ያለ መስዋዕት፤ ስለምን ድልን ትጠብቃላችሁ?!

የአንድ ሀገር ትልቁ ሀብት የሰው ልጅ ነው። የተፈጥሮ ሀብትን በትክክል መጠቀም የሚችል የተማረ፣ በዕውቀትና በመልካም ስብዕና የተሟላ ዜጋ ለማፍራት ለትምህርት ጥራት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። ትምህርት በዓለም ላይ ለሚታዩ ለውጦች ጉልህ ሚና የሚጫወት፣ ለእድገትና ለለውጥ ቀዳሚ መሠረት መሆኑንም አይዘነጉም።

ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። የትምህርት ዓላማ እውቀትን ማስጨበጥ እና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚጠቅም የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንደሆነ እሙን ነው።

በዚህ ረገድ ባለፉት 30 ዓመታት የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩበት የሚነገርለት፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ባለሙያዎቹ ሲገልጹ ይደመጣሉ። የትምህርት ዘርፍ የትምህርት ዓላማን ከማሳካት ይልቅ ያስከተለው ጉዳት የሚያመዝን መሆኑንም ይጠቁማሉ።

በተለይም በወቅቱ የነበረው መንግሥት ትምህርትን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ይጠቀምበት የነበረ በመሆኑ የትምህርት ዘርፉ ዋና ዓላማውን እንዲስት አድርጎታል። በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ እንደተሠራው ሁሉ፤ ሀገርን መለወጥ የሚያስችል ዜጋ ለመፍጠርም ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት በትኩረት አልተሠራም። በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ የትምህርት ዋጋ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማምጣት ሳይችል ቀርቷል የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ።

በዚህም አሁን ላይ ያለው መንግሥት የትምህርት ዘርፉ ከገባበት የችግር ማጥ የማውጣት ቁርጠኛ ፍላጎት እንዳለው ከመግለጽ ባሻገር፤ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ልባዊ መሻቱ እንደሆነ ትላልቅ ርምጃዎችን በመውሰድ አረጋግጧል። ለዚህም ቀድሞ የነበረውን የትምህርት ዘርፍ ችግር ያስቀራል የተባለ የትምህርት እና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ፤ አዳዲስ አሠራሮችን እስከማስተዋወቅ የደረሰ የትምህርት ማሻሻያ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ርምጃዎችን በመውሰድ አሳይቷል።

በተለይም አዲሱ ሥርዓት ትምህርት በኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት ሲሠራበት የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ ቀይሯል። ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የትምህርት ሥርዓት የግብረ ገብ ትምህርት መካተቱ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

በዘርፉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተከትሎ ጊዜያዊ ችግሮች ማጋጠማቸው እንደማይቀር ልብ ሊባል ይገባል:: ለዚህም ደግሞ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ውጤት አንድ ማሳያ ነው:: የውጤቱ አስደንጋጭነት የትምህርት ዘርፉን ከሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈ መላውን ሕዝብ ያነጋገረና ያስደነገጠ ጉዳይ ነው:: በትምህርት ዘመኑ ፈተናውን ከወሰዱት ከ845 ሺ በላይ ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡት 27 ሺ 267 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ይህም ከአጠቃላይ ተማሪዎች ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሸፍን ነው፤ ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ ሦስት ሺ 106 ትምህርት ቤቶች መካከልም አንድ ሺ 328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም::

ውጤቱ እንደ ሀገር በዘርፉ ውድቀት ላይ መሆናችንን የሚያሳይ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ባይሆንም፤ በተቃራኒው በርካቶች የተጀመረውን ለውጥ በጥርጣሬ ወደማየት ሲሻገሩ ታዝበናል። በብዙዎች ዘንድም «የምዘና ሂደቱን በግልጽ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው» የሚል አሉታዊ ሃሳብን ፈጥሯል። ሁሉም ተማሪዎች በድጋሚ መፈተን አለባቸው እስከሚሉ አስተያየቶች የተሰጡበት ጭምር ነው።

ነገር ግን ዛሬ ያስደነገጠን ውጤት የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመታት ሥራ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ከዚያም በላይ ተከማችቶ የቆየ ችግር ነው:: ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ተማሪዎች በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ችግሮች ነበሩ። ይህም ተማሪዎች በቂ ዕውቀት ሳይጨብጡና ሳይቀስሙ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ሲዘዋወሩ እንደቆዩ ይታወሳል። እነዚህና መሰል ችግሮች ከትናንትናችን ጋር ተደምረው አስደንጋጭ የሆነውን የ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት አስታቅፈውናል።

መዘንጋት የሌለበት ሐቅ በትውልዱ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈው ውጤት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል መጠቆም ያስፈልጋል። ይህ ሁኔታ ጀመረ እንጂ አያቆምም፤ ላለፉት 30 ዓመታት ሲፈርስ የነበረ ተቋም ባንድ ጀምበር ተዓምር አይሠራም፤ የሚቀጥለው ዓመትም ውጤት ከዚህ የሚለይ አይደለም። አሁን ዘጠነኛ ክፍል ያሉት ተማሪዎች ወደ 10ኛ ክፍል ሲደርሱ ነው ለውጥ ማየት የምንጀምረው።

ለዓመታት መንገድ የሳተን ሥርዓት በፍጥነት ወደ ትክክለኛው መንገድ ለማምጣት ያስቸግራል። የትምህርት ዘርፍ ስብራት በቶሎ የሚጠገን አይደለም። በትንሹ አንድ ትውልድ አክሽፎ እና ቀጣይ ትውልዶችን መርዞ ነው ያለፈው። ይህ እስከሚጸዳ ዓመታት የግድ መውሰዱ አይቀርም። ምክንያቱም፤ የትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት በሂደት ዛሬ ላይ እንደደረሰ ሁሉ፤ የተጀመረውም ለውጥ ፍሬው የሚታየው በሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት፤ በሥርዓት (የትምህርት) ውስጥ ሦስት ዓይነት ለውጦች አሉ። አንደኛው ተሃድሶ የሚባል ሲሆን ቀጣይነት የሌለውና ወቅታዊ ለውጥ ነው። ለጭብጨባ፣ ለሽብሸባ፣ ለስብሰባ ብቻ ታስቦ የሚደረግ ማለት ነው። ሁለተኛው ነገሮች ቦታ እንዲለውጡ የማድረግ ሲሆን በዚህ በኩል የነበረውን ለውጥ በዚያ በኩል ማውጣት ማለት ነው። የበሩ መውጫ ተለወጠ እንጂ የቤቱ ይዘት ያው ነው። ሦስተኛውና ትክክለኛው የሚባለው ለውጥ ስር ነቀል ለውጥ ነው ።

ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። ስለዚህ ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው ለውጥ ሲባል አሁን እንዲሆንለት ነው የሚፈልገው። ለውጥ ግን ሂደት ነው። አንዱ የለውጥ ባህሪ ሂደት መሆኑ ነው። ሂደቱን የማይጠብቅ እድገት ይፈርሳል። ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም በአንድ ሌሊት ብትገነባ ኖሮ በአንድ ሌሊት ትፈርስ ነበር።

እናም፤ የተጀመረው ሥር ነቀል ለውጥ የውጤት ፍሬው የሚያፈራው ከሰባት፤ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው። የትምህርት ሥርዓቱ ለዓመታት መስመሩን ስቶ ሲጓዝ የነበረ በመሆኑ፤ ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። የሥርዓቱ ሰለባ የሆነን የዛሬውን ትውልድ መስዋዕት እስከማድረግ የሚዘልቅ ነው።

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተና ተፈታኞች ላይ በተጨባጭ የታየው የዚሁ አካል እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ምንም እንኳን ለዛሬው ስብራታችን ትናንትናችን ተወቃሽ ቢሆንም፤ የትናንቱ ችግራችን እስከመቼ ነው ለዛሬው ውድቀታችን ምክንያት ሆኖ የሚቀጥለው የሚለው ግን መልስ ሊሰጠው የሚገባው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው ::

ስለዚህ የተጀመረው ስር ነቀል ለውጥ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በሂደት እንደመሆኑ፤ ይሄንኑ ከዳር ለማድረስ እንደ ሀገር ከሁሉም የነቃ ተሳትፎ ይጠበቃል። በዚህም መንግሥት ከትናንት የተሻገረው የትምህርት ሥርዓት ስብራቶችን ለመጠገን የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን ለማሻሻል እንዲሁም ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ የሄድንበትን መንገድ በሌሎች የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ መንገዶች ልንራመድ ይገባል። በተለይ ደግሞ የመምህራንን አቅም ስለማጎልበትም መጨነቅ ይኖርብናል። ከዚህ በተጓዳኝ ለተማሪዎች ዕውቀትን ማቀበል ያለበት የተማረ ኃይል እንደመሆኑ የመምህራኑ አቅምም እንዲሁ ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው:: በመሆኑም የመምህራን አቅምን በመገንባት ረገድ ሰፊ ሥራ መስራት ይኖርበታል።

ሌላው በሀገራችን ተማሪዎች ሁለንተናዊ አቅም እንዲያድግ መንግሥት በዋናነት ደሞዝን ጨምሮ የመምህራን አኗኗርና ሕይወት መቀየር የሚያስችሉ ሥራዎችንም መሥራቱ ለትምህርት ጥራቱ የማይተካ ሚና እንዳለው መታወቅ አለበት። ለዚህም አፋጣኝ ውሳኔ በመስጠት ለተግባራዊነቱ ሊሠራ ይገባል። በተጨማሪ ሌላው ከትናንትናችን ውስጥ የቱንም ያህል ችግሮች ቢኖሩ ዛሬም ያልተሻገርናቸው እጥረቶች ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም::

ለአብነትም ለተማሪዎች የመጻሕፍት አቅርቦት አለመኖር፣ ትክክለኛ የትምህርት ሰነዶችን የማጣራት ዘመቻው ደካማ መሆኑ፣ የምዘና ሥርዓቱ ግልጽነት የተሞላበት አሠራር ያልተዘረጋለት መሆን ወዘተ. አሁንም በትምህርት መስኩ የሚታዩ ጉድለቶች ናቸው።

በጥቅሉ ውጤታማ ባልሆነ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ ነገ ከነገ ወዲያ ምን ዓይነት መምህር፣ ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ኢኮኖሚስት …. ወዘተ ሊሆን ነው:: በዚህ መንገድ አልፎ የሚፈጠር ባለሙያ በዘርፉ ለሀገር በትክክል አበርክቶ ይኖረዋልን? ያጠራጥራል። በትምህርት ዘርፉ የተጀመረው ለውጥ ውጤት ማሳየት ለመጀመር እስከ 10 ዓመት የተሻገረ ጊዜን ሊጠይቅ ይችላል። ይልቁኑ፤ ለውጥ ጥቂት ተጫዋቾችን እና ከዳር ሆነው የሚመለከቱ ሳይሆን ሁላችንም በመጫወቻ ሜዳው ውስጥ በመግባት የእራሳችንን ድርሻ እንድናበረክት የሚፈልግ ሂደት ነው ፡፡ ለውጥ ተመልካቾች የሚመለከቱት እና መልካም ውጤት ሲታይ የሚጨበጨብለት እና ውጤቱ መልካም ሳይሆን ሲቀር ደግሞ የሚተችበት እና ቅሬታ የሚቀርብበት የጨዋታ ዓይነት አይደለም።

ፈረንጆቹ “There’s no victory without sacrifice” እንደሚሉት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተጀመረው ስር ነቀል ለውጥ ፍሬያማ ሆኖ እንዲታይ ዋጋ መክፈል ይጠይቃል። ዛሬ የለውጡ ጅማሬ መራር መሆኑን መጥላት አይገባም። ምክንያቱም በዘርፉ የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ያለ መስዋዕት የሚገኝ ድል ባለመኖሩ፤ ልባችን ጅማሮ ላይ ሳይሆን ፍጻሜው ላይ ሊሆን ይገባል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You