ወጣቱን ከሱስ የመታደግ ጠንካራ ጅምር

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የትምባሆ ምርት የመጠቀም ምጣኔን በተመለከተ በተካሄደው ‹GATS Ethiopia 2016› ሀገራዊ ጥናት መሠረት 29ነጥብ3 በመቶ፣ ወይም ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊየን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለደባል አጫሽነት መጋለጣቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ መዝናኛ ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲ እና መሰል በሆኑ ቦታዎች የሚሠሩ፣ የሚገለገሉ እና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለደባል አጫሽነት ተጋላጭ መሆናቸውን ይኸው መረጃ ያስቀምጣል።

ትምባሆን መጠቀም ለካንሰር፣ ለመተንፈሻ አካልና ለልብ ህመም፣ ለጭንቅላት ውስጥ ለደም መፍሰስ እና ሌሎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል። እንዲሁም፣ የአካል ጉዳት እና ሞትን እንደሚያስከትልም በሳይንስ ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ የትምባሆ ተጠቃሚ ወጣት ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የወጣቱን ተጋላጭነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይነሳል። ይህ ችግር መፍትሔ ካልተበጀለት የተጎጂዎች ቁጥር የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል። ይህም የጤና መታወክን በማስከተል የዜጎች የህክምና ወጪ እንዲጨምር ከማድረጉም ባሻገር ለመድኃኒት ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ይጨምራል። ምርታማነትን በመቀነስና መሰል ጉዳቶችን በማድረስም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረ ይሄዳል።

ትምባሆ ከአጫሹ ባሻገር ለጭሱ የተጋለጡ ሰዎችን ጤና የሚጎዳ በመሆኑ ሕዝብ የሚሰበስብበትን ቦታ ከትምባሆ ጭስ ነፃ በማድረግ ለመቆጣጠር እንዲያስችል ‹‹የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ›› መዘጋጀቱ ይታወቃል። የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና፣ መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከትምባሆ እና አደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ ይናገራሉ።

እንደ ሥራ አስኪያጇ ማብራሪያ፣ ከትምባሆ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በ2015 ሰፊ የንቅናቄ ሥራ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተሰርቷል። ትምባሆ ማጨስ የተከለከለባቸው የሕዝብ መገልገያና መሰብሰቢያ ሥፍራዎች ላይም ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።

ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ ትምባሆ ማጨስ በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሠራው ሥራም በ705 የትምባሆ ማስጨሽያ ቤቶች ላይ ርምጃ ወስዷል። ‹‹እኛ እንሥራ እንጂ ማኅበረሰቡ ካላገዘን ምንም ነው።›› ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ሰው ከሱስ እንዲወጣ እና ጤናማ ሕይወት እንዲመራ ለማድረግ ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ጣዕመ በበኩላቸው፤ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራን በተመለከተ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይም ከትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን በትምባሆ እና የአደንዛዥ እጽ ዙሪያ ግንዛቤ ለመስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል። በትምህርት ቤቶችም ‹የጸረ ትምባሆ› ክበባቶችን በማደራጀት ተማሪዎች እንዲያውቁት እየተሠራ ይገኛል።

በባለስልጣኑ የምግብ እና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ምሬሳ ሚደቅሳ፣ ባለስልጣኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን መካከል የኅብረተሰቡን ጤና ማስጠብቅ አንዱ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ አንጻር በትምባሆ እና አደንዛዥ እጽ ዙሪያ ኅብረተሰቡ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲኖረው በተለያዩ መድረኮች ላይ የንቅናቄ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰውም፣ ከዚህ በሻገር በመደበኛ እና ከመደበኛ ጊዜያት ውጭ የቁጥጥር ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል። ለአብነትም ከመደበኛ ውጭ የሌሊት የቁጥጥር ሥራዎችን በመሥራት፣ በዚህም የተለያዩ ለውጦች ሊመጡ እንደቻሉ አስቀምጠዋል። ይህም በተፈለገው ቦታ ላይ ሁሉ ትምባሆ ማጨስ እንደማይቻል ለማወቅ ያስቻለ ቢሆንም እነዚህ ለውጦች የተለያዩ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ጭስ ነፃ ሆነዋል ለማለት እንደማያስደፍሩ ገልጸዋል። ለዚህም ሠፊ ሥራን መሥራትን ይጠይቃል ይላሉ።

አቶ ምሬሳ ተቋሙ ስለወሰደው ርምጃ ሲገልጹም፣ ‹‹ትምባሆ ሲያስጨሱ በተገኙ ተቋማት ላይ የማሸግ ርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ ምርቶችን ሲሸጡ እና ሲያከፋፍሉ በተገኙት ላይም ምርቶችን በመሰብሰብ እንዲወገዱ፤ በሕግ አግባብም እንዲጠየቁ ተደርጓል›› ብለዋል።

ትምህርት ቤቶችን በተመለከተም ከትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በመሥራት ላይ እንደሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎች በሱስ እንዳይያዙ፣ አደንዛዥ እጾችን መጠቀም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በጤና ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳቶች እንዲያውቁት በሚኒ-ሚዲያ አማካኝነት መረጃ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። እነዚህ ርምጃዎች አጥጋቢ ባለመሆናቸው በቀጣይ በስፋት እንደሚሠራም ተናግረዋል። አሁን ላይ የታዲጊዎች እና የወጣቶች የትምባሆም ይሁን የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነት እየተስፋፋ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ምሬሳ፤ ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል። በቀጣይም ትምባሆ እና አደንዛዥ እጽን በተመለከት የትኛውም ተቋም ላይ እንዳይጨስ የተጠናከረ እና የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ታቅዷል።

ትምባሆ የሚያጨሰውን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን፤ የማያጨሰውን ጨምሮ ጉዳት ላይ ይጥላል። ጉዳቱም ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ይጨምራል። በተጨማሪም ራስና ቤተሰብ ላይ፤ ከፍ ሲልም ሀገር ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያጨሱት ብዙ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሚደቅሳ፣ ችግሩ የሁሉም እንደሆነው ሁሉ፣ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ቢችል ራስን፣ ቤተሰብን እና ሀገርን ማዳን እንደሚቻል ይገልጻሉ ።

የባለስልጣኑ ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ‹‹ወጣቱ ከሱስ መውጣት አለበት። ስለዚህም ቁጥጥሮች ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው በመረዳት ይህንን የሚመጥን ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ በኋላም ባለስልጣኑ አብሮ ለመሥራት የስምምነት ሰነድ ከተፈራረማቸው 17 ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠራበት ይሆናል›› በማለት ተናግረዋል።

የትስስር ሰነዱን ከፈረሙት መካከል የጤና፣ የንግድ፣ የፍትሕ፣ የግብርና እና የትምህርት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠቃሽ ናቸው። በሰነዱ ላይም የትምባሆ ቁጥጥርን በጋራ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ታምኖበታል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You