅል ነው። ሌላው ባህላዊ መጠጥ ደግሞ «ኪአ» የሚል መጠሪያ አለው። ይህ የመጠጥ ዓይነት ውሃ ሳይጨመርበት ድፍድፉ ብቻ ተጨምቆ የሚቀርብ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ ይነገርለታል። በልዩ ዝግጅት ወቅት የሚዘጋጀው ባህላዊ መጠጥም «ኡሻ» ይባላል።

የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው «ሀገርኛ» አምዱ ላይ በስፋት ለመዳሰስ የወደደው የየም ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴት የሆነው ደግሞ ጥቅምት 17 በየዓመቱ «በቦር ተራራ» ላይ የሚደረገው የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ አንዱ ነው።

ቦር- ዓመታዊ የመድኃኒት ለቀማ

አቶ በረከት ይገዙ ይባላል። በየም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪስት መስህብ ጥናት ልማት ግብይት ዳይሬክተር ነው። የየም ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብቶቹን ጠብቆ የማቆየትና ለትውልድ የማስተላለፍ እሴት እንዳለው ይናገራል። ከዚህ ውስጥ አንዱና ማኅበረሰቡ በስፋት የሚታወቅበት ጥንታዊ ሀብት «ባህላዊ ሕክምና» እንዲሁም የመድኃኒት ቅመማ መሆኑን በመግለፅ የሕክምና መድኃኒቱ አዘገጃጀት፣ አመታዊ የእፅዋት ለቀማ፣ የተፈጥሮ ጥበቃ እሴቶችን ያብራራል።

አቶ በረከት እንደሚለው፤ በየም ብሔረሰብ ከጥንት ጀምሮ ማኅበረሰቡ ለሕክምና አገልግሎት የሚውል ባህላዊ መድኃኒትና ቅመማን ይጠቀማል። ይህንን መድኃኒት ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሳት ለሚያጋጥማቸው ህመም ፈውስ እንዲሆን ጭምር ነው። ከብቶች፣ በጎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የቤት እንስሳት ሲታመሙ ጥቅምት 17 በዓመት አንድ ጊዜ ከቦር ተራራ የተለቀመው ባህላዊ መድኃኒት ተቀምሞ ጥቅም ላይ ይውላል ይህ ሥርዓት ከጥንት የነበረና ለትውልድ ሲተላለፍ የቆየ እሴት ነው።

በየም ጥቅምት 17 ታዋቂ በሆነው በዞኑ በሚገኝ «ቦር ተራራ» መድኃኒት ለቀማ ይወጣል። ከዚህ ቀን ውጪ በስፍራው ዓመቱን ሙሉ ምንም ዓይነት ለመድኃኒት ቅመማ የሚውል እፅዋት አይለቀምም። በዚህ ቀን አባቶች እና እናቶች ከፊት ሲሆኑ ወጣቶችና ልጆች እነርሱን ተከትለው ከኋላ እፅዋቶቹን ይለቅማሉ። ይህ የሚሆነው እውቀትና ጥበብ ከቀደምት አያቶቻቸው የተማሩት አባትና እናቶች በተመሳሳይ እውቀቱን ለማሸጋገር እንዲችሉ ልጆቻቸውን አስከትለው ትምህርቱን እንዲቀስሙ ያደርጋሉ።

በየም ዞነ ጥቅምት 17 ልዩ በዓል ነው። ከመድኃኒት ለቀማ ቀንነቱ ባሻገር ማኅበረሰቡ እርስ በእርስ መልካም ምኞቱን ለመገላለፅና ትስስሩን ለማጠናከር ይጠቀምበታል። በዚህ ምክንያት «እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን» የሚል መልዕክት ይለዋወጡበታል። የዞኑ አስተዳደር የባህል መሪዎች፣ አባቶች እናቶችና ሁሉም ማኅበረሰብ ቀኑን ልክ እንደ በዓል ቀን በመቁጠር በልዩ ድምቀት ያከብሩታል።

ጥቅምት 17 ከቦር ተራራ ላይ የሚለቀሙ ለባህላዊ መድኃኒት ቅመማ የሚያገለግሉ እፅዋት አባቶች እንደ «እርሾ» የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ይህም ማለት የባህላዊ መድኃኒት ቀማሚዎቹ ከሌላ አካባቢ፣ ከቤታቸው ጓሮና ከልዩ ልዩ ስፍራዎች የሚሰበስቡትን ግብዓት ጥቅምት 17 ከተለቀመው ጋር በማዋሃድ ልዩና ፈዋሽ ባህላዊ መድኃኒት ያዘጋጁበታል።

ከቦር ተራራ ላይ ጥቅምት 17 እፅዋት ለቀማ የሚደረግበት ዋንኛ ምክንያት የክረምቱ ጊዜ ወጥቶ የበጋው ወራት የሚጀምርበት በመሆኑ ምክንያት ነው። በተለይ በቦር ተራራ ላይ የሚደረገው የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ ጠዋት ፀሐይ ስትወጣ የሚደረግ ነው። ተራራው ከፍታ ላይ ያለ በመሆኑና የመጀመሪያዋ ፀሐይም በዚያ ስፍራ ላይ ስለምትወጣ የመድኃኒቱን ፈዋሽነት እንደሚጨምር አባቶች ያምናሉ። ይህንን የአባቶች እምነትና የባህላዊ መድኃኒት ቅመማ ሥርዓት ለማጥናትም የጅማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ምርምር እያደረጉበት ይገኛሉ።

የየም አባቶች በቦር ተራራ እፅዋት ለቅመው የሚቀምሙት ባህላዊ መድኃኒት ለልዩ ልዩ ሕክምና አገልግሎት ይውላል። ከእጽዋቱ ከ100 በላይ ለሚሆኑ የበሽታ ዓይነቶች «ፈዋሽ» እንደሆኑ የሚታመንባቸው ባህላዊ መድኃኒቶች ይቀመማሉ።

ጥቅምት 17 በአባቶችና እናቶች እፅዋቱ ከተለቀመ በኋላ ወደ ቤት ይወሰዳል። የተሰበሰበው እፅዋትም የሚፈለገው ስፍራ እንደደረሰ በፀሐይ ብርሃን እንዲደርቅና ንፅህናው በተጠበቀ ቦታ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ማንኛውም / ታማሚ ወደ ባህላዊ ሀኪሞቹ በመሄድ በሽታውን ሲያስረዳ እፅዋቱ እየተለየና እየተቀመመ ይሰጣል። በዚህ መንገድ የየም አባቶች የሕክምና ሥርዓቱን ዳግም ጥቅምት 17 መጥቶ ለቀማ እስኪያደርጉ ድረስ ይቀጥላሉ። የየም ማኅበረሰብ በእፅዋት ለቀማው ላይ በጋራ ይሳተፍ እንጂ መድኃኒት ቅመማውን የሚያደርጉት ግን እውቀቱና ጥበቡ ያላቸው ባህላዊ ሐኪሞች ናቸው።

የየም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ይህንን ባህላዊ እውቀት ለማስጠናት እንዲሁም ከዘመናዊው የሕክምና ዘዴ ጋር በማስተሳሰር ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ከዚህ ባሻገር ጥቅምት 17 በቦር ተራራ ላይ የሚደረገው የለቀማ ሥርዓት በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍልና በሌሎች ዓለማችን ላይ ባሉ ጎብኚዎች እንዲታወቅና እሴቱ ተጠብቆ እንዲቆይ በመሥራት ላይም ይገኛል። ሌላው መምሪያው ይህ እሴት በምርምርና ሳይንሳዊ ዘዴ እንዲዳብር ለማድረግ የማዕከል ግንባታም እያካሄደ ነው። በማዕከሉ ምርምር ከማድረግ ባሻገርም ሕክምና እውቀቱ ባላቸው አባቶች እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሠራ ነው። ሀገር በቀል እውቀቱን በሀገር ውስጥ ያሉም ሆነ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች እንዲያውቁት በማድረግ አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ እየተሠራ ነው። ይህ ማዕከል በነገው ዕለት ጥቅምት 17 ተመርቆ ሥ ራ ይጀምራል።

የየም ማኅበረሰብ ባህላዊ መድኃኒት በሚለቀምበት በቦር ተራራና በአካባቢው የሚገኘውን ሥነምህዳር የመጠበቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህ ባህላዊ የመድኃኒት ለቀማ ሥርዓት ለሥነ ምህዳርና ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን ድርሻ ይጫወታል። ማንም ሰው ከጥቅምት 17 ውጪ በዚህ ተራራ ላይ መድኃኒት መልቀምም፣ ደኑንና ልዩ ልዩ እፅዋትን መቁረጥም አይችልም። ይህ ሥርዓት መኖሩ ደግሞ አካባቢው እንዲጠበቅና ለም ሆኖ እንዲቆይ የራሱን ድርሻ ይጫወታል።

ከባህር ወለል/ ሲ ሌብል/ ሁለት ሺህ 939 ከፍታ ያለው የቦር ተራራ በየም ዞን የሚገኙ አራት ቀበሌዎች ያዋስኑታል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖር የማኅበረሰቡ ክፍል የደን ሽፋኑን እና የእፅዋት ስብጥሩን የሚያዛቡ ማንኛቸውንም ዓይነት ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይካሄዱ የመጠበቅ ኃላፊነት ይወስዳሉ። በብሔረሰቡ ዘንድ ለበሽታ ፍቱን መድኃኒትነት ያላቸው እፅዋት የሚገኙበት ይህ ስፍራ በዚህ መልኩ ከንክኪና ሕገወጥ ድርጊት ይጠበቃል።

ዳግም ከበደ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016

Recommended For You