በወደብ ጉዳይ እንነጋገር፡- የሕዝቦች አብሮ የማደግ መሻት ማሳያ

ኢትዮጵያ ወደብን በመጠቀም ረገድ ረዥም ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ዛሬ ድምጻቸው የሳሳውና ደብዛቸው የጠፋው ዘይላ፣ አዱሊስና ምጽዋ ለረዥም ዓመታት ስንገለገልባቸው የቆየንባቸው ወደቦቻችን ነበሩ። ራቅ ባለው ዘመን ተሽከርካሪዎች ባይኖሩም ሲራራ ነጋዴዎች ምርቶችን ከመሀል ሀገር ወስደው የወጪ ምርቶችን ተቀብለው በጋማ ከብቶቻቸው እየጫኑ አስገብተው ይነግዱ ነበር።

ቀረብ ባለው ዘመንም ዘመኑ ባፈራቸው ተሽከርካሪዎች የታገዘ የወጪና ገቢ ንግድ ማሳለጫ የባህር በር ሆነው ለኢትዮጵያ አገልግለዋል። ይሄ የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ደግሞ የራሱ የሆነ የታሪክ፣ የማኅበራዊ ጉድኝት እንዲሁም የመልከዓ ምድር ተፈጥሯዊ ትስስር ያለው ነው። በዚህም ኢትዮጵያ እነዚህን ወደቦች የተገለገለችባቸው ብቻ ሳይሆን፤ አንዳንዶቹም የራሷ የግዛት አካልና ሀብት የነበሩም ናቸው።

ዛሬ ላይ ግን እነዚህ የታሪክ አካል ከመሆን የዘለለ ለኢትዮጵያ ባዕድ ሆነዋል፤ የባህር በር የነበራት ሀገርም ወደብ አልባ ሆናለች። ይሄ ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የባህር በር አልባ መሆኗ የፈጠረባት ከፍ ያለ እና ዘረፈ ብዙ ጫና ስለመኖሩ ግን አያሌ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። እናም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ ዐብይ ጥያቄ አለ። እሱም ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗ እያሳደረባት ያለውን ከፍ ያለና ዘርፈ ብዙ ጫና እስከመቼ ተሸክማ ትቀጥላለች? ይሄንን ጫናዋን ለመቀነስና ቀጣናዊ የጋራ ልማትን እውን በማድረግ መርህ ላይ የተመሠረተ የባህር በር ተጠቃሚነቷንስ መቼና በምን መልኩ እውን ታደርጋለች? የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በዓለም 45 ወደብ አልባ ሀገራት ሲኖሩ ከነዚህም መካከል 16ቱ በአፍሪካ 14ቱ በአውሮፓ የሚገኙ ናቸው። ሀገራችንም በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ከሌላቸው ሀገሮች ተርታ ከተመደበች ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታትም ለወደብ ኪራይ በውጭ ምንዛሪ ከፍ ያለ ሀብት ለማፍሰስ እየተገደደች ነው። ይህም አጠቃላይ በሆነው ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።

በምሥራቅ አፍሪካ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት እና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት ሀገራችን፣ ወደብ አልባ ከመሆኗ ባለፈ በዙሪያዋ አማራጭ ወደቦች ባሉበት ሁኔታ፣ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ የተገደበ የወደብ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ተጨባጭ አውነታ ነው። ይህ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ አገልግሎት ከማግኘት አንስቶ አማራጭ ገበያን ታሳቢ ያደረገ የወደብ ክፍያ ለመፈጸምም የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው።

መንግሥትም ከወደብ ጋር የተያያዘውን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት ባዘጋጀው የትራንስፖርት ዘርፍ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድና ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ ላይ፣ አማራጭ ወደቦችን የማስፋትና ሌሎች ኮሪደሮችን የመጠቀም አማራጭን አስቀምጧል። በዚሁ መሠረትም፣ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ተስፋ አመንጪ፣ ፋና ፈንጣቂ ተግባራትን ማከናወን ጀምሯል። ለዚህም ከጂቡቲ በተጨማሪ በኬንያ፣ በሶማሊያ እና በኤርትራ የሚገኙ ወደቦችን በአማራጭነት ለመጠቀም ተንቀሳቅሷል።

በርግጥ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የወጪና የገቢ ሸቀጦችን ፍሰት ከማሳለጥ ባለፈ፤ አዳዲስ ከተሞችን በመፍጠርና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማሳደግ ያለው አዎንታዊ ሚና ከፍያለ ነው። የሀገራትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብርንም ለማጠናከር፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማሳደግም ጥልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

አማራጭ ወደቦች የመጠቀም ዕድሎች ሲፈጠሩ፣ ወደብ ተጠቃሚውም ወደብ አቅራቢውም፤ ወደ ወደብ የሚያደርሱ አዳዲስ መንገዶች ይገነባሉ። እነዚህን መንገዶች ተከትሎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይስፋፋሉ፤ ይህ ደግሞ አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩ መልካም ዕድል ይፈጥራል። አዳዲስ ከተሞች መፈጠር ደግሞ በራሱ ለሀገራቱ ኢኮኖሚ እድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከግምት ያለፈ ነው።

መንግሥት እንደ ሀገር የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ በዙሪያችን ባሉ ሀገራት የሚገኙ ወደቦችን አልምቶ አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፤ ይህ ጥረት የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድን ከማሳለጥ ባለፈ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቱን ተከትሎ በሀገራቱ አዳዲስ ከተሞችን በማዋለድ ከተሜነት ማጠናከር ያስችላል።

ለአማራጭ ወደቦች መዳረሻ መንገዶች እና መሠረተ ልማቶች ሲሟሉም ለሀገራቱ ዜጎች የተሻሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን (የትምህርት፣ የህክምና..ወዘተ) በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ፤ በሀገራቱ መካከልም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በመፍጠር፣ ሕዝቦቻቸውን የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ዕድል መፍጠር ይቻላል ።

ይህም የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ውስጥ ያለውን የማደግ መሻት በጋራ እውን ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ አቅም ይፈጥራል። ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ለተሻለ እድገት እንዲተጉ ዕድል ይሰጣቸዋል። ‹‹ጥርስና ከንፈር ሲደጋገፍ ያምር ›› እንደሚባለው አንዳቸው ለሌላቸው የስጋት ምንጭ ከመሆን ወጥተው በመተማመን ላይ የተመሠረተ አካባቢያዊ ልማት መፍጠር ያስችላቸዋል። በቀጣይም ለጋራ ተጠቃሚነት ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የተሻለ ዕድል ይፈጥራል።

ይሄን አስመልክቶ ከሳውዝ ሀምተን ዩኒቨርሲቲ ብሬይን ሆሊ ያወጡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈሩት፤ ወደቦችና የመሀል ሀገር ከተሞች በአቀማመጣቸው በአቅጣጫቸው ባብዛኛው በልማት ሥራና በንግድ መስተጋብር ያላቸውና ተመጋጋቢ ናቸው። ወደቦች በትራንስፖርት ድረ-ግብር (network) እንደ መስቀለኛ መንገድ የሚያገለግሉ ናቸው።

የሚመሠረቱት ባህር ዳርቻዎች አካባቢ ሆኖ ለማኅበረ ኢኮኖሚ መሳለጥ ሠፊ ሚና አላቸው። ለወደብ ቅርብ የሚሆኑ ከተሞች የማደግ ዕድላቸው ሠፊ ነው። ይህንንም የወደብ ንግድ መስመር የሌላቸው ከተሞችን ካላቸው ከተሞች ጋር በማነፃፀር መረዳት ይቻላል ይላሉ።

ከዚህ አኳያ ሲታይ አማራጭ ወደቦች ቢኖሩን፤ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የደህንነት ጉዳዮቻችንን ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩ ባለፈ፤ ለከተሜነትና ከተሜነትን ተከትሎ የሚፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ልማትና እድገቶች ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ ያስችለናል።

ይሄ ሲሆን ደግሞ እንደ ሀገር የሕዝቦችን ማኅበራዊም ኢኮኖሚያዊም ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት ያስችለናል፤ ከዚህ ባለፈም የጎረቤትም ሆኑ የቀጣናው ሀገራትና ሕዝቦች አብሮ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ ዕድላቸውን በጋራ የሚፈጥሩበትን አቅም እንዲጎናጸፉ ያደርጋል።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You