የባህር በር ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለምአቀፍ ደረጃ 44 ሀገራት የባህር በር የላቸውም፤ ከእነዚህ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ትልቅ የምትሰኘው ወደብ የሌላት ሀገር የመካከለኛዋ ኤዢያ ካዛኪስታን ናት።በቆዳ ስፋት ትንሿ ደግሞ በአውሮፓ ውስጥ ያለችው ቫቲካን ናት፤ ቫቲካን ደግሞ በቆዳ ስፋቷ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ቁጥሯም በዓለም በ195ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ናት።

በዓለም በሕዝብ ብዛቷ 11ኛ ላይ የተቀመጠችው እና 120 ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ያላት፤ ለዘመናት የባህር በር ኖሯት የቆየችው፤ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የባህር በሯ እየቀነሰ ከሦስት አስርት ዓመታት ወዲህ የባህር በር ያጣችው ደግሞ፤ አፍሪካዊቷ ሀገር የእኛዋ ኢትዮጵያ ናት።

የተባበሩት መንግሥታት ጥናት እንደሚያሳየው፤ የአንደ ሀገር አጠቃላይ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ከ25 እስከ 30 በመቶ የባህር በር ነው።ከሰሞኑ በቀይ ባህር እና በወደብ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በጥናቱ መሠረት ለምሳሌ ኢትዮጵያ ጂዲፒዋ 100 ቢሊዮን ዶላር ቢሆን፤ ዓይኗ እያየ ከ25 እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች ማለት ነው።ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን 15 ቢሊዮንም ሆነ 20 ቢሊዮን ወይም 30 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጋ የባህር በር ብታገኝ ያዋጣታል።

እንደኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆኑ ሀገሮች ከዋና ዋና የገበያ ማዕከሎች የተገለሉና የራቁ መሆናቸው፤ የባህር በር የሌላቸው መሆኑ ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ከፍተኛ ማነቆ ይሆንባቸዋል።‹‹አሰብ የማን ናት?›› በሚለው መጽሐፋቸው ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከውና ከውጭ የምታስገባው ጠቅላላ ንግድ ከ90 በመቶ በላይ የሚከናወነው በባህር ነው።ይህንን ለማከናወን ከ1983 ዓ.ም በፊት ኢትዮጵያን ከማስከፈል ይልቅ ገቢ የሚያስገኘው ወደብ በ2003 ዓ.ም አካባቢ በቀን ሦስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እያስወጣት ነበር።ይህ የክፍያ ወጪ እንጂ የሚያስገኘው ምንም ዓይነት ገቢ የለም።ኢትዮጵያ የባህር በር ባታጣና እንደቀድሞ በነፃ የራሷ ወደብ ቢኖራት፤ ገንዘቡ በየዓመቱ ሃያ እና ሰላሳ ፋብሪካ ለመገንባት እና ለብዙዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላት ነበር ሲሉ የኢትዮጵያን ጉዳት አስረድተዋል።

ዓለምአቀፍ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ ሀገሮች ላይ ጥናት ሲካሔድ ወደብ ያለው ሀገር በ24 ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚው በእጥፍ ሲያድግ፤ ወደብ የሌለው ሀገር ግን ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 34 ዓመት ይፈጅበታል።ለእዚህ ቀላሉ ማሳያ ወደብ የሌላቸው ሀገራት የወደብ የትራንስፖርት ወጪያቸው ወደብ ካላቸው ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ የሚጨምር መሆኑ ነው።

በሌላ በኩል የባህር በር አለመኖሩ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ሲታይ፤ የሀገር ውስጥ ምርትን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ፤ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የተለያዩ ከአምራቹ ሀገር ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳዮችም ያጋጥማሉ።ውጣ ውረድ እና ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ክፍያ ጉዳት ብቻ ሳይሆን የወደቡ ባለቤት ሀገር የሚሰጠው የተቀላጠፈ አገልግሎትም ወሳኝነት አለው።«አንድ ሀገር የባህር በር ከሌለው የግብርና ምርትም ሆነ ማዕድን እንዲሁም ሌሎችም ለዓለም ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ ምንም ዓይነት ምርቶች ቢያመርትም ምንም ዋጋ የለውም፤» የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርም ይሄንኑ እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

በእርግጥም መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ምርት አምርቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ፈተናው ከበዛ ውሎ አድሯል።ለጅቡቲ ወደብ ኢትዮጵያ የምትከፍለው ታሪፍ በየጊዜው እያደገ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ 25 በመቶ ጭማሪ የታየበት ጊዜ መኖሩ እየተጠቆመ ነው።በውጭ ምንዛሪ የተገዛው ጥሬ ዕቃም ሆነ መድኃኒትን ጨምሮ የተለያየ ምርት ወደ ሀገር ሲገባ የባህር በር ባለመኖሩ፤ ተጨማሪ ወጪን ያስከትላሉ።በዚህ ሳቢያ ዜጎች ከፍተኛ የኑሮ ጫና ያጋጥማቸዋል።

የባህር በር ባለመኖሩ ሰዎች ለሚለብሱት ልብስ፣ ለሚያድሩበት መጠለያ እና ለሚመገቡት ምግብ ሳይቀር የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ ይሆናል።ይህንን ገንዘብ ማግኘት ካልቻሉ የመኖር ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እስከ መግባት ይደርሳል።የዋጋ መናር ዜጎችን በእጅጉ ከማማረር በተጨማሪ የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ከባድ ይሆናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ አሁን ብቻ ሳይሆን በተለይ ወደ ፊት የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ዘላቂ ሠላም ወሳኝ ብቻ ሳይሆን የህልውናዋ ጉዳይም ነው።አሁን ላይ የወደብ ክፍያ እየተፈፀመ፤ ያለውን ሕዝብ ማኖር ችለናል።ወደ ፊት በ2030 ወደ 150 ሚሊዮን፤ በ2050 ደግሞ ቁጥሩ በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ የሚገመት ሕዝብን ያለባህር በር እንዲኖር መፍረድ በየትኛውም መልኩ ተገቢነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ሊሆን የሚችልም አይደለም።

የባህር በር ማጣት ይህንን ሁሉ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ያለፈውን በማስታወስ እንድንቆጭ ያስገድደናል።ያም ቢሆን ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳለፈ ታሪክ በርን ዘግቶ ከማለቅ እና ከመፍረስ በፊት የባህር በር ሊገኝባቸው የሚችሉ ሠላማዊ አማራጮችን ማየቱ የሚያስከፋ አይደለም።ከላይ እንደተገለፀው፤ የባህር በር አለመኖሩ በቀጣይም ኢኮኖሚውን አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡

ይህ ሲሆን ደግሞ የሀብት ሽሚያን እና የፖለቲካዊ ቀውስ ያመጣል።ፖለቲካው መታመሙ ለተደጋጋሚ ግጭት ይጋብዛል።ይህ ደግሞ እያደገ ሲሔድ ሀገር እስከማፍረስ የዘለቀ ጉዳት ይኖረዋል።ይህ ሁሉ ሲጠቃለል የባህር በር በተለይ የሕዝብ ቁጥሯ ሰፊ ለሆነ እንደኢትዮጵያ ላለች ሀገር የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጉዳይ ከመሆን አልፎ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ እስከመጣል የሚደርስ አሳሳቢ አጀንዳ ነው።

በእርግጥ የዓባይን ውሃ የመጠቀም ጉዳይ ከ50 ዓመት በፊት ህልም ነበር።በብዙ ትግል እና በምክክር አሁን በዓባይ ወንዝ ላይ የዓባይ ግድብ ተገንብቶ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።የባህር በር የማግኘት ጉዳይም ዛሬ ሃሳቡ መነሳቱ እንደትልቅ ጉዳይ ተገልፆ የሚያስወቅስ ሊሆን ይችላል።ነገር ግን ዛሬ ሃሳቡ ከተነሳ ይህኛው ትውልድ ባይችለውም፤ ቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ሠላም!

 ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016

Recommended For You