ሀገሬ፤ ስላንቺ ካወቅነው ያላወቅነው ብዙ ነው!

የጉዞ ማስታወሻ (ክፍል ሁለት)

ሌሊቱ ያለምንም ቅዠት ለማለፉ፤ ድህረ እንቅልፍ ውጣ ወረድ መብዛቱ ነበር ምክንያቱ። ከልካይ የሌለው ብርሃን በመስኮት በኩል ወደ መኝታ ክፍሉ ፈንጥቋል። ለቀጣዩ ጉዞ ለመነቃቃት ሻወር ወሰድኩ፤ ቀዝቀዝ ያለው ውሃ፤ ያደረውን ድካም ጠራርጎ ወሰደው። ‘እሰይ!’ አልኩ የሚሰማኝ ያለ ሰው ይመስል። አሁን አንድ ነገር ይቀረኛል፤ ቁርስ። የተገኘውን ቀማምሼ ፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል ወደሆነው የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ለማቅናት እየተንደረደረ ወዳለው መኪና ጥልቅ አልኩ።

ትንሽ ከማይባል ጉዞ በኋላ አንድ ስፍራ ስንደርስ ሁሉም መኪና በአንድ የመከረ ይመስል ዳር ይዞ ቆመ። የኮንታ ባህል ቡድን አባላት በባህላዊ የትንፋሽ መሳሪያዎች እየተቀባበሉ ድንቅ ዜማ ፈጠሩ። ዜማውን ተከትለው የብሔረሰቡን ባህላዊ ልብስ የለበሱ አስር ተወዛዋዦች የተለያየ ማራኪ እንቅስቃሴ በማሳየት የሁላችንንም ቀልብ ገዝተው መያዝ ችለው ነበር። ይህ ዓይነቱ ጭፈራና ዜማ የሚቀርበው ለእንግዳ ብቻ እንደሆነ ነው የተረዳነው።

ገና ምን አይታችሁ! በሚል ይመስላል፤ በስተቀኝ በኩል ጥላማ በሆነ ስፍራ ላይ አረፍ እንድንል የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ጋበዙን። እንግዳ ነንና ግብዣውን ተቀብለን አረፍ አልን። እንኳን ወደ አረንጓዴ ምድር በደህና መጣችሁ። በመምጣታችሁ ደስ ብሎናል አሉ የኮንታ ዞን አስተዳዳሪ። በዚህ ሳያበቁ በዞኑ ስለሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች መዘርዘር ጀመሩ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተገነባ ስላለው የኮይሻ ፕሮጀክትና ሲጠናቀቅ በስፍራው የሚገኘውን የተደበቀ ድንቅ የተፈጥሮ ውበት በምናብ እንድንስል አደረጉን።

እውነት ነው። ይህ የቱሪስት መዳረሻ ለምቶ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ቱሪስቶች ሲሸጥ ዳጎስ ያለ ገቢ እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም። የዞኑ አስተዳዳሪ በቃል ብዙ መናገር አልፈለጉም። ይልቁን የዞኑን ድንቅ ውበት በተግባር ገልጸው አሳዩን እንጂ። ንግግራቸውን እንዳበቁ በዞኑ የሚገኙትን የግብርና ውጤቶች ተጋበዙልን አሉ። ወለላ ማር፤ እርጎ፤ አይብ፤ ሙዝ፤ አናናስ፤ ፓፓያ፤ ማንጎ፤ ብርቱካን ወዘተ… የቀረ የግብርና ምርት የለም ማለት ይቻላል፤ ያ! ለምለም ምድር ያበቀለውን ሁሉ አቀረቡ። ማእዱ ሙሉ ነበር።

ከጥቂት እረፍት በኋላ ዋናውን የኮሮኮንች መንገድ ለቅቀን ወደ ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ገባን። ቀደም ሲል በዚህ ፓርክ ውስጥ የሚገኙትን እምቅ የቱሪዝም መስቦችን የማውቃቸው ለተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖች የቪዲዮ ክሊፕ ሆነው ነበር። በፓርኩ ውስጥ በአካል ተገኝቼ ይህን አምሳለ ገነት የሆነ ቦታ በዓይኔ በብረቱ አየሁት። ፓርኩ በ1997 ዓ.ም በኮንታና ዳውሮ ብሔረሰቦች ጥያቄና ተሳትፎ በመከለሉ ከማንኛውም ስጋት ነጻ ነው ማለት ይቻላል። ፓርኩ ለብዝሀ ሕይወትና ለዱር እንስሳት ምቹና አስተማማኝ የጥበቃ ስፍራም እንደሆነ ይነገርለታል። በኮንታና ዳውሮዎች ለደን ያላቸው ቦታ ትልቅ ነው። አንድ ሰው አንድ ዛፍ ከመቁረጡ በፊት ሶስት ችግኖች የመትከል ግዴታ አለበት።

ወደ 1190 ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት መሬት የሚሸፍነው ፓርኩ፤ ከባህር ወለል በላይ በ700 እና 2800 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። በእምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች የተንበሸበሸው ይህ ፓርክ፤ በዓለም ዙሪያ እየተመናመነ የሚገኘው የአፍሪካ ዝሆን እንዲሁም የሌሎች ብርቅዬና ድንቅዬ እንስሳት እና እጽዋት መገኛም ነው።

የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ የተለያዩ የውሃ ተፋሰሶችን፤ ማለትም ወንዞች፤ ጅረቶችና ሐይቆችን የያዘ በመሆኑ ብዛት ያላቸው የዱር እንስሳት እንዲርመሰመሱበት በነጻ የፈቀደ ይመስላል። በጠዋቱ ጉብኝታችን፤ ይህንን ድንቅ ስፍራ ማየት ለሚፈልጉ ሰዎች የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ተመልክተናል። መሠረተ ልማቶቹን ለማከናወን የተደረገው የቦታ መረጣና የዲዛይን ተለያይነት አስገራሚና እምቅ የተፈጥሮ ሃብቱን በጉልህ ለማሳየትም ሆነ ጊዜ ወስዶ ለመዝናናት የሚያመቹ ናቸው።

የፓርኩን ዙሪያ ገባ ለማየት የሚያስችለው የጥርጊያ መንገድ፤ ድልድዮች፤ የቱሪስት ማረፊያ ስፋራዎች፤ ካፌዎች፤ ሬስቶራንቶች በተመረጡ ስፍራዎች ተገንብተዋል። እየተገነቡም ነው። እነዚህ መሠረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ከመቻላቸውም በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ዚጊና፤ ሾሹማና አድኮላ የሚባሉ ወንዞች በፓርኩ ውስጥ ማለፋቸው ስፍራውን ከዓመት ዓመት ሐመልማላዊ ምድር እንዲሆን አድርጎታል። ጮፎሬ፤ ሙንኦ፤ ዎንባ ፤ ካርቤላ፤ ሺቫ እና ዶኖ ሐይቆችም ውበቱን አግዝፈው የሚያወጡት የፓርኩ ሃብቶች ናቸው። ከነዚህ ሐይቆች ውስጥ በአንደኛው በየትኛውም የዓለም ክፍል የማይገኝ “ጋራ ጨበራ” ተብሎ የሚጠራ ዓሣ ይገኛል። ይህ ፓርክ 37 መካከለኛና ትላልቅ አጥቢ እንስሳት፤ 237 የአእዋፍ ዝርያዎች የያዘ ነው። ከተጠቀሱት የአእዋፍ ዝርያዎች አምስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ መሆኑን ተገንዝበናል።

በፓርኩ ዝሆን፤ ጎሽ፤ ጉማሬ፤ ከርከሮ፤ ድኩላ፤ ድፋርሳ፤ አጋዘን፤ አሳማ፤ ዝንጀሮ፤ ጦጣ፤ አንበሳ፤ ነብር፤ የዱር ድመት እና ሌሎችም ይገኛሉ። ከፓርኩ እስካውቶች እንደተነገረን የዱር እንስሳቱን ለማየት ከጥቅጥቁ ደን፤ ለውሃም ለምግብም የሚወጡበትን ሰዓት ብቻ ሳይሆን ድምጽና ኮቴ ሳያሰሙ መጓዝ የዱር እንስሳቱን በቅርብ ርቀት ለማየት ይረዳል። የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ሰፊ በመሆኑ በእግር ብቻ ከሚገባባቸው ስፍራዎች ውጭ የፓርኩን ዙሪያ ገባ ለመመልከት መኪና መጠቀም አስፈላጊ ነው። በፓርኩ ወደሚገኘው የተፈጥሮ ሐይቅ ሄድንና በእስካውቶቹ ብርታት ቀይ ጉማሬ ተመለከትን።

ለምሳ እረፍት ያደረግነው በፓርኩ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሬስቶራንት ነው። የሬስቶራንቱ ባለቤት ፊቤላ ትባላለች። ፊቤላ፤ በትውልድ ፈረንሳዊ ስትሆን ባለቤትዋ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ወደ ፓርኩ የመጣችው ለአንክሮና ለተዘክሮ ቢሆንም ቅሉ፤ የስፍራው ውበት ማርኮ ካስቀራቸው ሰዎች አንዷ ናት። ፌቤላ አሁን ላይ ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ ባለሃብቶች ሞዴል ሆና ተሞክሮዋን እያጋራች ትገኛለች። አንዳንዶችም የሷን ፈለግ በመውሰድ ለፓርኩ ጌጥ የሆኑ ልማቶችን እያለሙ ይገኛሉ።

ከምሳ በኋላ ጸሐይ እያዘቀዘቀች ስትመጣ በፓርኩ የሚገኙ እስካውቶች ዝሆንን እናሳያችሁ በሚል እንደ ጦስ ዶሮ ይዞሩን ጀመር። ከብዙ ጎሾች መሀል አንድ ግዙፍ ዝሆን አየን። “ሌሎቹ ጥቅጥቅ ባለው ደን ይገኛሉ::” አለ አንደኛው እስካውት። ገሚሶቻችን ቫይናኩላር፤ ገሚሶቻችን የመኪና ኮርቶ መጋላ አንዳንዶችም ኮረብታማ ቦታዎች ላይ ሆነን ይሆናል ያልነውን ዘዴ በመጠቀም ብዙ ዝሆኖች ሲርመሰመሱ ለማየት አጮለቅን። ነገር ግን ከአንዲቷና በአካልም ግዙፍ ከሆነችው ዝሆን በቀር ሌሎቹ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ምናልባት ዝሆኖቹ የተደበቁበትን ቦታ ለማወቅ በሚል ድሮን ወደ ማእከላዊ የፓርኩ ስፍራ ተላከች። እሷም ብትሆን ለዛሬ አልተሳካም ብላ ተመለሰች።

ዝሆኖች በብዛት ሊገኙ ይችላል የተባለበት ቦታ ሁሉ ዞርን። የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል እንዲል ተረቱ፤ የኋላ ኋላ ከብዙ ድካም በኋላ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ፤ በቁጥር በርከት ያሉ ዝሆኖች በወንዝ ዳርቻ ሲጓዙ ተመለከትን። በትዕግስት በመጠበቃችን የሃሳባችን ሞልቷልና ባየነው ነገር ውስጣዊ ደስታ ተሰማን። የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ የመስክ ጉብኝት መጠናቀቁን ተከትሎ ከኮንታ አመራሮች ጋር የማስታወሻ ፎቶ ተነሳን። ኮይሻ የኃይል ማመንጫ ወደሚገኘው ማረፊያችን ሄደንና አዳራችንን በዛው አደረግን።

በነጋታው ጠዋት፤ የኮንታ ዞን ጉብኝታችንን ማጠናቀቃችን ተነግሮን ሻንጣችንን ሸክፈን ወደ ኮስተሮቹ መኪናዎች ወጣን። ምስጋና ለኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች ይሁንና የተሰበረው ባሌስትራ እዚያ ተጠገነ። የጉዞ መዳረሻችን ዳውሮ ዞን መሆኑ ተነግሮን ወደዛው አመራን። ትንሽ እንደተጓዝን የአፈር ቁፋሮ ላይ የሚገኘው የመንገድ ሥራ፤ ሌሊቱን ዘንቦ በነበረው ዝናብ ላቁጦ ወደ አቀበት የሚወጡትን መኪኖች ወደኋላ ይጎትታቸዋል። ሁሉም መኪኖች ከፊታቸው በሚገኝ ስካባተር ጋር በካቦ ታስረው እየተጎተቱ ወጡ። የሙያ ባልደረቦቻችን የመንገዱን ችግር መፍትሔ ያገኝ ዘንድ ትእይንቱን በምስል አስቀሩት።

የዳውሮ ዞን ከተማ የደረስነው ስምንት ሰዓት ላይ ነበር። ከተማዋ ነቃ ያለች እና አልፎ አልፎም ፎቆች የሚታዩባት ናት። ከብዙ ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ የአስፋልት መንገድም የሚገኘው ከተማው ውስጥ እንጂ ከዛ በፊት አይታሰብም። ወደ አንደኛው ሆቴል እንድንገባ ተነገረንና የምሳ ቆይታ በዚያ አደረግን። የዳውሮ ሰማይ ዝናብ አርግዟል። በፕሮግራማችን መሠረት በከተማው ወደሚገኘው የኤትኖግራፊ ሙዚየም አመራን። በሙዚየሙ የዳውሮን ብሔር ባህል፤ ታሪክ፤ ወግ፤ አኗኗር የሚያሳዩ ቁሳቁሶች፤ ባህላዊ ልብሶች፤ የሙዚቃ መሳሪያዎች እና ቅርሶች አንዱም ሳይቀር በአግባቡ ተሰድረዋል። ከጉብኝቱ ስንወጣ የብሔረሰቡ የሙዚቃ ቡድን አባላት የብሔረሰቡን ባህላዊ ልብስ ለብሰው ማራኪ ውዝዋዜ ቀልባችንን ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ሰቅዘው ያዙት።

የኤሌክትሪክ መብራት መጥፋቱ፤ የዳውሮ ከተማን የተወረረች አስመስሏታል። አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በዳውሮ የመብራት አገልግሎት በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። የዳውሮ ዞን መብራት እንደልቧ ባታገኘውም ወርቅን እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ባለቤት ናት። እራት ያገኘሁትን የአካባቢው ተወላጅ አንድ ጥያቄ አቀረብኩለት።

“ሕዝቡን አስተባብራችሁ፤ ለከተማዋ የሚበቃ ጀነሬተር መግዛት እንዴት አቃታችሁ?” ብዬ ጠየቅኩት።

“ገዝተን ነበር አለ።”

“እና ምን ሆኖ ነው?” ስል ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ።

“አንዱ ሹመኛ ከዚህ ሲነሣ ጭኖ ይዞት ሄደ።” አለኝ።

“ወደ የት!?” አሁንም ጠየቅኩት።

“እኔንጃ!” ሰውየው መለሰ።

“ቢያንስ የራሳችሁ ንብረት ሲወሰድ እንኳን ወደየት ነው የሚሄደው ብላችሁ አትጠይቁም!?” ሌላ ጥያቄ አከልኩት።

“ጊዜው የማይጠየቅበት ነበር::” ብሎ የማያዳግም መልስ ሰጠኝ።

አጠገቤ የሚንተከተከው ለሆቴሉ ብቻ የሚያበራው ጀነሬተር በመኖሩ እራት ለመብላትም ሆነ ወደ ማደሪያ አልጋችን ላይ ለመስፈር አግዞናል።

ጠዋት 12፡00 ሲሆን ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ቦታ ጎበኘን። በዞኑ ፍቃድ ከተሰጣቸው ስምንት ባለሃብቶች ስድስቱ የድንጋይ ከሰል በማበልጸጊያ ሥራ ጀምረዋል። ፍቃድ እንዲሰጣቸው ያመለከቱት 41 አልሚዎች ቢሆኑም፤ የአካባቢው ሥነ ምህዳር እንዳይጎዳ በሚል እሳቤ ለስምንቱ ብቻ እንደተሰጠ ሰምተናል። በሌሎች ማዕድን ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ግን አሁንም በራቸው ክፍት እንደሆነ ነው የተነገረን።

በዳውሮ ዞን የነበረንን ቆይታ አጠናቀን ወደ ሃላላ ኬላ የሚወስደውን መንገድ ይዘን ወደፊት ተወነጨፍን። ወደ ሃላላ ኬላ የሚወስደው መንገድ የአዲስ አበባ ከተማን የአስፋልት ደረጃ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። የጉዞ መዳረሻችን ወደሆነው የሃላላ ሪዞርት መድረሳችንን የሚያመለክተውን በር ጋር ደርሰናል። ድንቅ የሆነ የዲዛይንና የአርክቴክት ጥበብ ይታይበታል፤ በሪዞርቱ። የእንግዳ መቀበያ፤ የመሰብሰቢያ አዳራሹም ወደ 200 የሚጠጋ ሰው ይይዛል። በሰፊው የተንጣለለው የምግብ አዳራሽ (በአንድ ጊዜ 100 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ነው። የመዋኛ ገንዳ፤ እንዲሁም ከመለስተኛ እስከ ቅንጡ ወይም ቪ አይ ፒ የመኝታ ክፍሎች ንጹህ አየር እንዲያስገቡ ሆነው በከፍታ ቦታ ላይ ተገንብተዋል።

በቄንጠኛ አሰራር ተጊጠው በተራራ ላይ ጉች ጉች ያሉትና የጎጆ ቤት ቅርጽ ያላቸው የማረፊያ ክፍሎቹ፤ ይሄ ይቀራቸዋል የማይባልላቸው ናቸው። ሪዞርቱ በቦታው እንዲገነባ የተመረጠበት ምክንያት ስፍራው የሃላላ ኬላ ታሪካዊ ቅርስ መገኛ ብቻ ሣይሆን፤ በተራራው ግርጌ የሚገኘውና በግልገል ግቤ ሶስት ምክንያት የተፈጠረው የሰራው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ነው።

ሃላላ፤ የዳውሮ ንጉስ መጠሪያ ስም ነው። ንጉሱ የዳውሮን ሕዝብ ከጠላት ጦር ለመጠበቅ የድንጋይ ግንቦች አስገንብቶ ነበር። ይህ ቅርስ የሆነው አጥር፤ ከደረቅ ድንጋይ የተገነባ ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው ከ200 ዓመታት በላይ የፈጀና በሦስት ትውልድ ቅብብሎሽ የተጠናቀቀ ነው። ሥራው የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በካቲ(ንጉስ) ሃላላ ዘመን ነበር።

ስፍራውም በዳውሮዎች ካቲ ሃላላ ኬላ በመባል የሚጠራ ሲሆን፣ ትርጉሙም የንጉስ ሃላላ ግንቦች ማለት ነው። ንጉሱ ከንግስና ዘመናቸው አብላጫውን ወይም 25 ዓመታት ለዚህ ሥራ እንዳዋሉት ይነገርላቸዋል። ስያሜው ከንጉስ ሃላላ ጋር መያያዙ፤ ግንባታው ፍጻሜውን ያገኘው በእሳቸው ዘመን ስለሆነ ነው። ሃላላ ኬላ 1225 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያሉት ሲሆን፣ ሰባት በሮች አሉት። ዳራሚሳ ሚፃ፤ ጋራዳ ሚፃ፤ ዳራ ሚፃ፤ አባርጋ ሚፃ፤ ካላ ሚፃ፤ ሜልዶካሬ ሚፃ፤ አናይዶሎ ሚፃ ተብለው ይጠራሉ።

ይህን ድንቅ የመስህብ ስፍራ ከጎበኘን በኋላ የግልገል ግቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ ወደፈጠረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ በሪዞርቱ መኪኖች አመራን። ሐይቁ ውስጥ ብዙ የዓሳ ምርት ይገኛል። ዓሳ ስላችሁ፤ በየገበያው የምናገኛቸው ሥራ የተቀቡ የሚመስሉትን ዓይነት አይደሉም እዛ የሚገኙት። ከውፍረታቸው የተነሣ መረብም ዓይንም የሚሞሉትን ዓሶች አልኩኝ እንጂ። ይህን ሐይቅ በጀልባ ማቋረጥ ከቻላችሁ 50 ኪ.ሜ ከመንገዳችሁ ላይ ትቀንሳላችሁ። ነገር ግን መኪኖቹ በተለመደው መንገድ ይምጡ ያሉንን ሸጋ ምክር አደመጥን። እንደተነገረን ሐይቁን በሞተር ጀልባ ተሻገርነው።

ኮስትሮቹ በተጠበቁት ሰዓት ሳይመጡ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ቀኑ መሸ። በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ጠጋ ብለን የመኪኖቹን መምጣት በጉጉት መጠባበቅ ያዝን። ከብዙ ጥበቃ በኋላ ጢምቢራው እንደዞረ ሰካራም እየተንከላወሱ መጡ ፤ መኪኖቹ። የመዘግየታቸው ምክንያት አንደኛው መኪና ከስሩ የገባውን ሕጻን ለማትረፍ በሚል አደጋ ደርሶበት እንደሆነ ሰማን። መኪናው ግጭት እንደደረሰበት ግን እርግጠኛ እንድንሆን ያደረገን በሹፌሩ በኩል የሚገኘው በርና ከኋላም በቀኝ በኩል ያለው መስታወት አደጋ እንደደረሰበት ባየን ጊዜ ነበር።

ስለተፈጠረው አደጋ እያወጋን ወላይታ ሶዶ ከተማ ደረስን። ሰፊው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሃብቶች በወፍ በረር ቃኝተን፤ ሐመልማላዊው ምድር አጣጥመን ሳንጨርሰው፤ ጉዞአችን ተጠናቀቀ። ውብ ሀገሬ፤ ስላንቺ ካወቅነው፤ ያለወቅነው እጅግ ብዙ ነው።

 በግርማቸው ጋሻው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016

Recommended For You