ዛሬም
ስለ ፍቅር እንናገራለን፣ እንጽፋለ ንም፡፡
ምክንያቱም ፍቅር ቢነገር
ቢነገር የማያልቅ የምስጢር
ስንክሳር ነውና፡፡ የሰው
ልጆች ፍቅርን በተለየ
መንገድ ይገነዘቡታል፣ በተለያየ
መንገድም ይገልጹታል፡፡ የቡድሃ
ዕምነት ተከታዮችም ለፍቅር
ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡
ቡድሃዎች ፍቅርን የተረዱበትና የገለጹበት መንገድም
አስደማሚ ነው፡፡ እነርሱ
እንደሚሉት ደስታን ማግኘት
የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ
ፍቅር ነው፡፡ እኛም
እስኪ ዛሬ በቡድሃ
የፍቅር ጎዳናዎች ተጉዘን፤
የደስታ ቤተ መቅደሶችን
ጎብኝተን ደስ ብሎን
ዘና ብለን እንመለስ፡፡
ለቡድሃዎች ደስታን ማግኘት የሚቻ ለው ፍቅርን በመለማመድና በእርሷም ላይ በመመላለስ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ከሌለ ደስታ የለም፤ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ደግሞ ከእውነተኛ ፍቅር ነው፡፡ በጥቅም ላይ ያልተመሰረተ፣ እውነተኛ ንጹህ ፍቅር ልብን በደስታ የማጥለቅለቅ ኃይል አለው፡፡ ይህም ያለፈውን የሕይወት ጠባሳችሁን ሁሉ እንዲፈወስና ሕይወታችሁ ጥልቅ ትርጉም እንዲኖረው ያደርግላችኋል፡፡ «እናም ብራህማቪሃራስ ተብሎ ከሚጠራው እውነተኛው የፍቅር ምንጭ ጋር የሚያገናኙና ግንኙነቱ ቋሚ እንዲሆን የሚያደርጉ አራት ዓይነት የፍቅር ደረጃዎች አሉ” ይላል የዕምነቱ መስራች ህንዳዊው ቡድሃ ጉተማ፡፡ እነዚህ አራቱ የፍቅር ደረጃዎች ወደ ሁለንተናዊው ዓለም ምንጭ ያቀርቡናል፡፡ በተጨማሪም ከእውነተኛው የፍቅር በረከት እንድንቋደስ ብቻ ሳይሆን ስቃይና መከራን ወደ ፍቅርና ደስታ ለውጠን ለራሳችንና በዙሪያችን ላሉት ሁሉ የምናካፍልበትን ኃይልም ያጎናጽፉ ናል፡፡ ህይዎታችን በእንዲህ ዓይነት ፀጋና በረከት እንዲትረፈረፍ የሚያደርጉት የቡድሃ አራቱ የፍቅር ደረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ማይህትሪ(ፍቅር ወይም መልካምነትን ማፍቀር)፡- ይህ የመጀመሪያው የፍቅር ደረጃ ሲሆን ሰዎችን የመረዳት፣ ሰዎችን የማፍቀር ፍላጎትና ችሎታን ያመለክታል፡፡ ዓላማውም ለሰዎች ዓለማዊ ደስታንና የመንፈስ እርካታን መፍጠር ነው፡፡ ሰዎች ማን እንደሆኑና ምን እንደሚፈልጉ ለማወቅና ለመረዳት ከፍርድና ከትችት ርቀን በሙሉ ልባችን ልናዳምጣቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የምናፈቅረውን ሰው ካልተረዳነው በስተቀር እውነተኛ ፍቅር ሊገኝ አይችልም፡፡ ሰዎችን ቀርበን ስንረዳቸው ስለ እነርሱ የበለጠ እንድናውቅ ያደርገናል፤ ስቃያቸው፣ ፍራቻቸው እንዲሁም ምኞታቸውና የህይዎት ዓላማቸው ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በዚህ ጊዜ እኛ የምንፈልገውን ሳይሆን እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር ለሰዎች መስጠት ይቻለናል፡፡ ይህ በምላሹ ምንም ሳይጠብቁ ሰዎችን የማገዝና ፍቅርን የመስጠት ሂደት ነው እንግዲህ ንጹህ ፍቅር የሚባለው፡፡ ይህም ውስጣዊ የህሊና ሰላምንና የመንፈስ እርካታን ይፈጥርልናል፡፡
2. ካሩና (ርህራሄ)፡- ይህ የፍቅር ደረጃ ሰዎችን ቀርቦ ከማዳመጥ፣ ከመረዳትና ንጹህ ፍቅርን ከመለገስ አልፎ የምናፈቅራቸውን ሰዎች የግል መከራና ስቃይ በፈቃደኝነት የምንካፈልበት ደረጃ ነው፡፡ በአማርኛ “ርህራሄ” በእንግሊዝኛው ደግሞ “Compassion” የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉም የችግር ተጋሪ መሆንና “ካዘኑት ጋር አብሮ ማዘን” ማለት ነው፡፡ “ርህራሄ” እና ““Compassion” የሚሉትን ቃላት ይተካል ተብሎ የተመረጠው “ካሩና” የሚለው የህንዳውያኑ ቃል ግን ትርጉሙ ከዚህ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ “ካዘኑት ጋር አብሮ ማዘን” ሰዎች ለገጠማቸው ችግር መፍትሄ አይሆንም ብሎ ያምናል ቡድሃ፡፡ ምክንያቱም ሃዘን ከደረሰበት ሰው ጋር አብሮ ማዘኑ የመጨረሻ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ሊሆን ይችላልና፡፡ ስለሆነም ለሰው የሚበጀው አንድ ላይ ሆኖ እያዘኑ መኖር ሳይሆን ቀልቡን ሰብስቦ ውስጡን በጥሞና በማዳመጥ፣ በዙሪያው ያለውን ዓለም በሚገባ በማስተዋልና በመገንዘብ ርህራሄንና ፍቅርን መማር የሚችልበትን አዲስ ጉዞ መጀመር ነው፡፡ ይህን በምናደርግበት ጊዜ አንዲት ቃል እንኳን የእኛንና የማህበረሰቡን ህይዎት የመቀየር ኃይል ይኖራታል፡፡ አንዲት ቃል ወይም አንዲት ትንሽዬ ድርጊት ጥርጣሬን በማጥፋትና መተማመንን በመገንባት፣ ቅራኔን በመፍታትና ጥላቻን በመደምሰስ የስቃይ እስር ቤትን ሰብራ የነጻነትን በር ልትከፍትልን ትችላለች፡፡
3. ሙዲታ(ሐሴት)፡- አሁን “ሐሴት”ና “ደስታ” ልዩነት እንዳላቸው የምንገነዘብበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ደስታ ብዙውን ጊዜ ከዓለማዊ ነገሮች ጋር የሚገናኝ ሲሆን ሐሴት ግን የመንፈስ ደስታ ነው፡፡ ልዩነቱን ቡድሃ እንዲህ በማለት በምሳሌ ይገልጹታል፤“በአንድ ጭልጥ ባለ ደረቅ በረሃ ውስጥ ሆነን ውሃ በምናይበት ጊዜ የሚሰማን ስሜት ʻሐሴትʼ ሲሆን፣ ውሃውን ስንጠጣው የሚሰማን ስሜት ግን ʻደስታʼ ነው”፡፡ይህም ማለት አሁን የምንገኝበትን ቅፅበት ወዲያውኑ ስንገነዘበው፣ ይህንን የተገነዘብነውን ቅፅበትም ስንኖረው ሐሴት ይሰማናል፡፡ ራሳችንን በአንድ የሆነ ውበት ውስጥ ተከብበን ስናገኘው፤ ያ ዙሪያችን የከበበን ውበትም ምን እንደሆነ ስናውቀው በትንንሽ ነገሮችም እንደሰታለን፡፡ ሐሴት የምንለውም ይህንኑ በአሁንነት ውስጥ የሚገኝ ህያው የደስታ ስሜት ነው፡፡ እናም ይሉናል ቡድሂስቶች ከእውነተኛው ንፁህ የፍቅር በረከት ለመቋደስ ከሃላፊውና ከዓለማዊው ሥጋዊ የደስታ ስሜት ወጥተን ወደ እንደዚህ ዓይነቱ የመንፈስ እርካታ ደረጃ ላይ መድረስ አለብን፡፡
4. ምክንያቱም ዓለማዊ ደስታ በቁስና በማግኘት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ቁስ ደግሞ ያልቃል ያኔ ደስታውም አብሮ ያልቅና በጭንቀት ይተካል፡፡ ቁሶች አላቂ ሃብቶች ናቸው፣ እንዲኖሩን የምንፈልጋቸውን ነገሮ ችም ሁል ጊዜ ላናገኛቸው እንችላለን፡፡ እናም በዓለማዊ ደስታ ውስጥ ሁል ጊዜ እጥረት አለ፣ እጥረት ካለ ፍርሃት አለ፣ በፍርሃት ውስጥ ደግሞ ጭንቀት፣ ሰላም ማጣትና አለመረጋጋት ይወለዳል፡፡ ሐሴት ግን የመንፈስ እርካታ ነው፡፡ ከቡድሃ ምሳሌ መረዳት እንደሚቻለው ሐሴት ማግኘት ሳይሆን የአንድን ነገር መኖር መገንዘብ ነው፡፡ በረሃ ውስጥ የነበረው ሰው ውሃ መኖሩን በማወቁ ብቻ ገና ሳይጠጣው ውሃውን በማየቱ ጥሙ እንዳረካው ሐሴት ለማድረግ ማግኘት ግድ አይደለም፤ የሚፈ ለገው ነገር በዙሪያችን እንዳለ ማወቁ ብቻ መንፈሳችንን በደስታ ያጠግበዋልና፡፡ የደስ ታው ምንጭም ነገሩን በማወቃችን እንጂ በማግ ኘታችን ባለመሆኑ አዕምሯችን ላይ ህያው ሆኖ ይኖራል፤ ህልውናውን እስከተገነዘብነው ድረስ ንብረትነቱም የእኛ ነውና ሐሴት ስናደርግ ሁሌም ሙላት ይሰማናል፡፡
5. አፕሼካ (ምልዑነት)፡- እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ሦስት የፍቅር ደረጃዎች በብቃት አልፋችሁ እዚህኛው ደረጃ ላይ ስትደርሱ ጉዟችሁን በድል አጠናቃችኋልና የመጨረሻውን የእውነተኛ የፍቅር ዘውድ ትጭናላችሁ፡፡ አሁን የፍቅር ንጉስ ወይም ንግስት ብቻ ሳትሆኑ ቅዱስም ናችሁ፡፡ ማጣት አያስጨንቃችሁም፤ ማግኘትም አያስደስታችሁም፤ እናንተ ከሁኔታዎችም በላይ ሆናችኋልና! ለመደሰት ምንም ነገር አያስፈልጋችሁም፣ እናንተ በራሳችሁ ምንም የማይጎድላችሁ ምልዑ ናችሁና!፡፡ “አፕሼካ” የሚለው የሳንስክሪት ቃል “አፓ”(በላይ) እና “ኢክሻ”(ተራራ) ከሚሉ ሁለት ቃላት ተጣምሮ የተገኘ ሲሆን ትርጉምም “ተራራ ላይ” የሚል ይሆናል፡፡ እዚህ የፍቅር ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ሥጋዊ ምኞትን፣ ፍቅረ ንዋይን፣ ስግብግብነትን፣ ራስወዳድነትን፣ የእውነተኛ ደስታ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አሸንፎ ምንም ነገር ላያግደው ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ ቆሟል ማለት ነው፡፡ በዚህም ማንንም ከማንም ሳያበላልጥ ሁሉንም እኩል ይቀበላል፤ እኩል ይወዳል፡፡ በሰዎችና በሰዎች መካከል ብቻም ሳይሆን በራሱና በሌሎች ሰዎች መካከል አድልዖ ከማድረግ ይጸ ዳል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ቅድስና አለ? ለራስ እንኳን የማያዳላ፤ ራሱን የማይወድ ማን ነው? የ“አፕሼካ” ደረጃ ላይ ከደረ ሰው ከእርሱ ከምልዑው፣ ከቅዱሱ ሰው በቀር! እንደዚህ መሆን በእውነት መታደል ነው፡፡ “ከመታገል መታደል” ያለው ማን ነበር? ለነገሩ ትግልም ጥሩ ነው፣ አንዳንዴ መታደል በመታገል ሊሆን ይችላልና!
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
ይበል ካሳ