‹‹እኛ ወታደሮች የሀገራችን ዓርማ መሆን የምንችለው በሕዝብ ነው››ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው አያሌው በመሐንዲስ ዋና መምሪያ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ

ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሠራዊት ቀን የሚከበርበት ዕለት ነው። ሰሞኑን ‹‹በተፈተነ ጊዜ የሚጸና የድል ሠራዊት›› በሚል መሪ ሃሳብ 116ኛው የሠራዊት ቀን በተለያዩ መርሐግብሮች እየተከበረ መሆኑም ይታወቃል። ከዚህ ቀደም የሠራዊት ቀን የተባለው ጊዜ ጅማሬውን 1987 ዓ.ም አድርጎ የካቲት 7 ቀንን መርጦ ሲከበር የቆየ መሆኑ ይታወሳል። ይሁንና ይህ ዓ.ም እና ዕለት ግን የኢትዮጵያን የውትድርና ታሪክ ወደጎን የገፋ መሆኑ ታምኖበታል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ውትድርና ታሪክ የጀመረበትን መሠረት አድርጎ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም መነሻውን በማድረጉ 116ኛው የሠራዊት ቀን ካለፉት ሁለት ሳምንታት በፊት በተለያዩ ኹነቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሠላም ከማስከበር ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በቀጣናው ባሉ ሀገራት ሠላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ሠላም የማስከበር ተልዕኮን በመወጣት ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑም የሚታወቅ ነው። ይህ ሠላም ለማስከበር በተሠማራበት ስፍራ ሁሉ ድልን ማጣጣም የሚችል ሠራዊት፣ ዛሬ ቀኑን በተለያዩ ክንውኖች ከሕዝብ ጋር ሆኖ ያከብራል።

አዲስ ዘመንም ይህን የሠራዊቱን ቀን ምክንያት በማድረግ ስለቀኑ መከበር ፋይዳ እና የሕዝብንና የሠራዊትን ትስስር አስመልክቶ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር መሐንዲስ ዋና መምሪያ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው አያሌውን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሯል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የሠራዊት ቀን በየዓመቱ ማክበር ፋይዳው ምንድን ነው?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡– የሠራዊት ቀን የማክበራችን ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው። አንደኛ የሠራዊቱን ማንነትና ያለውን ጠንካራ እንቅስቃሴ ለትውልድ ማሸጋገር የሚያስችል በመሆኑ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር አስከብሮ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ማንነት ትልቁን ተጋድሎ ያደረገ እንደሆነ እሙን ነው። ይህ ተጋድሎና የዳር ድንበር መከበር ከአባቶቻችን ጀምሮ የመጣ እንደመሆኑ ትውልድ ይህንን በአግባቡ ይረዳ ዘንድ የሠራዊት ቀን ማክበሩ ተገቢነት ያለው በመሆኑ ነው። በተለይም የቀኑ መከበር በሀገር መከላከያ ሠራዊቱና በሕዝቡ መካከል ያለውን አንድነት እና ጥብቅ ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር የሚያደርገው በመሆኑ የሠራዊት ቀን መከበሩ ፋይዳው ብዙ ነው።

የሠራዊት ቀን እየተከበረ ያለውም ኢትዮጵያ የጦር ሚኒስትር የሰየመችበትን 1900 ዓ.ም ታሳቢ በማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ሀገርን ከውጭ ይሁን ከውስጥ ጠላቶች መክቶ ሕዝቧን የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ ተሳታፊ ማድረግ ትልቁ ጉዳይ ስለሆነ የሠራዊት ቀን ሲከበር የተለየ ድባብ እንዲኖረው ያደርጋል። እንደሚታወቀው የሕዝብን ደህንነትም ሆነ የሀገራችንን ክብር በማስጠበቅ በኩል በተለያየ ጊዜ ፀረ ሠላም ኃይሎችን ለመመከት ሠራዊቱ የከፈለው መስዋዕትነት አለ፤ ያንን ለመዘከርና ለዴሞክራሲ ግንባታም ያለውን ቁርጠኝነት ለሕዝቡ ለማስገንዘብም ጭምር የሚከበር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለተከታታይ ዓመታት የሠራዊት ቀን በመከበር ላይ እንዳለ እሙን ነው፤ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ነገር ይኖረው ይሆን?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- ለየት የሚያደርገው አንደኛ ከዚህ ቀደም ይከበር የነበረው የሠራዊት ቀን ትክክለኛ የሠራዊት ቀንን መነሻ ያደረገ አልነበረም። እንዲህም ሲባል የተለያየ የፖለቲካ ሥርዓትን መነሻ ያደረገ ነበር ለማለት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚከበረውን የሠራዊት ቀን ለየት የሚያደርገው በሀገር ደረጃ በ1900 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጦር ሚኒስትር የተመሠረተበትን ጊዜ ጀምሮ የሠራዊት ቀን እንዲከበር መደረጉ ነው። ምክንያቱም ጊዜው ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራዊት አመራር  የተሾመበት ቀን ስለሆነ ያንን ምክንያት በማድረግ የሚከበር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ የሀገርን ክብር የሚያስጠብቅና የሕዝብን ደህንነት የሚያረጋግጥ እንደመሆኑ ሕዝቡና ሠራዊቱ ያላቸው መስተጋብር እንዴት ይገለጻል?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- በእኛ አውድ መከላከያ ሠራዊት እና ሕዝብ ሲታሰብ ሠራዊቱ ከሕዝብ አብራክ የወጣ እንደመሆኑ ቁርኝቱ ከፍ ያለ ነው። በሠራዊቱ ዘንድ የሚታወቀው አንዱ እሴታችን ቅድሚያ ለሕዝብ የሚል ነው። ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለሕዝብ ነው።

ይህ በእኛ ሀገር ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአብዛኛው ሠራዊታችን በየትኛውም ጎዳናም ሆነ መንገድ ሲጓዝ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። ሕዝብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ይተማመናል። ለሠራዊቱ አክብሮትም አለው። መከላከያ ሠራዊቱም ያለ ሕዝቡ ተሳትፎ ውጤታማ መሆን የማይችል ነው። ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት መረጃ ሰጪውና በሚያስፈለገው ጉዳይ ሁሉ ተባባሪው ነው። ስለዚህ መከላከያ ሠራዊቱ ቁርኝቱ ከሕዝቡ ጋር ካልሆነ መረጃም ሆነ ድል ማግኘት አይቻለውም። ከሕዝብ ጋር በመሆን የሚገኘው ድል ደግሞ ለራሱ ለሕዝቡ ነው።

ወታደሩ መስዋዕትነት የሚከፍለው ለሕዝብ ነው። ስለዚህ ይህቺን ሀገር የመጠበቅ ግዴታ አለብን። ምክንያቱም ሀገር ማለት ሕዝብ ነው። ሕዝብን ማከበርም መደገፍም ማገልገልም ለሠራዊቱ ትልቀ ክብር ነው። ሕዝብ ሲኖር ከሕዝብ አብራክ የተገኘው ሠራዊትም ይኖራል።

አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የሚደርስ የስም ማጠልሸት ዘመቻ ይታያል። ይህንን እንዴት አስተዋሉት?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡– እኛ ወታደሮች የሀገራችን ዓርማ መሆን የምንችለው በሕዝብ ነው። ሕዝብን ስናገለግል የተለያዩ ድሎች ይመዘገባሉ። እነዚህ የተለያዩ ድሎች የሚገኙት ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ነው። ይህ ሠራዊት እንደሚታወቀው የድል ባለቤት ነው። ድል የማስመዝገቡ ጉዞ የተጀመረው ዛሬና ትናንት ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ እየተመዘገበ የመጣ ውጤት ነው።

የትኛውም ሀገራችንን ሊያጠቃ የሚፈልግ ጠላት ሠራዊታችንን አልፎ ሀገርን መንካት አልቻለውም። ይህ ሠራዊት ከጥንት አርበኞች ጀምሮ በየጊዜው ድል እየተቀዳጀ የመጣ ነው። ይህን የሚያደርገው ግን ሕዝብን ይዞ ነው። ሌሎች ሀገራችንን ለማጥቃት የመጡ ሰርጎ ገቦች ሁሉ በዚህ መልኩ ድል ተነስተው የተባረሩ ናቸው። እጅግ ትልልቅ ድሎችን እየተጎናጸፈ እዚህ የደረሰው መከላከያ ሠራዊታችን ዛሬም ይህን ድል እያስቀጠለ የሚገኝ ነው።

ነገር ግን የተለያዩ ጠላቶች የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል እንዲጎናጸፍ እና በሁለንተናውም እንዲጎለብት አይፈልጉም። ይህ የሚያሳየው ድላችን ሕመማቸው እንደሆነ ነው። የመከላከያ ሠራዊት ድል ለእነርሱ ሽንፈታቸውን ገልጦ የሚያሳይ ስለሆነ ይህንን ሽንፈታቸውን የሚበቀሉት ቴክኖሎጂው ባመጣው መሣሪያ በመጠቀም ነው። እንዲህም ስል የተለያየ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ነው።

ይህ ደግሞ ከወሬ የዘለለ ተግባር አይሆንም። በዚህ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባልተገባ አካሔድ የሚለቀቀውን እየተከታተለ ሠራዊቱን ሊለካ የሚችል አካል ግን የሠራዊቱን ማንነት ያልተረዳ በወሬ ነጋሪዎች የሚያምን ነው። ከዚህ የተነሳ ሠራዊቱ ምን እየሠራ እንዳለ አያውቅም።

ሠራዊቱ የተለዩ ድሎችን ሲያስመዘግብ ዓይናቸው የሚቀላ አሉ። እነዚህ ጸረ ሠላም ኃይሎች ደግሞ የሠራዊቱን የድል ባለቤትነትና ምስጉን ጀግና እንደሆነ ሁሌ ማብሰር አይወዱም። ሠራዊት ላይ አንዳች ስህተት የለም ለማለት አይደለም፤ ሊኖር ይችላል። ችግሮችም ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንደሚታወቀውም ሠራዊቱ የወጣው ከሕዝብ አብራክ ነው። ከሕዝብ አብራክ የወጣ ሠራዊት ደግሞ እድገቱም ሆነ አስተሳሰቡ የዚሁ የሕዝብ ውጤት ነው።

ይህ እያለ ጠላቶቻችን በተለያየ መገናኛ ብዙኃን የስም ማጥፋት ዘመቻ ያካሂዱብናል። ሠራዊቱን የማይመጥን መረጃም ሲያራግቡ ይስተዋላል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ተሽላ እንድትታይም ሆነ እንድታድግ አይፈልጉም።

እሱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች ተከባብረው እና እርስ በእርስ ተዋድደው በሚኖርባት ሀገር መተማመን እንዳይኖር ሲወጡ ሲወርዱ ይስተዋላሉ። ምክንያቱም ትልቁ ምኞታቸው ጠንካራዋ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ነው። ከዚህ የተነሳ ፍላጎታቸው በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ማዳከም ቢሆንም ይህን ምኞታቸውን ሊያሳካላቸው የሚችል ሕዝብም ወታደርም ግን የለም፤ አይኖርምም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የምትታወቀው ለየትኛውም ወራሪ ኃይል እጇን ባለመስጠቷ ነው፤ ከዚህም ባለፈ በአካባቢዋና ቀጣናዋ ሠላም በማስከበር ነው፤ ይህ እውነታ እያለ ስለምንድን ነው የሠራዊቱን ስም ለማጠልሸት የሚፈለገው? ትክክለኛ ፍላጎታቸውስ ምንድን ነው ይላሉ?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ግዳጁን በመወጣት ግንባር ቀደም ነው። ከበፊትም ጀምሮ ለሀገሩም ለቀጣናውም ለመዋደቅ ወደኋላ የሚል ሳይሆን ግንባሩን ለጥይት የሚሰጥ ነው። በእስካሁኑ ሒደቱም ድልን እየተጎናጸፈ የመጣ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። አሁንም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተለይም በሶማሊያ፣ በጂቡቲ፣ በቀይ ባህር አካባቢ ያለው ትልቁ ርብርብ ቀጣናውን በተወሰነ መልኩም ቢሆን የስጋት ቀጣና አድርጎታል። ይህ ስጋት እያደገ የመጣበት ሁኔታ ምንድን ነው ቢባል ኢትዮጵያ ታድጋለች ተብሎ ስለሚታመን እና ስለሚፈራም ጭምር ነው።

ይህ ምሳሌነታችን የሚታወቀው ዛሬ አይደለም። ኢትዮጵያ ያኔ ጣሊያንን ድል ካደረገች ጊዜ ጀምሮ ሀገራችንን ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት በአሁኑ ወቅት በተለያየ መልኩ የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት ይፈልጋሉ። ይህን የድል ባለቤት የሆነውን ሠራዊት ባገኙት ሚዲያ ስሙን ለማጠልሸት ይሯሯጣሉ፤ እነዚህ አካላት ማን ናቸው ቢባል የውጭ ተላላኪዎች ናቸው።

ወደዱም ጠሉም ኢትዮጵያ በሠራዊቷ ትልቅ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት። ይህን ታሪክ ማስቀጠል ደግሞ የማንም ግዳጅ ሳይሆን የወታደሩ እና የሕዝቧ ተልዕኮ ነው። ይህን ስለሚያውቁ ሕዝቦቿን እያመሱ ለማሰልቸት ይፈልጋሉ። ከሕዝቡ አብራክ ወታደር እንዳይወጣም በብዙ ይደክማሉ። ይሁንና ሊሳካላቸው አልቻለም፤ ምክንያቱም በትውልዱ ደም ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ስላለ ነው። እንዲያ በመሆኑም ውትድርናን የሚቀላቀል ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡።

የኢትዮጵያ እድገት ስለሚያስፈራቸው ግን ሁሌ ችግር ለመፍጠር ከመሞከር አይቦዝኑም። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና ያልተነካ ጥሬ ሀብት ያላት ሀገር ናት። በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካም ሆነ በጣሊያን ያልተደፈረ እንዲሁም በሌሎች ሀገሮች ያልተሞከረ ጥሬ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ከዚህ የተነሳ ገና የምታድግ ሀገር እንደሆነ እሙን ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ተፈጥሯዊ አቀማመጧም ምቹ ነው። ይህ ሁሉ እነርሱን የሚያስቀና ነው።

እኛ አንዳችን ብሔር ከሌላኛው ብሔር ጋር ተዋድደን፣ ተግባብተን እና ተጋብተን መኖራችን በራሱ ስለሚያስቀናቸው ይህን ኅብረት ሊበጥሱት በብዙ ይታትራሉ። ይህ ኅብረትና ማንነት እንዳይጠፋ በዚህ ልክ ጠብቆ ያቆየውን ወታደር በማይመጥነው ሁኔታ ስሙን በማንሳትና በማጠልሸት ሽባ ለማድረግ ይፈልጋሉ። ይህ ግን ከፍላጎት የሚዘል አይሆንም። እንደወትሮው ሁሉ ሠራዊቱ ጥንካሬውን ይልቁኑ በተሻለ ሁኔታ እያስኬደው ይገኛል።

ሠራዊቱ አሁንም እንደቀድሞው ሀገሩን የሚያስከብረው የሚወረወበትንና የማይመጥነውን ነገር ሁሉ ተቋቁሞ ነው። አሁንም በየክልሎች እየታየ ያለው ችግር ሌላ ምክንያት ኖሮ አይደለም፤ የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ሠራዊቱን ለማናጋት ከመፈለግ የተነሳ ነው። ልክ ድመት ልጇን እንደምትበላ ዓይነት ከሕዝቡ አብራክ የወጣው ሠራዊትም በራሱ ወገን እንዲበላ ያልተገባ ውዥንብር በመፍጠር ለማጭበርበር በመፈለግ ነው።

ምክንያቱም በውስጥ ሠላም እንዳይኖር በብዙ የሚደክሙ አሉ፤ አንዴ በአንዱ ክልል ሲሞክሩ፤ እሱ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ ሌላ ጊዜ ሌላ ክልል ሲሞክሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ሠራዊቱ በውስጥ ጉዳይ ተይዞ ሌላ ግዳጁን እንዳይወጣ ለማድረግ ይፈልጉ እንጂ ምኞታቸው አልተሳካም፤ አይሳካምም።

ከውጭ ሀገር ጣልቃ ገቦች በተጨማሪ የሀገራችን ውስጥ ተላላኪ የሆኑ ባንዳዎችም አሉ። ራሱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሆዱን ለመሙላት ብቻ ሲል የራሱን አሳልፎ የሚሰጥም መኖሩ የሚዘነጋ አይደለም። እርሱ የሚቆነጠርለትን ዶላር ብቻ በማሰብ ስለሀገሩ ግድ የማይለው ዜጋም አለ። ይህ ሠራዊት ግን እየሞተ እና እየቆሰለ ሀገሩን እዚህ ያደረሰ ሠራዊት ነው።

በሚገርም ሁኔታ ይህ ሠራዊት በቀን አንድ አስቃጥላ ማለትም 240 ግራም ምግብ እየበላ ሀገሪቱን እየጠበቀ ያለ ነው። ይህን ዋጋ የሚከፍለው ደግሞ ለሕዝብ እና ለሀገር ሲል ነው። ይህን የማይረዱ ኃይሎች ግን የኢትዮጵያን ጥንካሬ ለማፍረስ የሠራዊቱን ስም የማጉደፍ ሥራዎችን እየሠሩ ነው፤ ይሁንና እነሱ እንደሚመኙት የሠራዊቱ ስምም ሆነ ዝና በከንቱ የሚጎድፍ አይሆንም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች ሀገር ናት፤ ከእድገቷ ጋር የሚመጥን ሠራዊትን ከመገንባት አኳያ ምን እየተሠራ ነው ይላሉ?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡– እንደተባለው ኢትዮጵያን የሚመጥን ሥራ በሀገሪቱ ቁንጮ አመራር በተለይ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሥራ ተሠርቷል። ደረጃ በደረጃ ባሉ የስትራቴጂክ አመራሮችም በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። በተለይም በአሁኑ ጊዜ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም፣ በአስተሳሰቡ ዘመናዊ የሆነ፣ አስተማማኝ የሆኑ ትጥቆች ያሉት፣ ቁመናው የተደራጀ አደረጃጀት ተፈጥሯል። ለአብነት ደግሞ ከዚህ ቀደም ሀገራችን ያልነበራት የባህር ኃይልና መሰል አደረጃጀቶችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ ያለ ነው።

ከአደረጃጀቹ ውስጥ አንዱ የመሐንዲስ ክፍላችን ተጠቃሽ ነው። የመሐንዲስ ክፍላችን ትልልቅ ትጥቆችን በመታጠቅ፣ ለሠራዊቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማቅረብ ከፍተኛ ማሽኖች ድረስ ያሉት ነው። በሠራዊቱ አካባቢ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፈጣን በሆነ ሁኔታ መጠለያን ለመሥራት የሚያስችል ግብዓትንም ያካተተ ነው።

ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከክቡር ፊልድ ማርሻል እንዲሁም ከፍተኛ የሆኑ አመራሮቻችን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለ ነው። በጥቅሉ በመከላከያ ውስጥ በኃይል ማደራጀቱ፣ በትጥቁም፣ በአስተሳሰቡም ሆነ በሥልጠናው ዘርፍ ከፍ ያሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ኢትዮጵያ ገና የምታድግ ሀገር ናት፤ ያላትን ጥሬ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምና ወደምትፈልገው የእድገት ደረጃ እንድትደርስ የሠራዊቱ ጠንካራ መሆን ወሳኝ ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ እድገት አልጋ በአልጋ ሆኖ ይቀጥላል ማለት የዋህነት ይሆናል። ስለሆነም ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ጠላት አይመጣም ብሎ ማሰብ አይገባም። ሀገርን ለመጠበቅ መዘመን ያስፈልጋል። ይህም አደረጃጀት እየተዋቀረ ይገኛል። ከዚህም የተነሳ ግዙፍ የሆነ የመከላከያ ኃይል እየተገነባ ይገኛል ማለት ይቻላል።

በአሁኑ ወቅት ያለበት ደረጃ ለዕይታ እንደሚቀርብም ይታሰባል። ምክንያቱም ዘመናዊ ድሮን፣ ሚግ፣ ሔሊኮፕተር እንዲሁም የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች የታጠቀ መከላከያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ረጃጅም ሚሳዔሎችና መድፎች ባለቤትም ጭምር ነው። ይህ የሚያሳየው በሀገሪቱ ላይ ወደፊት ሊቃጣ የሚችለውን ነገር መመከት የሚችል የሠራዊት ግንባታ እንዳለ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በኃላፊነት ያሉበት ክፍል በዋናነት ለሠራዊቱ እያደረገ ያለው ነገር ምንድን ነው?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡– የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ትልቁ ተልዕኮውና ግዳጁ በሀገር ደረጃ ላሉ ዕዞችና ተዋጊ ኃይሎች የውጊያ ድጋፍ እና የውጊያ አገልግሎት መስጠት ነው። ለምሳሌ በቅርቡ በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ውጊያው እንዲሳለጥ ሲሠራ የነበረ ነው። ጠላት የሚሰብራቸው ድልድዮችን በተንቀሳቃሽ፣ ተገጣጣሚ እና ተንሳፋፊ ድልድዮች በመተካት የሠራዊቱን የውጊያ እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ ማድረግ ሌላው ሥራው። ከዚህም ሥራ የተነሳ ሠራዊቱ ፈጣን እንቅስቃሴ ያደርጋል። ታንኮች፣ መድፎች እና እግረኛ ሠራዊት እንዳይሻገር ጠላት የሚያወድመውና የሚያፈርሰውን ነገር ቀድሞ በስፍራው በመገኘት ጠላትን እግር በእግር በመከተል እየተዋጋ ጥርጊያውንም እያስተካከለ፣ የተለያዩ ፈንጂዎችን ያወድማል፤ ጠላት የቀበራቸውን ፈንጂዎችን ያመክናል፤ ያነሳልም። ከዚህ ጎን ለጎን ድልድይ እየዘረጋ ያሻግራል።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ጠላት የማጥቃት አቅጣጫ ቢከተልም የመከላከል ሥራ ለመሥራት ጸረ ፈንጂዎችን እየጠመደ ጠላትን የማጥቃት ሥራም ይሠራል።

ዘመናዊ ሠራዊት ከመገንባት አንዱ የመኖሪያ፣ የአመጋገብ ሁኔታን በማስተካከል የሠራዊቱን ኑሮ ማሻሻል ላይም ከከፍተኛ አመራሮች በተሰጠን አቅጣጫ መሠረት ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች (መጠለያዎች፣ መዝናኛዎች፣ ሆስፒታሎች፣ መጋዘኖች፣ የነዳጅ ማከማቻዎች እና መሰል ነገሮችን በመስራት) ለሠራዊቱ ድጋፍ የሚያደርግ ክፍል ነው።

በሌላ በኩል ሠራዊታችን በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው። ትልልቅ ማሽኖችን ወደስፍራው በማቅረብ ከ600 እስከ አንድ ሺ ሜትር ርቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር ንጹህ የመጠጥ ውሃን የሚያቀርብም ጭምር ነው። በዚህ መሠረት የሠራዊቱን ውሃ ጥም ለማርካት የሚሠራ ነው። በየትኛውም እዞች የማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች ብልሽቶች ሲኖሩ ማስተካከል፣ መንገድ መጥረግ፣ ምሽግ መሥራት ሁሉ ተልዕኮ ተሰጥቶት የሚሠራ ክፍል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጋር ያለው ቁርኝት የተሻለ ይሆን ዘንድ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- ሕዝቡ መረዳትና ማወቅ ያለበት የመጀመሪያው ነገር የመከላከያ ሠራዊት የመጣው ከየትም ሳይሆን ከራሱ አብራክ መሆኑን ነው። ከአጠገቡ ከቀበሌው፣ ከየወረዳውና ዞኑ ተመርጦ ከየክልሉም ተመልምሎ በኋላ ላይ አንድ ስታፍ ለመሆን በአንድ ማሰልጠኛ ሰልጥኖ ራሱ ሕዝቡን ለማገልገል የሚዘጋጅ ብርቱ ወታደር ነው። ወደማሰልጠኛ ከመግባቱ በፊት ሁሉም የየራሱ ቋንቋ፣ ብሔር፣ ባህል፣ እምነትና መሰል እሴት ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን ሁሉን ወደጎን አድርጎ እኩል ጸጉሩን ተላጭቶ ሀገርንና ሕዝብ ለማገልገል ብቁ ወደሚሆንበት ማሰልጠኛ የሚገባ ነው፤ ማሰልጠኛ ከገባ በኋላም ይዞ የመጣውን የተዥጎረጎረ ነገር ሁሉ ትቶ አንድ ዓይነት ምግብ፣ የደንብ ልብስ፣ ጫማ፣ አንሶላ እና ብርድ ልብስ ለብሶ የሚንቀሳቀስና ሁሉን በእኩልነት የሚያይ ብቁና ሥልጡን ሆኖ የሚወጣ ነው። በወታደራዊ ዲሲፒሊን ከታነጸ በኋላም ሀገሩንና ሕዝቡን በአንድ ዓይነት የሚመለከት ወታደር መሆኑን ብቻ ሕዝቡ ማወቅ አለበት ባይ ነኝ።

ስለዚህ ሠራዊቱ የመጣው ከራሱ ከሕዝቡ ነው። ከተለያዩ የሀገራችን ክፍል የተውጣጣም ሲሆን፣ ሀገርን የሚጠበቀው ደግሞ ወጥ በሆነ አተያዩ ነው። ሠራዊቱ የሀገርን ፍቅር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕዝብ እና የሕዝብ ሠራዊት መሆኑን በቅጡ ግንዛቤ ቢያዝበት መልካም ነው። የማንም ፖለቲካ ወጋኝ አይደለም፤ ፖለቲካ ሊቀያየርና ሊለዋወጥ ይችላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት መስመሩን ያስተጓጎሉ አመራሮች ነበሩ። አንዱ ፖለቲካ ሲወድቅ ሠራዊት እንደሠራዊት መቀጠል አለበት። ሌላው ፖለቲካ ሲመጣ ሌላ ነገር ይዞ መጀመር አይኖርበትም። ሠራዊት መቀጠል ያለበት እንደዚያው የሕዝብ እና የሀገር አገልጋይ ሆኖ ነው።

ዛሬ እያከበርን ያለው 116ኛውን የሠራዊት ቀንን ነው። ሠራዊቱ 116 ዓመት ሙሉ በተከታታይ ተገንብቶ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዚህ አይበገሬነቱ እና ጀግንነቱ የት ሊደርስ እንደሚችልም መገመቱ መልካም ነው። ምክንያቱም በየዘመኑ የነበረው ሠራዊት ተጋድሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉ ጠንቅቆ የሚያውቀው ነው። ይህ ሠራዊት በየትኛውም ቦታ ግዳጅ ሲሰጠው ባለድል እየሆነ እዚህ የደረሰ ነው።

ሠራዊቱም ያለሕዝቡ፤ ሕዝቡም ያለሠራዊቱ የትም መድረስ አይችልም። ስለሆነም ሕዝባችንም አንድ መረዳት ያለበት ሠራዊቱ የሚሰጠውን ተልዕኮ ያለአድልዎ የሚፈጸም ብርቱ መሆኑን ነው። አንድም ወታደር የሚንቀሳቀሰው ብሔሩን አሊያም ኃይማኖቱን ወይም አካባቢውን አስቦ እንዳልሆነ ልብ ማለቱ ተገቢ ነው እላለሁ።

ወገኔ ለሚለው ማንኛውም ሕዝብ በሕዝቡና በሕገ መንግሥቱ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችለውን ሁሉ ለመጋፈጥ ግዳጅ ሲሰጠው የሚሄድ ወታደር ነው እንጂ የእኔ ይኸኛው ነው፤ የእሱ ያኛው ነው ብሎ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ስለዚህ ሠራዊቱ የፓርቲ አሊያም የፖለቲካ ወታደር አለመሆኑ መታወቅ አለበት። መከላከያ ትልቅ ተቋም ነው። ይህ ትልቅ ተቋም ደግሞ ብሔርም ቋንቋም ማዕከል ያደረገ አይደለም። ማዕከሉ ሀገርና ሕዝብ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የነበረው ከለውጡ በኋላ ያለው የሠራዊቱ አወቃቀር የሚያዩት እንዴት ነው?

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- አሁን ላይ የሚታየው መከላከያ ፈርሶ የተገነባ ነው ማለት ይቻላል። በእኔ አመለካከት እንደ አዲስ የተገነባ ነው። ወታደር ፖለቲከኛ አይደለም፤ በተለይ በቀድሞ አመራር ሲመራ በነበረበት ወቅት አመለካከቱ ወደፓርቲ እንዲያዘንብል ተደርጎ ቆይቷል። ከከፍተኛ ጄነራል ጀምሮ እስከ ታችኛው ወታደር ድረስ ያዘነበለው በፓርቲው ዙሪያ ነው ማለት ይስደፍራል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በሕወሓት በተከፈተው ውጊያ ወቅት በወታደር ቤቱ አሉ የተባሉ ሁሉ የተመሙት ሲያገለግሉት ወደቆዩለት ፓርቲ ነበር። ባለፉት አምስትና አራት ዓመታት ውስጥ ግን ሠራዊቱ እንደ አዲስ ተቋቁሟል ማለቱ ይቀላል።

በአዋሽ፣ በቡልቡላ፣ በብርሸለቆ፣ በጦላይ፣ በብላቴና በሑርሶ ማሰልጠኛ እንደ አዲስ ወታደሩ ገብቶ ሠልጥኖ መውጣት ችሏል። አሁን ላይ በሀገሩና በሕዝብ የማይደራደር የሠራዊት ቁመና ላይ መሆን ችሏል። ስለዚህ ሠራዊቱ ባለፈው እንደነበረው አይደለም። እንደ አዲስ የተደራጀ ሠራዊት ነው ማለት ይቻላል። በትጥቅም በቴክኖሎጂውም ሆነ በሌላ ሌላው የተገነባ እና ጠንካራ የሆነ ሠራዊት መሆን ችሏል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ሌተናል ኮሎኔል ምስጋናው፡- እኔም አመሰግናለሁ። ሠራዊታችንንና መላ ሕዝባችንን እንኳን ለ116ኛ ዓመት የሠራዊት ቀን በእኔና በመከላከያ መሐንዲስ ስም በሠላም አደረሰን፣ አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You