የድል ዓርማ የሆነው መከላከያ ሠራዊታችን በፈተና ውስጥ እየጸና የሚቀጥል የሀገር ዋልታ ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉአላዊነቱ ቀናኢ ነው። በየዘመናቱም ከውስጥና ከውጭ የተቃጡ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን በጽኑ ታግሎ ሀገሪቱን ከነሙሉ ክብሯ ለአሁኑ ትውልድ አስረክቧል። የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን አደራ በመረከብ የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በደሙና በአጥንቱ አስከብሯል፤ በማስከበርም ላይ ይገኛል።

ከጥንት እስከ ዛሬ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል። በተለይም ዘመን አመጣሾቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል እርስ በእራሱ እንዳይተማመንና በሂደትም በሚኖሩ ግጭቶች ኢትዮጵያ እየተዳከመች እንድትሄድ ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

የውጭና የውስጥ ጠላቶች በአንድነት በማበር ለሀገሪቱ መዳከምና በሂደትም መፈራርስ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚሉትን ኃይል በማደራጀት፤ በማስታጠቅና በማሠልጠን ታሪካዊ ጠላትነታቸውን በገሃድ ሲያስመሰክሩ ኖረዋል::

እነዚህ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የዚህን ኩሩ ሕዝብ የዘመናት ዕሴቶች ለመናድ ሲሯሯጡ ይታያሉ። ልዩነቶችን ጌጡ አድርጎ የኖረውን ሕዝብ እርስ በእራሱ እንዳይተማመን እና እንዲጋጭ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመፍጠር በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ ያለመታከት በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ነን ባዮች የራሳቸው አንድም ሃሳብ ሳይዙ በተላላኪነትና በባንዳነት ጎራ ተሰልፈው አንዱን ብሔር በሌላው ላይ በማስነሳት ሀገርን ለማፍረስ ቆርጠው ተነስተዋል።

በዚህም የዜጎችን በሠላም የመኖር መብት አደጋ ላይ የጣሉና የሀገርን ሠላምና ደህንነት የሚያውኩ ሙከራዎችም ተከስተዋል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በነዚሁ የጥፋት ኃይሎች አማካኝነት በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ለአስከፊ ሕይወት ተጋልጠዋል።

ሆኖም ከሕዝብ አብራክ በወጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተጋድሎ የእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሴራ በየጊዜው በማክሸፍ ላይ ይገኛል። መከላከያ ሠራዊት በዱር በገደሉ በሚያደርገው ተጋድሎ ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯ ጸንታ ቀጥላለች።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጀግንነት መለያው፤ ድል ማድረግ ዓርማው ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የማይደረምሰው ተራራ፤ የማይወጣው አቀበት የማያሸንፈው ጠላት የለም። ይህን እንኳንስ ወዳጅ ጠላትም የሚመሰክረው ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ ሁልጊዜም ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮዎችን አንግቦ ይንቀሳቀሳል። የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሠላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል። በዱር በገደሉ ይዋደቃል። ደሙን ያፈሳል፤ አጥንቱን ይከሰክሳል።

የመከላከያ ሠራዊት አልፋና ኦሜጋ የሀገር ሉአላዊነትና የሕዝብ ደህንነት ናቸው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት በሠላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሠራዊት ነው። ሠራዊቱ እንደ ተኩላ በኅብረት የሚያጠቃ እንደ አንበሳ ቦታውን የማያስደፍር ጀግና መሆኑንም ብዙዎች ይስማሙበታል። ሠራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለዓላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ልበ ሙሉ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በየጦር ውሎው በጀግንነት እየተዋጋ ለእናት ሀገሩ ተሠውቷል። ለሀገርና ለወገን ያለውን አጋርነት በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይቷል።

በተለይ ሠራዊታችን እንደገና ሪፎርም ከተደረገበት ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ሕዝባዊ ባህሪ በመላበስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ባንዳዎች ሲታደግ ቆይቷል። ሠራዊታችን ደሙን አፍስሶ፤ አጥንቱን ከስክሶ በከፈለው መስዋዕትነት ሀገሪቱን ከመፈራረስ ታድጎ በብልጽግና ጎዳና እንድትጓዝም አድርጓል።

ሆኖም የውጭና የውስጥ ጠላቶች በመቀናጀት የሠራዊቱን ስም ለማጠልሸት ሲሯሯጡ ይታያሉ። ሆኖም ከሕዝብ አብራክ የወጣውና የጀግኖች ስብስብ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት በወሬና በአሉባልታ የሚረታና የሚናድ አይደለም።

ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በድል ላይ የድል አክሊል እየደረበ የሕዝብ ጥቅምንና የሀገር ሉአላዊነቱን የማስጠበቅ ቁመና ከምንጊዜውም በላይ ጎልብቶ ይገኛል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016

Recommended For You